የቤት ኪራይ መናር፤ የሱዳን ወረራ እና የመንግሥት ምላሽ፤ በረሃብ ሰዎች ሞቱ
ዓርብ፣ ኅዳር 21 2016በአዲስ አበባ የመኖርያ ቤት ኪራይ መናር፤ መንግሥት ሱዳን በወረራ የያዘችውን የኢትዮጵያ መሬት ለማስመለስ የሱዳን ሰላም እስኪመለስ ይጠበቃል ማለቱ፤ እንዲሁም በትግራይ እና በአማራ ክልሎች በረሃብ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር መጨመሩ በሚሉ ርዕሶች ስር የተሰበሰቡ አስተያየቶችን ጨምቀን ይዘናል።
በአዲስ አበባ ነዋሪዎች የመኖርያ ቤት ችግር እጅግ ከፍተኛ መሆኑ እየተነገረ ነዉ። በተለይ የመኖርያ ቤት ኪራይ በየግዚዉ የሚጨምርባቸዉ ሰዎች ምን አይነት መፍትሄ እንደሚኖር ጨንቋቸዋል። ደምወዛቸዉ ዉስን የሆኑ ዜጎች የቤት ኪራይ ሲጨምር የሚያገኙት ድጎማ የለም። ግን የቤት ኪራይ ጨምረዉ እንዲከፍሉ ይገደዳሉ። መፍትሄዉ ምን ይሆን ? መንግሥት ምን እርምጃ መዉሰድ ይኖርበት ይሆን? ለሚለዉ
አቡሽ ባሪ የሚባሉ የፌስቡክ ተከታታይ፤ እረ ምኑ ይነገራል ሲሉ ይገልፃሉ። ቦኒ ቢት የተባሉ በበኩላቸዉ ፤ ከዚህ በላይ ምን ይገጥመናል በአጥንታችን አስቀረን እንጂ ሲሉ አስተያየታቸዉን አስቀምጠዋል። አቡ ተስፋዬ የተባሉ አስተያየት ሰጭ ፤ ሰለ ቤት ኪራይ ማውራት ይከብዳል፤ መኖር ከብዶናል፤ ሲሉ ምሬታቸዉን ገልፀዋል። ቴዲ ማን የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ እንደሚሉት፤ መንግሥት የለም ሀገሪቷ ላይ የቤት ኪራይ ጨምሮ ሁሉም ነገር አዲስአበባ ላይ እሳት ሁኗል ሲሉ በቃል አጋኖ የችግሩን አሳሳቢነት አፅኖት ሰጥተዋል። ፌሊፒስ ጴጥሮስ የተባሉት አስተያየት ሰጭ የምንተዳደረው አከራይተን ነው፤ ለኛም ይታሰብ እንጂ ይላሉ። ሃብቴ ደስታ የተባሉ ሌላ አስተያየት ሰጭ በበኩላቸዉ ረዘም ያለ አስተያየት አስቀምጠዋል። የተለያዩ መጭበርበሮች እንዳይፈጠር ጥልቅ የሆነ ምርመራ የሚያስፈልገዉ ችግር ነዉ። የቤት ኪራይ ዋጋ በካሬ ሜትር መሆን አለበት። ለምሳሌ ቤት እያለ አለከራይም ፤ በተካራይ ላይ ዋጋ በመጨመር የሚተዳደሩ ደላሎች ችግር እንዳይፈጥሩ፤ የቤት ኪራይገንዘብ ለአከራዮች በባንክ ሲስተም በሚታይ ሁኔታ እንዲገባ ማድረግ ያስፈልጋል። በቅድሚያ ግን መንግስት በኪራይ ቤቶች ጽ/ቤት በኩል በእያንዳንዱ ግቢ ወይም ቤት ዉስጥ ስንት ኪራይ ቤት እንዳለ በጥንቃቄ መቁጠር አለበት፤ ሲሉ አስተያየታቸዉን ደምድመዋል። ሃይሎም ታደሰ የተባሉ ሌላዉ የፌስቡክ ተከታታይ ኸረ በመቀሌም ቤት ኪራይ ከመጠን በላይ ጨምሯል ፤ ውኃና መብራት እደ ፍላጎታችን መጠቀም አይፈቅዱልንም። ወደ ሚመለከተው አካል ችግራችንን አድርሱልን እባካችሁ ሲሉ አስተያየታቸዉን አስቀምጠዋል።
ሃብታሙ ኑኑ የተባሉ የፌስቡክ ተከታታይ እንደሚሉት ደግሞ፤ ቤት አግኝቼ እስክገላገል ድረስ ልሰቃይ እንጂ መንግስት አለ፤ መፍትሄ ይሰጠናል ብዬ አላምንም ሲሉ አስተያየታቸዉን ቋጭተዋል። አቤ ላቭ የተባሉ አስተያየት ሰጭ ትንሽ ለየት ያለ አስተያየት ነዉ ያላቸዉ። እኔ ተከራይ ነኝ ይላሉ። እኔ ተከራይ ነኝ። አከራዮቼ በጣም ጥሩ ስለሆኑ አልጨመሩብኝም። በጥሩ ዋጋ ነው ያከራዩኝም። ነገር ግን እንደ በአጠቃላይ የቤት ኪራይ ዋጋ ጨምሯል፣ ከላይ የጠቀሳችኋቸው ችግሮች በሙሉ አሉ፤ ሲሉ አረጋግጠዋል።
ሽብሬ ዳዊት በአስተያየታቸዉ፤ የቤት ኪራይ እንዲጨምር ያደረገዉ በመጀመርያ ደረጃ መንግሥት ነዉ ይላሉ። መንግሥት ነዉ። አንደኛ ማኅበረሰቡ ላይ ግብርን በመጫኑ፤ ሁለተኛ የመበራት የውኃ ክፍያ በመጨመሩ ነዉ። ህዝቡ ላይ ኑሮው ከምግብ ጀምሮ ተወዷል። ድሮ በ 3000 ብር ተከራይቶ 2500 ብር ጤፍ ይገዛ ነበር። ታድያ እዉን አሁን ቤት በ 15000 ብር ተከራይቶ ጤፍን በ 16000 ብር መግዛት ይችላል? ብዙ መጥቀስ ይቻላል። ይህ የመንግሥት ስራ ነዉ፤ ሲሉ ሽብሬ ዳዊት አስተያየታቸዉን ቋጭተዋል።
በትግራይ ክልል አበርጌሌ-ጪላ ዋርዳ በተከሰተው ከባድ ረሃብ ምክንያት ከ 210 በላይ ሰዎች መሞታቸዉ ሰባት ትምህርት ቤቶችም መዘጋታቸዉ ተዘግቧል። በአማራ ክልልም በዋግ ኽምራ ዞን ሰሃላ ሰየምት ወረዳ ቢላዛ ቀበሌ፣ በረሃብ ተጨማሪ ሰዎች እንደሞቱ፣ የአካባቢው ባለሥልጣን አስታወቃቸዉ ተነግሯል። በሌላ በኩል ከአንድ ዓመት በፊት ከምስራቅ ወለጋ ማንነት ላይ ባተኮረ ጥቃት ተፈናቅለው በአማራ ክልል አዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ቻግኒ ከተማ በተለያዩ ቦታዎች የሚኖሩ ዜጎች ከእርዳታ እጦት ጋር በተያያዘ ከ 50 በላይ ተፈናቃዮች ህይወት ማለፉም ተነግሯል። የከተማ አስተዳደሩ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጽ/ቤት እርዳታ ለተፈናቃዮቹ እየደረሰ አይደለም ብለዋል።
መለሰ አድማሱ የተባሉ የፌስቡክ ተከታታይ፤ ኸረ ኢትዮጵያውያን እንረባረብ እንድረስላቸው በጦርነት እንደዛ መከራቸውን አዮ አሁን ደግሞ በርሀብ። እባካችሁ ሰዎች፤ ጥላቻ ሰባኪዎች ሁሉን ተው፤ ህዝብ ይረዳዳ ሲሉ አስተያየታቸዉን አስቀምጠዋል። ሊዲያ ሃበሻ የተባሉ የፌስቡክ ተከታታይ፤ በአሁን ሰዓት ከተማ አካባቢ ያለው ቢያንስ በቀን አንዴ ሳይበላ አይውልም። በመላው የኢትዮጵያ ገጠራማው ክልል ግን ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ከባድ የምግብ እጦት ላይ ነው። ደጉ ገበሬ እንክዋን ለእሱ ከተማውን እሚያጠግበው ዛሬ ረሀብ ላይ ነው። ለዚሁሉ ተጠያቂው ደሞ እግዚአብሔር ይፍረድባቸውና ፖለቲከኛች ናቸዉ ሲሉ አስተያየታቸዉን አስቀምጠዋል።
ተመስገን ጁዶ የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ ህዝቡ እምነቱን ይላሉ፤ ህዝቡ እምነቱን ከመንግስት ወደ ፈጣሪው ካልቀየረ በቀር ችግሩ ይቀጥላል ሲሉ አስተያየታቸዉን አስቀምጠዋል።
ሱዳን በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ወቅት በወረራ የያዘችውን የኢትዮጵያ መሬት በድርድር ለማስመለስ የሱዳንን ከጦርነት መውጣት እና ሰላም መሆን እየጠበቀ መሆኑን መንግሥት ማስታወቁ ተሰምቷል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሦስት ወራት የሥራ ክንውኑን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ሲያቀርብ ፣ ሱዳን የኢትዮጵያን መሬት በወረራ ከያዘች ዓመታት ማለፉ እና አሁን ድረስ "የሁኔታ ለውጥ እንደሌለ" ፣ ሆኖም ሀገሪቱ ከችግር ስትላቀቅ መሬቱን በድርድር የመመለስ አቅጣጫ ስለመያዙ ተነግሮ ነበር። "ሱዳን ሰላም የሚሆነው መቼ ነው" የሚለውን ጥያቄ እርግጠኛ ሆኖ መመለስ ስለማይቻል የቀረበው ምክንያት ከመርህ አንፃር አሳማኝ አለመሆኑን አንድ ለዶቼ ቬለ አስተያየታቸዉን የሰጡ የአለም አቀፍ ሕግ እና ዲፕሎማሲ ተንታኝ ግልፀዋል።
ሰልማን ሰይድ የተባሉ የፌስቡክ ተከታታይ፤ እነሱ ግዜ አይተው ነው የወረሩን። እኛ ጦርነት ውስጥ በሆን ሰአት ነው ግዛታችንን የወሰዱት፤ የጃቸውን ማግኘት አለባቸው ሲሉ አስተያየት አስቀምጠዋል። ፌራፌስ ዲናፌስ የተባሉ የፌስቡክ ተከታታይ በበኩላቸዉ፤ ምን ይሰራልናል ያለን መሬት ከበቂ በላይ ነው::አሁን ምንፈልገው የባሕር በር ብቻ በመሆኑ የባሕር በርን መፈለግ ነዉ የሚያዋጣዉ ሲሉ አስተያየታቸዉን ደምድመዋል። አህመድ የወሎ ልጅ ለየት ያለ አስተያየት ነዉ የሰጡት ኤርትታም ይላሉ ኤርትራም ከትግራይ ክልል ዉልቅ ብላ ትዉጣ ብለዋል።
ሰዒድ አልባሺ የተባሉ አስተያየት ሰጭ በጣም ትልቅ ክልሎች የሆኑት አማራና ኦሮሚያ ከመንግስት ቁጥጥር እየወጡ፤ መሃሉ ሃገር ለጠላት በር ከፍቶ ስለ ድንበር ታወራለህ እንዴ? ሲሉ በጥያቄ አስተያየታቸዉን ዘግተዋል። ወልጫፎ ገብሬ የተባሉ አስተያየት ሰጭ፤ ሱዳን በወቅቱ ኢትዮጵያ ውስጥ የነበረውን ሁኔታ ተጠቅማ የኢትዮጵያን ግዛት ወስዳለች። አሁን ደግሞ ኢትዮጵያ የተገላቢጦሽ ካልተጠቀመች ይህ ግዛት ወደፊት በድርድር የሚመለስ አይሆንም ሲሉ ምክር አዘል አስተያየታቸዉን አስቀምጠዋል።
ሃብታሞ ገዛኸኝ የተባሉ አስተያየት ሰጭ ሱዳን ሠላም ስትሆን ነው ወይስ ኢትዮጵያ ሲሉ አጠር ያለ ጥያቄ አይነት አስተያየት ነዉ ያስቀመጡት፤ የተወረረዉ የኢትዮጵያ ግዛት እንዲመለስ ሱዳን ሠላም ስትሆን ነው ወይስ ኢትዮጵያ? . . .ሲሉ አስተያየታቸዉን ደምድመዋል። ጎበና በሻ ማሞ ፤ የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ ግራ መጋባት አይመስልም? ሲሉ ይጠይቃሉ። ግራ መጋባት አይመስልም? የሌላ አገር ወደብ ለመውሰድ ዱብ ዱብ የሚል እንዴት ነው ስለእራሳችን ድንበር ይደርሳል አይነት መልስ የሚሰጡን። ቡርሀን ያሉት ጉዳይ አሁን በደንብ ይገለፅልናል። ሱዳን ኢትዮጵያ የእርስ በርስ ጦርነት ላይ መሆኗን አይቶ አይደለም መሬታችንን የወረረችው። እኛን የህዝብ መፈናቀልና መገደል እልፎም ድንበር ቆርሶ ሲወሰድ ደንታ ያለን አይመስልም። ከዛ በላይ ለሥልጣን ሲባል ከራሳችን ህዝብ ጋር ጦርነት ማድረግ በልጦብናል በእውነት እጅግ ያሳዝናል፤ ሲሉ አስተያየታቸዉን አስቀምጠዋል።
ሄለን ዘማሪያ፤ የተባሉ የፌስቡክ ተከታታይ በበኩላቸዉ፣ እረ ሱዳን የኢትዮጵያን ግዛት፤ በኃይል አደለም የወሰደችው። አልቡርሀን የኢትዮጲያ መንግስት መሬታአችውን ውሰዱ በሎናል ብሏል። በአደባባይ በአልጃዚራ አረብኛ ፕሮግራም ላይ ተናግረዋል፤ ሲሉ አስተያየታቸዉን ጽፈዋል።
አዜብ ታደሰ
ነጋሽ መሐመድ