የማዳበሪያ እጥረት እና ይፈጸማል የተባለው ብልሹ አሰራር
ቅዳሜ፣ ሐምሌ 1 2015
“ማዳበሪያ ያው በአንድ ላይ ባይሆንም አልፎ አልፎ ይመጣል፡፡ ያው ከማጣት ለችግር ትሆናለች፡፡ ሰው በመጠበቅ ተሰላችተው አንዳንዱ ስንዴ አሊም ሌላ ምርት ለመዝራት ያዘጋጀውን ማሳ ማዳበሪያ ወደ ማይፈልጉ እንደ ባቀላ ወዳሉ ምርት ፊቱን አዙሯል፡፡ አንዳንድ ማሳ ደግሞ የአዝመራ ጊዜ በማለፉ በሳር እየተሸፈነ ነው፡፡ በብዛት ተስፋ አስቆራጭ ነው፡፡ እስካሁን አንድ 50 ኪሎ ማዳበሪያ ብቻ ያገኘ አርሶ አደር አለ፡፡”
ይህን ያሉን ከኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን በአፈር ማዳበሪያ እጥረት የተማረሩ አርሶ አደር ናቸው፡፡ በዚሁ ዞን ሜታ ሮቢ ከሚባል ወረዳም ተመሳሳይ ምሬታቸውን ያጋሩን አርሶ አደር ዘንድሮ ማዳበሪያ “እንደ ወርቅ ነው የሆነው” ሲሉ ተናግረዋል፡፡ እንደ እኚህ አስተያየት ሰጪ ዘንድሮ የማዳበሪያ አቅርቦት ችግሩ ከእጥረትም ባሻገር ነው፡፡ “የመንግስት አካላት ከነጋዴዎች ጋር ተመሳጥረው መንግስት የሚያቀርበውን ማዳበሪያ 100 ኪ.ግ. አራት ሺህ ብር ባልሞላ እየገዙ በእጥፍ ለገበሬው ይሸጡታል፡፡ ዛሬ ላይ እስከ 10 ሺ የሚሸጡም እንዳሉ እየሰማን ነው፡፡ ማህበረሰባችን በእጅጉ ተሰቃይቷል፡፡ ምን መደረግ እንዳለበት አናውቅም፡፡ አንዲት 50ኪ.ግ. እንኳ እያገኙ ያሉት ከሁለት ሳምንት እስከ አንድ ወር ተመላልሰው ነው፡፡ ከእሩቅ ገጠር እስከ 20 ኪ.ሜ. በእግር ተጉዘው ተመላልሰው ነው ይህችን የሚያገኙት፡፡”
እንደ እኚህ አስተያየት ሰጪ ሰሞኑን በመንግስት ስራ ላይ ያሉ ሰዎች ከነጋዴ ጋር ተመሳጥረው በጭነት መኪና ማዳበሪያ ወደ ሌላ ከተማ ወስደው ለመሸጥ ሲሰናዱም በፖሊስ ቁጥጥር ወደ መጋዘን ተመልሶ ያውቃል፡፡ ይሁንና ተጠያቂነት ባለመኖሩ በነዚህ ሰዎች ላይ ተወሰደ የሚባለውን እርምጃ አንሰማም ይላሉ ቅሬታ አቅራቢው፡፡ “የሚገርምህ ይህነ ሲያደርጉ እስከ 50 ሰው መዝግበው ነው በነሱ ስም ማዳበሪያውን ጭነው ወደ ሌላ ቦታ ለመውሰድ የተዘጋጁት፡፡ ይህን ሲያደርጉ ለተመዝጋቢዎቹ ሌላ ጊዜ የዛሬ ሳምንት-ሁለት ሳምንት ትወስዳላችሁ ይሏቸዋል፡፡ እነሱ ግን ሌላ ቦታ ወስደው በእጥፍ ይሸጡታል፡፡ ማዳበሪያ ለመግዛት ያለውን የሸጠው ገበሬ ግን በመመላለስ እግሩ ተልጦ በመጨረሻ ሲያጣ ከነዚያ ሌቦች እና ነጋዴዎች በውድ ዋጋ ለመግዛት ነው የሚገደደው ማለት ነው፡፡”
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ከትናንት በስቲያ ከኢትዮጵያ ፓርላማ አባላት የተነሳላቸውን ጥያቄ ተንተርሰው ማብራሪያ ሲሰጡ፤ በዓመቱ መንግስት አንድ ቢሊዮን ዶላር ገደማ ለማዳበሪያ ግዢ ማውጣቱን ገልጸው ነበር፡፡ የመንግስታቸው ቅድሚያ ትኩረት ምርታማነትን ማሳደግ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ አሁን ላይ ዘግይቶ ጅቡቲ ወደብ የደረሰውን ማዳበሪያ በአስቸኳይ ለማጓጓዝ በሙሉ አቅም እየተሰራም ነው ብለዋል፡፡ የችግሩ ምንጭም በዋናነት የዩክሬን-ሩሲያ ጦርነት ገቢያውን ማናጋቱ ነው ብለው ነበር፡፡
በግብርና ላይ ምጣኔ ሃብቷን ለመሰረተች ኢትዮጵያ ይህ ፈታኝ የኑሮ ሁኔታውን ሊፈጥር የሚችል በመሆኑ ጉዳዩ የተለየ ትኩረት አግኝቶ ስርዓት አልበኝነትም በመሰረቱ ካልተፈታ ህዝብን እስከ ማስራብ የሚችል አደጋ ሊያስከትል ይችላል ያሉን ደግሞ የፖለቲካል ኢኮኖሚ ተንታኝ አቶ ሸዋፈራሁ ሽታሁን ናቸው፡፡
ዘንድሮ እንደ አገር ያጋጠመው የማዳበሪያ እጥረትና ግብዓቱን በጊዜው በአዝመራ ወቅት የአለማዳረስ ችግር በተለይም በአማራ ክልልም አርሶ አደሩን ሲያስመርር መሰንበቱ ይታወሳል፡፡
ሥዩም ጌቱ
እሸቴ በቀለ