የማኀበረ ግዩራን የሽልማት ሥነ ስርዓት
ሐሙስ፣ ግንቦት 21 2017
ማኀበረ ግዩራን ዘረ ኢትዮጵያ ወይንም በእንግሊዝኛ ምህፃሩ ሲድ፣በኢትዮጵያና በዚህ በዩናይትድ ስቴትስ በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ከፍተኛ አስተዋጾኦ ላደረጉ ድርጅቶችና ግለሰቦች የዕውቅና ሽልማት በመስጠት፣ ዘንድሮ 32 ዓመት ሆነው። ድርጅቱ በዚህ መስክ፣አሜሪካ ውስጥ ለረጅም ጊዜ ካገለግሉ የትውልደ ኢትዮጵያውያን ድርጅቶች መኻከል አንዱ መሆኑን፣ መስራችና ፕሬዚደንቱ አቶ አክሊሉ ደምሴ ለዶቼ ቬለ ገልጸዋል።
የማኀበረ ግዩራን ዘረ ኢትዮጵያ ዕውቅናና ሽልማት
"የዘንድሮ፣32 ዓመታችን ነው፤ለብዙ ጊዜ ኖረናል። የዘንድሮው ከሌሎች ጊዜያት ለየት የሚያደርገው አንደኛውና ዋነኛው የምንለው፣በምስራቃዊ ዳርቻ ያሉ ሰዎች ነበሩ ተማሪዎች የሚጠቁሙት፤ ዘንድሮ ግን ከሲያትል ዋሽንግተን፣ከኦሃዮ፣ከሂውስተን ቴክሳስ እና እነዚህን ከመሳሰሉ ቦታዎች እና ከቨርጂኒያ ፣ከፊላዴልፊያ፣ከዋሽንግተን ነው ተማሪዎቹ የመጡት። እና ይሄ የሚያሳየው አሜሪካ ውስጥ የተስፋፋ ዕውቀት አለው ማለት ነው ማኀበረ ግዩራን ዘረ ኢትዮጵያ።"
ተሸላሚዎቹ እነማን ናቸው?
ሲድ ኢትዮጵያ፣ዘንድሮ ዕውቅና ስለሰጣቸው ግለሰቦችና አንድ ድርጅት አበርክቶን በተመለከተ፣ የማኀበረ ግዩራን ዘረ ኢትዮጵያ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ሰለሞን ገብሩ እንደሚከተለው አስረድተዋል።
"በተለይም ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ኃይማኖት ጋር በተያያዘ የቅርስ ጥበቃ የሚያደርገው ሐመረ ብርሃን፣ አቶ አጎናፍር ሽፈራው፣ ዶክተር ሞገስ ገብረማርያም፣ በህክምና ውስጥ በዚህ በከተማውና አከባቢው ብዙ ዓመት ያገለግሉ ለሕብረተሰባችን፣እንደዚሁም ደግሞ አርቲስት ሮፍናን እና ዶክተር ተሰማ ገብረ እግዚአብሔር ናሽናል ሳይንስ ፋውንዴሽን ውስጥ ትልቅ ሳይንቲስት የሆነ እና አርቲስት ተስፋዬ ሲማን፣ ድርጅታችን ተሸላሚ አድርጓል።"
ይኸው አንጋፋ ድርጅት፣መልካም ለሰሩ ኢትዮጵያውያን ግለሰቦችና ድርጅቶች ሽልማትና አክብሮት ከመቸር በተጨማሪ፣በትምህርታቸው የላቀ ውጤት ያስመዘገቡ ተማሪዎችንም መርጦ በመሸለም ማበረታቱን ዶክተር ሰሎሞን ገልጸዋል።
"አዳጊ የሆኑ፣ወደፊት ደግሞ ኮሌጅ በመግባት ለኢትዮጵያ ትልቅ አስተዋጽኦ ሊያበረክቱ ይችላሉ የሚላቸውን የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች የተለያየ መመዘኛዎች በማውጣት፣ከፍተኛ ጂፒኤ ያመጡ፣የኮሌጅ ትምህርታቸውንም በብዛት የወሰዱ ልጆችን ከስድስት ሰባት ግዛቶች፣ከፔንሲልቫኒያ፣ከኦሃዮ፣ከፊላዴልፊያ፣ከቨርጂኒያ፣ከዋሽንግተን ዲሲ እንደዚሁም ቴክሳስ ስምንት ልጆችን ሸልሟል።እነዚህ ስምንት ልጆች በተለያየ ጥሩ ጥሩ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ተቀባይነት አግኝተው ወደ ዩኒቨርሲቲ ለመግባት እየተዘጋጁ ነው።"
ድርጅቱ ያበረከተው ፋይዳ
ማኀበረ ግዩራን ዘረ ኢትዮጵያ፣ ምሳሌነት ያላቸውን ሰዎች በማበረታታት፣ተተኪው ትውልድ በሥነ ምግባርና በሙያ እንደታነጹ በማድረግ፣ትልቅ የሆነ ፋይዳ እያበረከተ መሆኑን ከፕሬዚዳንቱ ገለጻ ለመረደት ተችሏል።
"በሕይወት እያሉ ሰዎችን ማክበርና ለልጆቻችን ትልልቅ ምሳሌ ይሆናሉ ተብሎ፣ ከራሳችን ወገኖች ለልጆቹ ስናሳያቸው፣እነዛ ልጆች የሚጠበቅባቸውን አደራ ከትልልቆቹ እያዩ፣ ደግሞ ተመልካች ውስጥ ያሉት ህፃናት ልጆች የከፍተኛ ተመራቂዎችን እያዩ በጣም እየተነሳሱ ብዙ ቦታ ደርሰዋልና እዚህም ሃገር አሁንም ቢሆን ባሉበት በህክምናም ሆነ በሙዚቃ በማንኛውም መስክ ያሉ ሰዎች ትልቅ ቦታ የደረሱ ወገኖቻቸውንና ሃገራቸውን እንደሚረዱ አንጠራጠርም።"ብለዋል።
ታሪኩ ኃይሉ
እሸቴ በቀለ
ታምራት ዲንሳ