1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሸቀጦችና እቃዎች ዋጋ ንረት፤የፓስፖርት አገልግሎት ክፍያ ጭማሪ

ዓርብ፣ ነሐሴ 3 2016

ሊዮን አምሀራ በፌስቡክ «ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ኢትዮጵያ ዜጓቿን በረሀብ እየቀጣች ትገኛለች ያሳዝነኛል። የቀን ሰራ በጠፋበት፣የሚያሳዝነው ጧት 2 ስዓት ሰራ ፈላጊ አሰፓልት ላይ ተዘርግቶ ስታየው ውሰጥህን ያደማል ሰራ ካላገኙ ፀሐይ ሲሞቁ አርፍደው እያለቀሱ ወደ ቤታቸው ይመለሳሉ ሁሉንም ነገር ሰመለከት ከባድ ነው ሲሉ አስተያየታቸውን አጠቃለዋል።

  Ethiopia - Market in Amhara Region - Bahir Dar
ምስል Alemnew Mekonnen/DW

የሸቀጦችና እቃዎች ዋጋ ንረት፦የፓስፖርት አገልግሎት ክፍያ ጭማሪ

This browser does not support the audio element.

የኢትዮጵያ መንግሥት  የውጭ ምንዛሪ ተመን በገበያ ዋጋ እንዲመራ ከወሰነ በኋላ ከመሠረታዊ ሸቀጦች አንስቶ እስከ ግንባታ ዕቃዎች ዋጋ መጨመሩን  ነጋዴዎች እና ሸማቾች ለዶቼቬለ ተናግረዋል። በዋጋ ጭማሪው ሰበብ በርካታ የንግድ ቤቶች እየተዘጉ ጭምር መሆኑን ዶቼ ቬለ ያነጋገራቸው የአዲስ አበባ ከተማ ንግድ ቢሮ ኃላፊ አቶ ቢንያም ምክሩ ገልፀዋል። በቁጥጥሩ ሂደት በአዲስ አበባ ከ150 በላይ የንግድ መደብሮች መታሸጋቸውንም ገልጸዋል። የዋጋ ጭማሪውን አረጋግጦ ምክንያታዊ አይደለም ያለው የንግድ ቢሮው ተቀባይነት እንደሌለው አሳውቋል። ችግሩ በአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን በሌሎች ከተሞችም እየታዬ መሆኑን ዶቼቬለ ከነዋሪዎች ያገኘነው መረጃ ያስረዳል። ውሳኔውን ተከትሎ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የቲኬት ዋጋ በየእለቱ የውጭ ምንዛሬ ተመን መሠረት እንደሚወሰን አስታውቋል። በዚህ ምክንያት የሀገር ውስጥም ሆነ የዓለም አቀፍ በረራዎች የቲኬት ዋጋ ጨምሯል።  ከትናንት አንስቶ ደግሞ የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት የፓስፖርት አገልግሎት ክፍያ ላይ የዋጋ ጭማሪ አድርጓል። መንግሥት ዋጋ ጨመራችሁ ብሎ በነጋዴዎች ላይ እርምጃ ሲወስድ የራሱ ተቋማት በዚሁ ጊዜ የተጋነነ ሊባል የሚችል የአገልግሎት ዋጋ መጨመራቸው እንዲሁ መታለፉ እያነጋገረ ነው። በየአካባባቢያቸው የዋጋ ጭማሪው ስላሳደረው ተጽእኖና የዋጋ ጭማሪውን ለመቆጣጠር መንግሥት  ስለሚወስዳቸው እርምጃዎች ዶቼቬለ ያወያያቸው  የፌስቡክ ተከታዮች የተለያዩ አስተያየቶችን ሰጥተዋል።በኢኮኖሚ ማሻሻያ እርምጃው ላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች አስተያየት


ግርማ ገመቹ በሚል የፌስቡክ ስም የሰፈረ አስተያየት «ዋጋ የጨመረው መንግስት ሳይሆን ነጋዴው ነው።» ይልና ፣« ምሬቱና ብሶቱም  ስግብግብ ያሉት ነጋዴው ላይ ሊሆን ይገባል።ሁሉንም ነገር መቃወም ደግሞ ጤነኝነት አይደለም» ሲል ያበቃል ። ሀብለን ሃብ  ግርማ በሰጡት አስተያየት አልተስማሙም ። ሀብለን  ለግርማ ገመቹ መጀመሪያ ጥያቄ አቅርበዋል። ነጋዴው ነው የዶላር ምንዛሬን 100% የጨመረው? በማለት ከጠየቁ በኋላ ፣እረ ተው!። ሁሉንም ነገር መደገፍ ጤነኝነት አይደለም።  መንግስትን መደገፍ ማገዝ በመርህ ሲሆን ጥሩ ነው። ጭፍን ጥላቻም ጭፍን ድጋፍም ለሀገርም ለመንግስትም አይጠቅምም። ብለዋል። የያሬድ ማኅበረሰብ ድምጽ በበኩላቸው«በዶላር ዋጋ መጨመር ምክንያት በማህበረሰቡ የተለያዩ ፍጆታዎች ላይ የተጋነነ ዋጋ በሚቆልሉ ስግብግብ ነጋዴዎች ላይ መንግስት እየወሰደ ያለው እርምጃ የሚደነቅ ቢሆንም በስሩ ያሉ ህዝባዊ ተቋማት በተለያየ አገልግሎቶቻቸው ላይ በማን አለብኝነት ያስቀመጡት ተመን ከስግብግብ ነጋዴዎቹ የከፋ ነው»  ሲሉ ሃሳባቸውን አጠቃለዋል። 

የአትክልትና የሽንኩርት ገበያ በባህርዳርምስል Alemnew Mekonnen/DW


«በደንበራ በቅሎ ቃጭል ተጨምሮ ሆነና ነገሩ ቀደም ሲል የነበረውን የኑሮ ውድነት ያልቀለበሰው መንግሰት  በአሁኑ ሰዓት የበለጠ ቤንዚን መጨመሩን አረጋግጦልናል ። »ያሉት መብራቱ ከበደ ቀደም ሲል 600 ብር ይሸጥ የነበረ 3 ሊትር ዘይት አሁን 1,200 ብር ገብቷል ። ነጋዴው ቀደም ሲል በርካታ ዘይትን ከውጭ አጓጉዞ  በማስቀመጥ ለ600 ብር ሺያጭ የለም ሲል የነበረውን አሁን 1,200 ብር ሺያጭ በሚስጥር ቦታዎች መቸብቸብ ጀምሯል ። በማለት ሀሳባቸውን የቀጠሉት መብራቱ በመጨረሻም የነጋዴውን ድርጀት ማሸጉ በፍጹም መፍትሄ አይሆንም ለኑሮ ውድነቱ መባባስ ቤንዚን የጨመረው እራሱ መንግሰት ነው እንላለን ።»ሲሉ ሃሳባቸውን ቋጭተዋል።


አብዱል ካሀር  «ቀደም ሲል በ24 ሰዓት 1 ጊዜ እንደምንም ብለን እህል እንቀምስ የነበረው አሁን በ48 ሰዓት 1 ጊዜ እንኳ መብላት ተስኖን በህይወት ለመቆየት በመጨረሻው ትንቅንቅ ላይ እንገኛለን። በማለት ችግሩ አስከፊነት ለማሳየት ሞክረዋል። ክብሮም ገብረ ዮሐንስ በአጭሩ «በጣም ከባድ ነው በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ መቀጠል የሚቻል አይመስለኝም።» ብለዋል። ደረጀ አዳነ መንግስት ዶላርን እንደፈለገ ጨመረ ከዛላይ የሱ ደጋፊዎች እንዳይጎዱ ደመወዝ ጨመረ ይባስ ብሎ እንደ ዘይት ስኳር ፊኖ የመሳሰሉትን በቢሮ አምጥቶ ያከፋፍላል ሌላው ማሕበረሰብ የዚሕ ኑሮ ውድነት ገፈት ቀማሽ ሖኖ ቢጮሕ ማን ይስማው ፍትሕ በኑሮ ውድነት ለተንገላተው ማሕበረሰብ? ሲሉ ጥያቄአቸውን አቅርበዋል። 

መቀሌ ትግራይ የሚገኝ የገበያ ስፍራምስል Million Haileselasie/DW


 «በዓለም ላይ በንድፈ ሀሳብ  ወይም  በፍልስፍና ደረጃ ካልሆነ በስተቀር በእውኑ ዓለም ነጻ ገበያ የሚባል ነገር የለም!»በማለት ሀሳባቸውን የጀመሩት ማቴዎስ ጌሌቦ ለሜታ በፌስቡክ « በየትኛውም ሀገር የግብይት ሥርዓቱ ሲዛባ መንግስትና ሌሎች ተዋናዮች ጣልቃ መግባታቸው የግድ የሚሆንበት ሁኔታዎች አሉ፡፡ ይልቁንስ በአብዛኛው ሀገር ተግባራዊ እየሆነ ያለው በውድድር ላይ የተመሰረተ የንግድ ሥርዓት( ነው፡፡ በውድድር ላይ የተመሰረተ የንግድ ሥርዓት የሚከተል የንግድ ማህረሰብ በሸማቾች ላይ ዋጋ በመቆለል የሚመጣ ትርፍን እንደ አንድ የሀብት ማካበቻ ስልት አያስብም፡፡ በገበያ ላይ ያለው የዕቃዎች ዋጋንም በ''አዋጅ'' በሚመስል መልክ ከዳር እስከ ዳር ተመሳሳይ እንዲሆን አያደርግም፡፡በኢትዮጵያ ያለው ግጭት፤ የኢኮኖሚ ማሻሻያው አተገባበር ስጋት

በውድድር ላይ የተሰመረተ የግብይት ሥርዓት ዕቃውን ለማስመጣት ወይም ለማምረት የወጡ ወጪዎችን(ላኪዎችና አስመጪዎች የዕቃው የግዥ ዋጋ፣ የአውሮፕላን ትኬት፣ ኢንሹራንስ፣ የጭነት ዋጋ፣ የኮንቴይነር ኪራይ፣ ቀረጥና ግብር ወዘተ፣ አምራቾች  ደግሞ ከምርት ግብዓት እስከ ምርት/ገበያ  ያሉ ወጪዎች በእቃዎች ዋጋ ላይ የሚኖራቸው ተጽእኖ)በአግባቡ በማስላት ከዚያ ይህንን መነሻ አድርጎ ትርፉን ያሰላል፡፡ እኛ ሀገር ላይ የተለመደው ግን በሸማቾች ላይ ዋጋ በመቆለል ሀብት ማካበት ነው፡፡ ይህ መታረም አለበት ባይ ነኝ፡፡ »ብለዋል  ማቴዎስ ጌሌቦ ለሜታ ሌሎች ሀሳቦችም ሰጥተዋል። ሆኖም የሌሎቹን አስተያየቶች ጊዜ እንዳይሻማ በዚሁ ለመግታት ተገደናል። 

ሊዮን አምሀራ በፌስቡክ «ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ኢትዮጵያ ዜጓቿን በረሀብ እየቀጣች ትገኛለች ያሳዝነኛል ። የቀን ሰራ በጠፋበት፣ የሚያሳዝነው ጧት 2 ስዓት ሰራ ፈላጊ አሰፓልት ላይ ተዘርግቶ ስታየው ውሰጥህን ያደማል ሰራ ካላገኙ ፀሐይ ሲሞቁ አርፍደው እያለቀሱ ወደ ቤታቸው ይመለሳሉ ሁሉንም ነገር ሰመለከት ከባድ ነው ሲሉ አስተያየታቸውeን ደምድመዋል። 
የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት  አዲስ ፓስፖርት በመደበኛ ጊዜ ለመስጠት እስከ 2,000 ብር የነበረው 5,000 ብር እንደሚያስከፍል፣ በሁለት ቀናት ለሚደርስ አስቸኳይ ፓስፓርት 25 ሺህ እንዲሁም በአምስት ቀን ውስጥ ለሚደርስ ደግሞ 20 ሺህ ብር የአገልግሎት ክፍያ እንደሚጠይቅ ይፋ አድርጓል። በተመሳሳይ ለመደበኛ ጊዜ እድሳት አምስት ሺህ ብር፣ በሁለት ቀን ለሚደርስ አስቸኳይ እድሳት 25 ሺህ ብር እንዲሁም በ5 ቀን ውስጥ ለሚደርስ አስቸኳይ እድሳት 20 ሺህ ብር እንደሚጠይቅ ገልጿል።የኢሚግሬሽን የፓስፖrte አገልግሎት ጭማሪ ሰሞኑን በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች አነጋጋሪ ከነበሩት ጉዳዮች መካከል ነበር። 

የኢሚግሬሽንና ዜግነት ጉዳዮች አገልግሎትምስል Solomon Muche/DW


የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት የአገልግሌት ክፍያ ዋጋ ማሻሻያ ላይ የሕዝብ አስተያየትበዚህ ላይ አስተያየታቸውን ከሰጡት አንዱ ሰሎሞን አሰፋ አያሌው «መስተካከል አለበት» ሲሉ አሳስበዋል።» «የብዙ ኢትዮጵያዊያን ኑሮና ገቢ ይህንን ክፊያ ይችላል? ለኢትዮጵያዉያን ይህ ክፊያ አቅማቸዉ ነዉ? የሚሉትን ጥያቄዎች ያስቀደሙት መስፍን ሰሎሞን «አረ በፈጣሪ የኢትዮጵያዉያንን ኑሮ እወቁ» ሲሉ ተማጽነዋል።» ሚክያስ ፈለቀ ትክክል ያልሆነ አሰራር ፡፡»ሲሉ ተቃውመዋል። ማንዴላ ላቭ « እብደት ነው?» በማለት ጠይቀዋል። «እንደዚህ አይነት አሰራር በአለም ላይ ፈፅሞ የለም:: ግን ነውር የሚባል ነገር አያውቁም እንዴ? በሚል ጥያቄ የተጀመረው የሳሚ ያለው ካሳ አስተያየት «መደበኛ ዋጋው 5 ሺህ ብር ሆኖ በአስቸኳይ በአንድ ቀን ውስጥ ለሚፈልግ ቢበዛ ቢበዛ ከ6-7 ሺህ ብር ድረስ ሊሆን ይችላል እንጂ በምን መመዘኛ ነው 25 ሺህ ብር ሊሆን የሚችለው? ምን አይነት ትምህርት የተማሩ ሰዎች ናቸው ይህን ሂሳብ የሰሩት? ነው ወይስ ፓስፖርቱ የአሜሪካ የኢሮፕ ቪዛ ተመቶበት ነው የሚሰጠው? ቢበዛ እጥፍ ይሆናል እንጂ ፣እንዴት ተደርጎ ነው 5 እጥፍ የሚጠየቅበት??
«ውሾቹ ይጮሀሉ ግመሎቹ ይሄዳሉ» በሚል የፌስቡክ ስም የተሰጠ አስተያየት ደግሞ «ምን ይደረግ ይህ የደሃ ጮኸት ለበለስልጣኑ ጆሮ ገብ አይደለም ደግነቱ ስልጣን ዘላለማዊ አለመሆኑን ባወቁና ህዝብ በያስለቅሱ ቆንጆነው እላለሁ ለሀገሬ ከዳር እስከ ዳር ሠላሙን ያብዛላት! የሚል መልካም ምኞት በማከል ተጠቃሏል።

ኂሩት መለሰ 
ሸዋዬ ለገሠ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ
ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW