1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት የታኅሳስ 24 ቀን 2017 መሰናዶ

Eshete Bekele
ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 24 2017

ጀዋር መሐመድ “አልጸጸትም” የተሰኘ መጽሀፉ በማኅበዊ ድረ-ገጾች የተሰራጨው በኢትዮጵያ መንግሥት እንደሆነ ገልጿል። ደጋፊዎቹ መንግሥትን በመኮነን ከጎኑ ሲቆሙ ተቺዎቹ ከዓመታት በፊት በማኅበራዊ ድረ-ገጾች ያሰራጨውን ፈተና አስታውሰውታል። በአማራ ክልል የታጣቂዎች መመለስ በአዎንታ የመለከቱ ቢኖሩም በርካቶች በጉዳዩ ላይ ጥያቄ አላቸው።

 “አልጸጸትም”  የጀዋር መሐመድ መጽሀፍ ሽፋን
ከአፋን ኦሮሞ ወደ አማርኛ የተተረጎመው “አልጸጸትም” የተሰኘ መጽሀፍ በማኅበራዊ ድረ-ገጾች የተሰራጨው በኢትዮጵያ መንግሥት እንደሆነ ፖለቲከኛው ጀዋር መሐመድ ገልጿል። ምስል Eshete Bekele/DW

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት የታኅሳስ 24 ቀን 2017 መሰናዶ

This browser does not support the audio element.

የጀዋር መሐመድ “አልጸጸትም” የተሰኘ መጽሀፍ በማኅበራዊ ድረ-ገጾች ተሰራጭቷል። የ38 ዓመቱ ፖለቲከኛ በፌስቡክ እና በኤክስ ባሰፈራቸው መልዕክቶች ድርጊቱ በኢትዮጵያ መንግሥት ተፈጽሟል ብሎ እንደሚያምን ገልጿል። የመጽሀፉን ቅጂ ምልክት በማድረግ በኬንያ ለሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ሰጥቶ እንደነበር የገለጸው ጀዋር ስካን አድርጎ ወደ ሶፍት ኮፒ በመቀየር በኢንተርኔት እንዲሰራጭ አድርገዋል ያላቸውን ግለሰቦች እና ተቋማት በሥም በመጥቀስ ከሷል።

ድርጊቱ የጀዋር ደጋፊዎች እና ተቺዎችን ከፍተኛ ትኩረት የሳበ ነው። በርካቶች ከዚህ ቀደም ራሱ ጀዋር በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ጫና ለማሳደር የፈጸመውን ተግባር በማሳየነት በመጥቀስ ተችተውታል።  ፓፔሻ “ልክ እንደፈተናዋ ጉድ አደረጉህ አይደል?” ሲሉ አስተያየት ሰጥተዋል። ዮሴፍ “የአንተን ከእነሱ የሚለየው ፈተናውን ሰርቀህ አውጥተህ የጥያቄውን ይዘት አለወጥኸውም” የሚል አስተያየት አስፍረዋል።

ሳራ “የተዘራ ይታጨዳል የሚባለው ትክክል መሆኑ ገባኝ። የተማሪ የማትሪክ [ፈተና] ሰርቀህ ስትበትን ዓመት ሙሉ የተማረው ወጣት እንዴት እንደተቃጠለ። አንተ አንድ ግለሰብ ስለሆንክ ቻለው” የሚል ትችት እና ምክር በጣምራ አቅርበዋል። ሳራ “አልፀፀትም ብለህ መፅሀፍ ስታወጣ፤ ተከብቢያለሁ ብቻ ስትል የሞተው ወጣት ማን ይዘንለት?” ሲሉ ይጠይቃሉ።

ድርጊቱን ያወገዙ፤ ለጀዋር መሐመድ ድጋፋቸውን የገለጹ ጥቂት አይደሉም። ኢድሪስ ሐሰን “አንተ ከዓላማህ ፍንክች እንዳትል። እነሱ እንደ ህሊናቸው የቀነጨረ ፓለቲካቸው ግልፅ ያለ ነገር ነው። ዶክመንታሪ ቢሰሩ፤ እስካን ቢያደርጉ ሀቁ ሕዝብ የሚያውቀው ነው” በማለት ድጋፋቸውን ለጀዋር ገልጸዋል። ግሪን የሚል ሥም የሚጠቀሙ ግለሰብ “ብልጽግና [ፓርቲ] እንደዚህ በአንድ መፅሐፍ ሲደርማመስ ከማየት በላይ ደስታ የለኝም። የመጨረሻ ፋራ እና መሀይም ስብስብ መንግስት” ሲሉ ተችተዋል። ነሞ ወቅጋሪ “መንግሥት ለቅጂ መብት ቀርቶ ለሰው ሕይወትም ዋጋ የለውም” ባይ ናቸው።

መሐመድሳኒ ዙበር “እባክህ ብልፅግና ሥራ አላጣም። ድራማህን ትተህ ሸቅል” ሲሉ ጽፈዋል። ላሜሕን ማቱሳላ ደግሞ “ሁሉንም ነገር ብልፅግና ላይ መለጠፍ አግባብ አይመስለኝም። ይኼን አንድ ተራ ግለሰብ ሊያደርገው ይችላል” ብለዋል። ሲዲሴ በንቲ ደግሞ “መፅሃፍህን ለመሸጥ ጠቅላይ ሚኒስትራችንን መሳደብ እና መተቸት አለብህ እንዴ? ጠቅላይ ሚኒስትራችንን ካልሰደብከው እና ካልተተቸህ መፅሃፍህን አይሸጥም አይደል?” እያሉ ይጠይቃሉ።

ጀዋር አዘውትሮ በሚጠቀምባቸው ማኅበራዊ ድረ-ገፆች “ስካን አድርገው በለቀቁት ውስጥ ነገሮችን ሊያዛቡ እንደሚችሉ ገምቼ ነበር” በማለት ጽፏል። ጀዋር እንደሚለው በማኅበራዊ ድረ-ገጾች በተሰራጨው ቅጂ ውስጥ ሆን ተብሎ የተዛባ ክፍል ተገኝቷል። ጀዋር ተዛብቷል ያለውን እና ትክክለኛውን በምስል ለተከታዮቹ አቅርቧል። ይኸ ጉዳይ በማኅበራዊ ድረ-ገጾች የተሰራጨውን ቅጂ ባነበቡ ሰዎች ዘንድ ግርታ የፈጠረ ነው።

ዮናስ ጥሩዬ “ነፃ አገኘሁት ብየ አይኔ እስኪጠፋ ካነበብኩት በኋላ...ሌላ ጣጣ” ሲሉ ቅሬታቸውን አቅርበዋል። አብደላክበር ጣሒር “በጣም ጥሩ ተመስጠነ እያነበብን ነው። ቶሎ ቶሎ በል። ሌላም ካለ አጣራ። መጽሀፉ እንደሆነ አይከደንም። ወደ ኋላ መለስ ብለን ራሳችንን ምንፈትሽበት ታሪክ ነው” በማለት ጽፈዋል።

መንግሥትም ይሁን በኬንያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ጀዋር ባቀረበው ክስ ላይ ያሉት ነገር የለም። መጽሀፉ ለንባብ ከበቃ በኋላ መንግሥት እና ደጋፊዎቹ በጀዋር ላይ ኃይለኛ ትችት እያቀረቡ ይገኛሉ። ከመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት አንዱ የሆኑት ሱሌይማን ደደፎ በኤክስ በአማርኛ እና በአፋን ኦሮሞ ባሰፈሩት ጽሁፍ በጀዋር ላይ ጠጠር ያለት ትችት ካቀረቡ መካከል ናቸው።

ጀዋር መሐመድ በአፋን ኦሮሞ “ሒን ጋቡ” (Hin Gaabbu) በአማርኛ “አልጸጸትም” የተሰኘ መጽሀፉን ካሳተመ በኋላ በአውሮፓ የተለያዩ ሀገሮች በመዘዋወር ከደጋፊዎቹ ጋር ውይይት በማድረግ ላይ ይገኛል።ምስል Tamirat Dinssa/DW

በተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው የሠሩት ሱሌይማን “ለሕዝቡ መሠረታዊ ጥያቄዎች ቅንጣት መፍትሔ የማያስገኝና የድሃ ሕዝብ ልጆችን ሕይወት በመቶዎች እንዲቀጠፉ የሚያደርግ የፖለቲካ መስመር እያራመዱ በሕዝብ ጥቅም ስም ከፍተኛ ሐብት እያካበቱ አለመፀፀት ሕሊና ቢስነት ነው” ሲሉ ጀዋርን በኃይል ወርፈዋል።

“በሀገራችን ውስጥ እየተከሰቱ ባሉ አለመረጋጋቶች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ እጃቸውን የከተቱ፣ ከሕዝቦች አንድነት ይልቅ ልዩነቶችን የሚያባዙ ቅራኔ ጠማቂዎች ሁሉ ሊፀፀቱ ይገባል” የሚሉት ሱሌይማን “እስካሁን በተሳሳቱ የፖለቲካ አስተሳሰቦች የተነሳ በደረሱ ጥፋቶች አለመፀፀት ካሁን በኋላም ለባሰ ጥፋት መዘጋጀትን የሚያመለክት ስለሆነ ለሴራ ፖለቲከኞችና የደም ነጋዴዎች ዕድል ሊሰጥ አይገባም” ሲሉ ጽፈዋል።

አቤል አለማየሁ ግን ለአምባሳደር ሱሌይማን “ከስህተቱ የማይማር ግዑዝ ነገር ብቻ ነው” የሚል መልስ ሰጥተዋል። አቤል በኤክስ በኩል ባሰፈሩት መልዕክት “ትናንት ጦርነትን እየተነተኑ እና እያቀጣጠሉ የትግራይን ህዝብ አስጨፈጨፉ፤ ዛሬ ተረኛው አማራ ነው። ጦርነት የሚያውጀው የርስዎ ብልጽግና [ፓርቲ] ነው። ለስልጣን ሲባል እስከ መቼ?” ሲሉ ይጠይቃሉ። ቤተልሔም ደግሞ “ኢትዮጵያ ውስጥ ያለ ፓርቲ ሁሉም ቆምኩለት ያለውን ህዝብ የሚበላ የሚጎዳ እንጂ የሰለጠነው ፖለቲካ ገና ገና አልታየም” ሲሉ መልሰዋል።

በአማራ ክልል ተመለሱ የተባሉ ታጣቂዎች ጉዳይ

ገዥው የብልጽግና ፓርቲ በተረጋገጠ የፌስቡክ ገጹ “በአማራ ክልል የመንግሥትን እና የሕዝብን የሰላም ጥሪ የተቀበሉ ታጣቂዎች የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በሰራባ ማሰልጠኛ ማዕከል አቀባበል ተደርጎላቸዋል” የሚል መልዕክት አስፍሯል።

የታጣቂዎቹን መመለስ በአዎንታ ያመሰገኑ የመኖራቸውን ያክል በርካቶች ጥያቄ እና ትችት አቅርበዋል። ካቶር ጉዬ “ከሰላም ውጪ መጠፋፋት ለማንም አይጠቅምም እና ወደ መወያየት እና መነጋገር እንቅረብ። ብልጽግና በውይይት የሚያምን ፓርቲ ነው” ሲሉ ጽፈዋል።

ኢትዮፒካ የሚል ሥም የሚጠቀሙ ግለሰብ “ይህ ፓርቲ በፍፁም ሰላም የማስፈን አቅም የለውም። በታጠቁ ቡድኖች ከተጠየቁ በርካታ ጥያቄዎች መካከል አንዱን እንኳን እንደማሳያ አልመለሰም። 90% የአማራ ሕዝብ አይደግፈውም። ከካድሬ በስተቀር ምክንያቱም ከወረዳ ከተሞች ውጭ ያሉት ቦታዎች በታጠቁ ሀይሎች ቁጥጥር ውስጥ ስለሆኑ ብልፅግናን ቢደግፉ ለሚደርስባቸው ስቃይ የሚያድን መንግስት አለመኖሩን አውቀዋል” ብለዋል።

ዳኜ ልንገርህ “መንግሥት ለእናንተ እና መሰል ወዳጆች የዘረጋውን የሰላም እጅ ለሁሉም እንዲዘረጋ እንጠይቃለን” ብለዋል። ማሜ ሀበሻ “ተመለሱ” ከተባሉት መካከል “አንድም የፋኖ ታጣቂ የለም። እነዚህ ከተማ ውስጥ የተለያየ ሥራ በመስራት የሚኖሩ ወጣቶችን ለድራማ ቀረፃ ብቻ ተመርጠው የተሰራ ስራ ነው። ሀቁን ህዝብ ስለሚያውቀው ለህዝብ እንተወው። እውነት ሰላም ከተፈለገ እውነትን ብቻ ተከተል። ይኼ ከድራማ ያለፈ ፋይዳ የለውም” ይላሉ።

ገዥው የብልጽግና ፓርቲ በተረጋገጠ የፌስቡክ ገጹ “በአማራ ክልል የመንግሥትን እና የሕዝብን የሰላም ጥሪ የተቀበሉ ታጣቂዎች የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በሰራባ ማሰልጠኛ ማዕከል አቀባበል ተደርጎላቸዋል” የሚል መልዕክት አስፍሯል።ምስል Central Gondar Zone communications

የታጣቂዎቹን መመለስ “በጣም ጥሩ ነው” በማለት ያደነቁት አበበ አቦ ምላሽ የሚሹ ጥያቄዎች አሏቸው። “አለቃቸው ማን ይባላል? ከማን ጋር ነው የተፈራረመው? ስንት ናቸው? በየትኛው ግንባር የነበሩ ናቸው? ነው ወይስ ከሰሊጥ አጨዳ የተመለሱ ናቸው?” ሲሉ አበበ ይጠይቃሉ። አስፋው ዘውዴ “የሰላም ጥሪ ተቀብሎ ወደ ሰላማዊነት መምጣት ከጀግንነት ያለፈ ጀግንነት ነው። ሁላችንም ለሰላም ዋጋ እንስጥ” የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል።

መክሊት ዮሴፍ “ሰላም የሰፈነበት፣ ዜጎቹ በሰላም የሚንቀሳቀሱበት፣ ገበሬዉ በሰላም የሚያርስና ያመረተዉን የሚሸጥበት፣ ነጋዴዉ የሚነግድበት፣ የታመሙ የሚታከሙበት ክልል እንዲሆን ኑ በጋራ ስሩልን፣ አንድ ሁኑልን፣ ሰላም ስበኩልን ጫካ ለቀሩ ወንድሞቻችሁ ንገሩልን። ጦርነት ይብቃ” የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል።

እንዲህ አይነቶቹ መልዕክቶች በማኅበራዊ ድረ ገጽ ተጠቃሚዎች እየተባዙ ተሰራጭተዋል። የመንግሥት እና የገዥው ብልጽግና ደጋፊዎች ለማድነቅም ሆነ ለመተቸት ፌስቡክን በመሳሰሉ ማኅበራዊ ድረ-ገጾች በሚያደርጉት መስተጋብር ተመሳሳይ ስልት ሲከተሉ ይታያል።

ዘውዱ መኮንን “እንደ ሰላማዊ ሰልፉ አሁንም በየ መንደሩ በግድ ጎትታችሁ አወጣችሁት ይኼን መከረኛ ህዝብ። በሞቴ እስኪ ኮሜንቱን እንኳ በማንበብ ህዝቡ ምን ያክል እንደማያምናችሁ እዩት” ይላሉ። ውበቱ “ተራ በተራ እየተፈራረቃችሁ ድራማ ስሩ። የኢትዮጵያ ህዝብ እንደሆነ ጠባቂውም መሪውም ፈጣሪ ነው” ብለዋል። እስካሁን ድረስ በኢትዮጵያ መንግሥት እና በዋና ዋናዎቹ የፋኖ ታጣቂ ቡድኖች መካከል የተጀመረ ድርድር ስለመኖሩ የሚታወቅ ነገር የለም። 

እሸቴ በቀለ

ታምራት ዲንሳ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW