የምላጂች መያዝ ና የስርብያ የወደፊት ዕጣ
ማክሰኞ፣ ግንቦት 23 2003ምላዲች ከተከሰሱባቸው ውስጥ 11 የጦርና ሁለት የዘር ማጥፋት ወንጀሎች ይገኙበታል ። ከዛሬ 16 ዓመታት ወዲህ ፣ የስሬብሬኒስካ ከተማ እና የርሳቸው ስም ተነጣጥለው አያውቁም ። የጀነራል ራትኮ ምላጂች ስም ሲነሳ ስሬብሪኒስካም አትቀርም ።
ምላጂች በዚህች ከተማ እ.ጎ.አ በ 1995 በቦስኒያ ሙስሊሞች ላይ የተካሄደውን አስከፊ ጭፍጨፋ ጨምሮ ሌሌች የጦር ወንጀሎችን በማቀድና በማስፈፀም ዓለም ዓቀፉ የጦር ወንጀለኞች መዳኛ ፍርድ በጦር ወንጀለኝነት ሲያድናቸው የቆየ ጀነራል ናቸው ። በስሬብሬኒስካ በርሳቸው የጦር አዛዥነት የሰርብ ጦር ከ8 ሺህ በላይ ሙስሊም ወንዶችን በመጨፍጨፍ ይወነጀላሉ ። ከዚህ በተጨማሪም በክሮኤሽያ በተፈፀሙ የጦር ወንጀሎችና የቦስኒያን መዲና ሳራዮቮን ከ 3 ዓመት ተኩል በላይ ከበው በማስጨነቅም የሄጉ ፍርድ ቤት ተጠያቂ ያደርጋቸዋል ። በነዚህ ተደራራቢ ወንጀሎች የሚፈለጉት ጀነራል ራትኮ ምላጂች የመያዛቸው ዜና ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ይፋ እንደሆነ ልዩ ልዩ አስተያየቶችን አስከትሏል ። የምላዲች መያዝ ለአውሮፓ አዲስ ምዕራፍ የከፈተ እና ቤልግሬድም በአውሮፓ ህብረት እንድትታቀፍ ማድረግ የሚያስችል አንድ ትልቅ እርምጃ ተብሎ ሲወሰድ በሀገር ውስጥ ደግሞ ተቃውሞ ቀስቅሷል ። የቀድሞ የሰርብ ጦር አዛዥ ራትኮ ምላዲች መያዝ ያስከተላቸው እነዚህ ሁለት የሚቃረኑ ሁነቶች እንዴት ይታያሉ ? በወደፊቱ የሰርቢያ የፖለቲካ አካሄድ ላይስ ምን ዓይነት ተፅዕኖ ያሳድሩ ይሆን ? ለፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩ ዶክተር ለማ ይፍራሸዋ ያነሳኋቸው ጥያቄዎች ናቸው ።
ሂሩት መለሰ
ነጋሽ መሐመድ