1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

ሐሙስ፣ ጥቅምት 28 2017

በቀን ሦስቴ መብላት የብልፅግና ግብ አይደለም መባሉ፤ 47ኛዉ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሆነዉ ለተመረጡት ትራምፕ ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድን ጨምሮ ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ ፤የእስራኤል ጠ/ሚ እና የፈረንሳይ ፕሬዝደንት የላኩት መልዕክት፤ እንዲሁም አሜሪካ የአማራ ክልል ግጭት አሳስቦኛል ማለትዋ በተሰኙ ጉዳዮች ላይ አስተያየቶችን አሰባስበናል።

የኢትዮጵያዉያን ማዕድ
የኢትዮጵያዉያን ማዕድ ምስል Michael Marquand/IMAGO

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

This browser does not support the audio element.

በቀን ሦስቴ መብላት የብልፅግና ግብ አይደለም መባሉ፤ ለትራምፕ የደረሱ መልክቶች፤ አሜሪካ የአማራ ክልል ግጭት ያሳስበኛል ማለትዋ በተሰኙ ርዕሶች ስር በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ላይ የተሰጡ አስተያየቶችን ጨምቀን ይዘናል።     

47 ኛዉ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ሆነዉ ለተመረጡት ዶናልድ ትራምፕ የኢትዮጵያዉን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን ጨምሮ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ፤  እና የፈረንሳይ ፕሬዝደንት ኤማኑዌል ማክሮ የእንኳን ደስ አለዎ መልዕክት ካስተላለፉ የአገራት መሪዎች መካከል ቀዳሚዎቹ መካከል ናቸዉ።  የኤርትራው ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂበበኩላቸዉ ዶናልድ ትራምፕ ፕሬዝዳንት ሆነው መመረጣቸው በሀገራቸው እና በአሜሪካ መካከል "አዲስ የትብብር ምዕራፍ ይከፍታል" የሚል ተስፋቸውን በመግለፅ ለትራምፕ የእንኳን ደስ አለዎ መልዕክትን አስተላልፈዋል። ትራምፕ ለአፍሪቃም ይሁን ለኢትዮጵያ ምን ለዉጥ ሊያመጡ ይችሉ ይሆን?

ማንደፍሮ መንግሥቴ የተባሉ የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተጠቃሚ፤ ማንም ይመረጥ ማንም የአፍሪቃ መንግስታት እና መሪዋች የልዕል ሀገር አሜሪካ ፖሊሲ አስፈጻሚ ከመሆን በዘለለ የሚመጣ ለዉጥ የለም ሲሉ ጽፈዋል።

ተስፋዬ አየለ የተባሉ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተጠቃሚ ፤ በመሰረቱ ይላሉ፤ በመሰረቱ ዴሞክራራቶችም ይሁን ሪፓብልካኖች በውጭ ፖሊሲያቸው ተመሳሳይ አቋሞ ነው ያላቸው በመሆኑም፤ ከትራምኘ ምንም ዓይነት ለውጥ አልጠብቅም። ዴሞክራቶችም ያመጡት ለውጥ ወይም የተለየ አቋም ሲያሳዩ ባለማየቴ ነው። ለአፍሪካምይሁን ለኢትዮጵያ ምን ዓይነት ለውጥ ትጠብቃላችሁ ተብሎ ለተጠየቀው የተለየ ምንም ለውጥ ያመጣሉ ብዬ አልጠብቅም ነዉ መልሴ። ምክንያቱም አሜሪካ ከምትመራው የውጭ ፖሊሲ አንጻር በተለየ፤  በሌላው ጉዳዮ ላይ ትኩረት ሰጥታ አታውቅም። እንዲያውም በጥቅሟ ላይ የሚነሱ አገሮች ብቻ ሳይሆን አገራቸውን ለማሳደግ የሚጥር አገር እና የአገር መሪ ካሉ ለይታ በማደን ታጠፋቸዋለች። ለምሳሌ ሶሪያን እና ሊቢያን ማየት ይቻላለል፤ ሲሉ ተስፋዬ አስተያየታቸዉን ቋጭተዋል።

ተሻለ ገብረፃድቅ የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ ይህ መልካም ነገር ነው። በሀገራት መካከል ያሉ ግንኙነቶች መልካም እንዲሆኑ እንዲህ አይነት ቀና መልእክቶች ማስተላለፍ የዲፕሎማሲ አንዱ መንገድ ነው፤ ሲሉ አስተያየታቸዉን አስቀምጠዋል።


47 ኛዉ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ሆነዉ የተመረጡት ዶናልድ ትራምፕ ምስል DW

አሜሪካ የአማራ ክልል ግጭት ያሳስበኛል ማለትዋ

በአማራ ክልል እየተባባሰ የሄደው ግጭት እንዳሳሰባት አሜሪካ በያዝነዉ ሳምንት ማስታወቅዋ የብዙዎችን ቀልብ ስቦ ነዉ የሰነበተዉ። የዩናይትድ ስቴትሱ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አንቶኒ ብሊንከን ከጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ጋር በነበራቸው የስልክ ቆይታ «በኢትዮጵያ የእርስ በርስ ግጭቶች እልባት ያገኙ ዘንድ የፖለቲካ ውይይቶች መደረግአለባቸው ማለታቸዉ ተሰምቷል።

ሃና አህመድ የተባሉ የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተጠቃሚ፤ አሜሪካ ከመቼ ወድህ ነው ለሀገራችን አስባ የምታውቀው ሲሉ  በጥያቄ አስተያየታቸዉን ዘግተዋል።

አበበ አጋዜሽ የተባሉ በአስተያየታቸዉ፤ አሜሪካ አዲስ ፕሬዚዳንት በምትመርጥ ቀን ፤ ስልጣን ላይ ያሉት ዲሞክራቶች በመጨረሻ ሰአት የአማራ ክልል ጉዳይ ያሳስበናል አሉ? ሲሉ አበበ በጥያቄ ምልክት እንዲሁም አስተያየታቸዉን ዘግተዋል።

ዘለቀ በላይ የተባሉ የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተጠቃሚ በበኩላቸዉ፤ ለውይይቱ አለመጀመር የውጪ ሀይሎች እጅ አለበት። የሚያሳስበን እኛን እንጂ አሜሪካኖችን አይደለም። ስውር አቀራረቡ እኛኑ ለማመስ ነው። በማያግባቡን ነገሮች መቀራረብ ለመፍጠር መንግስት እየሰራ ነው በቃ ሲሉ አስተያየታቸዉን ደምድመዋል።

ሁሉም ነገር በሰላም ያልቃል ሲሉ አስተያየታቸዉን የሚጀምሩት አሜን ታፈሱ ጎንድዬ ናቸዉ ሁሉ ነገር በሰላም ያልቃል አራት ነጥብ:: አሜሪካና ተባባሪዋ ያኔ ይቃጠላሉ ።እኛ የኢትዮጵያ ልጆች ሰላም ፈላጊዎች ነን።

የአሜሪካ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ምስል Nathan Howard/AP/picture alliance´

“በቀን ሦስቴ መብላት ግባችን ሊሆን አይችልም ብልጽግና በዚህ አያምንም”

ባለፈዉ ሰሞን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ “በቀን ሦስቴ መብላት ግባችን ሊሆን አይችልም ብልጽግና በዚህ አያምንም”። የኛ ግብ በትንሹ ሦስት ነገሮችን ማሟላት ነዉ «አንደኛዉ ደስተኝነትን ማምጣት፤ ሁለተኛዉ «ህብረ ስምረት»  ሦስተኛዉ የሰብዓዊ ልህቀትን ማስረጽ እና እድገትን ማረጋገጥ ነዉ፤ ማለታቸዉ አብዛኞችን ሲያወያይ ነዉ የሰነበተዉ። 

መስፍን ተስፋዬ የተባሉ  ባስቀመጡት አስተያየት፤ እኛ መብላቱ ይቅርብን እና በሰላም እንኑር በነፃነት ወጥተን ከገባን ሁላችንም ለእራሳችን አናንስም እሱን ብቻ አስብበት ሲሉ ደምድመዋል። ቆይ እስቲ ክቡር ጠ/ሚ የተራበ ሰው እንዴት ደስተኛ ሊሆን እንደሚችል ቢያስረዱን ሲሉ አስተያየታቸዉን በጥያቄ ማህበራዊ ሚዲያ ላይ ያስቀመጡት ደግሞ ኮምባ ታየ የተባሉ ተጠቃሚ ናቸዉ።  

የሪያድ ማህበረሰብ ድምጽ የተሰኘ ስም ያላቸዉ ረዘም ያለ አስተያየት ፅፈዋል፤ የጠቅላይ ሚንስትሩን ንግግር ጥቂቶች የተረዱት በስሜት ነው። አባባሉ ለመለወጥ መቸገር እንዳለብህ ለማመላከት ነው። ይህን ደግሞ ማንም ጤናማ አይምሮ ያለው ሰብአዊ ፍጡር በግሉ ህይወት ጨምር የሚያደርገው እውነታ ነው። የጠቅላይ ሚንስትሩን ንግግር በቅንነት ካየነው እኛ ተርበን የሚቀጥለው ትውልድ ጠግቦ እንዲያድር መስወዓትነት እንከፈል ነው።በመሰረቱ ሁሌም ለሆዳችን እያሰቡን አይደለም። ሀገራችንን በተለያዩ ጊዜያት ስልጣን ላይ የሚቀመጡ መንግስታቶች የሚኖሩበትን ቤተ መንግስት ዘንግተው የዜጎች ማስቃያና ቆሻሻ ማጠራቀሚያ ሆኖ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው። አሁን ከዚህ አስተሳሰብ ወጥተን፤ ከሆዳችን ይልቅ አይምሮችንን የሚመግብ ልማት ላይ በመሰማራት ለከብራችን እንስራ፤ ሲሉ አስተያየታቸዉን ደምድመዋል።

አዜብ ታደሰ

ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW