1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

ዓርብ፣ ሐምሌ 1 2014

በሁለቱም ሥፍራዎች ሕፃን ካዋቂ፣ ሴት ከወንድ ሳይለዩ፣ በካራ፣በገጀራ፣ በጥይትና በእሳት እያጋዩ ጭምር ሰላማዊ ሰዎችን የገደሉት ኃይላት መንግስት ሸኔ ብሎ የሚጠራዉ፣ በአሸባሪነት የፈረጀዉ ራሱን የኦሮሞ ነፃ አዉጪ ጦር ብሎ የሚጠራዉ አማፂ ቡድን እንደሆነ በሰፊዉ ይነገራል።

 Workneh Gebeyahu mit Abdel Fattah al-Burhan und Abiy Ahmed
ምስል፦ Tony Karumba/AFP

የወለጋዉ ተደጋጋሚ ጭፍጨፋ፣ የኢትዮ-ሱዳን ግጭትና የመሪዉቹ ስምምነት

This browser does not support the audio element.


ጤና ይስጥልኝ እንደምን ዋላችሁ።በሳምንቱ ለአብዛኛዉ ኢትዮጵያዊ የጎላዉ ርዕስ ወለጋ ዉስጥ ዳግም ሰላማዊ ሰዎች በጅምላ መገደላቸዉና የኢትዮጵያና የሱዳን መሪዎች በሁለቱ ሐገራት መካከል ሰሞኑን የተካረረዉን የድንበር ዉዝግብ ለማርገብ መስማማታቸዉ ነዉ።በርካታ የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተከታታዮችም በሁለቱ ርዕሶች ላይ የተለያዩ አስተያየቶችን ሰጥተዋል።ከስድብና ከዘለፋ የፀዱትን  አስተያየቶች ቃርመናል አብራችሁን ቆዩ።
ባለፈዉ ሰኔ 11 ምዕራብ ወለጋ ጊምቢ አጠገብ ቶሌ ቀበሌና አዋሳኙ በኒሻንጉል ጉሙዝ ቀበሌ ዉስጥ የሚኖሩ በብዙ መቶ ምናልባትም በሺሕ የሚቆጠር በአብዛኛዉ የአማራ ተወላጆች በታጣቂዎች ተገድለዋል።የጊምቢዉ አጠገብ ጭፍጨፋ ሰበብ፣ ምክንያት፣ የገዳዮችና የሟቾች ማንነት-ስትነት አነጋግሮ ሳያበቃ በሁለተኛ ሳምንቱ ባለፈዉ ሰኞ ሰኔ 27 ቄለም ወለጋ ዉስጥ ሁለት ቀበሌዎች በሚኖሩ ሰላማዊ ሰዎች ላይ የዘመቱ ታጣቂዎች በመቶ የሚቆጠሩ የአማራ ተወላጆችን በመደዳ ገድለዋል።
በሁለቱም ሥፍራዎች ሕፃን ካዋቂ፣ ሴት ከወንድ ሳይለዩ፣ በካራ፣በገጀራ፣ በጥይትና በእሳት እያጋዩ ጭምር ሰላማዊ ሰዎችን የገደሉት ኃይላት መንግስት ሸኔ ብሎ የሚጠራዉ፣ በአሸባሪነት የፈረጀዉ   ራሱን የኦሮሞ ነፃ አዉጪ ጦር ብሎ የሚጠራዉ አማፂ ቡድን እንደሆነ በሰፊዉ ይነገራል።እራሱን የኦሮሞ ነፃ አዊጪ ጦር ብሎ የሚጠራዉ ቡድን አንድ ባለስልጣንን ከዩናይትድ ስቴትስ በስልክ ለማነጋገር ደጋግመን ብንሞክርም ፈቃደኛ አልሆኑም።ይሁንና ቡድኑ በእግሊዝኛ ለሚዘግቡ ዜና አገልግሎቶች በሰጠዉ መግለጫ ለግድያዉ መንግስትን ተጠያቂ አድርጓል።
የኢትዮጵያም የዓለም አቀፍም የመብት ተሟጋቾች ድርጅቶችና አንዳድ ተቃዋሚ ፓርቲዎች  ጭፍጨፋዉ በገለልተኛ ወገን ባስቸኳይ እንዲጣራ እየጠየቁ ነዉ።ሀገሬ ጣጣሽ የሚል የፌስ ቡክ ስም ያለዉ አስተያየት ሰጪ ከገዳዮች ማንነት፣ ከሟቾች ስንትነት፣ ይበልጥ ያሳሰበዉ ሰላማዊ ሰዉ በጅምላ ሲፈጅ ባካባቢዉ ያለዉ ሌላዉ ሕዝብ ያለ- ያደረገዉ አለመኖሩ፣ ከነበረም አለመሰማቱ ነዉ።
«ህዝቡ ግን እንዴት ዝም ብሎ ይመለከታል አማራ ሲታረድ----» ይላል ሀገሬ ጣጣሽ። ቀጠለ-አንዱን ጥያቄ ግን ሁለቴ። «የዱር እንስሳት የገደለ 100 ከብት ካሳ ይከፍላል ያለ አባ አገዳ እንዴት የአማራ ነፍስ ከዱር እንስሳት አነሰችበት? እንዴት?» 
ሺ ሃሳብ ፋጀ ቶላ ደግሞ ወደ ኋላ ተመልሶ ያለቀዉን ኢትዮጵያዊ መቁጠር አይቻልም ይላል። «በመላ ሀገሪቱ በሰው ዘር ላይ የተፈጠሩ ፍጅቶች እንኳን ሰው ፈጣሪ ቆጥሮ አይጨርሰውም። እስቲ ህውሓት ከተፈጠረ እና ኦነግ ከተፀነሰ ወዲህ ያለቀውን የሰው ዘር አስቡት።» ይላል።
ተደጋጋሚዉን ግድያ በማዉገዝ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የመብት ተሟጋቾች ድርጅቶች፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና ጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ አሕመድም መግለጫዎች አዉጥተዋል።ወንጀለኞች ለፍርድ እንዲቀርቡ ጠይቀዋልም።ባሶ ወራና ባላገሩ ስሜ  «የምታባሉን እናንተ ሆናችሁ ማን ለሕግ ይቅረብ» ይላል-በፌስ ቡክ።ፋጡማ ፋጡማ መግለጫ የሰለቻት ትመስላለች።«የመግለጫ ጋጋታ መች ጠቀመን።»  አለችና ርግማኗን ቀጠለች በፌስ ቡክ  «አላሕ ያቃጥላችሁ።እንዴት ምንም የማያዉቁ ህፃነት፣ ሴትና አዛውት ይጨፈጨፋል።» 
ዘር ቴድ «እግዚአብሔር ይበቀላቹሁ»  አለበፌስ ቡክ።ሐሰን ያሲን «የጎደሩን  አልሰማችሁም?  አማራ አይደል የሞተዉ ወይስ ኢስላም ስለሆኑ ነዉ?» ጠየቀ።ሐቅ በትዊተር «መጀመሪያ እንዲሕ ያሉ ጥቃቶች እንዳይፈፀሙ ምንተሰራ» የሱም ጥያቄ ነዉ።ሰዒድ ዓሊ በፌስ ቡክ «የሚገደሉት ወሎዬዎች ናቸዉ።ወለጋ ወሎዬ አማራዎች፣ ሸዋሮቢትና ጨና ወሎዬ ኦሮሞዎች ናቸዉ!!!» ይላል በሶስት ትዕምርተ አጋኖ።ቀጠለም «ፖለቲከኖቹ ወለዬዎችን በመግደል የፖለቲካ ቁማራቸውን ይጫወታሉ!» እያለ 
ዳዉድ አብራር «መንግስት የህዝብን ደህንነት ማስጠበቅ ካልቻለ ስልጣኑን ሊለቅ ይገባል» አለ በፌስ ቡክ።ዮናታን ይማኑ መፍትሔ ይጠቁማል።«በጋራ ቆሞ መታገል ነው።» ነገዱ ደስታ ደግሞ «ተባብረን ለዓለም ፍርድ ቤት እናቅርባቸዉ» አለ ወይም አለች በፌስ ቡክ።
                                                  
ወደ ሁለተኛዉ ርዕስ እንለፍ።ኢትዮጵያና ሱዳን እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር ከ1902 ጀምሮ የገጠሙት  የአዋሳኝ ድንበር ግዛት ይገበኛል ዉዝግብ ሰሞኑን ጠጠር፣ጠንከር ብሎ ምላጭ እስከማሳብ ደርሷልም።አወዛጋቢዉን የአልፋሻቅ ግዛትን አብዛኛ አካባቢ ከሕዳር 2020 ጀምሮ የምትቆጣጠረዉ ሱዳን ሰሞኑን የኢትዮጵያ ጦር የማረካቸዉን 6 ወታደሮችና አንድ ሲቢል ገድሎብኛል በማለት ኢትዮጵያን ወንጅላለች።
የኢትዮጵያ መንግስት የሱዳንን ወቀሳ አስተባብሏል።ሰዎቹ የተገደሉት የሱዳን ጦር በአካባቢዉ ከሰፈረዉ ሚሊሺያ ጋር ዉጊያ በመግጠሙ እንደሆነ የኢትዮጵያ ባለስልጣናት አስታዉቀዋል።ይሁንና የሱዳን ጦር የሟች ወገኖችቹን ደም ለመበቀል የኢትዮጵያን ግዛት በከባድ ጦር መሳሪያ ሲደበድብ ነዉ የሰነበተዉ።
የሁለቱ ሐገራት ወታደራዊ ቁርቁስ የሚያስከትለዉ መዘዝ ሲተነተን የሱዳን ወታደራዊ ገዢ ጄኔራል አብዱልፈታሕ አል ቡርሐንና የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ አሕመድ ባለፈዉ ማክሰኞ ናይሮቢ-ኬንያ ዉስጥ ተገናኝተዉ ጠቡን በድርድር ለማርገብ መስማማታቸዉን አስታዉቀዋል።የስምምነቱ ዝርዝር ይዘት ግን በዉል አልተነገረም።
አብረሐም ይስሐቅ  በፌስ ቡክ «የሀገር ዳር ድበርን አሳልፎ ሰጥቶ አብረን ነን ማለት የዳር ድበሩን አዋሳኚ ሰው መናቅ እጁ መልካምነት አደለም» የሚል አስተያየት አስፍሯል።በዶሬ ታምራት በበኩሉ «እቤት ሳንስማማ ከጎረቤት መስማማት ምን ሊረባን። ወይስ ቤታችንን እያፈረስን ማምለጫችንን እያመቻቸን ነው!?» በቃለ አጋኖ የታጀበ ጥያቄ ነዉ።ሲስ ላቭ ግን «ያምራል » አለ የሁለቱን መሪዎች ፎቶ ግርፍ መሆን አለበት ግን «ከተሳካ» ብሎ አከለበት።
ኮቦቦ  አበራ «ለረጅም አመታት በሱዳን ቁንጮ ከተሞች ተዘዋዉሬ ኖሬያለሁ» እያለ ይተርካል።«ሱዳናዉያን ለእትዮጵያ ያላቸው ፍቅር የተለየ ነዉ። አመራሮች ያመጡት ችግር ሕዝቡን ሁሉ ለእሰጥ አገባ ዳርጎታል እንጂ።
ኢድሪስ አሕመድ ሙሔም በኮቦቦ አስተያየት ይስማማል።«የሱዳን ህዝብ 75% የኢትዮጵያን ህዝብ ይወዳል የኛም እደዛው። መሪዎቹ ላይ ግን ያሰራር ችግር በጣም አለ።» ኢድሪስ አሕመድ በፌስ ቡክ የሰጠዉ አስተያየት ነዉ።አየለ ሌንዳሞ እሱም በፌስ ቡክ አጭር መልዕክት አስፍሯል።«ባስቸኳይ የኢትዮጵያን መሬት ለቅቀዉ ይዉጡ» ትላለች መልዕክቱ።በዚሁ ይብቃን።

ምስል፦ Alemenew Mekonnen/DW
ምስል፦ Nariman El-Mofty/AP/picture alliance
ምስል፦ G. Fischer/blickwinkel/picture alliance

ነጋሽ መሐመድ 

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW