የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት፣ የ12ኛ ክፍል ፈተና፣ የግዕዝ ጣጣ፣ የሰላም ጉባኤ
ሐሙስ፣ መስከረም 8 2018
ጤና ይስጥልኝ እንደምን አላችሁ።የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ብሔራዊ ፈተና ዉጤት፣ አማራ ክልል የግዕዝ ቋንቋን ለማስተማር ማቀዱና አዲስ አበባ የተደረገዉን የሰላም ጉባኤ በቃኙ ዘገቦች ላይ በርካታ አስተያየቶች ተሰጥተዋል።ምክንያታዊና በጨዋ ደንብ ከተሰነዘሩት አስተያዬቶች ጥቂቱን ባጫጭሩ እናሰማችኋለን።ከቻላችሁ አብራችሁን ቆዩ።
የኢትዮጵያ የከፍተኛ ትምሕርት መግቢያ ፈተና (EHEEE)
የ12ኛ ክፍል መልቀቀቂያ ወይም የኢትዮጵያ የከፍተኛ ትምሕርት መግቢያ ፈተና (EHEEE-አቤት የኢ ብዛት) አምና ተሰጥቶ ነበር።ዉጤቱ ይፋ የሆነዉ ባለፈዉ ሳምንት ማብቂያ ነዉ።የትምሕርት ሚንስቴር እንዳስታወቀዉ ፈተናዉን ከወሰዱት ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ያለፉት 8.4 ከመቶ ብቻ ናቸዉ።በሌላ አባባል ከ91 ከመቶ የሚበልጡት ተፈታኞች ወድቀዋል።
አስደንጋጩ ዉጤት የተወሰኑ ተፈ,ታኞች ሕይወትን እስከማጥፋት ማድረሱ ሲዘገብ፣ ብዙዎችን እያነጋገረ፣ በትምሕርቱ ሥርዓቱ ላይ ጠንካራ ግን ተቃራኒ ትችት እየተሰጠ ነዉ።ማስተዋል ጥበበ በፌስ ቡክ በእንግሊዝኛ ባሰፈረዉ ፅሁፍ ተማሪዎችን ይወቅሳል።«እስከ 80 በመቶ የሚገመቱት ተማሪዎች» ይላል ማስተዋል «በአካዳሚያዊ ማጭበርበር ባሕሪ የተጠመዱ ናቸዉ።»
ዳንኤል ከአቢሲኒያ ግን ዘለግ ባለ ፅሁፉ ተቃራኒዉን ነዉ-የሚለዉ።(ዶክተር ብርሐኑ የትምሕርት ሚንስትርነቱን) ዛሬም እንደ መርዶ ነጋሪ በዓመት አንዴ ይመጡና 8 በመቶ ብቻ ነዉ ያለፈዉ ይሉናል።» ዳንኤል ከአቢሲኒያ ቀጠለ «የተማሪዎቹ መዉደቅ የሱ ጥፋት ያልሆነ ይመስል፣ የመማሪያ መፅሐፍት እንኳን ለተማሪዎች ማደል ያልቻለ ትምሕርት ሚንስትር---» የዳናኤል አስተያየት በዚሕ አላበቃም።እኛ ግን ከዚሕ በላይ እንልም።
አበበ ይስማዉ------ «ከፍተኛ ድጋፍ እና ኢንቨስትመንት ያለበት የተሻለ ውጤት እንደሚኖር እውን ነው!» ይላል በፌስ ቡክ።
ሥለሺ ትዕግሥቱ----«ለምን ኮርጀዉ አያልፉም ነዉ የምትሉት?» ጠየቀ በፌስ ቡክ።ተሻለ ጊ ገላን---መልስ ብጤ አለዉ።«ኮርጀው ይለፉ የሚል ማንም አይኖርም» ብሎ ይጀምራል፣ ተሻለ ገላን-ረጅም አስተያየቱን «ነገር ግን መስራት የሚችሉ ተማሪዋች ያልሠሩበት ምክንያት መፈተሽ አለበት። በአገራችን ጎበዝ ተማሪ 8% ብቻ አይመስለኝም። ሌላው ትግበራው ከታች ጀምሮ ነው መሆን ያለበት።»
አዲስወግ ሆራ---ግን «ሳይሰሩ መብላትና ሳይማሩ ዶ/ር መባልን የለመደ ህዝብ፣ ስራ ሲባል እዬዬዬ
ተማር አጥና ሲባል እዬዬዬዬ---» በማለት ይተቻል።ዮኑስ ቸኮል---እሱም በፌስ ቡክ «ግዕዝ ሲማሩ 94% ያልፋሉ ብላችሁ ነዉ ነው ታዲያ አጀንዳ የፈጠራችሁብን?» ይጠይቃል።
የግዕዝ ቋንቋ በአማራ ክልል ሥርዓተ ትምሕርት መካተት
ዮኑስ ቸኮል «አጀንዳ» ያለዉ ግዕዝን የማስተማር ዉሳኔ በተለይ በአማራ ክልል በርግጥም ለሳምንቱ አነጋጋሪ ጉዳይ ነዉ-የኛም ርዕሥ።ተደጋግሞ እንደሚባለዉ ምክንያቱ ግጭት፣የበጀት እጥረት፣ ትኩረት አለመስጠት ሌላም ሊሆን ይችላል።ለአንዳድ አካባቢ የአማራ ክልል ተማሪዎች ወንበርና ጠረጴዛ፣ ደብተርና መፅሐፍት ብርቅ ነዉ።
ለሌሎቹ ደግሞ ትምሕርት ቤታቸዉ፣ የሐረግ-ዳስ፣ የዛፍ ጥላ፣ ወንበራቸዉ ድንጋይ፣ ጠረጴዛቸዉ-ጭናቸዉ መሆኑን ብዙዎች ከብዙ ጊዜ በላይ ተናግረዉታል።ከዚሕም አቅም ክልሉ ዘንድሮ ሊያስተምር ካቀደዉ 7.4 ሚሊዮን ተማሪዎች ዉስጥ እስከያዝነዉ ሳምንት የተመዘገቡት የክልሉ ትምሕርት ቢሮ እንደመሰከረዉ 3 ሚሊዮን አይሞሉም።
የአማራ ክልል ባለሥልጣናትተማሪዎች ትምሕርት የሚያቋርጡበትን ችግር ከማስወገድ፣ ወይም የሚማሩበትን ሥፍራና ቁሳቁስ ሳያስተካክሉ የግዕዝ ቋንቋ ለማስተማር ወስነዋል።ወይም ዮኑስ ቸኮል እንዳለዉ አዲስ «የዉዝግብ አጀንዳ» ፈጠሩ።
ወርቅነሽ ተስፋዬ--«ኤጭ» አለች በፌስ ቡክ-ዉዝግቡ ስልችት ሳይላት አልቀረም።«ለግዕዝም እንጨቃጨቅ» አከለች ወርቅነሽ።ኢዮአብ ቸርነት---«ሁላችንም ግዕዝ መማር አለብን» ይላል።ሙሕዲን አሕመድ አል ሐበሺ ግን---«አንድም ማህበረሰብ ተናጋሪ የሌለውን ቋንቋ በግድ ተማሩ ከማለት፣ ለስራ ጠቃሚ የሆነውን ኦርሚኛ፣ትግርኛ፣አፋርኛ፣ሶማልኛ፣ወላይትኛ...እና ሲዳምኛን ተማሩ።» የሙሕዲን አህመድ አስተያየት ነዉ።
ዝም ነዉ መልሴ---የሚል የፌስ ቡክ ሥም ያለዉ---በዚሕ ጉዳይ ላል ዝም አላለም።«አረብኛም ቢሰጡን እንወዳለን» አለ።በኪ በ,ኪ----«አጀንዳ ፈጥሮ በሰላም የሚማሩትን እንዳይማሩ ለማስተጓጎል ነዉ» በማለት ይተቻል። ኬ አሚ---በእንግሊዝኛ ባሰፈረዉ ወይም ባሰፈረችዉ አስተያየት፣ ግዕዝ መማር «ግዴታ መሆን የለበትም፣ እኛ የቋንቋ እጥረት የለብንም» ይላል ወይም ትላለች።
ሳሙኤል ታደሰ ሳሚ---ትዕዛዝ ብጤ ሰንዝሯል ---« አትጨቃጨቁ---- ዳይ ወደ ሥራ!!!» የምትል ቀጭን ትዕዛዝ።
የሰላም ጥሪና ጉባኤ በአዲስ አበባ
የኢትዮጵያ የሲቪል ማሕበራት ድርጅቶች ምክር ቤት ዘንድሮ በተለያዩ አካባቢዎች በተከታታይ ሊያደርጋቸዉ ካቀዳቸዉ የሰላም ጉባኤዎች አንዱ ባለፈዉ ማክሰኞ አዲስ አበባ ዉስጥ ተጀምሯል።ጉባኤዎቹ የጦርነት፣ የግጭትና የኃይል ርምጃ መነሻዎችን ተመርምረዉ፣ ችግሮቹን ለማቆም በሚረዱ ብልሐቶች ላይ የሚመክርና ለተፋላሚዎች ጥሪ የሚደረግባቸዉ ናቸዉ ተብሏል።
በማክሰኞዉ ጉባኤ ላይ ጥናታዊ ፅሁፍ ያቀረቡት የፖለቲካ ሳይንስ ምሑር ዶክተር ሰሚር የሱፍ «ሕዝብና መንግሥት በጥርጣሬ ከመተያየት ለመዉጣት ሥራ ያስፈልጋል» ማለታቸዉ ተጠቅሷል።የልብ አድራሽ ነኝ---በፌስ ቡክ «ምን ጥርጣሬ ብቻ? ከዛም በላይ ነው» ይልና ቀጠለ--- «ህዝብ አንገት ደፍቶም መኖር ማይችልበት ደረጃ ላይ ነው።» እያለ
ታደለ ፈለቀ---«የትም ሀገር መንግስት ለህዝብ ብሎ የሚሰራው የፅድቅ ስራ የለም» ይላል በፌስ ቡክ።በዚሕ አላበቃም።«መንግሥት የሚሠራዉ ለሥልጣኑ ሲል ነዉ።ለስልጣኑ የማያሰጋ ሰነፍ ህዝብ ካለ፣ የመንግስት ባለስልጣናት ተኝተው በፌስቲቫል በፋሽንና በጉብኝት ህይወታቸውን ይመራሉ::የሚፈሩት ህዝብ ካለ ህዝቡ ከስልጣን እንዳያባርራቸው ልማትና አገልግሎትን በማሻሻል ስራ ይጠመዳሉ:: የኢትዮጵያን ምድብ እንግዲህ ፈልገህ አግኝ::»---እስኪ ፈልጉ እስኪ።
አሸናፊ ለሜሳ ግን ---«ያሁኑ መንግስት ምንም ብዥታ የለበትም።----ግድያና ብልግናዉ ከመንግስት ወደ ጎንለጎን ነው የባሰው።» አለ በፌስ በኩ።
አሰፋ ደበበ በፋንታዉ «የዘር ፖለቲካ እስካለ ድረስ፣ ሰላምም እድገትም ሊኖር አይችልም» ሲል፣ አቤል ቦጋለ «መንግስትን ማመን አሁን ከባድ ነው።» አለ---ቀጠለናም «ነገሮቹ ሁሉ ቁማር ናቸዉ» አበቃም
እኛም ይብቃን።
ነጋሽ መሐመድ ነኝ።መልካም ጊዜ
ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር