የምሁራን ውይይት በባሕር ዳር
ሐሙስ፣ ነሐሴ 15 2017
ከ200 በላይ የዩኒቨርሲቲ ምሁራን በባሕር ዳር ተወያይተዋል
የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ባዘጋጀው መድርክ ላይ ከ10ሩም የአማራ ክልል ዩኒቨርሲቲዎች የተውጣጡ 200 ያክል ምሁራን የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ተግባሩን በተሟላ ሁኔታ መፈጸም በሚችልበት ሁኔታ እስካሁን ወደ ምክክር ያልመጡ የፖለቲካ ድርጅቶችንና ሌሎች ኃይሎችን ወደ ምክክሩ ለማምጣት "የምሁራን ሚና ምን መሆን አለበት”? በሚለው ዙሪያ ነሐሴ 14 እና 15 ቀን 2017 ዓ.ም. በባሕር ዳር ውይይት አድርገዋል።
የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር) በምሁራን እውቀትና የምርምር ሥራ የታገዘ አስተያየት ለኮሚሽኑ ጠቃሚ መሆኑን ተናግረዋል።
እውቅት መር ሀሳቦች ለኮሚሽኑ ያስፈልጋሉ” ዶ/ር ዮናስ አዳዬ
የመድረኩን አስፈላጊነትም ሲያብራሩ፤ «...እውቀት መር የሆኑ ሀሳቦችንለኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ስኬት ከምሁራን ግብዓት ለመሰብሰብ ነው፣ ሀሳብ ከምንስበስብባቸው መንገዶች አንዱ የምርምር ውጤቶችን ማግኘት ነው፣ በምክክሩ ያልተሳተፉ ወገኖቻችን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሊሆኑ ይችላሉ፣ በግጭት ውስጥ ያሉ ወገኖቻችን ሊሆኑ ይችላሉ፣ እነኚህን ወገኖች በእናንተ (በምሁራን) አማካኝነት ለመድረስ ነው»” ብለዋል። ይህ የሚደረገው የኮሚሽኑ ጥረት እንዳል መሆኑን ያመለከቱት ዶ/ር ዮናስ፣ ምክክር አካታች በመሆኑ በአሁኑ ሰዓት ወደ ምክክሩ ያልመጡ አካላት እንዲመጡ የምሁራን ሚና ከፍተኛ መሆኑን ነው ያስረዱት።
«ታሪክን ማወቅ የታመመ አእምሮን ይፈውሳል»
The study of history is the best medicine for sick mind፣ «ታሪክን ማወቅ የታመመ አእምሮን ይፈውሳል» የሚለውን የታይተስ ሊቬየስን ድንቅ አባባል ያስታወሱት የደብረ ብርሐን ዩኒቨርሲት መምህር ዶ/ር ዘመነ ወርቅ፣ በአገሪቱ ስር የሰደደውን የታሪክ መዛባት ወደ ተቀራረበ ሀሳብ ለማምጣት የታሪክ ምሁራን በብሔራዊ ደረጃ በጋራ ሊወያዩ እንደሚገባ አመልክተዋል።
የዶ/ር ዘመነን ሀሳብ የሚጋሩት ታደሰ አምሳሉ የተባሉ ምሁር በየክልሉ ያሉ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምሁራን በጋራ ሊወያዩና ወጥ መረዳት ሊኖር ይገባል ነው ያሉት። ምሁራንን በዚህ መልኩ ለማወያየት ኮሚሽኑ ዘግይቷል በማለት የተቹት እኚህ ምሁር በአገሪቱ ከሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች የተውጣጡ ምሁራን የተሳሳት ወይም ያልተሳሳት እየተባለ ውሉ የጠፋበትን «ትርክት» ኅብረተሰቡ ወጥ የሆነ አረዳድ እንዲኖረውሊያደርጉ እንደሚገባ ነው የገለጡት።
ውይይት ለችግሮች ሁሉ መፍቻ ቁልፍ ስለመሆኑ
ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የመጡት እንዳላማው አራጌ በበኩላቸው ለሁሉም ነገር በእውነት ላይ የተመሰረተ ውይይት ቅድሚያ ሊሰጠው እንደሚገባ ነው አስተያየት የሰጡት። «የነፃነት አብዮት የሚጀምረው የእውነትን አብዮት በመቀስቀስ ነው» ብለዋል። አክለውም፣ ጽኑና ብልህ የሆነ ማኅበረሰብ የነፃነትን ትግል የሚጀምረውሰለ ነፃነትና ስለእውነት አበክሮ ለማወቅ ሲችል እንደሆነ ነው የተናገሩት።
«በአማራ ክልል 6000 ሰዎች በአጀንዳ መረጣ ተሳትፈዋል» አገራዊ ምክክር ኮሚሽን
በአማራ ክልል በባሕር ዳር ከተማ ከመጋቢት 27 እስከ ሚያዝያ 4 ቀን 2017 ዓ.ም. በነበረው የምክክር መድረክ ከክልሉ 263 ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች የተመረጡ ከነዋሪዎች ከማኅበራት፣ ከፖለቲካ ድርጅቶች፣ ከሃይማኖት ተቋማት፣ ከተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች፣ ከተፈናቃዮች፣ ከአካለል ጉዳተኞችና ከሌሎችም አካላት የተወከሉ፣ በአጠቃላይ ከ6000 በላይ ተሳታፊዎች የአጃንዳ መረጣና በብሔራዊ ደረጃ የሚወከሉ ተሳታፊዎች መምረጣቸውን መዘገባችን ይታወሳል።
ዓለምነው መኮንን
ሸዋዬ ለገሠ
ታምራት ዲንሳ