1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት የታኅሳስ 17 ቀን 2017 መሰናዶ

Eshete Bekele
ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 17 2017

የሶማሊያ ፕሬዝደንት ሐሰን ሼይክ ሞሐመድ እና ከፍተኛ ባለሥልጣኖቻቸው በኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ኤርትራ ጉብኝት አድርገዋል። የሲቪክ ድርጅቶች ዳግም መታገድ ሌላ አነጋጋሪ ጉዳይ ነው። ከብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ስብሰባ በኋላ ባለሥልጣናት የመንግሥትን ስኬት ከፍ አድርገው ቢያቀርቡም የዜጎች አስተያየት ከሹማምንቱ እጅግ የተለየ ሆኖ ይታያል።

የሶማሊያ ፕሬዝደንት ሐሰንይ ሼይክ ሞሐሙድ፣ የቱርክ ፕሬዝደንት ረቺብ ጠይብ ኤርዶኻን እና የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በአንካራ
የሶማሊያ ፕሬዝደንት ሐሰን ሼይክ ሞሐሙድ ውጪ ጉዳይ ሚኒስትራቸውን ወደ ግብጽ፣ ምክትል የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር እና የደሕንነት ኃላፊያቸውን ወደ ኢትዮጵያ ልከው ወደ ኤርትራ ያቀኑት በቱርክ አሸማጋይነት ከኢትዮጵያ ጋር የተፈጠረውን ውጥረት ወደፊት በሚደረግ ድርድር ለመፍታት የጋራ መግለጫ ከወጣ በኋላ ነው። ምስል Murat Kula//TUR Presidency/Handout/Anadolu/picture alliance

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት የታኅሳስ 17 ቀን 2017 መሰናዶ

This browser does not support the audio element.

የሶማሊያው ፕሬዝደንት ሐሰን ሼይክ ሞሐሙድ የኤርትራ ጉብኝታቸውን አጠናቀው ዛሬ ሐሙስ ወደ ሞቃዲሾ ተመልሰዋል። ፕሬዝደንቱ ወደ አስመራ ያቀኑት ውጪ ጉዳይ ሚኒስትራቸውን ወደ ግብጽ፣ ምክትል የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር እና የደሕንነት ኃላፊያቸውን ወደ ኢትዮጵያ ከላኩ በኋላ ነበር።

የፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ እና የፕሬዝደንት ሐሰን ሼይክ ሞሐሙድ የአስመራ ውይይት “የመደበኛ ምክክራቸው” አንድ አካል እንደሆነ የኤርትራ የማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ ገብረ መስቀል በኤክስ ባሰፈሩት መልዕክት ገልጸዋል።

ኢሳያስ በውይይቱ የአፍሪካ ቀንድ ቀጠና “ብዙውን ጊዜ ግጭት እና ቀውስ የመቀስቀስ አጀንዳ ከሚያራምድ የውጪ ጣልቃ ገብነት መላቀቅ”  እንደሚገባው መናገራቸውን የማነ ያሰፈሩት መልዕክት ይጠቁማል። ከዚህ ቀደም በአስመራ የተካሔደው የኤርትራ፣ የግብጽ እና የሶማሊያ መሪዎች ጉባኤ የሶማሊያን ሰላም እና መረጋጋት ከማረጋገጥ የዘለለ ዓላማ እንደሌለው ኢሳያስ ገልጸዋል።

ሐሰን ሼይክ ወደ አስመራ ያቀኑት በቱርክ ፕሬዝደንት ረቺብ ጣይብ ኤርዶኻን አሸማጋይነት ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር ተገናኝተው በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ መካከል የተፈጠረውን ውጥረት ወደፊት በሚካሔድ ድርድር ለመፍታት ከተስማሙ በኋላ በመሆኑ ትኩረት የሚስብ ነው።

የኢትዮጵያ መንግሥት ደጋፊዎች ፌስቡክ በመሳሰሉ ማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የጋራ መግለጫው “መንግሥት ለዘላቂ ሠላምና ፣ለበጎ ጉርብትና ብሎም በወንድማማችነት ስሜት ላይ ለሚገነባ የጋራ ብልጽግና በመትጋት ከመጡ አንፀባራቂ ውጤቶች ውስጥ አንዱ ነው” የሚል መልዕክት በብዛት አሰራጭተዋል።

በጋራ መግለጫው መሠረት ወደፊት የሚደረግ ድርድር ኢትዮጵያ የሶማሊያን ሉዓላዊነት አክብራ ከሶማሌላንድ ጋር የተፈራረመችን ሥምምነት እንድትተው ያደርጋታል ተብሎ ቢጠበቅም ፕሬዝደንት ሐሰን ሼይክ ሞሐሙድ ላይ ትችት የሰነዘሩ አልጠፉም።

አብዱል አሊ የተባሉየፌስቡክ ተጠቃሚ ፕሬዝደንቱ የፈረሙት የጋራ መግለጫ ሶማሊያን “ከዋና አጋሮቿ ኤርትራ እና ግብጽ ያገለለ የተሳሳተ እርምጃ” ብለውታል። መግለጫውን መሠረዝ አብዱል አሊ እንደሚሉት “ሶማሊያ ከኤርትራ እና ከግብጽ ጋር ያላትን ግንኙነት ለማረቅ ኹነኛ እርምጃ ነው።”

የጋራ መግለጫው ከተፈረመ በኋላ ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ የተበላሸ ግንኙነታቸውን ለማረቅ ፍላጎት እንዳላቸው ቢታይም በዶሎ ተፈጠረ የተባለው ግጭት መልሶ አጥልቶበታል። የኢትዮጵያ ውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር በፌስቡክ ባሰራጨው መግለጫ ለግጭቱ “የአፍሪካ ቀንድን ለማተራመስ ፍላጎት አላቸው” ያላቸውን “ሦስተኛ ወገኖች” ተጠያቂ አድርጓል።

የሶማሊያ ምክትል ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር አሊ ሞሐመድ ኦማር ከኢትዮጵያ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ምሥጋኑ አረጋ ጋር ተገናኝተው በሁለቱ ሀገራት መካከል ውይይቶች እና የሥራ ግንኙነቶቻቸውን ለማጠናከር መስማማታቸው ተገልጿል። ሶማሊያ እና ኢትዮጵያ አንዳቸው የሌላውን ሉዓላዊነት፣ ነጻነት እና የግዛት አንድነት ለማክበር በድጋሚ ቁርጠኝነታቸውን ማረጋገጣቸውን የሶማሊያ ውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት መግለጫ ይጠቁማል።

የኢትዮጵያ የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል ሬድዋን ሁሴን ከሶማሊያ ብሔራዊ ደሕንነት እና ጸጥታ ኤጀንሲ ኃላፊ አብዱላሒ ሞሐመድ አሊ ጋር በአዲስ አበባ ተገናኝተው ከከተወያዩ በኋላ “ከቅርብ ከሩቅም ሊነሱ የሚችሉ አደፍራሾችን ለማራቅ” መስማማታቸውን ገልጸዋል።

የሶማሊያ ባለሥልጣናት በግብጽ እና በኤርትራ ያደረጓቸው ጉብኝቶች ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እና ፕሬዝደንት ሐሰን ሼይክ ሞሐመድ ለመደራደር የደረሱበት ሥምምነት ላይ ምን አይነት ተጽዕኖ እንደሚያሳርፍ ወደፊት የሚታይ ይሆናል። ነገር ግን አሁንም ጦርነት ሊቀሰቀስ ይችላል የሚል ሥጋት ያላቸው አሉ።

አብዲናስር ሐሰን የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ “በሶማሊያ እና በኢትዮጵያ መካከል የሚደረግ ጦርነት የሕልውና ነው። አሁን በሥልጣን በሚገኙ ወይም ወደፊት በሚመጡ መንግሥታት መካከል የሚደረግ የትኛውም ሽምግልና ወይም ሥምምነት ማስታገሻ ብቻ ይሆናል” የሚል እምነታቸውን ጽፈዋል።

የሲቪክ ድርጅች መታገድ ያስከተለው ሥጋት

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ማዕከል የተባለው የሲቪክ ድርጅት በሲቪል ድርጅቶች ባለሥልጣን መታገዱን ይፋ አድርጓል። ማዕከሉ “ለሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች ጥበቃ ለማድረግ፣ ሙያዎ ክህሎታቸውን እንዲዳብር እና መብቶቻቸው” እንዲከበሩላቸው ከሕዳር 2013 ሲሰራ የቆየ ነው።

የኢትዮጵያ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ታኅሳስ 14 ቀን 2017 በጻፈው ደብዳቤ ከማንኛውም እንቅስቃሴ መታገዱ እንደተገለጸለት ማዕከሉ ዛሬ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። “ድርጅቱ ከተቋቋመበት ዓላማ ውጪ በመንቀሳቀሱ፣ ገለልተኛ አለመሆኑ፣ ግልጽ የሆነ የአደረጃጀት መዋቅር የሌለው መሆኑ እና ኃላፊነት በጎደለው መልኩ የተንቀሳቀሰ መሆኑ” ባለሥልጣኑ በጻፈው ደብዳቤ ለዕግዱ የቀረቡ ምክንያቶች ናቸው።

የመብቶች እና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል ከሁለት ሣምንታት በፊት “ከማንኛውም የሥራ እንቅስቃሴ” የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን መታገዱን አስታውቆ ነበር።ምስል CARD

አንጋፋው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ እና እና የሕግ ባለሙያዎች ለሰብአዊ መብቶች የተባሉ የሲቪክ ድርጅቶች ተመሳሳይ እጣ ፈንታ ገጥሟቸዋል። የመብቶች እና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል ከሁለት ሣምንታት በፊት “ከማንኛውም የሥራ እንቅስቃሴ” የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን መታገዱን አስታውቆ ነበር።

ዕገዳው ጉዳዩን በቅርብ ለሚከታተሉ ሥጋት የፈጠረ ነው። አሊ ሞሐመድ “ያለ ከሳሽ በድብቅ እና በፈለገዉ መንገድ ህዝቡን እንደፈለገ ለመጨፍለቅ እንዲመቸዉ ነዉ” ሲሉ መንግሥትን ተችተዋል። ኤፍሬም ማዴቦ በበኩላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሥልጣን ላይ እስካሉ ድረስ “ስለ ሰብዓዊ መብቶች መረገጥ፣ስለ ባለሥልጣኖች ዝርፊያ፣ስለ ህገወጥ እስር፣ መንግስት በሰላማዊ ዜጎች ላይ ስለሚፈፅመው ሰቆቃ፣ማፈናቀል እና ግድያ የሚናገር ሁሉ ግለሰብ ከሆነ ይታፈናል፣ እንደ ኢሰመጉ አይነት ተቋም ከሆነ ደሞ ይታገዳል” ሲሉ ጽፈዋል።

አሰፋ ሥልጣን የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ “ትክክል ይህ የሰብአዊ መብት ተቋም የምዕራባውያን አሻንጉሊት ነው። መንግሥት አስፈላጊውን ጠበቅ ያለ ክትትል ማድረግ አለበት” በማለት የእግድ እርምጃውን የሚደግፍ አስተያየት አስፍረዋል። ሐምዱ ዳውድ “እሰይ ደግ ሆነ ለምትሉ ይብላኝ ጽዋው፣ ግፉ ወደ እናንት ሲዞር ሰብአዊ ተከራካሪ ድምፅ ለማታገኙት” የሚል ሐሳባቸውን አጋርተዋል። “ጠንካራ ተቋም የሌለው አገር ፋይዳ ቢስ ህግ አልባ አገር” በማለት አክለዋል።

የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባ

ገዥው ብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ለሁለት ቀናት ያካሔደውን ስብሰባ እንዳጠናቀቀ በፌስቡክ ገጽ ሲያሳውቅ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የተሰጡ አስተያየቶች ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሚመሩት ፓርቲ ያለውን አቀባበል ለመገንዘብ ፍንጭ ይሰጣሉ። ፓርቲው ከጥር 23 እስከ 25 ቀን 2017 ጠቅላላ ጉባኤውን እንደሚያካሒድ አስታውቋል።

በፓርቲው የፌስቡክ ገጽ ሥር ከተሰጡ አስተያየቶች መካከል “በውጤት የተደገፈ ጉባዔ እንደምናካሄድ ምንም ጥርጥር የለውም” የሚለው በተለያዩ የማኅበራዊ ድረ ገጽ ተጠቃሚዎች ተደጋግሞ ተጽፎ ይታያል። “እቅዳችን ይሳካል በርቱልን” እንዲሁም “የብልፅግና ጉዟችን በተሳካ ሁኔታ ይቀጥላል” የሚሉ አስተያየቶችም ከተደጋገሙ መካከል ናቸው።

ከተመሠረተ አምስት ዓመታት ያስቆጠረው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ብልጽግና ፓርቲ 15 ሚሊዮን ገደማ አባላት አሉት። ምስል Prosperity Party -Ethiopia’s ruling party

ከሥራ አስፈጻሚው ስብሰባ መጠናቀቅ በኋላ መንግሥት እና ገዢው ፓርቲ በሚቆጣጠሯቸው መገናኛ ብዙኃን የመንግሥትን ስኬቶች የሚያንጸባርቁ ቃለ-መጠይቆች ተሰራጭተው ይታያሉ። ከእነዚህ መካከል “ኢትዮጵያን በዓለም ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ካስመዘገቡ ሀገራት ተርታ ማሰለፍ ተችሏል” የሚል ርዕስ የተሰጠው እና የፕላን እና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ የሰጡትን ማብራሪያ ጨመቅ ያደረገ ጽሁፍ በብሔራዊው የቴሌቭዥን ጣቢያ የፌስቡክ ገጽ ይገኛል።

“ግራ ገብቶኛል፡፡ ቆይ ከእድገታችሁ ጥቂት እንኳን ለህዝብ አይደርስም ወይ?” ሲሉ የጠየቁት ደበሮ ለፈቦ “በየክልሉ ህዝብ መኖር አቅቷቸው እያለቀሰ ፈጣን ዕድገት አስመዝግቧል ትላለች” የሚል አስተያየት አስፍረዋል። ተማም ሱር “እነዚህ ሰዎች ኢትዮጵያ የምትባል ሌላ ሀገር ፈጥረዉ ነዉ? ወይስ እኛ ያለንባት ኢትዮጵያን ናት?” ሲሉ ይጠይቃሉ።

ዎን ሐብቴ “ይመቻችሁ አቦ! ከተበጠረቁ አይቀር እንደ እናንተ ነው እንጂ” በማለት ተሳልቀዋል። ደስታ አበራ ግን የሚኒስትሯ አስተያየት “100% እውነት ነው” ሲሉ ይሞግታሉ።

ደስታ “ዜጎች በቀን አንድ ጊዜ መመገብ እየተሳናቸው፣ ልጆቻቸውን ማልበስ፣ ማብላት እና ማስተማር እየተሳናቸው፣ዜጎች ለቤት ኪራይ የሚከፍሉት አጥተው፣ የለት ጉርሳቸውን የሚያሟሉበት አጥተው፣ ትንሽ ትልቁ፣ ወጣት አቅመ ደካማው ሁሉ ለተመጽዋችነት ተዳርጎ ፣የእድገት መለኪያው ረሀብ ጉስቁልና ከሆነ፣ ችግር፣ የከፋ ድህነት፣ በኑሮ ውድነት መንገብገብ ከሆነ፣ አዎ ፈጣን ፈጣን አድገት አስመዝግበናል” ሲሉ ጽፈዋል።

እሸቴ በቀለ

ኂሩት መለሠ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW