የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት
ሐሙስ፣ መስከረም 22 2018
በዚህ ሳምንት በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች መነጋገሪያ ከነበሩት ጉዳዮች መካከል የመሸጋገሪያ እንጨት ተደርምሶ የበርካታ ሰዎች ህይወት ማለፉ ነው።
በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ምንጃር ሸንኮራ ወረዳ አረርቲ ማርያም ለግንባታ መሸጋገሪያ የተሰራ እንጨት ተደርምሶ የበርካታ ሰውች ህይወት ማለፉን የወረዳው ባለስልጣናት ገልፀዋል።የወረዳው ፖሊስ እንዳስታወቀው ፥ የመደርመስ አደጋው የደረሰው ምዕመናን በወረዳው እየተሰራ ያለውን ቤተክርስቲያን ግንባታ በመጎብኘት ላይ በነበሩበት ወቅት ነው፡፡በአደጋው ከሞቱት ሰዎች በተጨማሪ ከ200 በላይ ሰዎች ጉዳት እንደደረሰባቸው የወረዳው ፖሊስ አመልክቷል።አደጋውን ተከትሎ የኢትዮጵያ የሀይማኖቶች ህብረት እንዲሁም መንግስት በደረሰው አደጋ የተሰማቸውን ሀዘን ገልፀዋል።ይህንን ተከትሎ
ታረቀኝ በቀለ«-በጣም ያሳዝናል እግዚአብሔር ነፍሳቺሁም አፀደ ገነት ያኑር.»ሲሉ፤ዘምዘም አስማው፤ ምንአለበት እንደዚ በጦርነት የሞተውን ብትናገሩ ? ብለዋል።ሞገስ ታዬ -«መስቀል አደባባይ የደረሰው አደጋስ አይዘገብም?»ሲሉ ጠይቀዋል።አማሩ ተሻገር ደግሞ «-እዚህ ሀገር የተፈጥሮ አደጋ ከሚገድለው መንግስት በየቀኑ የሚገድለን ይበልጣል ።ስለየትኛው ሀዘን ነው መንግስት የሚገልጠው።»በማለት ፅፈዋል።በላይሁን በዛብህ«እንዴት በእንጨት ርብራብ ላይ ጉዞ ተፈቀዴ? ነብስ ይማር።»የሚል አስተያየት ሰጥተዋል።ፍቅር ሁሌም-«በመንግስት ተቋም ስህተት ሲሰራ ሰው ሲሞት ዜና ሆኖ የማይነግርባት ሀገር!።»ሲሉ፤ጌጡ አበጄ -«ነፍስ ይማር እንዴው ድልድይ መስራት አቅቶን የስንት ሰው ህይወት ተቀጠፈ።»ብለዋል።ሰብለ ፀጋ -ነፍሳቸውን ይማርልን! የኮንስትራክሽ ስራዎች አከባቢ ምናለ ጠንካራ ጥንቃቄ ቢደረሰግ ያሳዝናል በጣም።»ብለዋል።ገብረፃዲቅ በለጠ«ምነው ሰውም ግኡዙም አጥፊያችን ሆነ። ፈጣሪ ሆይ ተማለደን ህዝብህን አድን።» የሚል አስተያየት ሰጥተዋልል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ኢትዮጵያን በተመለከተ ሰሞኑን ያወጣው መግለጫ
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርኢትዮጵያን በተመለከተ ሰሞኑን ያወጣው መግለጫ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች መነጋገሪያ ከነበሩ ጉዳዮች አንዱ ነው።የአሜሪካ መንግሥት ሰሞኑን ባወጣው መረጃ "የኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ኹኔታ "ለአሜሪካ እና ሌሎች የውጭ ንግዶች ፈታኝ ነው" ሲል አስታውቋል።የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ሪፖርት እንዳመለከተው ፤የኢትዮጵያ መንግሥት የከተሞች የመንገድና የዳርቻ ወይም የኮሪደር ልማት የባለሃብቶችን መዋዕለ ንዋይ ፈሰስ የማድረግ ፍላጎት ገድቧል። ዝርዝር ሪፖርቱ እዚህ ድምዳሜ ላይ የደረሰው "የውጭ ይዞታዎችን ጨምሮ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች እና የንግድ ድርጅቶች ንብረታቸው ያለ በቂ ማስጠንቀቂያ መፍረሱን ተከትሎ መሆኑን አብራርቷል።
ግጭት በሚካሄድባቸው አማራና ኦሮሚያ ክልሎች የመንቀሳቀስ ሁኔታ ገደብ መኖሩን የጠቀሰው ይህ ሪፖርት ባለሥልጣናት ወይም ታጣቂ ቡድኖች በተደጋጋሚ የግል ንብረቶችን እንደሚነጥቁ፣ የንብረት ባለቤትነት መብቶች በቂ ጥበቃ እያገኙ እንዳልሆነ ጭምር አመልካቾችን ጠቅሷል። ይህንን ተከትሎ ብርሃኑ ዲያሞ-አሜሪካን ያወጣችው ሪፖርት ዶክተር አቢይ ከራሽያ ፕሬዝዳንት ፑትን ጋር ጥሩ የሚበል ውይይት ስለደረጉ USA ደስተኛ ስላልሆነች ነው። ሲሉ፤ ኤፍሬም በቀለ- ደግሞ «ትራምፕ ስራ ፈቶ እንዲህ ወሬ አይፈተፍትም፡፡ የመንገድ መሰረተ ልማት ለኢንቨስትመንትን ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል እንጂ ፈተና አይሆንም።» ብለዋል። ጣና ነሽ-«አይደለም ኢንቨስትመንት ዜጎች ወተው መግባት አልቻሉም።» ሲሉ፤ መሀመድ ሁሴን ረዘም ያለ አስተያየት ነው የሰጡት ። እንዲህ ይላል አስተያየታቸው።«እነዚህ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያወጣቸው ሪፖርቶች ፍፁም ትክክል ናቸው ብሎ ለመቀበል ይከብዳል። የኢትዮጵያ መንግሥት የከተሞችን መንገድና ዳርቻ (ኮሪደር) ልማት እያካሄደ ያለው ለዜጎቹ ጥቅም ሲል እና ከተሞችን ዘመናዊና ምቹ ለማድረግ ነው።ይህ ልማት የባለሃብቶችን ፍላጎት "ገድቧል" ከማለት ይልቅ፣ ለዘላቂና ፍትሃዊ ኢንቨስትመንት አዲስ ዕድል ይፈጥራል ብሎ ማሰብ ተገቢ ነው። መንግሥት የከተማዋን ገፅታ እያስተካከለ፣ አዲስና የተሻለ የንግድ ምህዳር ለመፍጠር እየጣረ ነው ማለት ይቻላል። በእርግጥ ፈተናዎች ቢኖሩም፣ ልማቱ
ለነገው ጠንካራ ኢኮኖሚ መሠረት የሚጥል እንጂ ኢንቨስትመንትን የሚያኮላሽ አይደለም።»ብለዋል።አሌክስ ታከለ፤-«በየአቅጣጫው ጦርነትና ውጥረት ባለበት ሁኔታ ገንዘቡን አፍስሶ አተርፋለሁ የሚል አይኖርም:: እና እውነታን መቀበል ነው: እውነትን የተናገረ በሙሉ ጠላት አርጎ መፈረጅ የትም አያደርስም።»የሚል አስተያየት ፅፈዋል።ብርሃኑ ለገሰ -ምቀኞች !! ሲሉ፤ኤዲ ኤ አንዱ-ቀልደኞች ናቸው ኢትዮጵያን ጨምሮ የአፍሪካ የኢንቨስትመንት ፍሰት ከእስያ አገራት እንደሆነ ይታወቃል። አሜሪካኖች ደካማ የሆነች ኢትዮጵያን ለምን ማየት ፈለጉ ግን?።የሚል አስተያየት ሰጥተዋል።ፈቃዱ ታምሩ፣-ለመበዝበዝ ተቸገራችሁ አይደል።የህንንማ የተለመደና አለም ሁሉ ያዉቀ ነዉ !
አበቃ ዘመኑ-«አሁን ያለ ብልጽግና አይደለም ለኢንቨስትመንት ለህቡም ፈታኝ ብቻ ሳይሆን ህዝብ እንደ ህዝብ ሀገር መብት ያጣበት ከወያኔ ሰባት እጅ የከፋ ነው።» አብዱል ከሪም ከድር -«ትተወዋ ከፈተናት» አሜሪካን ማለታቸው ነው።የልብ አድራሽ በሚል ስም ደግሞ «አይደለም የውጭ ዘጋ እዚ አገር እምቨስት ለማድረግ ይቅርና እኔ ራሴ የማይንቀሳቀስ ንብረት ቤትና መሬት በ1000 ብር አልገዛም ፣ ያካበድኩ ልመስላቹ ይችላል እውነቴን ነው ደስተኛ ሆኜ ምንም ገንዘብ አላወጣም፣ አንድ ንብረት ገዝተህ ቆየት ብሎ የምመጣው የባለቤትነት ጥያቄ ከባለጊዜ ጋር መመሳጠር ህገወጥ ነው ወዘተ የመንገድ ልማት ወንዝ ልማት ወዘተ ምትቀማው ንብረትህ ስንት ሰው አለ እያለቀሰ የተቀመጠ?»በማለት ፅፈዋል።ቤካ ተመስገን -«ወሬ በሉአቸው» ሲሉ፤« ነበልባሉ- በሚል የፌስቡክ ስም የሰፈረው አስተያየት።«ፈታኝ ብቻ ሳይሆን ሞቷል ነው የሚባለው፡፡ Look በየቦታው ጦርነት እኮ ነው ፡፡ ያሉትም ከትንሽ ጊዜ በኋላ ጠቅልለው መውጣታቸው አይቀርም።»ይላል።
ኢትዮጵያ በመድሀኒት ቁጥጥር ደረጃ 3 ውስጥ መካተቷ
በዚህ ሳምንት ሌላው የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች መነጋገሪያ ጉዳይ፤ ኢትዮጵያ በመድሀኒት ቁጥጥርደረጃ 3 ውስጥ መካተቷን ዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት ማስታወቁ ነበር።ኢትዮጵያ እዚህ ደረጃ የገባችው የምግብና መድሀኒት ቁጥጥር ባለስልጣን ከውጭ የሚገቡ መድሀኒቶችና ክትባቶች አለም አቀፍ ጥራትን፣ ብቃትንና ደህንነትን ያሟሉ እንዲሆኑ ከፍተኛ ስራ በመስራቱ መሆኑ ተገልጿል።ኢትዮጵያ እዚህ ደረጃ ውስጥ በመግባቷም ከግብፅ፣ ጋና፣ ናይጄሪያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ታንዛኒያ፣ ዚምባቡዌ፣ ሴኔጋልና ሩዋንዳ ጋር መቀላቀሏ ታውቋል።ይህንን ተከትሎ፤የአለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴዎድሮስ አድሀኖም በኤክስ ገፃቸው ላይ እንኳን ደስ አላችሁ የሚል መልእክት አስተላልፈዋል፡፡ ይህንን ተከትሎ፤ «ዶክተር ደግሞ፤መድኃኒት ሳይኖራት ቁጥጥር» ይላል Rational Previews በሚል ስም የሰፈረው አስተያየት።ሁንዴ ደጋጋ«እርሶም፡እንኳን፡ደስአልዎት፡ዶክተር፡፡»ብለዋል።ኤልያስ አስራት በበኩላቸው -እነአዬዬ ምን ልትሉ ይሆን ይሄንን ሪፖርት። ዶክተሩ ተደምረው ይሆን?ሲሉ ጠይቀዋል።
ናፖሊዮን ቦና ፓርቲ በሚል ስም ደግሞ፤ «አቤት ስንቱ በመዳህኒት እጥረት እናበተበላሸ መድሀኒትእየተሰቃየ እንደሆነ ብታዮ»ብለዋል። ሃና መሰለ--ይህ የሆነው በርሶ ጥረት ነው በጣም እናመሰግናለን 🙏 ብለዋል። አበበ ደምሴ ደግሞ ፤የማንሰራራት ዓመታችን ስንል በምክንያት ነው፤ ድሉ ይቀጥላል!!»የሚል አስተያየት ሰጥተዋል።ፈንታ በቀለ-«-ተቃራኒውን ማመን ይጠቅማል ባይነኝ!!እንደ ቤሔራዊ ባንክ ሪፎርም።»ሲሉ፤ ክፍሌ ቦኒ፤ደግሞ-«ለማንኛውም "ፌጦ" መድሀኒት ነው።» ሲሉ፤ ሳሙኤል የጌታ ልጅ፤ «ተመሰገን ይህም ለሀገሬ ሌላ በረከት ነው።»ብለዋል።
ሰብለ በላይ-«እኛ ውስጡን ምናውቅ ሰዎች ደረጃውን እንመን ??? እና ቁጥጥሩ ,...?? ይሁና»በማለት አስተያየታቸውን አስፍረዋል።ዜዶ ነኝ በሚል ስም ደግሞ ፤«እኮ ይቺ የኛ ኢትዮያ የወባ ክኒን በየሸቀጥ ሱቁ የሚሸጥበት ሀገር።»አብዲ ሀይሌ «-ሀላፊነት ማለት ዕንዲ ነው የአገርንና የህዝብን ጉዳት መጠበቅ መከላከል ዕንዲ ነው በዳኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን በግሌ ዕንደ አንድ ኢትዬጵያዊ ዜጋ ከልቤ በጣም አመሠግናለሁኝ።»ብለዋል።
ገረመው አሰፋ -የፌደራል የምግብ እና የመድሃኒት አስተዳደር /Federal Food & Drug Authority በርቱልን👌 እንደሀገር ጥሩ ስራ እየሰራችሁ ነው። የዚህ መ/ቤት ችግሩ ከተማና ክፍለ ከተማ ቅርንጫፎች ላይ ነው።»ብለዋል።ስጦታው ማሞ፤«-ጥሩ ነው ይህን ስራ ለሰሩት ምስጋና ይገባቸዋል።» ሲሉ፤«የጤና ባለሞያዉ ደረጃ ግን ስንት ይገባ ይሆን ?ከማን ሃገር ተሽላ ትቀርብ ይሆን ?የበሬን ምስጋና ወሰደዉ ፈረስ እንዳይህን ነገሩ። የሚል አስተያየት ያሰፈሩት ደግሞ አዲሱ ጌታ የተባሉ አስተያየት ሰጪ ናቸው።
ፀሐይ ጫኔ
ነጋሽ መሐመድ