1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች፣ደሞዝ ጭማሪ፣? የአማራ ተማሪ ቁጥር፣አዲስ አበባ ግንባታና ጎርፍ

ዓርብ፣ መስከረም 17 2017

የገንዘብ ሚንስቴርና የሲቪል ሠርቪስ ኮሚሽን በጋራ አጠኑት በተባለዉ ሠነድ መሠረት ጭማሪዉ ከ5% እስከ 332% ይደርሳል።ከ2017 መጀመሪያ ጀምሮ ይፀናል የተባለዉ ዕቅድ የሠራተኛዉን ኑሮ ለማሻሻል እንደሚረዳ የመንግሥት ባለሥልጣናት ይናገራሉ።

የኮሪደር ልማት በተባለዉ ግንባታ ከተሠሩ መንገዶች፣ መናፈሻዎችና ሌሎች የመሠረተ ልማት አዉታሮች አንዳዶቹ በጎርፍ መሞላታቸዉ ግንባታዉ አጠያያቂ አድርጎታል
አዲስ አበባ።የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ባለፈዉ ዓመት ከተማይቱን የመሠረተ ልማት አዉታሮች ለማሻሻል ለጀመረዉ ግንባታ ስኬት በርካታ ቤቶችን አፍርሷል።ምስል Solomon Muchie/DW

የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች፣ደሞዝ ጭማሪ?የአማራ ክልል ተማሪ ቁጥር፣አዲስ አበባ ግንባታና ጎርፍ

This browser does not support the audio element.

ሳምንቱን የአብዛኛዉን የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተከታታይ ትኩረትን ከሳቡ ርዕሶች ለዛሬ ሶስቱን መርጠናል።ለመንግሥት ሠራተኞች ይደረጋል የተባለዉ የደሞዝ ጭማሪ፣የአማራ ክልል ተማሪዎች ቁጥር ማነስና አዲስ አበባ ዉስጥ የኮሪደር ልማት በሚል ዘመቻ የተሠሩ የመሠረተ ልማት አዉታሮች ያጋጠማቸዉ የጎርፍ አደጋ ናቸዉ።በየርዕሶቹ  ላይ ከተሰጡ አስተያየቶች የጎሉ፣ ከሥድብና ዘለፋ የፀዱትን ባጫጭሩ እናሰማችኋለን። አብራችሁን ቆዩ።

የደሞዝ ጭማሪ ወይስ?
                               
 የኢትዮጵያ መንግሥት ለተቀጣሪዎቹ ደሞዝ ለመጨመር አቅዷል።የገንዘብ ሚንስቴርና የሲቪል ሠርቪስ ኮሚሽን በጋራ አጠኑት በተባለዉ ሠነድ መሠረት ጭማሪዉ ከ5% እስከ 332% ይደርሳል።ከ2017 መጀመሪያ ጀምሮ ይፀናል የተባለዉ ዕቅድ የሠራተኛዉን ኑሮ ለማሻሻል እንደሚረዳ የመንግሥት ባለሥልጣናት ይናገራሉ።ይሁንና ባለሙያዎችና ራሳቸዉ የመንግሥት ሠራተኞች እንደሚሉት ጭማሪዉ ከቁጥር ባለፍ አለቅጥ በናረዉ የዋጋ ግሽበትና የኑሮ ዉድነት ችግር ዉስጥ ለወደቀዉ ሠራተኛ የሚፈይደዉ ነገር የለም።
ቡቺ የናቱልጅ የሚል የፌስ ቡስ ስም ያለዉ አስተያየት ሰጪም «ኑሮ የጨመረው 1000% ደሞዝ የጨመረው አንድ ሺህ ብር።» ይላል።አክሊይ አስክ፣ እሱም በፌስ ቡክ «ህዝብ ቢደመጥ ጥሩ ነበር። ሐገር ከፍ ያለ ዋጋ ልትከፍል ተቃርባለች።» ብሏል።በላይ በቀድሞዉ ትዊተር (ባሁኑ X) ጥያቄ አከል አስተያየት ፅፏል።«አንድ የቤት መኪና በአርባ ሚሊየን ብር የሚገዛ ሙሰኛ ጀነራል ባለበት አገዛዝ ውስጥ ምን ይጠበቃል?» የሚል።
አዱኛ መኮንን «አጭበርባሪ በሉት» ይላል።«ደሞዝ ቅናሽ ነዉ ያደረገዉ» አለ።መንግሥትን መሆኑ ነዉ።ምሳሌ ይጠቅሳልም።«የዶላር (ዋጋ) ከመጨመሩ በፊት እኔ 150 ዶላር ነበር የማገኝው። አሁን በአዲሱ ጭማሪ 89 ዶላር ነው የማገኝው።» የአዱኛ መኮንን አስተያየት ነዉ።ማሒር ማሒርም ምንም ጭማሪ አልተደረገም ባይ ነዉ-በፌስ ቡክ።«ምንም ጥናት ያልተደረገበት። ከ 1 ብር በታች ነዉ ጭማሪ የተደረገው።» ይላል ማሒር ማሒር። ነሥረዲን አጭር ጥያቄ አለዉ በፌስ ቡክ «ጭማሪ አላችሁት?» የምትል።
ታገል ታደለም ይጠይቃል።«ለሀገር ቆሰለን ቦርድ (ጡረታ) ለወጣ ወታደር ጨምሮ ይሆን?» ታገል ታደለ ነዉ ጠያቂዉ በፌስ ቡክ።ዎዳሎ ዎልታሞ አማራጭ ብጤ ይጠቁማል።«የስራ ግብር መነሳት አለበት» የሚል።
ሸምሱ አማንም እንደ ዎዳሎ ሁሉ አማራጭ ይጠቁማል።በርከት ያለ አማራጭ «ደሞዝ ከሚጨምሩ ግብር ቢቀንሱና ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞችን ቢያመቻቹ ይሻላል። የቤት ኪራይ ክፍያ፣ የትራንስፖርት  ድጎማ፣ የጤና መድህን፣» እያለ አማራጮቹን ይዘረዝራል።ሸምምሱ አማን በፌስ ቡክ።
                             
አማራ ክልል ከ7 ሚሊዮን ተማሪ፣ የተመዘገበዉ 2 ሚሊዮን አይሞላም

ባለፈዉ ዓመት አዲስ አበባ ዉስጥ ከደረሱ የጎርፍ አደጋዎች አንዱ።በአደጋዉ የሰዉ ሕይወት፣ ሐብትና ንብረት ጠፍቷልምስል Seyoum Getu/DW

የአማራ ክልል ትምሕርት ቢሮ በያዝነዉ ሳምንት እንዳስታወቀዉ ለዘንድሮ የትምሕርት ዘመን ሊያስተምር ካቀደዉ 7 ሚሊዮን ተማሪ መካከል እስከያዝነዉ ሳምንት ድረስ ለመማር የተመዘገቡት 2 ሚሊዮን አይሞሉም።ቢሮዉ ለተማሪዎቹ ቁጥር መቀነስ ከጠቀሳቸዉ ምክንያቶች አንዱ የፀጥታ መታወክ ነዉ።ተማሪዉ ዘግይቶ ትምሕርት ቤት የመሔድ ዳተኝነት-ሁለተኛዉ ነዉ።ዛሬ ከተከበረዉ የመስቀል በዓል በኋላ ተጨማሪ ተማሪዎች ይመዘገባሉ የሚል ተስፋ እንዳለዉም ቢሮዉ አስታዉቋል።
ተካበ አቡሐይ ግን በፌስ ቡክ ትምሕርት ቤቶች ወደ ጦር ሠራዊት ሠፈር (ካምፕነት) ተለዉጠዋል ባይ ነዉ።«የት ይማሩ» ይጠይቃል ተካበ።«ለምሳሌ ጎንደር ዙሪያ ማክሰኝት ከተማ ከኤለመንተሪ እስከ ቴክኒክና ሙያ በሙሉ በካምፕነት እያገለገሉ ነው::ለመከላከያ።» ተካበ አቡሐይ ነዉ-ይሕን ባዩ።አዳም ጌትነትም የተካበን አስተያየት ይጋራል።«ትምህርት ቤቱ በሙሉ የፋኖ እና የመንግስት ሀይሎች ካምፕ ሆኗል ።» ይላል።
በለጠ አበበ ደግሞ «ክልሉ ከመንግስት ቁጥጥር ውጪ መሆኑን ያሳያል።»ይላል በፌስ ቡክ።ንጉስ ወዳጄነዉ ማሙዬ--- እንደ ስሙ ሁሉ የሰጠዉ አስያየትም ረዘም ያለ ነዉ።«የፖለቲካ መፍትሄ ከማምጣትና ከመደራደር ይልቅ በሁለቱም ወገን ጦርነት በመመረጡ ፣ክልሉ ለከፋ ውድቀት እየተደረገ ነው።»አበቃ።
ተከስተ ተክላይ እሱም በፌስ ቡክ።«የጦርነቱ ውጤት ይሄ  ነው።» ይላል።
 
የአዲስ አበባ የኮሪደር ልማትና የጎርፍ አደጋ

በ2016 አዲስ አበቦችን ብዙ ካነጋገሩ፣ አንዳዶቹን ካበሰጩ፣ ሌሎችን ካስደሰቱ ጉዳዮች አንዱ የከተማይቱ አስተዳደር «የኮሪዶር ልማት» ያለዉ የመንገድና የሌሎች የመሠረተ ልማት አዉታሮች ግንባታ ነዉ።በዘመቻ መልክ በተወሰደዉ ርምጃ ብዙ ቤቶች፣ መደብሮችና ሕንፃዎች በመፍረሳቸዉ  ነዋሪዎች ቅሬታቸዉን ሲያሰሙም ነበር።አምና ክረምት ደግሞ ኢትዮጵያ ዉስጥ የጣለዉ ዝናብ ያስከተለዉ ጎርፍና የመሬት መደርመስ አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የሐገሪቱ ክፍሎች የሰዉ ሕይወት አጥፍቷል።ንብረት አዉድሟልም።
አደጋዉ አዲስ አበባ ዉስጥ አዳዲስ የተገነቡ መንገዶችና መናፈሻዎችን መጉዳቱ ግንባታዉ የጥድፊ ነዉ አለያም የዉኃና የፅዳጅ መፍሰሻዎችን ዘንግቷል የሚሉ ትችቶች ማስከተሉ እየተዘገበ ነዉ።
ተሾመ ጉዱራ ከተቺዎቹ አንዱ ሳይሆን አይቀርም።«ዱሮም በፖለቲካ ግፊትና በዘመቻ የሚሰራ ልማት ውጤቱ የሰመረ አይሆንም::» ይላል በፌስ ቤኩ።ምክር ቤትም አክሎበታል።«ጥናትን መሠረት አድርጎ የሚሰራ ልማት ምን ጊዜም ውጤቱ የላቀ ነው።» የሻምበል ልጅ ባለፈዉ ነሐሴ በX «ይሕ ሁሉ ፓርክ፣ ሎጅ፣ የኮሪደር ልማት፣ ዳቦ ከሆነ፣ ከረሐብ ከታደገን እስኪ እናያለን።« ብሎ ነበር።

የአማራ ትምሕርት ቢሮ ለዘንድሮዉ የትምሕርት ዘመን 7 ሚሊዮን ለማስተማር አቅዶ እስከ መስከረም አጋማሽ 2017 የተመዠገቡት ግን 2 ሚሊዮን አይደርሱምምስል Alemnew Mekonnen/DW

አይኔንግዳ አበበ ግን «ምን አገባችሁ ይላል።ወይም ትላለች በፌስ ቡክ።«እኛ ተመችቶናል።»መለሰ ቶላም ተመሳሳይ አስተያየት አለዉ።እሱም በፌስ ቡክ።«የተሰራው ትልቅ ስለሆነ ትልቁ ከትንሿ ችግር ይበልጣል።» ሮሚ የኋላ ባንጻሩ፣«ባያልተማረ ካድሬ የሚመራ ሐገር» ብላለች በፌስ ቡክ።ፈቃዱ ቤኛ ጭብሳ ግን »ጎርፍ የፈጣሪ ስራ ነው። ምን አገናኘው። ኮሪደር ትላለህ ውጣ ወደ ገጠር እህልም እየተበላሸ ነው።» የፈቃዱ ቤኛ ጭብሳ አስተያየት ነዉ።
ዲላሞ ተረፈ ኤርጊቾ ምክር ቤት አለዉ።«ሁሉንም የወደፊት ችግርን ታሳቢ ካልተደረገ ችግር አለዉ።» የሚል የፌስ ቡክ ምክር።ታደሰ ዋቆያ በየነ «የተሰራው በባለሙያ ነው» ይላል በፌስ ቡክ
ደም መላሽ ፋኖ ግን «በልማት ስም ሌብነት እየተለመደ  ነዉ::» አለ።አዲስ ተስፋ አለኝ።ጎርፉን የፈጠሪ ቁጣ ያደርገዋል።«የድሀ አምላክ። ያለቀሱት እምባ ተጠራቅሞ ጎርፍ ሆኖ በበላቸው።» እያለ በፌስ ቡክ።መልካም የሳምንት መጨረሻ።

ነጋሽ መሐመድ ነኝ

ታምራት ዲንሳ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW