የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት የነሐሴ 01 ቀን 2017 መሰናዶ
ሐሙስ፣ ነሐሴ 1 2017
ከየመን የባሕር ዳርቻ በደረሰ የጀልባ አደጋ ሕይወታቸውን ያጡ ስደተኞች ቁጥር 92 መድረሱን የሀገሪቱ ባለሥልጣናት አስታውቀዋል። አደጋው የደረሰው በሀገሪቱ አብያን ክፍለ-ግዛት ባለፈው እሑድ ነበር። አንድ ሥማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ የየመን ባለሥልጣን በአደጋው የሞቱ ኢትዮጵያውያን አስከሬን ተገኝቶ በአካባቢው ሰዎች ርዳታ ቀብር መፈጸሙን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያውያንና ሱማሌያውያን የሚያዘወትሩት የስደት መስመር የበርካታ ሰዎችን ሕይወት ሲነጥቅ የመጀመሪያው አይደለም። በተባበሩት መንግሥታት የፍልሰተኞች መርጃ ድርጅት (IOM) ቢያንስ 558 ሰዎች በ2024 ብቻ ቀይ ባሕርን ለማቋረጥ ሲሞክሩ ሕይወታቸውን እንዳጡ አስታውቋል።
የበርካታ ኢትዮጵያውያንን ልብ የሰበረው አሳዛኝ አደጋ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች መነጋገሪያ ሆኖ ሰንብቷል። በርካቶች ኢትዮጵያውያን በእንዲህ ዓይነት አደገኛ የጉዞ መስመር ለምን መጓዝ እንደመረጡ ሐሳባቸውን ይሰጣሉ።
«መቼስ ራስህን በገዛ እጅህ ከምታጠፋ፤ እንጥፍጣፊ ተስፋ ይዘህ መጓዝ ሳይሻል አይቀርም» የሚሉት ሚካኤል መስፍን «ሀገርህ ላይ ተሥፋ እንዳይኖርህ ተደርገህ እየኖርክ ምን አማራጭ አለህ?» ሲሉ ይጠይቃሉ። «ተምረህ ሥራ አታገኝም፤ ሥራ ብታገኝ የምታገኘው ገቢ አያስተዳድርህም። ለራስህ መሆን የማትችልበት ደረጃ ላይ ነው ያለኸው» የሚሉት ሚካኤል «ብቻ ምን አለፋህ ግራ የገባ ነገር ነው የኛ ነገር» የሚል የሚያስተክዝ ሐሳብ ሰንዝረዋል።
ውብአንተ አድማሱ «ጦርነት የመረጠ መንግሥት ለዜጎች መሰደድ ዋነኛው መንስኤ ነው» ሲሉ ተችተዋል። ታጌ ሎን የሚል የፌስቡክ መጠሪያ የሚጠቀሙ ግለሰብ «ወደ አረብ እና አውሮፓ ሃገራት የሚያስመኝ ምንም ዓይነት ገፊ ምክንያት የለም። እድሜ ለመንግሥታችን። በሦስት ቀን አንዴ የተገኘውን ተቃምሰን እንውላለን። ሰልቫጅ መግዣ ከተገኘ በሁለት ዓመት አንዴ እንቀይራለን። ልጆቻችን ዳቦ እያሉ የሚያስቸግሩ ከሆነ ሰፈር ቀይረን እንለምናለን። ወደ ባእድ ሀገር ሄዶ መንከራተት አያስፈልገንም» በማለት ተሳልቀዋል።
ዳምጤ ጎንጤ ደግሞ «ወጣቶችን ወደ ሥራ የሚያስገባ ከዕወቀት የመነጨ አሠራር መኖር አለበት» የሚል ምክረ-ሐሳብ አቅርበዋል። «ሥራ ማለት ግድ የመንግሥት» ሊሆን እንደማይገባ የገለጹት ዳምጤ ጎንጤ «ወጣቶችን በማሕበር በማደራጀት በከብት እርባታ፣ በንብ ማነብ ፣ ዶሮ እርባታ፣ በእርሻ ፣የከብት መኖ ዝግጅት፣ በብዙ የልማት ሥራዎች መደራጀት ይቻል ነበር» እያሉ አማራጮችን ይዘረዝራሉ። «ወንበሩን የያዙት ሰዎች ኃላፊነትም ግደታም መወጣት አልቻሉም። የሕዝብ ኃላፊበት ይዘው ስለ ራሳችው ነው የሚኖሩት» የሚሉት ዳምጤ «በዚህ ምክንያት ሙስና ፣ የመልካም አስተዳደር ችግር ፣ወጣቱን ለስደት ዳርጐታል። ስለዚህ መንግሥት እዚህ ላይ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት አለበት» ሲሉ መክረዋል።
አባዲ ወልደገብርኤል «በአገር ውስጥ ከሞት የማይታደግ የጤነኛ አመራር የዜጎችን አያያዝ ጤነኛ ፖሊሲ ስለሌለ ነው ዜጎች በሞት መካከል ለመጓዝ የወሰኑት» በማለት ዶይቼ ቬለ በሠራው ዘገባ ሥር ሐሳባቸውን በፌስቡክ ገልጸዋል። «አትፍረድ ይፈረድብሃል» የሚሉት ሔለን ባዬ «ወደው አይደለም ሀገራቸውም ሰላም የለ፤ ሥራ የለ። ምን ያድርጉ? ረሐብ መጥፎ ነው» የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል።
«ሀገር ላይ ሠርቶ መለወጥም ሆነ በሠላም ወጥቶ መግባት ጭንቅ ሆነ። ሆድ ደግሞ ችግር አያዉቅም» የሚሉት ሞረሼ በፊናቸው «በአሁኑ ጊዜ በዓለም ላይ እንደ ኢትዮጵያ ሕዝብ በሀገሩ መንግሥት የሚሰቃይ የት ይገኛል?» ሲሉ ይጠይቃሉ። «ከነዚህ ሟቾች ባሻገር ዛሬ በከተማችን ልጆቼን ምን ላብላቸዉ? እያሉ የሚያለቅሱትን ወላጆች ቤት ይቁጠራቸዉ። ሕዝብ በጦርነት መጠበስ ከጀመረ አራት ዓመት አለፈዉ። ትንሽ ተስፋ የሚጣልበት ነገርም ጠፋ» የሚሉት ሞረሼ «ለዛም ነዉ ወይ ይለፍልኝ ወይ ይለፍብኝ የሚል ዉሳኔ ላይ የሚጥለዉ» ብለዋል።
ሚካኤል መስፍን «የሐመልማል አባተ ምነዉ ልቤን ስደት ስደት አለው የሚለው ሙዚቃዋ ለዚህ ዘመን የተሠራ ነው የሚመስለኝ» የሚል አስተያየት ሲጽፉ ሌላ አንድ ኢትዮ-ኢንግሊሽ የሚል መጠሪያ ጀርባ የተደበቁ ግለሰብ «እኔ ራሴ ኢትዮጵያ ውስጥ በድህነት ታስሬ ከምኖር ከኢትዮጵያ ወጥቼ ከሀብታም አገር ብታሰር ይሻለኛል» ብለዋል። ተክለሚካኤል በርኸ «አንደኛ የርስ በርስ ጦርነት፤ ሁለተኛ የሥራ አጥነት» የስደት ገፊ ምክንያቶች እንደሆኑ አተያያቸውን አስፍረዋል።
ብሔራዊ ባንክ የውጪ ምንዛሪ ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች ወደ ኢትዮጵያ የሚላክበትን የትይዩ ገበያ ለመቆጣጠር ዘመቻ ጀምሯል። የብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ እስመለዓለም ምሕረቱ በትናንትናው ዕለት በትይዩው ገበያ የሚንቀሳቀስ ገንዘብ እንደሚወረስ ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል። ብሔራዊ ባንክ ባለፈው ቅዳሜ መቀመጫቸውን በአሜሪካን ያደረጉ አራት የሐዋላ አስተላላፊዎችን «በሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር» ወንጅሏል። የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ አባላት በድርጅቶቹ በኩል ገንዘብ እንዳይልኩ የመከረው ብሔራዊ ባንክ ለሚመለከታቸው «አግባብነት ያላቸው የሕግ አስፈጻሚ አካላት ምርመራ እንዲያከናውኑ» ጥያቄ ማቅረቡን አስታውቋል።
ብሔራዊ ባንክ ከአሜሪካ በተጨማሪ በተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች በተለይ በዱባይ በሚከወን ሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር ላይ ዐይኑን ጥሏል። የብሔራዊ ባንክ ገዥ «ከቅርብ ቀናት ወዲህ በተለይ በዱባይ ዩናይትድ አረብ ኤሚሬትስ ከገበያ ሁኔታ ያፈነገጠ የትይዩ ገበያውን የሚያስፋፉ ሕገ-ወጥ ድርጊቶች እንዳሉ በውል ስለተረዳን ይህን ተከታትለን ጠንካራ እርምጃዎችን እንወስዳለን» ሲሉ ተናግረዋል። እንግዳወርቅ መጋዜ «ገበያ መር የዶላር ግብይት የመከተል እና የመፍጠር ሂደቱ ዋነኛው አላማ ትይዩ ገበያን የማስቀረት አልነበረም ወይ? ይሄ በሆነበት አግባብ እንዴት አሁንም ጥቁር ገበያው ስጋቱ አይሎ ሌላ ፖሊስ አስፈለገው?» ሲሉ ጠይቀዋል።
መሌ «ማሻሻያው ይሄን ሊቀርፍ ነበር የተደረገው። ስላልተቻለ በጉልበት ሊሆን ነው» የሚል ትችት ጽፈዋል። ብሔራዊ ባንክ በትይዩ ገበያ ወደ ኢትዮጵያ የሚላከውን የውጪ ምንዛሪ ወደ መደበኛው የሐዋላ ሥርዓት ለመመለስ ጥረት ከጀመረ ቆይቷል። ነገር ግን በትይዩ ገበያ ያለው ከፍ ያለ የምንዛሪ ተመን ዋና ችግር ሆኖ ይታያል። ሁሴን መሐመድ «ለማን ብየ ነው በባንክ የምልከው? ኑሮ ውድነቱን ጣራ ለሰቀለ መንግሥት ነው በባንክ የምልከው?» ሲሉ ይጠይቃሉ።
ለይላ ሑሴን በበኩላቸው «አስቀምጠዋለሁ እንጂ በባንክ በኩል አልክም። ሀገር ውስጥ ያለው ብር አለቀ። እኛ በላክነው ብር ብልፅግና መሳሪያ ነው የሚገዛበት» ሲሉ ይነቅፋሉ። ሜሮን «ከብላክ እኩል ካረጋችሁ እሺ፤ እስኪ ከፊሊፕንስ መንግሥት ተማሩ» ሲሉ ጽፈዋል። ነጃ ዳሪ «የዋጋ ንረትን ከሚያባብሱ ነገሮች አንዱ የጥቁር ገበያን ተጠቅመው ሸቀጣሸቀጦች ከውጭ የሚያስገቡ ነጋዴዎች ናቸው። ድርጊቱን ለታክስ ስወራም ስለሚጠቀሙበት ነው። አስተማሪ የሆነ እርምጃ መወሰድ ይኖርበታል» የሚል አቋም አላቸው።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በዚህ ሣምንት ይፋ ባደረገው ዓመታዊ ሪፖርት «በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች በመንግሥት ኃይሎች እና በታጣቂ ቡድኖች መካከል የሚካሄደው የትጥቅ ግጭት በሕይወት የመኖር፣ የአካል ደኅንነት፣ የነጻነት እና ሌሎች የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ጥሰቶች ማስከተሉን» ይፋ አድርጓል።
ከሰኔ 2016 እስከ ሰኔ 2017 ባለው አንድ ዓመት ውስጥ የነበረውን የሰብአዊ መብቶች ይዞታ የሚፈትሸው ሪፖርት «በተራዘመ የግጭት ዐውድ ውስጥ በተፋላሚ ቡድኖች በተፈጸሙ ጥቃቶች አካል ጉዳተኞች፣ አረጋውያን፣ ሴቶች እና ሕፃናትን ጨምሮ በሰዎች ሕይወት፣ አካል እና ንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን» የሚያሳይ ነው። የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ሪፖርት «የእገታ ተግባራት ተስፋፍተው መቀጠላቸውን፣ በማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መብቶች ዘርፍም ጥሰቶች መመዝገባቸውን» አትቷል።
ሪፖርቱ ብርሀኑ አዴሎ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር ሆነው ከተሾሙ ወዲህ የወጣ የመጀመሪያ ዓመታዊ ዘገባ ነው። የቀድሞው የኢሕአዴግ ከፍተኛ ባለሥልጣን ኮሚሽኑን እንዲመሩ የተሾሙት ባለፈው ጥር 2017 ነበር። ከዚያ በኋላ ሁለት ኮሚሽነሮች ሥራቸውን ለቀዋል።
ኮሚሽነር ብርሀኑ አዴሎ የተቋማቸው ሪፖርት ይፋ ሲደረግ የኢትዮጵያ መንግሥት የጸጥታ አስከባሪዎች በአማራ ክልል ከፋኖ ታጣቂዎች ጋር በኦሮሚያ ክልል ከኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ጋር በሚያደርጓቸው ውጊያዎች ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን ተናግረዋል። ይሁንና በዓመቱ በአማራ ክልል ተፈጽመዋል ስለተባሉ የድሮን ጥቃቶች ለቀረበላቸው ጥያቄ የሰጡት መልስ ለትችት ዳርጓቸዋል። አቶ ብርሀኑ ተቋማቸው በምርመራ እንዳላረጋገጠ ነገር ግን በድሮኖች ተፈጽመዋል ስለተባሉ ሁለት ጥቃቶች ለመከላከያ ሠራዊት ጥያቄ ማቅረባቸውን ተናግረዋል። ኮሚሽነሩ «ወደ ጥርጣሬ የሚወስዱ ስለሆነ በከባድ መሣሪያ ጥቃት አድርገን ወስደናቸዋል» ሲሉ ተደምጠዋል።
ጴጥሮስ መስፍን የኮሚሽነሩ ማብራሪያ አልተዋጠላቸውም። «በዚህ አንድ ዓመት ውስጥ የድሮን ጥቃት አልተፈጸመም የሚል ሪፖርት ያወጣው ብርሀኑ አዴሎ እንኳን ሕዝቡን መከላከያን አስገርሟል» ሲሉ በፌስቡክ ገጻቸው አስፍረዋል። ሌላ የፌስቡክ ተጠቃሚ «ነጻና ገለልተኛ ሪፖርት መውጣት አለበት። ለሥልጣን ማስጠበቂያ ተብሎ የማይመስል ሪፖርት የሚቀርብ ከሆነ በታሪክ ተጠያቂ ከመሆን አያድንም። ተቋም የራሱ ነጻነት ካልተሰጠው በስተቀር በግለሰቦች ጥንካሬና ድክመት ላይ ከተመሰረተ ውጤት አልባ ነው»ብለዋል።
እሸቴ በቀለ
ሸዋዬ ለገሠ