የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት የነሐሴ 08 ቀን 2017 መሰናዶ
ሐሙስ፣ ነሐሴ 8 2017
የግብጽ ፕሬዝደንት አብደል ፋታ አል-ሲሲ እና የዩጋንዳ አቻቸው ዩዌሪ ሙሴቬኒ በካይሮ በጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ ሲሰጡ ካተኮሩባቸው ጉዳዮች መካከል የናይል ወንዝ እና በሃገራት መካከል የሚነሳው የውኃ ድርሻ ጉዳይ አንዱ ነበር። የ80 ዓመቱ ሙሴቬኒ ወደ ካይሮ ያቀኑት በግብጽ ፕሬዝዳንት ግብዣ ነበር።
በጉብኝቱ ወቅት የግብጽ እና ዩጋንዳ የቢዝነስ ፎረም ተካሒዷል። የተለያዩ ሥምምነቶችም ተፈርመዋል። ትልቅ ትኩረት ያገኘው ግን ግብጽ እና ዩጋንዳን የሚያስተሳስራቸው የነጭ ናይል ወንዝ ጉዳይ እና በአጠቃላይ የቀጠናውን ሃገራት የሚያሳስበው የውኃ ክፍፍል ነገር ነበር።
ሁለቱ መሪዎች በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ አብዱል ፋታ አል-ሲሲ የነጭ እና የጥቁር ናይል ወንዝ ውኃ አጠቃላይ ፍሰት 1,600 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ቢሆንም አብዛኛው በደኖች፣ በረግራጋማ መሬቶች እና በትነት እንደሚባክን ሲናገሩ ተደምጧል። ግብጽ እና ሱዳን የሚደርሳቸው 85 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ወይም 4 በመቶ ብቻ እንደሆነ የገለጹት ፕሬዝዳንቱ ሀገራቸው ይገባኛል በምትለው የውኃ ድርሻ እንደማትደራደር አስጠንቅቀዋል።
በናይል ወንዝ ላይ የሚከናወኑ ግንባታዎችም «ወደ ግብጽ የሚደርሰውን የውኃ መጠን መቀነስ የለበትም» ያሉት አል-ሲሲ ሀገራቸው «የተናጠል ውሳኔዎች» እንደማትቀበል መንግሥታቸውም «በዓለም አቀፍ ሕግ የተረጋገጡ ሁሉንም እርምጃዎች» እንደሚወስድ ተናግረዋል።
ሙሴቬኒ በአንጻሩ በናይል ወንዝ የውኃ ክፍፍል ረገድ በላይኛው እና የታችኛው ተፋሰስ ሃገራት መካከል የሚደረጉ ድርድሮች የአቀራረብ ችግር ሳይኖርባቸው እንደማይቀር ጠቆም አድርገዋል። ግብጽ ከብሪታኒያ ጋር የተፈራረመቻቸውን ሥምምነቶች እያጣቀሰች «ታሪካዊ መብቶችን» እንደመከራከሪያ እንደምታቀርብ የጠቀሱት ሙሴቬኒ «የተቀሩት ሕዝቦች እኛስ?» ብለው እንደሚጠይቁ አስታውሰዋል።
የናይል ተፋሰስ አገሮች ፍላጎት ብልጽግና መሆኑን የገለጹት የዩጋንዳ ፕሬዝደንት «ኤሌክትሪክ፣ መስኖ እና የሚጠጣ ውኃ ያስፈልገናል» ሲሉ ተደምጠዋል። መፍትሔው በጉዳዩ ላይ የሚደረገውን ድርድር ማስፋት እንደሚሆን ምክረ-ሐሳብ አቅርበዋል።
ሁለቱ መሪዎች ቢያንስ በአደባባይ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ የኢትዮጵያን ሥም ባያነሱም የሰነዘሯቸው ሐሳቦች ግን በቀጥታ የሚመለከቷት ናቸው። ዶይቼ ቬለ በጉዳዩ ላይ በሠራው ዘገባ ሥር ኢትዮጵያውያን ሀገራቸውን እየተከላከሉ ግብጽን ሲተቹ ታይተዋል። ሙስጠፋ ሙዘይን «ሲሲ ሲናገር ካይሮ ላይ ግድብ የገነባን እኮ ነው የሚመስለው» ሲሉ ደግነት ድላሴ «የናይል ወንዝ ዋና ምንጭ ከኢትዮጵያ ነው። ስለዚህ ኢትዮጵያ ያለ ማንም ጣልቃ ገብነት ሐብቷን 100 % የመጠቀም መብት አላት» የሚል አስተያየት አስፍረዋል።
ጀማል መሀመድ «ግብጽ ታውራ ብቻ። ሲታቀድም ሲገነባም እያወራች ነው። ሲመረቅም ታውራ፤ ገና ሌላ አባይ ይጀመራል። የጊዜ ጉዳይ እንጂ ጠብቁ» የሚል አስተያየት አስፍረዋል። ጥላሁን አስፋውወሰን «የምንጩ ባለቤቶች እነሱ እኮ ነው የሚመስሉት! ሌላ ግድብን እንጨምራለን። እርማችሁን አውጡ በሏቸው» ሲሉ ጽፈዋል።
አቡሐሊድ ጀማል «ግብጽ ፉከራ እና ቀረርቶ የጀመረችው ዛሬ አይደለም እኮ የቆየ ነው። እሷ ትፎክር፣ ትሸልል እኛ ሥራችንን እንሠራለን» የሚል ሐሳብ አንጸባርቀዋል። አሜን አዲሱ «ግብጽ ከድርሻዋ በላይ ነዉ እያገኘች ያለችዉ። ባታለቃቅስ እና ብትስማማ ነዉ የሚሻላት» የሚል ምክረ-ሐሳብ ለግሰዋል።
በኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን መካከል በታላቁ የኅዳሴ ግድብ ላይ ይደረግ የነበረው ድርድር እንደተገተረ ነው። ለግብጽ ያደላ አስተያየት በቅርቡ የሰጡት የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ድርድሩን ዳግም ለማስጀመር ጥረት እያደረጉ እንደሚገኙ ተናግረዋል። የኢትዮጵያ የመንግሥት ኮምዩንኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሠ ቱሉ የግድቡ ግንባታ «ሊጠናቀቅ ጥቂት ቀናቶች ናቸው የሚቀሩት» ሲሉ ትናንት ረቡዕ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አርማ ለምን ተቃውሞ በረታበት?
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና አሠርቶታል የተባለ አዲስ አርማ ወይም «ሎጎ» በሣምንቱ ዋነኛ መነጋገሪያ ሆኖ ሰንብቷል። ጉዳዩን ለመጀመሪያ ጊዜ የዘገበው ሪፖርተር ጋዜጣ ነው። ወርቃማ ቀለም ያለው እና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሚል ሥያሜ የያዘውን ነባር አርማ በአዲስ ለመተካት በአጠቃላይ 600 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ወጪ መደረጉን ጋዜጣው ዘግቧል።
ተዘጋጀ የተባለው አዲሱ አርማ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የእንግሊዘኛ ምህጻር (CBE) በእንግሊዘኛ «ሁልጊዜም አስተማማኝ» ወይም (always reliable) የሚል መፈክር የያዘ ነው። አዲሱ አርማ በአማርኛ የተጻፈ ነገር አለማካተቱ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እንዳልተወደደም ዘገባው ይጠቁማል።
በኢትዮጵያ የባንክ ገበያ 50 በመቶ ገደማ ድርሻ የሚይዘው እና ወትሮም ውዝግብ የማያጣው ንግድ ባንክ ጉዳዩ ለብርቱ ትችት ተዳርጓል። በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የታዩት ትችቶች ለሥራው ወጪ ተደረገ በተባለው የገንዘብ ብዛት እና የአዲሱ አርማ ጥራት ላይ ያነጣጠሩ ናቸው። በአዲስ አበባ ፍልውኃ አካባቢ ከሚገኘው የንግድ ባንክ ዋና መሥሪያ ቤት ሕንጻ አናት አዲሱ አርማ ተለጥፎ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የተሠራጩ ምስሎች አሳይተዋል። ይሁንና አርማው ተሸፍኗል።
ሲሳይ ኤም አዲሱ «የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሕዝብ ሀብት መሆኑ ይታወቃል። ምንም እንኳ ባለቤትነቱ የመንግሥት ቢሆንም በተዘዋዋሪ መንገድ የሕዝብ ሀብት እንደሆነ ይታመናል። ስለሆነም ለውጥ ማድረግ ሲያስፈልግ የሕዝብን በአጠቃላይ እና የደንበኞቹን ደግሞ በተለይ ስሜት እና ፍላጎት ግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርበታል። ወቅቱንም ማገናዘብ ብልህነት ነው» ሲሉ ጽፈዋል።
«ከ50 ዓመት በላይ ያገለገለውንና በእኔ እምነት በቅርጽም ይሁን በይዘት ምንም ዓይነት ሳንካ ወይም እንከን የሌለውን የንግድ ምልክት (Logo) ለመቀየር ብር 600,000,000 (ስድስት መቶ ሚሊዮን ብር) አወጣ ሲባል መስማት በእጅጉ ያስደነግጣል» የሚሉት ሲሳይ «ሎጎ ለመቀየር ይኸን ያህል ሀብት የሚያፈሰው በምትኩ ምን ዓይነት እሴት ሊጨምር ይሆን? ምን ያህልስ ያስገኝለት ይሆን?» ሲሉ ይጠይቃሉ።
ሱልጣን አሕመድ «የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ማስተካከል የነበረበት ቀርፋፋ የአገልግሎት አሰጣጡን እንጂ ታሪካዊ ሎጎውን አልነበረም» ሲሉ ተችተዋል። ሐኒ ድሬ «ንግድ ባንክ 600 ሚሊዮን ብር አውጥቶ ሎጎ ከመቀየር ለአዲስ አበባ ነዋሪ 300 ሥራ አጥ ወጣቶች አንዳንድ ሚሊዮን ብር አበድሮ ሥራ እንዲጀምሩ ቢያደርግ ይሻል ነበር» የሚል አማራጭ ምክረ-ሐሳብ አላቸው።
ለሜሳ ጉግሳ «ንግድ ባንክ 600 ሚሊየን ብር አውጥቶ የባንኩን ሎጎ ለመቀየር ባሰበበት መንገድ 600 ሚሊየን ብር አውጥቶ ሥራ ፈጣሪ ወጣቶችን ቢደግፍ፤ በሥራ ላይ ያሉ ማሕበራትን ወደ ተሻለ ከፍታ የሚያደርስ ድጋፍን ቢያስጀምር፤ ብሩን ለብድር ቢያመቻቸው ምን ያህል የምንተማመንበት ባንክ መሆኑን እናምን ነበር» የሚል ተቀራራቢ ሐሳብ ሰንዝረዋል።
ብርሀኑ አየነው «አሁን ለዚህ ሎጎ ነው ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ የተከፈለው ወይም ሊከፈል የተዘጋጀው? ግን የሕዝብ ሀብት ለዚህ ከበፊቱ ለማይሻል ነገር እንዲወጣ ለምን ተፈለገ? አንድ ጢንጥዬ ጤና ጣቢያ በገጠር የሀገሪቱ ክፍል መስራ አያስችልም ወገን ይኼ ገንዘብ? እውነትም እነሱ ጋ የኑሮ ውድነት የለም። ብር እንደሆን እነርሱ ጋር በሽ ነው» ሲሉ ተችተዋል።
ሰላማዊ ዝምታ የሚል የፌስቡክ መጠሪያ የሚጠቀሙ ግለሰብ «ቤት ቁጭ ብላችሁ በሰዓት 20,000 ትሠራላችሁ ሲባል አላምንም ነበር። ንግድ ባንክ ለዛ ሎጎ 600 ሚሊዮን እንደከፈለ ስሰማ፤ በሰዓት 600 ሚሊዮን መሥራት እንደሚቻል አመንኩ» ሲሉ ተሳልቀዋል።
የቲክቶክ መዘዝ እና አዲስ አበባ
የአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ «ቲክቶክን በመጠቀም ግጭት ቀስቃሽ መረጃ ሲያሰራጩ» ነበር ያላቸውን አምስት ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር እንዳዋለ አስታውቋል። በቁጥጥር ሥር የዋሉ ተጠርጣሪዎችን ፎቶ ግራፍ በፌስቡክ ያሠራጨው ፖሊስ ሌላ ግለሰብ ላይ ክትትል እያደረገ እንደሚገኝ ነሐሴ 06 ቀን 2017 ይፋ አድርጓል።
የዋና ከተማዋ ፖሊስ እርምጃ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ ተጠቃሚዎች ዘንድ የተደበላለቀ ምላሽ አግኝቷል። አሸናፊ ዲ ጉደታ «ይህ ትክክለኛ የሕግ የበላይነት እርምጃ ነው። መንግሥት እንደዚህ ዓይነት ፀረ ሰላም ሰዎች ላይ እርምጃ እንዲወሰድባቸው» በማለት ድጋፋቸውን አሳይተዋል። ዑመር ሱልጣን «እንደነዚህ ዓይነት ጋጠወጦች አስተማሪ እርምጃ ሊወሰድባቸው ይገባል» በማለት ጽፈዋል።
ይሁንና በርካቶች ቲክ ቶክን ጨምሮ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች አወዛጋቢ ግፋ ሲልም በተለያዩ ማኅበረሰቦች መካከል ግጭት ሊቀሰቅሱ የሚችሉ አስተያየቶች የሚሰጡ ግለሰቦችን በተመለከተ ፖሊስ በቂ እርምጃ አልወሰደም አሊያም ሆን ብሎ ቸል ብሏቸዋል የሚል ቅሬታ ያቀርባሉ።
«ሕግ እና ፖሊስ ሁሉንም በእኩልነት ማገልገል አለበት» የሚል አቋም ያላቸው ሊና በተሳዳቢነታቸው የሚታወቁ የቲክቶክ ተጠቃሚ በቁጥጥር ሥር መዋል እንዳለባቸው አቋማቸውን ገልጸዋል። መኩ «አቤት ፍትኅ ለአንዱ እናት ለአንዱ እናጀራ እናት» ሲሉ ታዝበዋል። አቡ መስዑድ «ነውር የሚባለው እንግዲህ ይሄ ነው። ሁሉንም እኩል ብትመለከቱ የተሻለ ነው። ለራሳችሁ ስትሉ» የሚል ምክር ለግሰዋል።
ኢሰሬ ሙርጃን «ቲክቶክ ከፖለቲካ ወጥቶ ወደ መንደር ድብድብ አጀንዳውን ቀይሯል። ይኸ ሚዲያ ቤንዚን ማውጫ፣ መሸጫ ነው። ጥንቃቄ ይፈልጋል። በፍጥነት ነገሮችን የመቀየር ባህሪ አለው» የሚል ሥጋት የተጫነው አስተያየት ጽፈዋል። ፖሊስ «በማኅበራዊ ሚዲያ (ቲክቶክ) ፕላትፎርምን በመጠቀም” የአዲስ አበባን «ሰላም ለማወክ እና በኅብረተሰቡ ላይ የደኅንነት ስጋት ለመፍጠር በተደራጀ መንገድ በሚንቀሳቀሱ ግለሰቦች እና ቡድኖች ላይ ተገቢውን ክትትልና ቁጥጥር እያደረገ» እንደሚገኝ ገልጿል።
እሸቴ በቀለ
ሸዋዬ ለገሠ