1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ
ሳይንስኢትዮጵያ

አዲሱ የሜታ ፖሊሲ የመናገር ነጻነትን የማበረታታ ወይስ የጥላቻ ንግግርን የሚያስፋፋ?

ፀሀይ ጫኔ
ረቡዕ፣ ጥር 14 2017

የፌስቡክ፣ ኢንስታግራም እና ትሬድ ባለቤት የሆነው ሜታ ኩባንያ ከዚህ በፊት የይዘት ክትትል የሚያደርጉ የእውነታ አጣሪዎችን ከመድረኮቹ ላይ በማስወገድ ከተጠቃሚ በሚመጡ «የማህበረሰብ ማስታወሻዎች» ለመተካት መወሰኑን በቅርቡ አስታውቋል። ይህ የሜታ ርምጃ የተሳሳቱ መረጃዎች እና የጥላቻ ንግግሮችን ያስፋፋል የሚል ስጋት አሳድሯል።

Logo | Meta Konzern
ምስል፦ Jens Büttner/dpa/picture alliance

አዲሱ የሜታ ፖሊሲ የመናገር ነጻነትን ማበረታታት ወይስ የጥላቻ ንግግርን ማስፋፋት?

This browser does not support the audio element.


በማርክ ዘከርበርግ የሚመራው እና የፌስቡክ፣ ኢንስታግራም እና ትሬድ ባለቤት የሆነው ሜታ ኩባንያ ከዚህ በፊት  የይዘት ክትትል የሚያደርጉ የእውነታ አጣሪዎችን /Fact checkers/ን ከመድረኮቹ ላይ በማስወገድ ከተጠቃሚ በሚመጡ «የማህበረሰብ ማስታወሻዎች» /community notes/ለመተካት መወሰኑን  በቅርቡ አስታውቋል።
በኤለን ማስክ ባለቤትነት የተያዘው የቀድሞው ቲዊተር የአሁኑ X  ይህንን  መንገድ መከተል ከጀመረ ውሎ አድሯል። 
ሜታ ከይዘት ክትትል ፖሊሲ ለውጡ ባሻገር በፌስቡክ፣ ኢንስታግራም እና ትሬድን በመሳሰሉ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ መድረኮቹ ላይ የፖለቲካ ይዘቶች ያሏቸው ዜናዎችን ለማሰራጨት መወሰኑን ሜታ ልጿል።
እንደ ሜታ እና ኤክስ ገለፃ  ይህ መሰሉ የይዘት ክትትል ለውጥ የንግግር ነፃነትን ለማጎልበት የተደረገ ነው ። ሆኖም አዲሱ ፖሊሲ የበለጠ ጎጂ የሆኑ ይዘቶች በመድረኮቹ ላይ እንዲንፀባረቅ ያደርጋል የሚል ስጋት ፈጥሯል። በተለይም የተሳሳቱ መረጃዎች እና የጥላቻ ንግግሮች ከፍተኛ ስጋት በሆኑባቸው እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሀገራት ችግሩ  ከፍተኛ  ሊሆን ይችላልም ተብሏል። በአሜሪካ ሚኒሶታ  ነዋሪ የሆኑት እና በመገናኛ ብዙሃን ፣ በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች እና በማህበረሰብ ለውጥ ላይ ገለልተኛ ምርምር የሚያደርጉት ዶክተር እንዳልክ ጫላ ስጋቱን ከሚጋሩት መካከል አንዱ ናቸው። እሳቸው እንደሚሉት ርምጃው በኢትዮጵያ አሉታዊ ተፅዕኖ ይኖረዋል።

የሜታ ባለቤት ማርክ ሱከርበርግ ከጎርጎሪያኑ ጥር 7ቀን 2025 ዓ/ም ጀምሮ የእውነታ አጣሪዎችን ከዲጅታል መድረኮቹ ለማስቀረት መወሰኑን አስታውቋል።ምስል፦ Andre M. Chang/ZUMA Press Wire/Imago Images

የሜታ እውነታን የሚፈትሹ አጋሮች እነማን ናቸው?

ከዚህ ቀደም በነበረው የሜታ አሰራር በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የሚቀረቡ መረጃዎች ላይ ማጣሪያ የሚደረገው ገንዘብ በሚከፈላቸው የእውነታ አጣሪ ባለሙያዎች እና ድርጅቶች ነበር።እነዚህ ባለሙያዎችም መረጃን በመመርመር የተሳሳቱ መረጃዎችን እንዲታረሙ እና ተጠያቂነት እንዲሰፍን አስተዋፅኦ ያደርጋሉ። በዚህ መልኩ በዓለም ዙሪያ፣ ሜታ ከ60 በላይ ቋንቋዎችን የሚሸፍን ከ90 በላይ ከሆኑ የእውነታ አጣሪ ድርጅቶች ጋር ይሰራል።
ለአብነትም ሜታ በዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ ከአዣንስ ፍራንስ ፕሬስ፣ ዩኤስኤ ቱዴይ እና የሮይተርስን ከመሳሰሉ ሌሎች ድርጅቶች ጋርም  በመረጃ ማጣራት ላይ ይሰራል።በአፍሪካም «አፍሪካ ቸክ» ከተባለው እውነታ አጣሪ ድርጅት ጋር ይሰራል።

ተመራጩ ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ስልጣናቸውን ከመረከባቸው ጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ በተደረገው የሜታ አዲሱ ፖሊሲ ግን እነዚህን ድርጅቶች በመጠቀም እውነታን ከመፈተሽ ይልቅ ከቀድሞው ትዊተር ከአሁኑ X  ጋር በሚመሳሰል መልኩ ይዘትን ለመፈተሽ "የማህበረሰብ ማስታወሻዎችን" ይጠቀማል።
ከዚህ ለውጥ አንፃር  የሜታ ስልተቀመር  ከባለሙያዎች ይልቅ ተጠቃሚዎች እውነታን እንዲያጣሩ የሚያደርግ ነው። ዶክተር እንዳልክ ይህ ርምጃ የኢትዮጵያን ማኅበረሰብ ችግር ውስጥ ይከታል ይላሉ።

የሜታ አዲሱ ፖሊሲ እውነታን ከመፈተሽ ይልቅ ይዘትን ለመፈተሽ "የማህበረሰብ ማስታወሻዎችን" ይጠቀማል።ምስል፦ Jaap Arriens/NurPhoto/picture alliance

የማህበረሰብ ማስታወሻዎች ውጤታማ ናቸውን?

አንዳንድ ጥናቶች እንደሚያሳዩት የማህበረሰብ ማስታወሻዎች  በኤክስ ገፅ ላይ  የኮቪድ-19ን መረጃ በተመለከተ የተወሰነ ውጤት አሳይተዋል።
ይሁን እንጂ የጥናቱ ናሙና መጠን ትንሽ ነበር እና በተጠቃሚዎች አመለካከት እና ባህሪ ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ በውል አይታወቅም።
ነገር ግን  የጆርናል ኦፍ ኦንላይን ትረስት ኤንድ ሴፍቲ/Journal of Online Trust and Safety/  የ2023 ጥናት እንዳመለከተው ተጠቃሚዎች በፖለቲካ ጉዳዮች ይዘቶችን  ሲገመግሙ መግባባት ላይ ለመድረስ በጣም አስቸጋሪ ነው። 
በ2024 በአምስተርዳም ዩንቨርስቲ መሪነት በአውሮፓ ዩኒቨርስቲዎች የተደረገ ጥናት እንደሚያሳየው አንድ ይዘት በእውነታ አጣሪዎች የተሳሳተ መሆኑ ከተረጋገጠ  ለመረጃ ምንጩ  ፖለቲካዊ ድጋፍ ያለው ሰው ቢሆን እንኳ መረጃውን ውድቅ ሊያደርግ ይችላል። 
እንደ ጥናቱ  ከማኅበረሰብ ማስታወሻ ይልቅ ለውጤታማነት አስፈላጊ የሚሆነው የእውነታ አጣሪዎች ይዘት በመሆኑ፤ የተሳሳተ የመረጃ ምንጭን ለሚደግፉም ጭምር አሳማኝ ሊሆን ይችላል።

የማህበረሰብ ማስታወሻዎች እነማንን ያካትታል?

ለመሆኑ በእነዚህ ባለሙያዎች የተተኩት የሜታ «የማህበረሰብ ማስታወሻዎች» እነማንን ያካትታል? እንዴትስ ነው የሚሰሩት?ለመሆኑ በእነዚህ ባለሙያዎች የተተኩት  የሜታ «የማህበረሰብ ማስታወሻዎች» እነማንን ያካትታል? እንዴትስ ነው የሚሰሩት?
«የማኅበረሰብ ማስታወሻዎች የሚሰጡ ሰዎች «ቮለንቲር» የሆኑ ሰዎች ናቸው።ለምሳሌ ኢትዮጵያ ውስጥ የሆነ ግጭት ተከሰተ እንበል እና የግጭቱ መንስኤ ምንድነው ?የት አካባቢ ነው ?ስንት ስዓት ተጀመረ ?የግጭቱ ተዋናዮች እነማን ናቸው? የሚል ዘገባ ሊቀርብ ይችላል።እና ይህንን ዘገባ አንድ  የማኅበረሰብ ተጠቃሚ የሆነ ሰው ሊፅፍ ይችላል።ያንን ፅሁፍ ትክክለኛ ነው አይለም በሚል ደረጃ ይሰጣሉ።አስተያየት ይሰጣሉ ወይም የ«ላይክ»በማድረግ ሊሆን ይችላል።የግጭቱ መንስኤ ይሄ ነው ።ተዋናዮቹ እነኝህ ናቸው።የተጎዱት ምናምን ብለው ሊዘረዝሩ ይችላል።የማኅበረሰብ ማስታወሻዎች ማለት ተጠቃሚዎች ናቸው።ፌስቡክ ከሆነ የፌስቡክ፣ኢንስታግራም ከሆነ የኢንስታግራም ኤክስ ከሆነ የኤክስ ተጠቃሚዎች ማለት ነው። እና ያንን ግጭት በተመለከተ የሚሰጡት አስተያየት ፣አውድ ዘገባ ነው የማኅበረሰብ ማስታወሻ የሚባለው።» በማለት አብራርተዋል።

ሜታ ከይዘት ክትትል ፖሊሲ ለውጡ ባሻገር በፌስቡክ፣ ኢንስታግራም እና ትሬድን በመሳሰሉ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ መድረኮቹ ላይ የፖለቲካ ይዘቶች ያሏቸው ዜናዎችን ለማሰራጨት ወሳeኗል።ምስል፦ Dado Ruvic/REUTERS

ከዚህ በተጨማሪ በኢትዮጵያም ሆነ በማሊ  የእውነታ አጣሪዎች የፖለቲካ ሁኔታዎችን ሲያጣሩ ችግር እንደሚገጥማቸው በጥናቱ  መስፈሩን አመልክተዋል።እነዚህ ተግዳሮቶች ለበይነመረብ ትንኮሳ፣ የመንግስት የበቀል ስጋት  እና ታማኝ ምንጮችን የማግኘት ውስንነትን ያካትታሉ። 

ከዚህ አንፃር በበጎ ፈቃደኝነት በነፃ  መረጃን ያጣራሉ  የተባሉት ተጠቃሚዎች ወይም የማኅበረሰብ ማስታወሻዎች  ይህን ችግር  ተቋቁቁመው ይሰራሉ ወይ? የሚለውም ሌላው ፈተና መሆኑን አመልክተዋል።ባለሙያው እንደገለፁት የማኅበረሰብ ማስታወሻዎች ማለት የመረጃ መጣረስን ለማስተካከል አውዱን ባገናዘበ መንገድ አስተያየት  ሊሰጥ የሚችል ተጠቃሚ ነው።
ከዚህ አንፃር የማኅበረሰቡ ንቃተ ህሊና ባልዳበረበት እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ሀገራት  በዚህ መልኩ ሊሰራ የሚችል ተጠቃሚ ማግኘት አስቸጋሪ መሆኑን ገልፀዋል።
በሌላ በኩል «የማህበረሰብ ማስታወሻዎች» /community notes/ የሚባለው አዲሱ የይዘት መከታተያ  ስርዓት እንግሊዘኛ የመጀመሪያ ቋንቋ ባልሆነባቸው የብዙ ቋንቋ ተናጋሪ ሀገሮች እንዴት እንደሚሰራ ግልፅ አለመሆኑም የአዲሱ ፖሊሲ ሌላው ክፍተት  መሆኑን ዶክተር እንዳልክ ይናገራሉ።

የማኅበረሰብ ማስታወሻዎች መረጃን ሙያዊ በሆነ መንገድ ከማጣራት ይልቅ በመረጃው ላይ በርካታ ተጠቃሚዎች በሚሰጡት አስተያየት እና ምላሽ ላይ ያተኮረ ነው። በመሆኑም የመረጃው እውነታ የሚወሰነው በዚሁ መንገድ ይሆናል።ይህም ለተሳሳተ መረጃ  እና ለጥላቻ ንግግር መስፋፋት አስተዋፅኦ ያደርጋል የሚል ስጋት አሳድሯል።ከዚህ አንፃር እውነታውን የሚያረጋግጡ ድርጅቶችእና  የዲጂታል መብት ባለሙያዎች የሜታ እርምጃ በበይነመረብ ላይ የጥላቻ ንግግርን የሚያበረታታ እና ከበይነመረብ  ውጭ ደግሞ ሁከትን የሚያባብስ ነው  በሚል የሜታን ውሳኔ እየተቹ ነው። 

በአዲሱ የሜታ ፖሊሲ ተጠቃሚዎች  በበጎ ፈቃደኝነት በነፃ መረጃን እንዲያጣሩ የሚያደርግ ነው ምስል፦ Jaap Arriens/NurPhoto/picture alliance

የሜታ ርምጃ በመረጃ መሠረተ ልማት ላይ አደጋን የሚደቅን ነው

የዓለም አቀፉ የእውነታ አጣሪ  ትስስር በእንግሊዝኛው ምህፃሩ  /IFCN)/ባደረገው ጥናት መሰረት እውነታውን የሚያረጋግጡ ኩባንያዎች ገቢያቸው በሜታ የገንዘብ ድጋፍ በእጅጉ ጥገኛ ናቸው።
በአፍሪካም እንደ «አፍሪካ ቼክ »ያሉ  የእውነታ አጣሪ  ድርጅቶች የሚሰጠው የገንዘብ ድጋፍም ከዋና ዋና የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች በተለይም ከሜታ የሚመጣ ነው።
አዲሱን የሜታ ፖሊሲ ለውጥ አስመልክተው  ዶክተር እንዳል በፃፉት ጦማር እውነታን የማጣራት ውጥኖች  የመገናኛ ብዙሃን ገጽታ ወሳኝ አካላት ሆነው ቆይተዋል። በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ሀገሮች ለሀገር ውስጥ የመገናኛ ብዙሃን  ሥነ-ምህዳር ወሳኝ አስተዋፅዖ አላቸው።እንደ ባለሙያው  በኢትዮጵያ  በአማርኛ  ፣በኦሮምኛ እና በትግርኛ ቋንቋዎች እውነታወችን የማጣራት ውጥን  የነበረ ቢሆንም፤ተደራሽነት እና ውጤታማነታቸው በቋንቋ  እና በገንዘብ ውሱኑነት የተገደበ ነበር።
በቅርቡ ሜታ እነዚህን የእውነታ ማጣራት ውጥኖች መደገፉን ማቆሙ ደግሞ በመረጃ መሠረተ ልማት ላይ አደጋን የሚደቅን ነው። ለዚህም በግጭት ወቅት በኢትዮጵያ እና በማሊ ያለውን እውነታ የማጣራት አሰራርን የመረመረ አንድ የቅርብ ጊዜ ጥናትን በዋቢነት ይጠቅሳሉ።

የዲጂታል መብቶች ባለሙያዎች ምን ይላሉ?

የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ቮልከር ቱርክ  በበይነመረብ የጥላቻ ንግግርን እና ጎጂ ይዘትን መፍቀድ በገሃዱ ዓለም አሉታዊ ውጤት አለው ሲሉ የሜታን ውሳኔ ተችተዋል። ይዘትን መቆጣጠር ሳንሱር አይደለምም ብለዋል።
የኤሌክትሮኒክስ ፍሮንትየር ፋውንዴሽን የተባለው የዲጂታል መብቶች ድርጅት በበኩሉየማህበረሰብ ማስታወሻዎች ጠቃሚ ሊሆኑ ቢችሉም የባለሙያዎች ስራ ግን  አስፈላጊ ነው ብሏል።
ከዚህ አንፃር ሜታ የእውነታ አጣሪዎችን እንደ አንድ አስፈላጊ መሳሪያ መመልከቱን እንደሚቀጥል ተስፋ እናደርጋለን" ብሏል ድርጅቱ።
ሜታ አንዱን ስርዓት ለማካተት ሌላውን ማግለል ተገቢ አለመሆኑንም ድርጅቱ አመልክቷል።
ሌሎች ባለሙያዎች  በበኩላቸው በሳይንስ እና ጤና ላይ የተዛባ መረጃ በሜታ መድረኮች ላይ ሊጨምር እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።
እንደ ኢትዮጵያ ባሉ የሴቶች የበይነመረብ ትንኮሳ በበዛበት ሀገርም ችግሩ የበለጠ እንዲስፋፋ የሚያደርግ ነው።በስደተኞች እና በህዳጣን ላይ ፖሊሲው የሚያስከትለው መዘዝም ቀላል አለመሆኑን ባለሙያው ያብራራሉ።
ባለሙያው እንደሚሉት እነዚህ የቴክኖሎጅ ኩባንያዎቹ ትልቅ ሀብት እና አቅም ያላቸው በመሆኑ፤የሚያደርሱትን ችግር ለመፍታት ሰፊ ፣ውስብስብ እና ብዙ ተዋናዮችን የሚያሳትፍ መፍትሄ የሚፈልግ ነው።ያምሆኖ ማኅበረሰቡ ራሱን ከሀሰተኛ መረጃ መከላከል፣ በመንግስታት በኩልም ድርጅቶቹን ተጠያቂ ማድረግ፣አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል።

ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።

ፀሐይ ጫኔ
ማንተጋፍቶት ስለሺ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ
ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW