1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት የሰኔ 12 ቀን 2017 መሰናዶ

ሐሙስ፣ ሰኔ 12 2017

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ተወካዮች ጋር የሚያደርጓቸው ውይይቶች፣ መርማሪዎች ከሞት በመለስ ለሚፈጽሟቸው ወንጀሎች ተጠያቂ እንደማይሆኑ ይለፍ የሰጠው አዋጅ እና የትራምፕ የጉዞ ማዕቀብ በሳምንቱ መነጋገሪያ ከነበሩ እጅግ በርካታ ጉድዮች መካከል ነበሩ።

ሶሻል ሚዲያ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሚያደርጓቸው ውይይቶች፣ መርማሪዎች ከሞት በመለስ ለሚፈጽሟቸው ወንጀሎች ተጠያቂ እንደማይሆኑ ይለፍ የሰጠው አዋጅ እና ትራምፕ የጉዞ ማዕቀብ መነጋገሪያ ነበሩ።ምስል፦ Jakub Porzycki/NurPhoto/picture alliance

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት የሰኔ 12 ቀን 2017 መሰናዶ

This browser does not support the audio element.

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ነጋዴዎች፣ መምህራን እና የጥበብ ሰዎችን ጨምሮ ከተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ተወካዮች ጋር የሚያደርጓቸው ውይይቶች በመገናኛ ብዙኃን በመተላለፍ ላይ ይገኛሉ። ውይይቶቹ ከመሠራጨታቸው በፊት ምስሎች በመንግሥት፣ በገዥው ብልጽግና ፓርቲ እና በደጋፊዎቻቸው መዋቅሮች የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎችን ያጥለቀልቃሉ።

ከዚያ ከአንድ ሰዓት በላይ የሚረዝሙት ቪዲዮዎች ይከተላሉ። ውይይቶች የሚሠራጩት የፌድራል መንግሥት እና የክልል መስተዳድሮች እንዲሁም ገዥው ብልጽግና ፓርቲ በሚቆጣጠሯቸው የቴሌቭዥን ጣቢያዎች ነው።

በውይይቶቹ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄ ይቀበላሉ። ከዚያ ረዘም ያለ ማብራሪያ ይሰጣሉ። ከመምህራን ሲወያዩ ትምህርት ሚኒስትሩ ታዳሚ ናቸው። ከንግድ ማኅበረሰቡ ተወካዮች ሲገናኙ የመንግሥት ባለሥልጣናት በቦታው ቢኖሩም አስተያየት ሲሰጡ አልታዩም።

ውይይቶቹ ምን ይፈይዳሉ?

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ውይይቶቹ የሚካሔዱት የሚቀጥለውን ዓመት ሥራ ከመታቀዱ በፊት ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር በመወያየት “ግብዓት መሆን የሚገባቸው ጉዳዮች ካሉ” በሚል እንደሆነ ተናግረዋል። የማኅበራዊ ድረ-ገጾች ተጠቃሚዎች ግን የተለያዩ ሐሳቦች ይሰጣሉ።

ዐቢይ ከፖለቲከኞች ጋር ውይይት ማድረጋቸውን በፎቶግራፍ አስደግፈው በገለጹበት የፌስቡክ መረጃ ሥር ነስሩ ኡስማኖ “የኢትዮጵያን ዴሞክራሲ ለመገንባት የተባረከ ውሳኔ ነው። ለኢትዮጵያ ብልጽግና ብዙ ጥቅም አለው” የሚል አስተያየት አስፍረዋል። ሲሳይ ደምሴ “ከአቢቹ ጋር ዛሬም እንደ ትላንቱ ፈተናዎችን በድል እንሻገራለን ብልጽግናችንንም እውን እናደርጋለን” ሲሉ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የፌስቡክ ገጽ በተለጠፉ ፎቶግራፎች ሥር ጽፈዋል።

ለማ መኩሪያ ደግሞ “የበሰለ አመራር ሕዝብ ውስጥ ላሉ ባለሙያተኞች ጆሮ በመስጠት የነገን ኢትዮጵያ ለማበልፅግ መሰረት ይጥላል” የሚል እምነት አላቸው። ሔዋን አብርሐም “ጦርነት ከዉስጥ እና ከዉጭ እያመሳት ባለበት በዚህ ዘመን ይህንን ድንቅ ሥራ መሥራት መቻሉ በጣም የሚያስገርም ነው” የሚል አስተያየት ጽፈዋል።

በማኅበራዊ መገናኛ ድረ-ገጾች በውይይቶቹ የሚሳለቁ አስተያየቶች የጻፉም ይገኛሉ። ደጀኔ ጌታቸው “እኛም እየተጠባበቅን ነው፤ ከአብይ ጋር ለመወያየት የጎዳና ተዳዳሪዎች እና ቤት አልባ ወጣቶች” ሲሉ በፌስቡክ አስፍረዋል። መሐመድ ዑመር “የቤት ሰራተኞችም ሰብስበን ብለዋል” የሚል ለስላቅ የሚቀርብ አስተያየት ሰጥተዋል።

“ፓርቲያችን መንግስታችን በልማት ምክንያት የምናፈናቅለውን ህዝብ ሰብአዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን እየጎዳ ነው። ካሳ ክፍያ ሳይከፍል፣ ምትክ ቦታ እና ቤት ሳይሰጥ በዘፈቀደ እስር እና ድብደባ እየተፈፀመ ነው” የሚሉት አቡ ኡዎይስ “ለምንድን ነው መብታቸው የማይከበረው?” ሲሉ ይጠይቃሉ።

ጋሻው አድጎ “ውይይት ብቻውን ምን ያደርጋል? ዳቦ ሲጨመርበት ነውጅ” የሚል ሐሳብ አላቸው። አበበ ምንተስኖት “ወሬ ልማት እና ሰላም አይሆንም” ሲሉ መሐመድ ዑመር ባቲ “ወሬ ብቻ ይሰለቻል” በማለት ነቅፈዋል። ወማዶ ዲራጎ “ምርጫ ሲደርስ የተለመደ ነው” ሲሉ ሕይወት መኮንን “ምርጫ ደረሰ መሰል” በማለት ተቀራራቢ አስተያየት አስፍረዋል። 

ሐብተማርያም መንጌ “ውይይት ሳይሆን የገጽታ ግንባታ ነው” የሚል አቋም አላቸው። ደመቀ ጫኔ “መፍትሔ የሌለው ስብሰባ፤ አስፈራርቶ እና ወቅሶ መስደድ ነው እንዴ? መፍትሔ ማለት?” ሲሉ ጠይቀዋል። ምሥጋናው ወርቁ “የካድሬ ስብሰባ ነው” ሲሉ አጣጥለውታል። አሼ ሔሮ “እኛኮ ስብሰባ፣ ውይይት ወይም ወሬ ጠግበናል። ዳቦ አጣን እንጂ” የሚል አስተያየት አላቸው። ሰዒድ ሐሰን ደግሞ “ብዙዎች እንደሚሉት ሴረኛ ቢሆኑም እንኳ ከአንደበትዎ የሚወጣው ንግግር ከልብዎ የተቀዳ አይደለም ብየ እንዳምን አላደረገኝም። ሁሉም ንግግሮች በጅምላ ፍሬ አልባ ናቸው ብለው ከሚደመድሙት አይደለሁም” ብለዋል።

ሥጋት ያጫረው ንዑስ አንቀጽ

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያጸደቀው “በወንጀል የተገኘ ንብረት ሕጋዊ ማስመሰል እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳትን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር” የተዘጋጀ አዋጅ የፈጠረው ሥጋት በማኅበራዊ ድረ-ገጾች በስፋት ተንጸባርቋል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያጸደቀው “በወንጀል የተገኘ ንብረት ሕጋዊ ማስመሰል እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳትን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር” የተዘጋጀ አዋጅ የፈጠረው ሥጋት በማኅበራዊ ድረ-ገጾች በስፋት ተንጸባርቋል።ምስል፦ Solomon Muchie/DW

በተለይ ለበርካቶች ሥጋት የሆነው “በዚህ አዋጅ መሠረት በሽፋን ሥር የሚደረግ ምርመራ ወይም በቁጥጥር ሥር የሚደረግ ማስተላለፍን እንዲያስፈጽም የተመደበ ሰው በግዴታው ላይ እያለ ከአቅሙ በላይ በሆነ ምክንያት እና ከፈቃዱ ውጩ ሆኖ ከግድያ ወንጀል በስተቀር ለሚፈጽመው የወንጀል ድርጊት የወንጀል ክስ አይቀርብበትም” የሚል ንዑስ አንቀጽ ማካተቱ ነው።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በተደረገው ውይይት ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአዋጁ ላይ የሰላ ትችት ቢሰነዝሩም በሶስት ተቃውሞ እና በአንድ ድምፀ ተአቅቦ በአብላጫ ድምፅ ከመጽደቅ አላቆሙትም። ታደሰ የኔዓለም “ኢትዮጵያ ፓርላማ ቀርቦ ሳይፀድቅ የቀረ ነገር ንገረኝ እስኪ። ገዢው ፓርቲ የሆነ ነገር ይዞ ይቀርባል ወንበሩን በአብላጫ የያዘው እራሱ ስለሆነ ይጥቀም አይጥቀም አይመለከታቸውም” በማለት በሀገሪቱ የሥልጣን አወቃቀር ከፍተኛውን ቦታ የያዘውን ሕግ አውጪ ምክር ቤት በኃይል ታዝበውታል። ውቤ ውብ አዲስ “ምንም የማያውቁ ጉዶች እጅ ማውጣት ነው እንጂ ስራቸው ምን እንደ ሆነ የት ያውቃሉ” የሚል አስተያየት ዶይቼ ቬለ በጉዳዩ ላይ በሠራው ዘገባ ሥር አስፍረዋል።

የሰብአዊ መብቶች ተሟጋቹ ያሬድ ኃይለማርያም በሕጉ “ከአቅሙ በላይ በሆነ ምክንያት እና ከፈቃዱ ውጭ ሆኖ የሚለው ሃሳብ በግልጽ ያልተቀመጠ በመሆኑ ለትርጉም የተጋለጠ ነው። የትኞቹ ሁኔታዎች ናቸው ከመርማሪው አቅም ወይም ፈቃድ ውጪ ተብለው የሚበየኑት የሚለው ግልጽ አይደለም” ሲሉ ተችተዋል። አቶ ያሬድ “ከግድያ ወንጀል በስተቀር ለሚፈጽመው የወንጀል ድርጊት የወንጀል ክስ አይቀርብበትም የሚለው እጅግ አደገኛ አገላለጽ ደግሞ መርማሪው ከግድያ መልስ በተመርማሪው ላይ የማሰቃየት (torture) ጾታዊ ጥቃት፣ ሙስና፣ ዝርፊያ፣ አፍኖ መሠወር የመሳሰሉ አሰቃቂ ወንጀሎችን ቢፈጽም አይጠየቅም ማለት ነው” በማለት በፌስቡክ ሐሳባቸውን አስፍረዋል።

ጌታሁን ወርቁ “በጣም አደገኛ ሕግ። የሕገ መንግሥቱን ምዕራፍ 3 የሻረ። ዜጋ እንዳይሞት አድርጎ የማሰቃየት ሕጋዊ መብት የሚሰጥ ሕግ” ሲሉ ተችተዋል። ጌታሁን “እነ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ተብሰክስከው ይሆን?” ሲሉ ይጠይቃሉ። ብሩክ “ይች አገርማ ሲኦል እየሆነች ነዉ። ብቻ ነፍስ አይጥፋ እንጂ መርማሪ እንደፈለገ መቀጥቀጥ ይችላል እያሉን ነዉ” ሲሉ ጽፈዋል። ምህረት “በህግ የማይዳኝ ሰለህግ የማያገባው ህግ አስፈፃሚ…ኖርናታ” ይላሉ። ብሩክ ደጀኔ “በጣም ያሳዝናል። የፀረ ሽብር ህጉን ያሻሽላል ብለን ጠብቀነው የነበረው መንግስት ሌላ የባሰ አፋኝ ህግ አፀደቀ” የሚል ትዝብት አላቸው።

ሽመልስ ቲ ፋንታሁን “በህግ የሚተዳደር ሐገር ከሆነ ሰዎች ለሚፈፅሙት በግል ወይም በቡድን የተደራጀ የትኛዉንም ወንጀል በመመርመርና በማረጋገጥ በህግ አግባብ ተጠያቂ ማድረግ ይገባል እንጂ ከመግደል በመለስ የትኛዉንም ወንጀል ቢፈፅም አይጠየቅም ማለት ህግ አልባ ከመሆን አይለይም። አንድ ሰዉ የአካል መጉደል ጉዳት ቢደርስበት ወይም ለመኖር በማይችልበት ሁኔታ ጥቃት ቢፈፀምበት አልሞተም ነዉ የሚባለዉ?” በማለት ጠይቀዋል። “መሞትማ ግልግል ነዉ” የሚሉት ሽመልስ “በእኔ እምነት ማንም ሰዉ በየትኛዉም ወንጀል ተሳትፎ ቢገኝ በሰብአዊ አያያዝ ለፍርድ መቅረብ ይገባዋል ብዬ አምናለሁ” ብለዋል።  

የፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ የ36 ሀገራት ዜጎች ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ የጉዞ ማዕቀብ የመጣል ሐሳብ እንዳለው ምስል፦ Alex Brandon/AP Photo/picture alliance

የትራምፕ የጉዞ ማዕቀብ

የፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ የ36 ሀገራት ዜጎች ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ የጉዞ ማዕቀብ የመጣል ሐሳብ እንዳለው በዚህ ሣምንት ተዘግቧል። የአሜሪካው ዋሽንግተን ፖስት እንደዘገበው በዩናይትድ ስቴትስ የውጪ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የውስጥ ማስታወሻ የጉዞ ዕቀባ ይጣልባቸዋል ተብለው ከሰፈሩ መካከል 25 የአፍሪካ ሀገራት ይገኙበታል። ግብጽ፣ ጅቡቲ፣ ናይጄሪያ እና ደቡብ ሱዳን በዝርዝሩ ውስጥ ከተካተቱ መካከል ናቸው። ትራምፕ በዚህ ወር በ12 ሀገራት ዜጎች ላይ ሙሉ በሌሎች ሰባት ሀገራት ዜጎች ላይ ደግሞ ከፊል የጉዞ ማዕቀብ ጥለዋል።

ሞሳላ “ኢትዮጵያ ራሷ በአሜሪካ ላይ ማዕቀብ መጣል አለባት” የሚል ሐሳብ አቅርበዋል። ወርቁ ከማን “ይህ ለአፍቃሬ አሜሪካን የሚያሳሰብ ቢሆንም ከእነ ችግሮቿ በሀገራችን ለመኖር ለመረጥነው ዜጐች አጀንዳ አይደለም ወይም አያሳስበንም” ብለዋል። በድሉ ጠናጋሻው የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ “በዚህ ሁኔታ ጠቅላላ አፍሪካዊያንን የሚያባርር ይመስለኛል” የሚል ሥጋታቸውን አጋርተዋል። ለሜሳ ጋዲሳ “ከአሜሪካ ወደ አገራችን የሚላከዉ ዶላር ካልታቀበ ሌላዉ ችግር የለዉም” የሚል አተያይ አላቸው።

ቡና ገበያ የሚል ስም በፌስቡክ የሚጠቀሙ ግለሰብ “እኛም ወደ አሜሪካ የምንከውን ቡና እና ጥራጥሬዎች ቀረጡን ወይም ታክሱን መጨመር አለብን። ምላሽማ መስጠት አለብን” ብለዋል። “ይሻላል” የሚሉት ካሳሁን ዲላ ደግሞ “ፖለቲከኛው ጉበኛው ሌባው መጠለያ ጫካ አረጋት እንደ አባይ በረሐ” የሚል አስተያየት ሰጥተዋል። አማረ ተክሌ “ትራምፕ ማለት ዓለምንም አሜሪካንንም ለመበጥበጥ የተመረጠ ሰው ነው” ሲሉ ነቅፈዋል። መኮንን ባይሳ ግን “ኧረ ተዉ ጋሽ ትራምፕ፤ አብሮ መኖሩ ይሻላል። ከሀብታም ቤት መርፌ ሊጠፋ ይችላልና” የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል።

እሸቴ በቀለ

ታምራት ዲንሳ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW