1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

ዓርብ፣ ጥር 10 2016

በውዝግብ የታጀበውን የዘንድሮው የጥምቀት በዓል አከባበር፤ ትምህርት ሚኒስቴር በ2015 ዓ.ም. የከፍተኛ ትምህርት መውጫ ፈተና ተፈትነው ላላለፉ እጩ ተመራቂዎች ፈተናው በድጋሚ ከጥር 27 እስከ የካቲት 1 ቀን 2016 ዓ.ም. እንደሚሰጥ ማስታወቁን፤ እንዲሁም በአፍሪቃው ቀንድ የተባባሰውን ቀውስ በሚመለከት ከተሰጡ አስተያየቶች መራርጠናል።

አሁን ለፈተና የተጠሩት ከዚሕ ቀደም ተፈትነዉ ያላለፉት ናቸዉ
የኢትዮጵያ ትምሕርት ሚንስቴር ተመራቂዎችን ዳግም ለፈተና መጥራቱ እያወዛገበ ነዉምስል Alemnew Mekonnen/DW

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

This browser does not support the audio element.

በዕለቱ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት በውዝግብ የታጀበውን የዘንድሮው የጥምቀት በዓል አከባበር፤ ትምህርት ሚኒስቴር በ2015 ዓ.ም. የከፍተኛ ትምህርት መውጫ ፈተና ተፈትነው ላላለፉ እጩ ተመራቂዎች ፈተናው በድጋሚ ከጥር 27 እስከ የካቲት 1 ቀን 2016 ዓ.ም. እንደሚሰጥ ማስታወቁን፤ እንዲሁም በአፍሪቃው ቀንድ የተባባሰውን ቀውስ በሚመለከት ከተሰጡ አስተያየቶች መራርጠናል። 

የዘንድሮው የጥምቀት በዓል አከባበርን በተመለከተ ስለዝግጅትና ስጋቱ መነገር ከጀመረ ቀናት ተቆጥረዋል። በዓሉ በየዓመቱ ደምቆ ከሚከበርባቸው አካባቢዎች አንዱ በሆነው ጎንደር ከተማ የሃይማኖት መሪዎችና የመንግሥት ባለሥልጣናት በድምቀት በተለመደው አደባባይ እንደሚከበር ቢገልጹም የከተማዋ ነዋሪዎች ግን በአካባቢው ባለው የጸጥታ መታወክ ምክንያት በዓሉ በአደባባይ ላይከበር እንደሚችል ስጋታቸውን ገልጸዋል። በአዲስ አበባም በተለይ በዓሉን በጃንሜዳ ለማክበር ዝግጅቱ መጠናቀቁ የተነገረ ሲሆን የአዲስ አበባ ፖሊስም በዓሉ በሰላም እንዲከበር መዘጋጀቱን አስታውቋል። ዳጊ ዘ አማራ የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ፤ «ለመንግሥት ፖለቲካ መስሪያ ተብሎ የሚከበር ምንም አይነት በዓል የለም ሲያምራችሁ ይቅር» ሲሉ፤ ቲና ደስታ በበኩላቸው፤ «መንግሥት በእምነት ጉዳይ ምን አገባው? ህዝቡ የዓመት በዓሉን በሰላም እንዳያከብር ብዙ ጊዜ እንቅፋት መፍጠር የተለመደ አድርጎታል::» በማለት ተችተዋል፤ ወርቅነሽ ተካ ግን፣ «እንደ እኔ መንግሥት እና ቤተ እምነት በትብብር ቢሰሩ፤ ሁሉን ነገር ለምን በመጥፎ እንተረጉማለን? ቅን ቅኑን ብናስብ መንግሥት እኮ የሃይማኖት ተቋምን የመጠበቅ ሀላፊነት ያለበት ይመስለኛል።» ነው የሚሉት። ከጥምቀት በዓል አከባበር ዝግጅት ጋር በተያያዘ በዓሉን ለመበጥበጥ ያቀዱ በሚል ወጣቶች እየታፈኑ ነው ሲል ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ ድርጊቱን ኮንኗል። እስራኤል ኢሳያስም፤ «በዓል ምክንያት በማደርግ ወጣቶችን ማፍን ይቁም።» ብለዋል። ሊዲያ ሀበሻ ደግሞ፤ «ኢትዮጵያ ላይ በዓል በመጣ ቁጥር ጭንቀት ፈጣሪ ደግ ቀን አምጣልን።» በማለት በጎ ተመኝተዋል።


ትምህርት ሚኒስቴር በ2015 ዓ.ም. የከፍተኛ ትምህርት መውጫ ፈተና ተፈትነው ላላለፉ እጩ ተመራቂዎች ፈተናው በድጋሚ ከጥር 27 እስከ የካቲት 1 ቀን 2016 ዓ.ም. እንደሚሰጥ አስታውቋል። ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በሐምሌ 2015 ዓ.ም. የተሰጠውን የመውጫ ፈተና ተፈትነው ያላለፉና ፈተናውን በድጋሚ ለመውሰድ በመጠባበቅ ላይ ያሉ ተፈታኞችን ምዝገባም ከጥር 8 ቀን ጀምሮ እስከ ጥር 15 ቀን 2016 ዓም ድረስ እንደሚካሄድ መግለጹን ተከትሎ በርካቶች በማኅበራዊ መገናኛው ሃሳብ አስተያየታቸውን አጋርተዋል። ከእነዚህ መካከል ጊዜው ጸጥ አለ የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ፤ «ምን አውቀዋል ሳይሆን በምን ይወድቃሉ የሚል መርህ ያለው ትምህርት ሚኒስቴር፤ ደጋግሞ ቢፈተኑት ምን ዋጋ አለው?» በማለት ሲጠይቁ፤ አሌክሶ ሙሉጌታ ደግሞ፤ «የመውጫ ፈተና ወይም ኤግዚት ኤግዛም በጭራሽ የትምህርት ጥራት አያመጣም! የተመራቂ ተማሪዎችን ቴምፖ (ዉጤት) ከመያዝ በስተቀር። የትምህርት ስርዓቱ ሞቷል በነብርሃኑ» ነው የሚሉት። ዘለግ ያለ ተመሳሳይ አስተያየታቸውን በእንግሊዝኛ ቋንቋ ያጋሩት ጅግሳ ዋታም፤ «የመውጪያ ፈተና አስፈላጊ አይደለም፤» ነው የሚሉት በቀመጠልም፤ «የሀገሪቱ ክሬም የሆኑ ዜጎች ቀደም ሲል በመምህርነት ወይም በተማሪነት የሚገኙት ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ነው። የዩኒቨርሲቲ መምህራን ወደዚህ ደረጃ የሚመጡት በከፍተኛ ውጤት ካጠናቀቁ በኋላ ሲሆን ተማሪዎችም ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚገቡት የ12ኛ መልቀቂያ ፈተናን በጥሩ ውጤት ካለፉ ነው። ስለዚህ በቀለም ትምህርቱ በኩል ዝቅተኞች ናቸው ማለት አይቻልም። የትምህርቱን ጥራት ለማሻሻል ከመጀመሪያው አንስቶ እስከመጨረሻው ዓመት ድረስ የቅርብ ክትትል ማድረግ ነው። ተማሪዎችም እንዲሁ ከመጀመሪያው ዓመት ጀምሮ ሊመዘኑ ይገባል። በመጨረሻው ዓመት ደግሞ የብቃት ማረጋገጫ ፈተና ሊሰጥ ይችላል። አሁን የትምህርት ሚኒስቴር የሚያደርገው ግን ጊዜና ገንዘብን ማባከን ነው። እናም በእኔ ዕይታ የመውጪያ ፈተናውን መተው የተሻለ ነው።» በማለት ሃሳባቸውን በዝርዝር አጋርተዋል።

የ2016 የከተራ በዓል አከባበር በኢትዮጵያምስል Solomon Muche/DW

 

ዘርዑ ተክላይ በበኩላቸው፤ «የትምህርት ሚኒስቴርም ይፈተን» ነው የሚሉት፤ ሸምስ መሀመድ ደግሞ፤ «ትችቱን ለማስታገስ ነው ወይስ የተማሪዎች ዕጣ ፈንታ አሳስቧቸው? አሁንም የሚወድቁ ካሉ ድጋሜ ይፈተኑ ይሆን? ወይ ትምህርት ሚኒስትር!» በማለት ጥያቄዎቻቸውን ደርድረዋል፤ አበቃ ዘመኑ የተባሉት አስተያየት ሰጪ በበኩላቸው፤ «ሰው ሆኖ በሰው አይቀለድም። የድሮ አባቶቻችን ሰው ናቸው እና ሰው ላይ አይቀልዱም። የዛሬዎቹ እኛ ሰው አይደለንም እና ሰው ላይ እንቀልዳለን ፤ ደግ ሰው የለም፤ ሰው ሆኖ ሰው ላይ መቀለድ አውሬነት ነው።» በማለት ምሬታቸውን አጋርተዋል። መልሰው ደምሌ ግን፤ «ምንም ምክንያት የለውም ትውልዱ ሰነፍ ስለሆነ ነው።» ነው ያሉት።

የአፍሪቃው ቀንድ አካባቢ ቀውስ ከዕለት ወደ ዕለት እየጦዘ በመሄድ ላይ ነው። ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ ጋር በቀይ ባሕር ወደብ ላይ የባሕር ኃይል ሰፈር ለመመስረት የተፈራረመችው የመግባቢያ ሰነድ ከሶማሊያ ከፍተኛ ተቃውሞና ውግዘት ከማስከተል አልፎ ሌሎች የቅርብ አጎራባችም ሆኑ የሩቅ ሃገራትን ትኩረት ስቧል። ግብፅ ኢትዮጵያን በአፍሪቃው ቀንድ አካባቢ አለመረጋጋትን በመፍጠር ስትከስ፤ የአረብ ሊግ በበኩሉ የሶማሊያ ሉአላዊነት እና የግዛት አንድነት እንዲከበር በመጠየቅ ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር ያደረገችውን ስምምነት ኮንኗል። 
ታምራት ገቻሞ፤ «ሶማሊ ላንድ የሶማሊያ አካል አይደለችም የራሷ ፓርላማ የራሷ መከላከያ ያላት ግን የአገር ዕዉቅና ያልተሰጣት ሉዓላዊት ነች።» ነው የሚሉት። ደገፋ ደምሴ ደግሞ፤ «ኢትዮጵያ ስትፈልግ አይሆንም፡ ምዕራባውያን ሲፈልጉ ደግሞ የተቀደሰ ያደረገው ማነው? የኢትዮጵያ ስኬት እውን ይሆናል።» ብለዋል። 
ጀማል ሀሰን፤ «ግብፅ በኢትዮጵያ ጉዳይ ሳትጠራ አቤት የምትለው ነገር ይገርመኛል» ሲሉ፤ ባሻ የዤሎይ የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ ደግሞ፤ «የአረብ ሊግ አቅም ቢኖረው እስራኤል በፍልስጤሞች ላይ የምትፈጽመውን ግፍ ያስቆም ነበር» ባይ ናቸው። አበባየሁ ዱፌራም፤ «ለመሆኑ የአረብ ሊግ የተባበሩት አረብ ኤሜሬት ከሶማሊላንድ ወደብ ስትጋራ የት ነበር?» በማለት ጠይቀዋል። ጌቲማክር ሀበሻ በበኩላቸው፤ «በዓባይ ግድብ እየጮኻችሁ ገድበናል አሁንም የባሕር በር እየጮኸችሁ እንገነባለን» ነው ያሉት። አሊ ዩሱፍ ኢትዮ ደግሞ፤ «የወደብ ጉዳይ ለሀገራችን የህልውና ጉዳይ ነው። ከውስጥም ከውጪም የፈለገ ቢንጫጫ ምንም አያመጣም የተከፈለዉ መስዋዕትነት ተከፍሎ ወደባችንን እና ባሕር ሀይላችንን እንገነባለን።» ይላሉ። ሰለሞን ድንቁ ደግሞ፤ «የባሕር በር አስፈላጊ ነው፤ አዎ አስፈላጊ ነው ። ይሁን እንጂ አማራጭ እንዲኖረን ካስፈለገን በውስጥ መጠንከር እና አንድነት ሊኖረን ይገባል።» ነው የሚሉት። አሚንጎ ዊዝደምም፤ «ከሁሉም ነገር በላይ ቀዳሚው ሰላም ነው። የውሰጥ ሰላም ይቅደም።» ብለዋል። ገነት ጌቱም እንዲሁ፤ « ሰው የሀገሩን ችግር ሳይፈታ ዘሎ ጎረቤት? ምን ጉድ ነው?» ነው ያሉት። አሜን አወል ደግሞ፤ «እውነት ለመናገር ከሆነ የውስጥ ችግር ሳይቀረፍ ወደ ውጭ ማየት ለውስጥ ጠላቶች ክፍተት ማስፋት ነው። መንግሥታችን በዚህ ጉዳይ ጠለቅ ላለ ግዜ እንዲያስብበት እና በሳል አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያንን በጉዳዩ እንዲያማክር እላለው በኋሏ ከብዙ ጥፋት ያድነዋል።» በማለት መክረዋል። 

ኢንቴቤ ካምፓላ ዉስጥ በተደረገዉ የኢጋድ አባል ሐገራት የመሪዎች ጉባኤ ላይ የሱዳንና የኢትዮጵያ መሪዎች አልተገኙምምስል DW

 

የምሥራቅ አፍሪቃ የልማት በይነ መንግሥታት ኢጋድ በሶማሊያ እና ኢትዮጵያ መካከል የተፈጠረውን ውዝግብ ለማለዘብ ያለመ ስብሰባ ትናንት ሐሙስ ዩጋንዳ ላይ እንደሚያካሂድ ቢገልጽም አንዳንድ የተቋሙ አባል ሃገራት እንደማይሳተፉ ተነግሯል። በተለይ ሱዳን በውስጥ ፖለቲካዋ ኢጋድ ጣልቃ ገብቷል በሚል ያላትን ግንኙነት ማቋረጧን አሳውቃለች። የሱዳን መንግሥት ከኢጋድ ጋር ያለውን ግንኙነት ማቆሙን አስመልክቶ፤ ቹቹ ቦክሰር የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ፤ «ትክክለኛ እርምጃ በራሱ የሚተማመን መንግሥት የአፍሪቃም ይሁን የሌሎች ኃያላን ተብየ አካላት ተፅዕኖ አያስፈራውም።» በማለት ሲያወድሱ ነብዩ ሳሙኤል በበኩላቸው፤ « አልቡራን የግብጽ ተሳፍሪ ነው ሾፌሩ አለሲሲ ነው መዳረሻው ወዴት ነው? እነሱም አያውቁትም።» በማለት ትዝብታቸውን አጋርተዋል። እኛም በዚሁ የዕለቱን የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት ጥንቅር አበቃን። 

ሸዋዬ ለገሰ

ታምራት ዲንሳ

 

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW