1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት-የወደብ ጥያቄ፣ የአዉሮፕላን ግዢና ድርድር

ዓርብ፣ ኅዳር 7 2016

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ አሕመድ ባለፈዉ ጥቅምት 2፣ 2016 ኢትዮጵያ የባሕር በር እንደሚያስፈልጋት ካስታወቁ ወዲሕ የወደብ ጉዳይ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ወደብ ያላቸዉ የኢትዮጵያ አጎራባች ሐገራት መንግስታትና ሕዝብ ርዕስም ሆኗል።

 የዘንድሮዉ የዱባይ የአየር ትርዒት
የኢትዮጵያ አየር መንገድ 31 አዉሮፕላኖች ለመግዛት የተስማማዉ በዱባዩ የአየር ትርዒት ወቅትምስል Kamran Jebreili/AP Photo/picture alliance

የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት-የወደብ ጥያቄ፣ የአዉሮፕላን ግዢና ድርድር

This browser does not support the audio element.

የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት በሳምንቱ ዉስጥ የበርካታ ተከታታዮችን አስተያየቶች ከሳቡ የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ዘገቦች ለዛሬዉ በሶስቱ ላይ ያተኩራል።የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ አሕመድ ሥለ መንግስታቸዉ የወደብ ጥያቄ ከሐገሪቱ ምክር ቤት አባላት ለቀረቡ ጥያቄዎች የሰጡትን መልስና ማብራሪያ በቃኘዉ ዘገባ ላይ የተሰጠዉ አስተያየት ቀዳሚዉ ነዉ።

የኢትዮጵያ ዓየር መንገድ 31 አዳዲስና ዘመናይ አዉሮፕላኖችን ከአሜሪካዉ አዉሮፕላን አምራች ኩባንያ ቦይንግ ለመግዛት መስምማቱን በቃኘዉ ዘገባ ላይ የተሰጡ አስተያየቶች ተከትለዉ፣ የኢትዮጵያ መንግስትና የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት (ኦነሠ-በምሕፃሩ) ሥለሚያደርጉት ድርድር የተሰጡ አስተያዮቶች ያሰልሳሉ።ከመጀመሪያዉ እንጀምራል።

 

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ አሕመድ ባለፈዉ ጥቅምት 2፣ 2016 ኢትዮጵያ የባሕር በር እንደሚያስፈልጋት ካስታወቁ ወዲሕ የወደብ ጉዳይ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ወደብ ያላቸዉ የኢትዮጵያ አጎራባች ሐገራት መንግስታትና ሕዝብ ርዕስም ሆኗል።የጠቅላይ ሚንስትሩን አስተያየት ኤርትራን የመሳሰሉ መንግስታት የጦር ነት ዛቻ፣ አንዳዶች የትኩረት አቅጣጫ ለማሳት፣ሌሎች ተገቢ ግን ጊዜዉን ያላገነዘበ እያሉ መቃወም፣ መጠራጠር መደገፍና ማሰላሰላቸዉን እንደቀጠሉ ነዉ።

ወደብ

ባለፈዉ ማክሰኞቹ የተሰበሰቡት የኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላትም ጥያቄዉን እንደገና ለጠቅላይ ሚንስትሩ አንስተዉ ጠቅላይ ሚንስትሩ ተጨማሪ መልስና ማብራሪያ ሰጥተዉበታል።የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተከታታዮችም የየራሳቸዉን አስተያየት እየሰጡ ነዉ።ሪድዋን ሁሴን ሺፋ በፌስ ቡክ «ኢትዮጵያ የባህር በር የስፈልጋታል!» ይላል ባጭሩ ግን ቃል አጋኖ አክሎበታል።

ትግስት ትግስትየሜርሲ የሚል የፌስ ቡክ ስም ያላት አስተያየት ሰጪ እንደ ሪድዋን ሁሉ «ያስፈልጋል» ትላለች።«ወደብ ፖለቲካ አይደለም።» አለች።አበቃችም ትዕግስት።እስራኤል አለማየሁ ግን አስፈላጊዉ «ሰላም» ነዉ ባይ ናት።«ሠላም ለሁሉም» በእንግሊዝኛ እንደፃችዉ።

ጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ አሕመድ ምስል AP/picture alliance

ብሮከር ያሲኖ፣ በሰፊዉ ባሰፈረዉ አስተያየቱ «ይህ የመብት ብቻ ሳይሆን የህልውና ጉዳይ መሆኑ የሚያጠያይቅ፣ የሚያወያይ አይመስለኝም።» ብሎ ጀመረ ብሮከር ያሲኖ።«ግብፆች የአባይ ውሃ ከማንም ይመንጭ ከማን የህልውናቸው ጉዳይ በመሆኑ ያለቅንጣት ይሉኝታ የሚያሻቸው የውሃ መጠን ንክች እንዳይደረግ ይደራደራሉ፣ ይሞግታሉ፣ ይጮሃሉ ወዘተ.... ይህም ተመሳሳይ ነገር ነው።» እያለ ይከራከራል ብሮከር ያሲኖ የተባለ አስተያየት ሰጪ።

አበቃ ዘመኑ፣- ግን ጊዜዉ አሁን አይደለም ዓይነት ባይነዉ።«አሁን የህዝብ ፍላጎት በጦርነት በረሀብ መሞት ይቁም፣ የደሀ ቤት መፍረስ የህዝብ በየቢሮዉ መንገላታት፣ ጉቦ፣ ሴት ደፈራ ይቁም የኑሮ ውድነት ይቀንስ ነው።» ይላል አበቃ ዘመኑ በፌስ ቦክ ግን አላበቃም »ዳቦ የራበው ህዝብ አይደለም አብይን እውነተኛው ክርስቶስን አይሰማም እርቦታል እና።» አሁን አበቃ።አበቃ ዘመኑ።አብዱልወሐብ ገቢ ሄይ እሱም በፌስ ቡክ ረጅም አስተያየት ሰጥቷል።ከረጅሙ አስተያየት እንጥቀስ ባጭሩ፣- «ኢትዮጵያ ወደብ ያስፈልጋታል የሚለው አቋም የዶ/ር አብይ ብቻ ሳይሆን የሀገሪቷ ብሔርብሔረሰብ በሙሉ አቋምም ጥቅምም ነው።የመሪ ብቻ አድርጎ መሳሉ ስህተት ነው።» አብዱልወሐብ ገቢ ሄይ ነዉ።

ነጋሽ ኤርትራ «የኢትዮጵያ መንግስት በኤርትራ ሉዓላዊ መሬትና ባሕር ላይ ግልፅ ጦርነት አዉጇል።» አለ በእንግሊዝኛ፣ በፌስ ቡክ እና ቀጠለ «የኢትዮጵያ መንግስት እንዲሕ ዓይነት ትርጉም አልባ ነገር በጅቡቲና ሶማሊያ ላይ አልቃጣም።» እያለ።የነጋሽ ኤርትራ አስተያየት ነዉ።ፀጋዬ ካስ ለጠንካራዉ የነጋሽ ኤርትራ አስተያየት መልስ ብጤ አለዉ።«ጁቡቲና ኤርትራ የኢትዮጵያ ናቸዉ።አንድ ቀን ማለት አንድ ቀን ነዉ» አለ እሱም በእንግሊዝኛ።

             የአዉሮፕላኖች ግዢ

 

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከአሜሪካዉ አዉሮፕላን አምራች ኩባንያ ቦይንግ፣ 31 ዘመናይ አዉሮፕላኖች ለመግዛት መዋዋሉ ለኢትዮጵያዉያን ከፖለቲካ-ዉዝግቡ ፈንጠር ወደ ምጣኔ ሐብት ንግዱ ቀረብ ያለ ዜና ነዉ-ለሳምንቱ።ዱባይ-የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ዉስጥ በተደረገዉ የአዉሮፕላን ትርዒት ላይ በተፈረመዉ ዉል መሠረት የኢትዮጵያ አየር መንገድ 11 ቦይንግ 787-9 እና 20 ቦይንግ 737 ማክስ 8 የተባሉትን ዘመናይ አዉሮፕላኖች ይገዛል።የሸመታ-ሽያጩን የሚያዉቁ እንደሚሉት አፍሪቃ ዉስጥ አንድ አየር መንገድ ባንድ ጊዜ ይሕን ያሕል አዉሮፕላኖች ሲገዛ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የመጀመሪያዉ ነዉ።

የኢትዮጵያ አየር መንገድምስል Kola Sulaimon/AFP/Getty Images

ብርሐኑ አስናቀ በፌስ ቡክ «ለአገራችን ትልቅ እድል ነው።ቀጥሉበት። በርቱ» ይላል።ለሁሉም ጊዜ አለዉ ግን ተቃራኒዉን ባይ ነዉ።«እና ከእኔ ህይወት ጋ ምን አገናኘው?» ይጠይቃል-ለሁሉም ጊዜ አለዉ።ሐምዱ ሐምዱ ባንፃሩ «በዚሕ ይቀጥል ፣ኩራታችን» አለ አየር መንገዱን።ዳዊት ጀስቲን ማን፣ እሱም በፌስ ቡክ «ዳቦ እየራበን፣ በስደት፣ በበርሀም እየተቃጠልን፣» እያለ አዘገመና---- «አውሮፕላን ምን ይሰራልናል። ጦርነቱ ይቁምልን» ብሎ አሳረገ።ዳዊት ጀስቲን ማን

ማርክ መድሕን፣ «በመስተንግዶው ፣ በአስተማማኝነቱ፣ በቅልጥፍናዉ በአጠቃላይ የኢትዮጵያን ስም ከፍ ያደረገ ተቋም ስለሆነ እኛ ኢትዮጵያዉያን ብቻ ሳንሆን የአፍሪካ ኩራታችን ነዉ።» በማለት ያወድሰዋል አየር መንገዱን።

                                           

ድርድር

የኢትዮጵያ መንግስት እና የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት (ኦነሠ በምሕጻሩ) ዳሬ ኤስ ሰላም ታንዛኒያ ዉስጥ ድርድር መጀመራቸዉን ከሰማን ትናንት 10ኛ ቀናችን።ይሕን ዝግጅት እስካጠናቀርንበት እስከ ትናንት ሐሙስ ማምሻ ድረስ ድርድሩ ስለደረሰበት ደረጃ በይፋ የተነገረ ነገር የለም።

ይሁንና አንዳድ ምንጮች  እንደጠቆሙት ድርድሩ በቀና መንፈስ እንደቀጠለ ነዉ።ባለፉት አምስት ዓመታት የኦሮሚያ ክልልን የሚያብጠዉ ግጭት  በሺሕ የሚቆጠር ሕዝብ ፈጅቷል።ብዙ ሺዎች ተፈናቅለዋል።የሚሊዮኖች ሐብት ንብረት ወድሟል።

ተደራዳሪዎች አስከፊዉን ግጭት በሰላም እንዲያቆሙ ከሕዝብና ከማሕበራት የሚደረገዉ ግፊት እንደ ድርድሩ ሁሉ እንደቀጠለ ነዉ።ስንታየሁ መስፍንም «ሠላም ለሁሉም» ይላል-በፌስ ቡክ።«ያማራ ክልልንም ሠላም አስመልሱልን እባካቹህ» አከለ አቤቱታ ብጤ ነዉ።ተወከል ፈረሐ ግን ኃላፊነቱን ለመንግስት ይሰጣል «መጀማሪያ መንግስት ቁርጠኛ ይሁን።» ባይ ነዉ ተወከል።እድሪስ አማን በፈጣሪዉ ይመጀናል።«በአላህ ፍቃድ ኦሮምያ በቅርብ ግዜ ሁሉም ዜጎች ሊኖሩባት የሚመኙዋት ትሆናለች። ሁሉም በእሱ እጅ ነው። እንሻ አላህ በቅር ግዜ» አበቃ። እድሪስ አማን ነዉ ደዓ አድራጊዉ።

የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት አርማምስል Seyoum Getu/DW

ቢፍቱ የኑስም ፈጣሪዉን ይማፀናል-በፌስ ቡክ «ፈጣሪ ሠላሙን ያውርድልን» እያለ።ሰቆጣ ኒዊስ ፔፔር የሚል የፌስ ቡክ ስም ያለዉ አስተያየት ሰጪ ደግሞ «ጥሩ ነዉ ሰላም ይሻለናል» አለ።ዮናስ ልዑል ዘለግ ባለ የፌስ ቡክ አስተያየቱ «የኦሮሚያ ነዋሪዎች ብቻ ሳይሆን የሰላም ወዳዱ የመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ብትሉት በግሌ ይመቸኛል። የአንዱ ሰላም መሆን የሁሉም ደህንነትና ደስታ ስለሆነ።» ይላል።-ዮናስ ልዑል።

መኮንን መንገሻ በፌስ ቡክ እንደፃፈዉ ተስፋ የቆረጠ ይመስላል።«ምንም ተስፋ የለም-በዓብይ ዘመን።» ደበላ ቀልቤሳ ግን የመኮንን መንገሻን አስተያየት ይቃረናል።«ተስፋ ብቻ አይዴለም ፀሎትም ጀምሬያለሁ» ብሎ።በዚሁ ይብቃን።መልካም የሳምንት መጨረሻ።

ነጋሽ መሐመድ 

ታምራት ዲንሳ

 

 

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW