1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

ፀሀይ ጫኔ
ሐሙስ፣ ኅዳር 12 2017

ያለፈው እሁድ የተካሄደው የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ፣መርካቶ የተከሰተው ሁለኛው የእሳት አደጋ፣ ስድስት የፖለቲካ ፓርቲዎች፣የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት የጉባኤ ውሳኔ ውጤትን አንቀበልም ማለታቸው,በዚህ ሳምንት በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በስፋት መነጋገሪያ ሆነው የሰነበቱ ጉዳዮች ናቸው።

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች
እሁድ የተካሄደው የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ፣መርካቶ የተከሰተው ሁለተኛው የእሳት አደጋ፣ ስድስት የፖለቲካ ፓርቲዎች፣የጋራ ምክር ቤት ጉባኤ ውሳኔ ውጤትን አንቀበልም ማለታቸው መነጋገሪያ ነበርምስል Jonathan Raa/NurPhoto/picture alliance

የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ፣መርካቶ የተከሰተው ሁለተኛው የእሳት አደጋ እና የስድስት የፖለቲካ ፓርቲዎች ተቃውሞ

This browser does not support the audio element.

የዘንድሮው የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ

በዚህ ሳምንት በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች መነጋገሪያ የነበረው ጉዳይ፤ ያለፈው እሁድ ሕዳር 8 ቀን 2017 ዓ.ም የተካሄደው የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ነበር።'«የተመጣጠነ ምግብ ለሁሉም ሕፃናት'» በሚል መሪ ሀሳብ  ለ24ኛ ጊዜ የተካሄደው እና 50 ሺህ ሰዎች ተሳትፈውበታል የተባለው ይህ ውድድር፤ በሳምንቱ መጨረሻ የተካሄደ ቢሆንም በዚህ ሳምንት በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች መነጋገሪያ  ሆኖ ነው የሰነበተው።

ማሚቱ አበበ የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ«ታላቁ የካድሬዎች ሩጫ ነበር መባል የነበረበት።» ሲሉ፤ ዴቭ ደረጀ  የተባሉ የፌስቡክ አስተያየት ሰጪ ደግሞ «ወይ ጉድ ! 20ሺ ካድሬ በታላቁ ሩጫ ማሰለፍ » ብለው አስተያየታቸውን በቁጥር የተደገፈ አድርገዋል። ሃቢባ ሀጅ «መንግስት ማንን ፈርቶ፤ ሰው ትንፍሽ ካለ ያው እንዳለፈው ዓመት እስር ቤት ይገባል።»የሚል አስተያየት አስፍረዋል።«ለመሆኑ ምን ማረጋገጫ ኑሮ ነው ይህንን የምትሉት»ይላል ጆኒ ጆኒ በሚል ስም የሰፈረው አስተያየት።አልአዛር የጥንቱ በሚል ስም ደግሞ«ታላቁ ሩጫ ብሶት መግለጫ ነበር የሚባለው።እንግዲህ የመንግስት ካድሬ እዚያ ድረስ ከመጣ አርፈን መቀመጥ ነው።ምን ይደረጋል።»ሲሉ ፤ብሌማ ዳይኮ ደግሞ«አንድ ነገር ብለን አንድ ነገር ከምንሆን ይሄው ይሻላል።»ብለዋል።መካሻ ሰይፉ የተባሉ አስተያየት ሰጪ «ይህ ሁሉ ማለቃቀስ ሩጫው ለምን በሰላም ተጠናቀቀ ነው»የሚል አስተያየት ሰጥተዋል።ሀይሉ አለማየሁ ደግሞ «ስፖርትም ፖለቲካ የሆነባት ሀገር አሁንስ በዛ » ሲሉ በምሬት ገልፀዋል።

መርካቶ የተከሰተው ሁለኛው የእሳት አደጋ

ሌላው በዚህ ሳምንት በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች መነጋገሪያ የነበረው ጉዳይ  ያለፈው እሁድ በአዲስ አበባ መርካቶ  ጃቡላኒ ህንፃ አካባቢ በተለምዶ "ድንች በረንዳ" እየተባለ በሚጠራው ስፍራ የእሳት አደጋ መከሰቱ ነበር።በንብረት ላይ ጉዳት አድርሷል የተባለው ይህ አደጋ የተከሰተው በቅርቡ ጥቅምት 11 ቀን 2017 ዓ.ም በእሳት ከጋየው ሸማ ተራ አከባቢ ብዙም በማይርቅ ስፍራ ነው።
የአዲስ አበባ ከተማ የእሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ቃጠሎው ሳይዛመትና የከፋ ጉዳት ሳያደርስ አንድ ሰዓት ተኩል በፈጀ ርብርብ መቆጣጠሩንም አመልክቷል፡፡ቆየት ብሎ በወጣ ዘገባም፤ ኮሚሽኑ በቦታው ተመሳሳይ ችግር እንዳያጋጥም ቦታውን እንደ አዲስ መልሶ ማልማት ወይም የአደጋ ደህንነት መስፈርትን ባሟላ እና ደረጃውን በጠበቀ መልኩ መገንባት አለበት የሚል  ምክረ ሃሳብ እንዳቀረበ ተሰምቷል።

ሸምሱ ሸምሱ የተባሉ አስተያየት ሰጪ«ድሮም ጠርጥረን ነበር።»ሲሉ፤ኢትዮጵያ አሸናፊ በበኩላቸው«የአሮጌ ሰፈርና የቆሻሻ ወዳጆች ሙሾ ሊጀምሩ ነው በለኛ።»የሚል አስተያየት አስፍረዋል።ተመስገን ማረልኝ«ስታቃጥሉት ይሄን እንደምትሉ እናውቅ ነበር።»ሲሉ።ካሊድ ኢማ ሚፍታ ሚፍታ ደግሞ «መልሶ ማልማት ሳይሆን መልሶ ማጥፋት በሚል ይስተካከል»ብለዋል።አብዲ ማሂር «ቃጠሎውም ኮሪደር ልማቱም ቀጥሏል።ታዲያ ሳያቃጥሉት ቢነግሩን ቢያንስ ንብረታችንን እናተርፍ ነበር።»ብለዋል።ዳዊት ደማደም «አዲስ አበባን አይመጥንም የመኅትሄ ሀሳቡ ቢተገበር መልካም ነበር።»ብለዋል።ዘሩ መብራህቱ በበኩላቸው«ጥሩ ሀሳብ ነው ግን ባለንብረቶቹ ማልማት አይችሉም?»ሲሉ ጠይቃዋል።ጌቴ ላሎ በበኩላቸው«ኮሚሽኑ ያቀረበው ሀሳብ አደጋ ስለማስቀረት ነው። እናንተ ግን መንግስት አቃጠለ ትላላችሁ።ይህ ምን ያህል ከእውነት እንደተጣላችሁ ያሳያል።» ብለዋል።ገብረማርያም ታፈረ ግን ሃሳቡ የተዋጠላቸው አይመስልም  «የኔ ጥያቄ ብዙ አመታት ሳይቃጠል እንዴት አሁን ቃጠሎ ተደጋገመ ነው?»ብለዋል።ዳዊት ኤች ኤም «አቃጥሎ ማልማት አይ ኢትዮጲያ።ይልቅስ ለ 3ተኛ ጊዜስ መቼ እንጠብቅ?እባካችሁ አሰውቁን።»በማለት ነገሩን ወደ ቀልድ ወስደውታል።

በመርካቶ አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ሁለት የእስት አደጋ ደርሷልምስል Yared Shumete

 የፓለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት እና የስድስት አባል ፓርቲዎቹ ተቃውሞ 

ስድስት የፖለቲካ ፓርቲዎች፣የጋራ ምክር ቤት ጉባኤ ውጤትን አንቀበልም ማለታቸው። በዚህ ሳምንት በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች መነጋገሪያ ከሆኑ ጉዳዮች አንዱ ነው።

በኢትዮጵያ ሰላምና መረጋጋት እንዲኖር፣ የዴሞክራሲ ሥርዓት እንዲጠናከር፣ የሰብዓዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን እንዲከበሩ እና የሕግ የበላይነት እንዲጠበቅ ለማገዝ በሚል  መጋቢት 5 ቀን 2011 ዓ.ም የተቋቋመው፤የኢትዮጵያ የፓለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በዚህ ሳምንት ከአባል ፓርቲዎቹ ጋር ውዝግብ ውስጥ ገብቷል።
ገዥው  ብልፅግና ፓርቲን ጨምሮ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች አባል የሆኑበት የኢትዮጵያ የፓለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት፤ ያለፈው ሳምንት ማብቂያ ባደረገው  ጉባኤ ሰባት አባላት ያሉትን አዲስ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ መርጧል። መተዳደሪያ ደንብም አፅድቋል። ያም ሆኖ ተቃዋሚውን ኢሕአፓን ጨምሮ ስድስት አባል የፖለቲካ ፓርቲዎች፣የተለያዩ ምክንያቶችን በማንሳት የጋራ ምክር ቤቱን የጉባኤ ውጤት አንቀበልም ብለዋል።

እሁድ የተካሄደው የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ፣መርካቶ የተከሰተው ሁለተኛው የእሳት አደጋ፣ ስድስት የፖለቲካ ፓርቲዎች፣የጋራ ምክር ቤት ጉባኤ ውሳኔ ውጤትን አንቀበልም ማለታቸው መነጋገሪያ ነበርምስል Infinity News Collec/imagebroker/IMAGO

ይህንን ተከትሎ፤ ተሰማ ያለው«የየት ሀገር ፕርቲዎች ናቸው።እዚህ ሀገርፓርቲ አለ እንዴ?»ሲሉ ጠይቀዋል።ለሁሉም ሰላም የተባሉ አስተያየት ሰጪ ደግሞ «ዝም ብለው ፈቃድ አውጥተው የተቀመጡ አሻንጉሊቶች እንጅ በአገሪቱ አንድም ጠብ የሚል ውጤት ወይም አወንታዊ አስተዎፅኦ የላቸውም። ምንም የረባ ስራ አይሰሩም።» ካሉ በኋላ  «በይህን ስል ተቀናቃኝ ሆነው ልዮነትን ይዘው በጋራ ጉዳይ አብረው የሚሰሩ እና አገርን እየጠቀሙ ያሉ ጀግኖች ስላሉ እነሱን አይመለከትም።»በማለት በስም ያልጠቀሷቸውን ፓርቲዎች አወድሰዋል።ዲዬ ጋበር«ከቻላችሁ ተዋሀዱና አንድ ፓርቲ መስርቱ። በየ ሰፈሩ በየ ብሄሩ ፓርቲ ከምትሆኑ አንድ ሆናችሁ በጋራ ስሩ»የሚል ምክር ሰጥተዋል።

ዳኛቸው አንተነህ «የፓለቲካ ፓርቲዎች አይደለም መባል ያለባቸው።መባል ያለባቸው የፓለቲካ ነጋዴዎች ነው ።» በማለት ፓርቲዎቹን ወርፈዋል።አመለ ፍቅር የተባሉ አስተያየት ሰጪ በደፈናው«ፓለቲካን የማያውቁ ፓለቲከኞች ናቸው።»ሲሉ፤ ዘላለም ጦና በበኩላቸው አሽሙር ይሁን ሙገሳ ባይታወቅም«ፖለቲካ ማወቅ እንደ ብልፅግና ነው።የተለዬ ሀሳብ ያነሳን ሁሉ ወደ እስር ቤት በመውሰድ አፍ ማስያዝ።»ብለዋል። ሰው እና ኑሮው በሚል የፌስቡክ ስም የሰፈረው አስተያየት«ወዳጄ ዘንድሮ ፖለቲካ የእንጀራ መፈለጊያ ነው።ከዚያ ውጭ ሕዝቡም አያውቃቸው እነሱም ሕዝቡን አያውቁትም ።»ብለዋል።ወንድሙ ሰለሞን «የአነዚህ ሰዎች ለህዝብ ያላቸው ጥቅም ምንድን ነው? ምንም። ሰው እየሞተ እየተፈናቀለ እየተራበ ምን ያመጡት ለውጥ አለ? ምንም።»በማለት  ለራሳቸው ጥያቄ ራሳቸው መልስ ሰጥተዋል።ካሳሽ ካሳሽ «ከመንግስት በላይ የበደሉን ተቃዋሚ ፖርቲዎች እና የፖርላማ አባላት ናቸው።»በማለት የላይኛውን አስተያየት ደግፈዋል።
ወንድሙ ዋንጃሎ ቱንታ ደግሞ «አሁን ለኢትዮጵያውያን የሚያስፈልገው አንድ ብቸኛ ተፎካካሪ ፓርቲ ነው። ልክ እንደ ጥቃቅንና አነሰተኛ ማህበር ሊሆን አይገባም።»ብለዋል።
 

ፀሐይ ጫኔ
ታምራት ዲንሳ

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW