1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሜርክል የ«አያቅተንም» የስደተኞች መርህ 5ኛ ዓመት

ማክሰኞ፣ ነሐሴ 19 2012

የጀርመን ህዝብ በሃገሪቱ የስደተኞች ፖሊሲ ሁሌም እንደተከፋፈለ ነው።ይሁንና «አያቅተንምን»ከተሰኘው ከሜርክል አባባል በላይ ህዝቡን የከፋፈለ ቃል አልነበረም እንደዚህ ጽሁፍ አቅራቢ እንደ ክሪስቶፍ ሃዝልባህ። ከጀርመን ህዝብ 60 በመቶው ሃገሪቱ የስደተኞችን ጉዳይ መቋቋም  ትችላለች ብለው ያምናሉ።40 በመቶው ደግሞ በተቃራኒው ነው የሚያስቡት።

Deutschland Merkel Selfie mit Anas Modamani
ምስል Getty Images/S. Gallup

የሜርክል የ«አያቅተንም» የስደተኞች መርህ አምስተኛ ዓመት612

This browser does not support the audio element.

ቁጥራቸው አንድ ሚሊዮን የሚጠጋ ስደተኞች ጀርመን ከገቡ እነሆ 5 ዓመት እየደፈነ ነው። የጀርመን መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል «አያቅተንም፣እንቋቋመዋለን » ሲሉ ሶርያውያን የሚያመዝኑባቸው ስደተኞች ያኔ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ጀርመን እንዲገቡ በመፍቀዳቸው ከተቃዋሚ ፖለቲከኞች እና ደጋፊዎቻቸው የትችት ናዳ ወርዶባቸዋል።ሜርክል ያኔ ያሉት ከአምስት ዓመት በኋላ አሁን ምን ደጃ ላይ ይገኛል? 
የጀርመን መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል በአጠቃላይ የሥልጣን ዘመናቸው በብዙዎች ላይ ተጽእኖ በማድረግ ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛል ተብሎ የሚታመነው የዛሬ 5 ዓመት «እንቋቋመዋለን» ሲሉ የተናገሩት ቃል ነው። ሜርክል ይህን አባባል የተጠቀሙት በርሳቸው ይሁንታ አንድ ሚሊዮን ስደተኞችን ያለ ገደብ ጀርመን እንዲገቡ ከፈቀዱ በኋላ ከየአቅጣጫው ለተሰነዘሩባቸው ትችቶች በሰጡት መልስ ነው።በጥቂት ሳምንታት ውስጥ በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በዋነኛነት በባልካን ሃገራት በኩል ጀርመን ገቡ።ጀርመን ከመድረሳቸው በፊት ሃንጋሪ እንዲቆዩ የተገደዱት እነዚሁ ስደተኞች በአመዛኙ ከሶሪያ፣ከሰሜን አፍሪቃ፣ከኢራቅ ከአፍጋኒስታን ነበር የመጡት።ምንም እንኳን ያኔ ሌሎች የአውሮጳ ህብረት አባል ሃገራት ስደተኞቹን የመቀበል ሃላፊነት የነበረባቸው ቢሆንም አላደረጉትምና ሜርክል የተገን ጥያቄአቸው ጀርመን ከገቡ በኋላ እንዲታይ በማለት የጀርመን ድንበር እንዲከፈትላቸው ፈቀዱ።በስተመጨረሻም በጎርጎሮሳዊው 2015 የተገን ማመልከቻ ያስገቡት ስደተኞች ቁጥር አንድ ሚሊዮን ተጠጋ።ያኔ ብዙዎች በጀርመን የስደተኞች ቀውስ ተፈጥሯል ይሉ ነበር።የያኔው የጀርመን የሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ቶማስ ደሚዜር በዚህ ዓመት በነሐሴ ወር እንደተናገሩት በወቅቱ ሁኔታዎች ከቁጥጥር ውጭ የሆኑበት ጊዜም ነበር።እርሳቸውን የተኩት የያኔው የደቡብ ጀርመንዋ የባቫርያ ፌደራዊ ክፍለ ሃገር ጠቅላይ ሚኒስትርና የሜርክል ፓርቲ የክርስቲያን ዴሞክራት ሕብረት እህት ፓርቲ  የክርስቲያን ሶሻል ህብረት ፓርቲ በምህጻሩ የCSUው ኽርስት ዜሆፈር በጎርጎሮሳዊው 2015 የተፈጠረውን ኢፍትሃዊነት የተንጸባረቀበት በማለት ኮንነውት ነበር።አንጌላ ሜርክል ግን ከርሳቸው ተቃራኒ በሆነ መንገድ ነበር የተመለከቱት።
«ጀርመን ጠንካራ ሃገር ናት።ብዙ ነገሮችን አሳክተናል።አያቅተንም። ይህን ጉዳይ የምንይዝበትን ዓላማ በዚህ ጽንሰ ሃሳብ መሠረት የሚታሰብበት መሆን አለበት። በመንገዳችን ላይ ሊደናቅፈን የሚቆም ካለም መወገድ  አለበት።»
በወቅቱ ሜርክል ከእህት ፓርቲያቸው ከCSU ከፍተኛ ተቃውሞ ቢገጥማቸውም የተጣማሪ መንግሥታቸው አባል የሶሻል ዴሞክራቶች ፓርቲ SPD እንዲሁም የአረንጓዴዎቹ ፖርቲ ግራዎቹና የነጻ ዴሞክራቶቹ ፓርቲ በምህጻሩ FDP የሜርክልን እርምጃ ብዙም አልተቹም።ከዚያ ይልቅ የአውሮጳ ህብረት አባል ሃገራት ስደተኞቹን ለመውሰድ ባለመተባበራቸው ላይ ነበረ ቅሬታቸው።በአንጻሩ ስደተኞች ጀርመን መግባታቸውን የሚቃወመው ከተቋቋመ ብዙ እድሜ ያላስቆጠረው «አማራጭ ለጀርመን» በጀርመንኛው ምህጻር AFD የተባለው ቀኝ ጽንፈኛ ፓርቲ ግን ሜርክል ስደተኞቹን መመለስ ነበረባቸው ብሎ ነው የሚያስበው። AFD ሜርክል ስደተኞቹን አባረው  ቢሆን ኖሮ በሜዴትራንያን ባህር አድርገው በአደገኛ ጉዞ ወደ አውሮፓ የሚመጡትን ቁጥር መቀነስ ይቻል ነበር ባይ ነው።ሆኖም የሜርክል «አያቅተንም»ብዙ ተከታዮችን አስገኘላቸው።በተለይ ከውጭ ዓለም አድናቆት ጎረፈላቸው።የዩናይትድ ስቴትሱ ኒውዮርክ ታይምስ ጋዜጣ በጎርጎሮሳዊው መስከረም 5ቀን 2015 ዓም ባወጣው እትሙ «ጀርመን እጆቿን ዘርግታ ስደተኞችን ተቀበለች ሲል ጽፏል።አልጀዚራ በበኩሉ «ጀርመን ተገንና ደህንነታቸው የሚጠበቅበትን ቦታ ለሚፈልጉ ሁሉ በሮችዋንና ድንበሮችዋን ከፈተች ሲል ዘግቦ ነበር።
መጀመሪያ ላይ ስደተኞቹ ከጀርመን አቅም በላይ ይሆናሉ የሚሉ ተጠራጣሪዎች ነበሩ።አንዳንዶች ደግሞ  ስደተኞችን በማስጠጋት ጀርመን በተጨባጭ ምን ልታገኝ ትችላለች?ከተለያየ ባህል ለመጡ ህዝቦችስ ሃላፊነት ልትወስድ ይገባታልስ ወይ?የሚሉ ጥያቄዎች ያነሱ ነበር። የጀርመን ህዝብ በሃገሪቱ የስደተኞች ፖሊሲ ሁሌም እንደተከፋፈለ ነው።ይሁንና «አያቅተንምን»ከተሰኘው ከሜርክል አባባል በላይ ህዝቡን የከፋፈለ ቃል አልነበረም እንደዚህ ጽሁፍ አቅራቢ እንደ ክሪስቶፍ ሃስልባህ። ከጀርመን ህዝብ 60 በመቶው ሃገሪቱ የስደተኞችን ጉዳይ መቋቋም  ትችላለች ብለው ያምናሉ።40 በመቶው ደግሞ በተቃራኒው ነው የሚያስቡት። ከክፍፍሉ በላይ በጀርመንዋ አራተኛ ትልቅ ከተማ በኮሎኝ በጎርጎሮሳዊው 2016 ዋዜማ አዲሱን ዓመት ለመቀበል በከተማይቱ ዋና ባቡር ጣቢያ በተገኙ ሴቶች ላይ ስደተኞች የፈጸሙት ማዋከብ የሜርክል የ«እንቋቋመዋለን» የስደተኞች እንኳን ደህና መጣችሁ  ፕሮፖጋንዳ ፍጻሜ መስሎ ነበር።ከዚያ በኋላ በየቦታው በስደተኞች መጠለያዎች ላይ በርካታ ጥቃቶች ተፈጸሙ።በሜርክል የስደተኞች ፖሊሲ ላይ የተነሳው ይህ ተቃውሞ ቀኝ ጽንፈኛውን AFDን በእጅጉ ጠቀመ። ከዚያ በኋላ ፓርቲው በተለያዩ አካባቢዎች በተካሄደ ምርጫ ብዙ ድምጽ ለማግኘት በቃ።በጎርጎሮሳዊው 2017ቱ የጀርመን ብሔራዊ ምርጫም ብዙ ድምጽ በማሸነፍ ጠንካራ ተቃዋሚ ሆኖ የጀርመን ምክር ቤት አባል ለመሆን በቅቷል።ይሁንና ሜርክል በጎርጎሮሳዊው 2015ቱ ውሳኔያቸው እስከ መጨረሻው ጸኑ እንጂ ሃሳባቸውን አልቀየሩም።ስደተኞች ካስገቡ ከአንድ ዓመት ከ3 ወር በኋላ በጎርጎሮሳዊው ታህሳስ 2016 ዓም ፓርቲያቸው የክርስቲያን ዴሞክራት ሕብረት ባካሄደው ጉባኤ ላይ አቋማቸውን ግልጽ አደረጉ።
«በ2015 ዓም በበጋው ማብቂያ ላይ የነበረው ሁኔታ በምንም ዓይነት መደገም የለበትም ይህ የኛና የኔ ፖለቲካዊ አቋምና ዓላማ ነበር፣ ነውም።»
ታዲያ ያኔ ጀርመን የገቡት ስደተኞች ዛሬ ምን ያህል ከህኅብረተሰቡ ጋር ተዋህደዋል።የስራ ቅጥርን በተመለከተ ስደተኞች ከጀርመኖች ጋር ሲነጻጸር ከአማካዩ ደረጃ በታች ነው ያሉት። የጀርመን የሥራ ገበያ እና የሥራ ቅጥር ምርምር ተቋም በጎርጎሮሳዊው 2020 ባካሄደው ጥናት መሠረት ከጎርጎሮሳዊው 2013 ወዲህ ጀርመን ከገቡት ስደተኞች ግማሽ ያህሉ ብቻ ናቸው ደህና ሥራ የያዙት።በጥናቱ መሠረት  በኮሮና ተህዋሲ ወረርሽኝ ምክንያት ብዙ ስደተኞች ከሥራቸው በመቀነሳቸው የቀደመው በጎ አካሄድ በከፊል ወደ ኋላ እየተመለሰ ነው።
ወንጀልን በተመለከተም የፌደራል የወንጀል ምርመራ ቢሮ ስለ ስደተኞች የግድያ ፣የአካል ጥቃትና የአስገድዶ መድፈር ወንጀል ያወጣው ዘገባ የተጋነነ  መሆኑ ተገልጿል።ያ ማለት ግን ወንጀል ውስጥ የሚሳተፉ ወጣቶች የሉም ማለት አይደለም።ሌላው እንደ ችግር የሚነሳው ጉዳይ የፌደራል ግዛቶች የተገን ጥያቄ ማመልከቻቸው ተቀባይነት ያላገኘ ስደተኞችን በሕጉ መሠረት ወደ ትውልድ ሐገራቸው ሊመልሱ ሲገባ  ብዙውን ጊዜ አለመሳካቱ ነው።ታዲያ የጀርመን ኅብረተሰብ ከአምስት ዓመት በኋላ ዛሬ በሜርክልን ታዋቂ አባባል መሠረት የስደተኞችን ጉዳይ ተቋቁሞታል?።የዛሬ አምስት ዓመት የጀርመን የሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩት ቶማስ ደ ሚዜር ውጤቱን እንዲህ ገምግመዋል።
«ብዙ አሳክተናል፤የተገን አሰጣጥ ሂደቱን አሳጥረናል።እስካሁን ጎዳና የወደቀ ስደተና የለም።የጤና እንክብካቤው አልተጓደለም።አስተዳደሩ ከበጎ ፈቃደኞች ጋር እየተካሄደ ነው።ይህ በእንዲህ እንዳለ አንዳንድ ነገሮች አልተሳኩም።ወደ ሃገራቸው ልናባርራቸው የሚገባቸው ወንጀለኞችን ጨምሮ ሌሎችንም ማባረር አልቻልንም። ከኅብረተሰቡ ጋር መዋሃድ የሚያስችላቸውን የውህደት ትምህርት የማይወስዱ ስደተኞች አሉ።ከተገን ጠያቂዎች መካከል በወንጀል የሚፈለጉም አሉ።ይህ በሌላኛው ጎኑ ነው።በዚህ የተነሳም ብዙ መሥራት ያለባቸው ጉዳዮች አሉ። »
የጀርመን የምጣኔ ሃብት ምርምር ተቋምም ተመሳሳይ አመለካከት ነው ያለው።በተቋሙ አስተያየት ጀርመን ጉዳዩን የማሳካቱ መንገድ ላይ ናት።ይህን ለማስፈጸም ደግሞ በዙ ጥረት ማድረግ ይገባል።እንደ ተቋሙ ጥረቱ የሚጠበቀው ከሁለት ወገኖች ነው። ከስደተኞች እንዲሁም ከተቀበላቸው ኅብረተሰብም ጭምር።

ምስል picture-alliance/dpa/R. Jensen
ምስል picture-alliance/dpa/A. Burgi
ምስል Getty Images/AFP/C. Stache
ምስል picture-alliance/dpa/A. Weigel

ኂሩት መለሰ

እሸቴ በቀለ 
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW