1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሜርክል ቅርስ

ማክሰኞ፣ ጥቅምት 30 2014

ሜርክል በጎርጎሮሳዊው 2015 ዓም የጀርመን ድንበር እንዲከፈት ባሳለፉት ውሳኔ አንድ ሚሊዮን እንደሚደርሱ የሚገመቱ ስደተኞችን ታድገዋል።ይህ ውሳኔያቸው በዓለም አቀፍ ደረጃ በሰብዓዊነት ለወሰዱት ለዚህ እርምጃ ክብርና አድናቆትን ሲያስቸራቸው በሀገር ውስጥ ደግሞ ጽንፈኛ አስተሳሰብ ከሚያራምዱ ፖለቲከኞችና የኅብረተሰብ ክፍሎች ተቃውሞ አስነስቶባቸዋል።

DW Interview mit Bundeskanzlerin Angela Merkel +++ SPERRFRIST 7.11. 18h ++++
ምስል R. Oberhammer/DW

ቃለ ምልልስ ከአንጌላ ሜርክል ጋር

This browser does not support the audio element.

በጀርመን ታሪክ የመጀመሪያዋ ሴት መራኄ-መንግሥት ናቸው።የተዋሀደችውን ጀርመን በመምራት የመጀመሪያዋ የምሥራቅ ጀርመን ሰውና ሳይንቲስትም ጭምር። በሃገራቸው በጀርመን፣ ብዙ አስተዋጽኦ ባበረከቱበት በአውሮጳ፣ በአፍሪቃ ብሎም በመላው ዓለም ክብርና አድናቆት የሚቸራቸው በአርአያነት የሚጠቀሱ መሪ ናቸው።ብልህ፣አርቆ አስተዋይ ታጋሽ ከስሜታዊነት የራቁ፣ ስራ ወዳድ፣ መፍትሄ ፈላጊ እረፍት የለሽ መሪ እንደሆኑ ብዙዎች ይመሰክሩላቸዋል፤የጀርመን መራኂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል።
«ሁሌም በደስታ ነው ስራዬን የማከናውነው።አሁንም መስራት ያስደስተኛል።አዎ እስከመጨረሻው የስራ ቀን ድረስ ጠንቃቃ መሆን ያስፈልጋል።»
ሜርክል ከስልጣን ከመሰናበታቸው በፊት ለዶቼቬለ በሰጡት የመጨረሻ የተባለ ቃለ ምልልስ የተናገሩት ነው። ሙሉ ስማቸው አንጌላ ዶሮትያ ሜርክል ነው። ከጎርጎሮሳዊው 2005 ዓም አንስቶ የጀርመን ከፍተኛው የስልጣን ማማ ላይ ናቸው። የፖለቲካውን መንገድ ካቃኑላቸው ከአርአያቸው ከመራኄ መንግሥት ሄልሙት ኮል ቀጥሎ ጀርመንን ለ16 ዓመታት በመምራት ሁለተኛዋ የሀገራቸው ታዋቂ ፖለቲከኛ ናቸው፤ ምዕራብ ጀርመን ተወልደው በቀድሞዋ ምሥራቅ ጀርመን ያደጉት ሜርክል ህዝባቸው በጀርመንኛ «ሙቲ» ወይም እናት ሲል ነው የሚጠራቸው።  የፖለቲካውን ዓለም በር የከፈተላቸው ጀርመንን ለሁለት ከፍሎ የቆየው የበርሊን ግንብ ከ30 ዓመት በፊት መፍረሱ ነው። ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ስልጣናቸውን የሚያስረክቡት ሜርክል በ16 ዓመታት ሥልጣናቸው እጅግ ከፍተኛ የመወሰን ሥልጣን ካላቸው የዓለማችን ሴቶች አንዷ እስከመባል ደርሰዋል። ሜርክል በአውሮጳ ኅብረትም ሆነ በሌሎች ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ አስታራቂ ሃሳብ አቅርቦ አለመግባባቶችን በመፍታትም ይታወቃሉ።ያነጋገራቸው የዶቼቬለው ማክስ ሆፍማን ሜርክልን የዚህ ብልሀቱ ምንድን ነው? እንዴትስ ነው የሚሳካልዎት ሁሉንም በአንድ ዓይነት መንገድ ነው የሚቀርቡት ወይስ አካፋን አካፋ ይላሉ ሲል ጠይቋቸው ነበር።
«እንደሚመስለኝ አካፋን አካፋ አልልም ማለት ስህተት ነው፤ የወዳጅነት ግንኙነት ካለን  መራኄ መንግሥታትም ጋር ቢሆን ።ምን ጊዜም ቢሆን በልባችን የጀርመን ጥቅሞች አሉ። ፈረንሳይ ወይም ሌሎች የተለዩ ፍላጎቶች ይኖራቸዋል።እነዚህን ፍላጎቶች ወደ አንድ መስመር ማምጣት አለብን።እርግጥ ነው እኛ በጋራ እሴቶቻችን በጋራ የዴሞክራሴ ግንዛቤያችን አንድ ነን።ምናልባትም በንግግሮች ወቅት ቁጥብነት ወይም የሌላውን ስጋት ከግምት ውስጥ ማስገባት ከሌለ ፤ አለያም በተለየ ጉዳይ ላይ መነጋገር ካለብን ንግግሩ ይበልጥ በተለየ ሁኔታ ነው የሚካሄደው።ሁልጊዜም ወደ እነዚህ ዓይነት ንግግሮች የምገባው አቋም ሳልይዝ ነው።ሁሌም በመነጋገር ለውጥ ያመጣል ብዮ ተስፋ አደርጋለሁ።የምቆመው የጀርመን ጥቅሞችን ለማስከበር ነው። ከዚሁ ጋርም ሁሌም ለጥሩ የሁለትዮሽ ግንኙነቶችም እቆማለሁ። ሆኖም አንድ ሰው መሰረታዊ ልዩነት ያለው ግንዛቤ ይዞ ቢቀርብ ምን ይሁን ምን ማድመጥ ያስፈልጋል።ምክንያቱም አንዳችን ሌላኛውን ካላደመጥን ምንም ዓይነት መፍትሔዎች ማግኘት አንችልም።»
በምዕራብ ጀርመንዋ ሀምቡርግ ተወልደው በህጻንነታቸው በሄዱበት በኮምኒስት ምሥራቅ ጀርመንዋ ፔርለቤርግ ያደጉት ሜርክል በዚያው በምሥራቅ ጀርመን በኳንተም ኬምስትሪ በዶክትሬት ዲግሪ በጎርጎሮሳዊው 1986 ዓም ተመርቀዋል።እስከ 1989 በተመራማሪ ሳይንቲስትነት የሰሩት ሜርክል ከ1989 ከምሥራቅ ጀርመን አብዮት በኋላ ነበር የፖለቲካውን ዓለም የተቀላቀሉት።ያኔ በዴምክራሲያዊ መንገድ በተመረጠው የምሥራቅ ጀርመኑ የሎታር ደሚዜር መንግሥት ለአጭር ጊዜ ምክትል ቃል አቀባይ ነበሩ። በወጣትነታቸው ህዝባዊ መሰረት ያለውን አንጋፋውን የክርስቲያን ዴሞክራት ኅብረት ፓርቲ የተቀላቀሉት ሜርክል በጎርጎሮሳዊው 1990 ምሥራቅና ምዕራብ ጀርመን ከተዋሀዱ በኋላ የሰሜን ጀርመኑ የሜክለንቡርግ ፎርፖመርን ፌደራዊ ክፍለ ሃገርን ወክለው ጀርመን ፓርላማ ገቡ።በሄልሙት ኮል መንግሥት በ1991 የሴቶችና የወጣቶች ሚኒስትርነት ሹመት ተሰጣቸው።ከዚያም በ1994 የአካባቢ ጥበቃ ሚኒስትር ሆኑ።ፓርቲያቸው የክርስቲያን ዴሞክራት ኅብረት በ1998ቱ ምርጫ ከተሸነፈ በኋላ በፓርቲው ዋና ፀሐፊነት ተመረጡ።የመጀመሪያዋ ሴት የፓርቲው ዋና ጸሀፊም ሆኑ።በ2005 በመራሄ መንግሥትነት ተሾሙ። ከዚያን ጊዜ አንስቶ ከተካሄዱት ሦስት ምርጫዎች በኋላም ፓርቲያቸው ተጣማሮ የመሰረታቸውን መንግሥቶች ሲመሩ ቆይተዋል። ሜርክል በስልጣን ዘመናቸው ካከናወኗቸው ዐበይት ተግባራት ውስጥ የዓለም የገንዘብ ቀውስ በተከሰተበት በጎርጎሮሳዊው 2008 ዓም ሃገራቸውንና የአውሮጳ ኅብረትን ከቀውሱ ያወጡበት ብልሀት ሁሌም ስማቸውን ከፍ አድርጎ ያስነሳል። ከሰባት ዓመት በኋላ በአውሮጳ የተከሰተው የስደተኞች ቀውስ እንዲሁም የቅርብ ጊዜውን የኮሮና ወረርሽኝ ለመቋቋም የወሰዷቸው እርምጃዎችም የሜርክልን ጥንካሪ አጉልተው በማሳየት ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛሉ። ሜርክል በስልጣን ዘመናቸው ካጋጠሟቸው ቀውሶች ውስጥ በተለይ ሁለቱ ፈታኝ እንደነበሩ ለዶቼቬለ ተናግረዋል።
«በግሌ ሁለት ጉዳዮች በጣም ፈታኝ ነበሩ።አንዱ በርካታ ቁጥር ያላቸው ስደተኞች እዚህ ጀርመን የገቡበት ወቅት ነው።ሆኖም ይህን ቀውስ ብዬ ልጠራው አልፈልግም።ምክንያቱም ሰዎች ሰዎች ናቸው።በመጀመሪያ በተለይ ከሶሪያና ከሶሪያ አጎራባች ሃገራት ተሰደው ከመጡ በርካታ ሰዎች የደረሰበን ጫና ነው።አሁን ደግሞ የኮቪድ 19 ወረርሽን ነው።እነዚህ ሰዎችን በቀጥታ የሚመለከቱ ሁለት ጉዳዮች ለኔ በጣም ፈታን ነበሩ።ሌላው ቀውስ ተብሎ ሊጠራ የሚችል ጉዳይ ብዙ ወገኖችን አሳታፊ በሚያደርጉ ተግባራት ላይ በርካታ ሰዎች የሚያድርባቸው ጥርጣሪ ነው።ለኔ ይህ በጣም ጠቃሚ ጉዳይ ነው።ሁሌም ዓለም አፈe ድርጅቶችን ለማጠናከር እሞክራለሁ የኦለም የገንዘብ ድርጅት የዓለም ባንክ የዓለም የስራ ድርጅት እና ሌሎችንም።በየዓመቱ እጋብዛቸዋለሁ።ለ13 ያህል ጊዜያት ጋብዣቸዋል።ይህን በማድረግም የአብሮ መስራትን አስፈላጊነት ለዓለም ለማሳየት ሞክሬያለሁ። በኔ ዘመን ነው ቡድን ሀያ የተመሰረተው።ይህም በጋራ በመስራት ብቻ ችግሮችን ማስወገድ እንደሚቻል ግልጽ ያደረገ ጠቃሚ መድረክ ነው።»
ሜርክል በጎርጎሮሳዊው 2015 ዓም የጀርመን ድንበር ለስደተኞች እንዲከፈት ባሳለፉት ውሳኔ አንድ ሚሊዮን እንደሚደርሱ የሚገመቱ ስደተኞችን ታድገዋል።ይህ ውሳኔያቸው በዓለም አቀፍ ደረጃ በሰብዓዊነት ለወሰዱት ለዚህ እርምጃ ክብርና አድናቆትን ሲያስቸራቸው በሀገር ውስጥ በርካቶች እርምጃቸውን ቢደግፉም  ጽንፈኛ አስተሳሰብ ከሚያራምዱ ፖለቲከኞችና የኅብረተሰብ ክፍሎች ተቃውሞ ተነስቶባቸው ነበር።ያኔ ተቃውሞው ያየለባቸው ሜርክል «ማድረግ አያቅተንም« «እንችላለን» ሲሉ ተቃዋሚዎቻቸውን ፊት ለፊት ተጋፍጠው በውሳኔያቸው ገፍተዋል። በዶቼቬለ ቃለ መጠይቅ ላይ ማክስ ሆፍማን ታዲያ አሁን ችለነዋል ተሳiክቶልናል ብለው ያምናሉ ሲል ጠይቆአቸው ነበር።
« አዎን እኛ አሳክተነዋል። እኛ ስል ግን ስራው እንዲሳካ ድጋፍ ያደረገውን በርካታ ቁጥር ያለውን ህዝብ ማለቴ ነው።በርካታ ከንቲባዎች፣በጎ ፈቃደኞች እና ያስጠጓቸውን ስደተኞች እስካሁን ድረስ በመርዳት ላይ የሚገኙ በርካታ ሰዎች።እርግጥ ነው ሁሉንም ነገር መሆን እንዳለበት አለመሄዱን አይተናል። አንዳንድ ከባድ አጋጣሚዎች ነበሩ።ይህም በአዲስ ዓመት ዋዜማ በኮሎኝ የደረሰውና ብዙዎቻችን በመጥፎ የምናስበው ትውስታም አለን።በአጠቃላይ ግን በጥሩ ምሳሌነት የሚጠቀሱ ስኬታማ ጉዳዮችም አሉ።ስደተኛ ወጣት ሴቶችና ወንዶች  የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና መውሰዳቸው በምሳሌነት ይነሳል።» 
ግን ይላሉ ሜርክል መሰረታዊው ችግር እስካሁን አልተነካም።
«የመፈናቀልና የስደትን መሰረታዊ ምክንያቶች መከላከልን በሚመለከት ብዙ ይቀራል።እስካሁን የጋራ የአውሮጳ የስደት ና የተገን አሰጣጥ ስርዓት የለንም። የልማት እርዳታንና ሕጋዊ ስደትን በሚመለከት ብዙ መስራት አለብን። በዚህ ዘመን በተለይ ህገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎችና ደላሎች የበላይነትን መያዛቸው አሳፋሪ ነው።ሕጋዊ የፍልሰት መንገዶች አሉን። የተመ የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን UNHCR ስደተኞችን ተቀበሉ ሲል በትክክል እርዳታ የሚፈልጉ መሆናቸውን እናውቃለን።በዚህ ረገድ ብዙ መሰራት አለበት።»
የ67 ዓመትዋ ሜርክል ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ስልጣን ይለቃሉ ተብሎ ይጠበቃል።ሜርክል ስልጣናቸውን ካስረከቡ በኋላ ምን ለመስራት እንዳሰቡም ተጠይቀው ሲመልሱ እስከዛሬ በሄዱበት መንገድ እንደማይቀጥሉ ነው የተናገሩት።
«ስልጣን ከለቀቀሽ በኋላ ምን ታደርጊያለሽ ለተባልኩት ከአሁን ወዲያ በፖለቲካ ውስጥ በፍጹም አልሳተፍም። የፖለቲካዊ ግጭቶች መፍትሄ ፈላጊም አልሆንም።ይህን ለብዙ ዓመታት ስሰራ ቆይቻለሁ፤በመራኄ መንግሥትነት በአውሮጳ ኅብረት በዓለም አቀፍ ደረጃም ይህን ለ16 ዓመታት በደስታ ስሰራ ነበር። ሁሌም ሁሉንም ለሚያሳትፍ የጋራ ስራ ነበር የምቆመውአሁን ከስራ ስሰናበት ምን እንደምሰራ አላውቅም።በመጀመሪያ ትንሽ ለማረፍ እፈልጋለሁ።ከዚህ ሌላ ወደ ዐዕምሮዬ የሚመጣው ምን እንደሚሆን አያለሁ፤ አዎ አነባለሁ አተኛለሁም ለብዙ ዓመታት በሚዘጋጅልን አጀንዳ በጣም ተጠምጄ ነበር።ሁሌም ዝግጁ ሆኜ መገኘት አለብኝ። የመንግሥት መሪ ስትሆን ይህን ማድረግ አለብህ አንድ ነገር ሲሆን ወዲያውኑ መልስ መስጠት ትችላለህ አሁን ግን በኔ ምርጫ የማደርገውን እፈልጋለሁሁ።ይህ በጥቂት ወራት ውስጥ ግልጽ ይሆናል።»

ምስል Ludovic Marin/AFP/Getty Images
ምስል AP
ምስል picture-alliance/dpa/A. Altwein

ኂሩት መለሰ

አዜብ ታደሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW