1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

ሐሙስ፣ ኅዳር 5 2017

በሁለቱ የህወሃት ጎራዎች መካከል የቀጠለው ውዝግብ፤ የአንጋፋው ጋዜጠኛ እና ደራሲ ዜናነህ መኮንን ሕልፈተ ሕይወት እንዲሁም የዶቼ ቬለ የሠራተኞች ማኅበራት የሥራ ማቆም አድማ ጥሪ ላይ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ከተሰጡ አስተያየቶች የተወሰኑትን መራርጠናል።

 የዶቼ ቬለ መለያ አርማ
ቦን ከተማ ከራይን ወንዝ ዳርቻ የሚገኘው የጀርመን ዓለም አቀፍ ራዲዮ ጣቢያ የዶቼ ቬለ መለያ አርማምስል Carsten Koall/dpa/picture alliance

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

This browser does not support the audio element.

በሁለት ጎራ የተከፈለው ሕዝባዊ ወያነ ሀርነት ትግራይ በምኅጻሩ ህወሀት ከገባበት ውዝግብ ለመውጣት አቅም ያጣ መስሏል። በሃይማኖት መሪዎች አሸማጋይነት ወደ ውይይት መመለሳቸው የተነገራለቸው እነዚህ ጎራዎች ዳግም ወደሌላ ፍጥጫ መግባታቸው እየተነገረ መሆኑን ከሰሙት የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተጠቃሚዎች ገሚሱ የፓርቲውን የውስጥ ቀውስ እውንነት ጥያቄ ውስጥ ከቷቸዋል። ከእነዚህ መካከል ያበሽ ነሪ በፌስቡክ፤ «ድራማ ነው አንድም ቀን ተወዛግበው አያውቁም።» ሲሉ ጌታነህ ወንዲ በበኩላቸው፤ «እናንተ ውዝግብ ብላችሁ የምታቦኩትን ወሬ ሳይቀር ደፂና ጌቾ በጋራ ነው የሚልኩላቹሁ...ንቁ እንጂ ምነው ፈዘዛችሁ!» ነው ያሉት።

መብራቱ ከበደ የተባሉ ሌላኛው የፌስቡክ ተጠቃሚ ደግሞ፤ «ህወሃት መላ ቅጡ የጠፋበት ፓርቲ ሆኗል !! ይህ ለትግራይ ህዝብ ያለማሰብና እውቀቱም ቢሆን ከመለሰ ዜናዊ ጋር የቀረ መሆኑን ፍንትው አድርጎ ያሳያል ።» ይላሉ። ሮቤል ሮቤልም፤ «የህዝቡን ብዙ ጥያቄ ላለመመለስ አውቀው ዕቃ ዕቃ እየተጯወቱ ነው» ነው ሲሉ፤ ናሆም ቺጃሞም ሃሳባቸውን በመጋራት፤ «ምናልባት ይህ ይሆናል ነጥቡ» ሲሉ አስተያየታቸውን በእንግሊዝኛ አጋርተዋል።  

ዳንኤል ግርማይ ደግሞ እንዲህ ይላሉ፤ «ሁለት ዓመት ሙሉ የሕዝብ ችግር የጤፍ ፍሬ ያክል ያልፈታ ጊዜያዊ የትግራይ አሰተዳደር በምኑ መለክያ የሕዝብ አሰተዳደር ይባላል እንደውም የህዝብ የችግርና መክራ እያራዘሙ ይገኛሉ።» በማለት ሲወቅሱ፤ ዳዊት ጂ ትግራይ የተባሉ ሌላኛው የፌስ ቡክ ተጠቃሚ ደግሞ፤ «የጊዜያዊ አስተዳደሩና የህወሐት ድራማ አስገራሚ ነው።» ተመሳሳይ ትችት ሰንዝረዋል።

ሳሚያ መሀመድ፣ «አረ ሰለቸን የህዋህት ፖለቲካ ኡፍፍፍ፤ ኢትዮጵያ እኮ ሰፊ ናት» ነው ያሉት። በትግሪኛ አስተያየታቸውን ያጋሩት መብራቱ ፀጋይ፤ «አደብ ግዙ፤ ምሩ ወይም አምሩ!» ሲሉ፤ ሚካኤል ልጅሻል ደግሞ፤ «ሰላም ለትግራይ» ብለዋል።


የሕዝባዊ ወያነ ሀርነት ትግራይ በምኅጻሩ ህወሀት አርማፎቶ ከማኅደር ምስል Million Haileyessus/DW

ባለፉት ቀናት ከተሰሙና የብዙዎችን ትኩረት ከሳቡት አንዱ የአንጋፋው ጋዜጠኛ ዜናነህ መኮንን ሕልፈተ ሕይወት አንዱ ነው። ለዓመታት በኢትዮጵያ ራዲዮ እና በቴሌቪዥን ዜና አንባቢነቱ ዜናነህን የሚያውቁት፤ እንዲሁም በዶቼ ቬለ እና በሌሎችም መገናኛ ብዙሃን የፖለቲካ ትንታኔውንም ሆነ ዘገባዎቹን የተከታተሉ በርካቶች በሞቱ ሀዘናቸውን እየገለጹ ነው። ብዙዎቹ ነፍስ ይማር እያሉ ለቤተሰብ ወዳጅ ዘመዶቹ መጽናናትን ሲመኙ የአንዳንዶቹ አስተያየቶች ደግሞ ትኩረት የሚስቡ ዓይነት ናቸው። ይርጋ መላኩ አስጨንቅ፤ «ነፍስ ይማር ዜና ነህ! እስከዛሬ ዜነኛ ይሞት ነበር ዛሬ ዜና ሞተ» ብለዋል። ሚኪ ታደሰ ደግሞ፤ «አገራችን አንድ ሰዉ አጣች ማለት ይቻላል። ጋዜጠኛ ዜናነህ መኮንን ለነበረበት ሞያ የተሠጠ ፣ ከአቀራረቡ አልፎ እስከ ተፈጥሯዊ ድምፀ መረዋ ለረጅም ዘመናት ደከመኝ፣ ታከተኝ ሳይል የኢትዮጵያ ሕዝብን ሲያገለግል የነበረ እጹብ ድንቅ ጋዜጠኛ ነበር። ከዚህ ዓለም በሞት በመለየቱ ለወዳጅ ዘመዶቹ ብሎም አድናቂዎቹ መጽናናትን ይሥጥልን። በሰላም እረፍ» ነው ያሉት።

ሚካኤል ብርሃኑ፤ ደግሞ በጣም ያሳዝናል በማለት ዶቼ ቬለ ያጣቸውን አንጋፋ ጋዜጠኞች ሁሉ ነው ያስታወሱት፤ «በጣም ያሳዝናል፤ ያ ወርቃማ በስነ ምግባር የታነፀ የምሁራን ትውልድ ያፈራቸው እንደ ጋዜጠኛ እና ደራሲ ዜናነህ መኮንን የመሰሉ ምሁራንና ጋዜጠኞች ወደ ማይቀረው ዓለም አንድ በአንድ እንዲህ ሲለዩ ልብ ይሰብራል።

እግዚአብሔር ነፍሱን በአፀደ ገነት ያኑርልን፤ ለቤተሰቦቹ ፣ ለወዳጆቹ፣ ለስራ ባልደረቦቹ መፅናናትን እመኛለሁ። የጀርመን ድምጽ ራዲዮ ወርቃማ ዘመን ምሁራን እና ባለሙያ ጋዜጠኞችም እንዲህ ተለይተውናል። አማኑኤል በረከት፤ ዘውዱ ታደሰ፤ ተክሌ የኋላ፤ ጌታቸው ደስታ፤ ጌታቸው ተድላ ኃይለጊዮርጊስ፤ ለሁሉም ነፍሳቸውን ይማር።» ብለዋል፤

ሰላም ውቤም፤ «ዜናነህ መኮንን ባልሳሳት ደራሲም ነው በኢትዮጵያ ሬድዮ የተተረከ ከጣሪያው ስር የተሰኘው ልብወለድ ደራሲ እንደነበርም የማውቅ ይመስለኛል! ፈጣሪ ነፍሱን በአፀደ ገነት ያሳርፋት ልጆቹንና ቤተሰቡን ያጽና!» ሲሉ ስለዜናነህ የሚያውቁትን አጋርተዋል።

ተሾመ ሰይፉ፤ «ዜናነህ በሙያው ጀግና ጋዜጠኛ ነበር:: ያ ታሪክ አዋቂ፤ ሀገሩን ወዳድ ከተወዳጅ ድምፁ ጋር ተለየን ማለት ነው? ያሳዝናል!» ሲሉ፤ ኢትዮ እማማ ደግሞ፤ «በጣም የምወደው ከእስራኤል ዘገባ ሲኖር ያን የሚያስገመግም ድምፁን ለመስማት በጣም እጓጓለት የነበረው ልዩ ጋዜጠኛ ዜናነህ መኮንን ፈጣሪው አፈር ነህና ወደአፈር ትመለሳለህ አለውና ወሰደው ለቤተሰቦቹ መፅናናትን አመኝላቸዋለሁ።» ብለዋል። ከሀገሩ ውጪ መቀበሩ የቆረቆራቸው አበበ አርአያ ረዳ በበኩላቸው፤ «ዜና ነህ ለአገሩ የነበረው ፍቅርና ክብር ልዩ ነበር። የሞተልሽ ቀርቶ የገደለሽ በላ ሆነ። እንደወጡ መቅረት በጣም ያሳዝናል። ነፍስ ይማር።» ነው ያሉት አንትሽ ብርሃኑም፤ «ዜናነህ መኮንን በኢትዮጵያም ማስታወሻ ሊቆምለት የሚገባ ድንቅ ጋዜጠኛ ነበር፤ ይህም ሆኖ እንደምናይ ተስፋ እናደርጋለን ነፍሱ በሰላም ትርፍ!« በማለት ሃሳባቸውን አካፍለዋል።

ባደረበት ህመም ለረዥም ዓመታት በህክምና ሲረዳ ቆይቶ ከዚህ ዓለም ድካም ያረፈው አንጋፋው ጋዜጠኛ እና ደራሲ ዜናነህ መኮንንምስል privat

የዶቼ ቬለ የሠራተኞች ማኅበራት የጠየቁትን የደመወዝ ጭማሪ ምክንያት በማድረግ የተጠራውን የሥራ ማቆም አድማ ያመለከተው መረጃም ሌላው ትኩረትን የሳበ ርዕሰ ጉዳይ ነበር። ብርሃኑ ዩሱራ፤ «የኑሮ ውድነት ያለው ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ይመስለን ነበር» በማለት ሲገረሙ፤ አንቺ ዓለም፤ «አይ ኢትዮጵያ ውስጥ ቢሆን ኖሮ የተለያየ ስም ተለጥፎ ነበር አፈር ደሜ የሚያስበሉህ» ነው ያሉት።

በየነ ካሱ፤ «ጀርመን ውስጥም የደመወዝ ችግር አለ እንዴ ወይስ ችግሩ ሌላ ነው?» ብለው ሲጠይቁ፤ አጂብ ሀጅ ዑመር ደግሞ፤ «ጀርመኖች የሥራ ማቆም አድማ ያደረጉት ምን ያህል እየተከፈላቸው ይሆን? ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል ስንት ነው ይሁን? የኢትዮጵያ ጉድ ቢሰሙ ምን ይሉ ይሆን?» ነው ያሉት። ሙሉጌታ መንግሥቱም ሌላው ጠያቂ ናቸው፤ «እኛም መሳተፍ እንችላለን እንዴ በአንቀፅ 9 መሠረት» በማለት፤ ጌቾ ሚካኤል፤ «ታድለዋል ባያስተካክልም የሚሰማ መንግሥት አላቸው።» አሉ፤ ጋሻው ታደሰ የተመለከቱት እንዲህ ነው፤ «የሥራ ማቆም አድማው በDW መዘገቡ የሙያ ነጻነት መኖሩ እና ዴሞክራሲ ትክክለኛ ትግበራ ያሳያል።» ሲሉ፤ መኩ አቤል ደግሞ፤ «በረከቱ በርሃብ እና ጉስቁልና ያሉ ኢትዮጵያውያን መንግሥት ሠራተኛ ይሁን» ብለዋል። 

ሸዋዬ ለገሠ

እሸቴ በቀለ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW