1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

ዓርብ፣ ግንቦት 11 2015

«ህገ መንግስቱ መነካት የለበትም የሚሉና ተቀዶ ይጣል የሚሉት ሁለቱም ፅንፍ የያዙ አስተሳሰቦች ናቸው። ህገመንግስቱ ከጥቅማቸው ጉዳታቸው የሚያመዝኑ አንቀፆች መቀየር አለባቸው በሚለው እንስማማለን፤ »ብለዋል። ሌላው ደግሞ «ጥናቱ ተአማኒነት ይጎድለዋል! ምክንያቱም ሀገሪቱ በቀለጠ ጦርነት ውስጥ በነበረችበት ወቅት የተደረገ በመሆኑ ነው !» ብለዋል።

Social Media Apps | WhatsApp Facebook Twitter Instagram
ምስል Nasir Kachroo/ZUMA Press/imago images

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

This browser does not support the audio element.

የኢትዮጵያ ፖሊሲ ጥናት ተቋም በህገ መንግስት ማሻሻያ ላይ ለሁለት ዓመታት ሲያደርግ የነበረውን ጥናት ይፋ አድርጓል። የፌደራል የመንግስት የራስን እኩይ ፍላጎት በሌሎች ላይ በሐይል በመጫን የትኛውንም ዓይነት ፍላጎትም ሆነ ጥቅም ማረጋገጥ አይቻልም በማለት «ጽንፈኛ» ባላቸው ኃይላት ላይ የጀመረውን ህግ የማስከበር እርምጃ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ዐስታውቋል። የኢትዮጵያ ብሄራዊ የምርጫ ቦርድ ሕዝባዊ ወያነ አርነት ትግራይ ህወሃት የህጋዊ ሰውነት ስረዛ ይነሳልኝ ብሎ ያቀረበውን ጥያቄ ውድቅ ማድረጉም ተሰምቷል። ጤና ይስጥልን አድማጮች የዕለቱ የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት ዝግጅታችን በሶስት ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ያተኩራል፤ መልካም ቆይታ !
የኢትዮጵያ ፖሊሲ ጥናት ተቋም ባደረገው የህገመንግስት ጥናቱ ለዓመታት ማሻሻያ እንዲደረግባቸው በተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ውትወታ ሲቀርብባቸው የነበሩ አንቀጾችን ጨምሮ በተለያዩ የህገ መንግስት አንቀጾች ላይ ሲያደርግ የነበረውን የማሻሻያ ጥናት ማጠናቀቁን አስታውቋል።  ተቋሙ የግኝቱን ውጤት ይፋ ባደረገበት ወቅት እንዳለው ህገ መንግስቱ ከተግባራዊነቱ ጊዜ አንስቶ አጨቃጫቂ ነበሩ ጉዳዮች መልስ እንዲያገኙ ማስቻልን ታሳቢ ማድረጉን ገልጿል። ነገር ግን አሁን በስራ ላይ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ህገ መንግስት ጋር በተያያዘ በህብረተሰቡ ዘንድ ሶስት የተለያዩ እሳቤዎች እንደሚንጸባረቁ ዶይቼ ቬለ ከጥናቱ አስተባባሪ መረዳት ችሏል።«አንዱ ይኽ ሕገ መንግሥት በምንም መልኩ መነካት የለበትም እንደውም ተጠናክሮ በደንብ ወደ መሬት መውረድ አለበት ሲል፤ ሌላኛው ጽንፍ ሕገ መንግሥቱ የተጻፈበትን ቀለም እንኳ ያህል ዋጋ የለውም ተቀዶ መጣል አለበት በሚል እንደሚጣጥል፤ ሦስተኛው ደግሞ ሕገ መንግሥቱ ጥሩ ነገሮች አሉት እነሱን ማስቀጠል፤ የሚሻሻሉ ካሉ ደግሞ እነሱን እያሻሻሉ መቀጠል እንጂ  ከዜሮ መጀመር አስፈላጊ አይደለም የሚል ነው።»  የጥናቱ ዉጤት ይፋ መደረጉን ተከትሎም የተለያዩ የማህበራዊ መገናኛ ዘዴ ተጠቃሚዎች የተለያዩ አስተያየቶችን ሲያንሸራሽሩ ቆይተዋል። 
አድማማ ዋዴንጎ በፌስ ቡክ ባሰፈሩት አስተያየት «ህገ መንግስቱ መነካት የለበትም የሚሉና ተቀዶ ይጣል የሚሉት ሁለቱም ፅንፍ የያዙ አስተሳሰቦች ናቸው። በማለት እኔና ብዙዎቹ በህገመንግስቱ ከጥቅማቸው ጉዳታቸው የሚያመዝኑ አንቀፆች መቀየር አለባቸው በሚለው እንስማማለን፤ »ብለዋል።
ሃዋዝ ክፍሌ የጥናቱን ተዓማኒነት መጠራጠራቸውን በገለጹበት አጭር መልክታቸው «ጥናቱ ተአማኒነት ይጎድለዋል! ምክንያቱም ሀገሪቱ በቀለጠ ጦርነት ውስጥ በነበረችበት ወቅት የተደረገ ጥናት በመሆኑ ነው !» ብለዋል።
አወት ኃይለማሪያም ብርሃነ በበኩላቸው 
«ይህ ጥናት በኢትዮጵያ ህገመንግስት ውስጥ ብሔርና ብሔረሰቦች ላይ ብቻ ያደረገ ጥናት ስለሆነ የተሟላ አይደለም »: ይላሉ ። አወት ምክንያቱን ሲገልጹም  «አንቀፅ 8 የኢትዮጵያ ሉአላዊነት በብሔር: በብሔረሰቦች: ህዝቦች ይላልና::» ብለዋል። «ህዝቦች ያልተካተቱበት ጥናት ፉርሽ ነው: ያሉት አወት  የፖሊሲ ተቋሙ ተመራማሪዎች ስራ ቢቀይሩ እመክራለሁ:: »በማለት የጥናቱን ውጤት አለመቀ።በላቸውን በገለጹበት መልዕክት ገልጸዋል። 
ምስክር የተባሉ ሌላው የማህበራዊ መገናኛ ዘዴ ተጠቃሚ ባሰፈሩት አጭር መልዕክት «ህግ መንግሥቱ ላይ አንድም ችግር የለበትም ችግሮች በተደጋጋሚ እንዲፈጠሩ መንስኤዎች ህግ መንግስቱን የሚያከብር መንግስት በሀገሪቱ አለመኖሩ እና የተባሉትን ትዕዛዛ ብቻ የሚያስፈፅሙ እንዲሁም ለህግ መንግስት ክብርም እዉቀትም የሌላቸው ጸጥታ አስከባሪዎች መበራከታቸው ነው።» ብለዋል።
ዱጋ ሞኢ የተባሉ አስተያየት ሰጭ የጥናቱን ተአማኒነት በተመለከተ በፌስ ቡክ በሰጡት አስተያየት «ጥናቱ መፍቀሬ አሃዳዊ ሥርዓት ከሆኑትና የአንድ ወገንን ፖለቲካዊ ፍላጎት ለማሳካት ከሚታትሩ ወገኖች ተውጣጥተው የተሠራ ስለሆና የብዙሃኑን ብሔር ብሔረሰብ ፍላጎት ያልተንጸባረቀበት ስለሆነ ታዓማኒነት የለውም» ብለዋል። 
ራቢያት ሁሴን በበኩላቸው «ይህንን ጥናት አቅርቦ ለመገምገም የተደረገ ይመስላል»ሲሉ በጥናቱ ሂደት ላይ ያላቸው ጥርጣሬ ገልጸዋል።  «በግሌ» አሉ ራቢያት  «ማህበራዊ ሚድያዎች ላይ ተሳትፎ ያላቸው ወገኖች የአንድ አካባቢ በመሆናቸው ግምገማው የተሳሳተ መንገድ እንዳይዝ ትኩረት መደረግ አለበት ። ሌላትርምስ እንዳይፈጠር ።» ብለዋል። አያይዘውም «አሁንም እንኳን አንዳንዶች ያለመከሰስ መብት አለኝ በሚል ህዝብን የሚያደናግር ነገር ውስጥ እየገቡነው ፤ » በማለት ሃሳባቸውን አጋርዋል። 

ምስል Solomon Muche/DW

አንተነህ የተባሉ የማህበራዊ መገናኛ ዘዴ ተሳታፊ «ከመጀመሪያውም ህገ መንግስቱ እንከኖች እንዳሉበት ሁሉም ይስማማበታል ፡ በየወቅቱ ወደ ስልጣን የሚመጣውም መንግስትም ቢሆን ችግር እንዳለበት ጠንቅቆ ያምናል።» ብለዋል። ነገር ግን አሉ ቀጥለው ባሰፈሩት መልዕክታቸው አንተነህ፤ «አንድ መሰመር ያለበት ጉዳይ ቢኖር ይህ ህገመንግስት በየወቅቱ ወደ ስልጣን የሚመጣን ገዢ ፓርቲ ህልውና ያስጠብቅለታል፡ በስልጣን እንዲቆይ ዕድሎች ይፈጥሩለታል በብሄር ሽፋን። በመሆኑም እንዲነካ አይፈቅድም ፡ ከነ እንከኑም ቢሆን እንዲቀጥል ይፈልጋል። ስለዚህ የኢትዮጵያ ህገመንግስት ሊሻሻል የሚችለው በስልጣን ላይ ካለው መንግስት ይሁንታ ሲያገኝ ብቻ ና ብቻ ነው። ህዝቡማ እንዲሻሻል ፍላጎቱን ካሳየ ቆይቶአል፡ አሁንም አሳይቶአል፡  በህዝቡ በኩል ችግር የለም።ብለዋል።»
ነስሩ መሀመድ ሁሴን በበኩላቸው ዘራችን ቆጥሮ ለኛው አስረዳን ከሰብዓዊነት አስወጥቶ አምልኮ ፣መተዳደሪያ፣መኗኗሪያ፣መከታ ፣ስልጣን ፣ሌሎችም....በእውቀት ና ብቃት እንዳንወዳደር አድርጎ በቁጥር ስብስብ እንድንመራ ጠምዝዞናል ። እዳውን መዘርዘር አልችልም።ኢትዮጵያዊ ሁሉን ያማረረ ጉዳይ ነው። የዘር ፖለቲካ አልበጀንም ።» በማለት ሃሳባቸውን አጋርተዋል። 
ከሰሞኑ በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ላይ በሰፊው ካወያዩ እና በርካቶች ሲቀባበሏቸው ከነበሩ ጉዳዮች ውስጥ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ህዝባዊ ወያነ አርነት ትግራይ ህወሓት የህጋዊ ሰውነት ስረዛ ይነሳልኝ አቤቱታ አንዱ ነበር ። ቦርዱ ለህወሃት በሰጠው ምላሽ የፓርቲው ህጋዊ ሰውነት ከተሰረዘ በኋላ ለመመለስ የሚያስችል የህግ መሰረት የለም ብሏል። የቦርዱን ውሳኔ ህወሃት እና የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ተቃውመውታል። ቦርዱ ውሳኔውን በድጋሚ እንዲያጤነውም ጠይቀዋል። 
መብራቱ ከበደ የተባሉ የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተጠቃሚ የቦርዱን ውሳኔ አስመልክተው በሰጡት አስተያየት 
«አሸባሪነቱ በመንግሰት ተፈርጆ በፓርላማው የጸደቀበት ህወሃት በእርቅ ሰምምነት በተፈጸመ የፖለተካ አውድ አሸባሪነቱ ተነስቶለት በፓርላማው መነሳቱ ከጸደቀለት ወደ ህጋዊ ፓርቲነት የመመለስ መብቱን ማግኘቱ የግድ ነው» ብለው ፤  ምክንያቱን ሲጠቅሱም « የፓርቲ ህልውናው ያከተመበት አሸባሪ ከሚለው ፍረጃ ተነስቶ ሰለነበርና አሁን የፈረጀው አካል በስምምነት ፍረጃውን ካነሳለት ወደነበረበት የፓርቲ አቋሙ መመለስ መብቱ ብቻም ሳይሆን ግዴታውም ነው ።» ብለዋል። 
አስታራቂ ሀሣብ በማለት አጭር መልዕክት ያሰፈሩት ደግሞ ጉበና ፈንታው ናቸው። አስታራቂው ሃሳብ ህወሀት "ህዝባዊ ወያነ ሀድነት ትግራይ" በማለት እንደእዲስ ይመዝገብ፣ በማለት ምክር አዘል ሃሳብ አስፍረዋል። 
ዮኒ ክፍሌ በበኩላቸው «ህወሓት ምነው ዳግም በመራን  «ህወሓት ሆይ ! ማረን ይቅር በለን» ሲሉ ለፓርቲው ያላቸውን ድጋፍ የገለጹበትን ሃሳብ አስፍረዋል። 
ተሜ ገብረየሱስ የተባሉ ሌላው አስተያየት ሰች በፌስ ቡክ ባሰፈሩት ሃሳባቸው «ሕወሓት የሚሰረዘዉ በምርጫ ቦርድ ሳይሆን በትግራይ ብቻ ነዉ።» ብለዋል። 
ግሩም ወንድሙ ደግሞ የምርጫ ቦርድ ኃላፊዋን ስም በመጥቀስ «ሀገራችን ያለችበት ደረጃ የገባቸው  አይመስለኝም።»በማለት ስሜታቸውን ገልጸዋል። 
አማኑኤል ትዕግስቱ በበኩላቸው « ልዩነቶችን በውይይትና በሰለጠነ መንገድ መፍታት፤ እና የምንፈልገው ሰላም ነው። »ብለዋል። 
የፌደራል የመንግስት በዚህ ሳምንት ባወጣው መግለጫ «የራስን እኩይ ፍላጎት በሌሎች ላይ በኃይል በመጫን የትኛውንም ዓይነት ፍላጎትም ሆነ ጥቅም ማረጋገጥ አይቻልም»ብሏል። በዚህም መንግስት  «ጽንፈኞች» ባላቸው አካላት ላይ የጀመረውን ህግ የማስከበር እርምጃ አጠናክሮ እንደሚቀጥል የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገልጿል። 
ማሜ ሁሴን የተባሉ አስተያየት ሰች በፌስ ቡክ ባሰፈሩት አስተያየት «ፅንፈኞች የግል ፍላጎታቸዉን በሌሎች ላይ ለመጫን ስለምታገሉ ብዙኃኑን አይወክሉም » ብለዋል ።  ማሜ አያይዘውም  «ህዝብን የሚወክሉና የህዝብን ፍላጎት ያማከለ ሀሳብ ያምያራምዱ ከመንግስት ጋር ተደራድረው ወደ ትክክለኛ መንገድ እየገቡ ነዉ።» ብለዋል። 
ደመላሽ የተባሉ አስተያየት ሰጭ በበኩላቸው " ጽንፈኛ እኳ ራሱ ምንግስት ነው " ብለው «በነገራችን ላይ አሉ ደምመላሽ «መንግስት ጉልበቱን ነው የተማመነው እንጅ ለሰላም እጁን አልዘረጋም ። ለሰላም እጁን ቢዘረጋ ኑሮ በአንድ እጅ ሰላም በአንድ እጅ አፈሙዝ ተይዞ እንዴት ነው መግባባት የሚቻለው ? በማለት ጠይቀዋል። 
ካሳዬ ወንድሙ በበኩላቸው «ማንም መሳሪያ የታጠቀ የሰፈር ጎረምሳ ባኮረፈና ጫካ በገባ ቁጥር መንግስት ተደራደር እየተባለ እስከመቸ ሲጎተት ይኖራል?» ጠይቀዋል። 
በአምላክ ደሳለኝ ፤«እውነት ነው» አሉ። ከምክክር ውጭ ጉልበት አዋጭ አይደለም። አሻጋሪው መንግስት ግን በህዝብ ገንዘብ በውድ የገዛቸውን ድሮኖች የተማመነ ይመስላል።» በማለት የመንግስትን የኃይል አማራጭ የነቀፉበትን አስተያየት አስፍረዋል። 
አማኑኤል መገርሳ ደግሞ፤ «በልመና የሀገር ህልውና አይረጋገጥም» ብለዋል።  መንግስት እንደመንግስትነቱ ህገ ወጦችን ባለው አቅም በሙሉ ተጠቅሞ ህግ መስከበር አለበት።  ሀገሪቱ የጎበዝ አለቃ አያስፈልጋትም፤ ተቀበልነውም አልተቀበልነውም በህዝብ የተመረጠ መንግስት ሀገሪቱ አላት በማለት የመንግትን መግለጫ የደገፉበትን ሃሳባቸውን አስፍረዋል። 
እንግዲህ አድማጮች በርዕሰ ጉዳዮቹ ላይ በማህበራዊ የመገናኛ ዘዴ ተጠቃሚዎች በርካታ አስተያየቶች የሰፈሩ ቢሆንም የመራረጥናቸው እነዚህን ይመስሉ ነበር ። ለአብሮነታችሁ ምስጋናችን ትልቅ ነው። 

ምስል Solomon Muche/DW
ምስል DW/M. Haileselassie
ምስል Ethiopian National Election Board

ታምራት ዲንሳ

ኂሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW