1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የግብጽ እና ሱዳን ሰሞነኛ እንቅስቃሴ ትኩረት ስቧል

ማክሰኞ፣ ጥር 8 2010

የግብጽ ፕሬዘዳንት አብዱል ፈታህ ኤል ሲሲ ባለፈው ሰኞ የኤርትራ ፕሬዘዳንት ኢሳያስ አፈወርቂን በካይሮ አስተናገዱ። የኢትዮጵያዊው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ ደግሞ ይፋዊ ጉብኝት ለማድረግ የፊታችን ረቡዕ ወደ ግብጽ ያመራሉ። በሶስት ቀናት ቆይታቸውም በሀገሪቱ ፓርላማ ንግግር እንደሚያደርጉ ተዘግቧል።

Erdogan zu Besuch im Sudan
ምስል picture-alliance/dpa/Y. Bulbul

የግብጽ እና ሱዳን ሰሞነኛ እንቅስቃሴ ትኩረት ስቧል

This browser does not support the audio element.

የኢትዮጵያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ባለፈው ሳምንት ኳታር፤ ሰሞኑን ደግሞ ሱዳን ነበሩ፡፡ የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ የመካከለኛው ምስራቅ አማካሪ የሆኑት የቀድሞው የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ስዩም መስፍን ባለፈው ሳምንት ሳዑዲ አረቢያ መልዕክት ለማድረስ በሚል መጥተው ነበር፡፡
የሱዳንም ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም በቅርቡ አዲስ አበባላይ ታይተዋል፡፡ የዜና አውታሮች እንደሚዘግቡት ከሆነ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ስራው እየተገባደደ መሄድ የግብጽ ባለስልጣናትን የልብ ምት ጨምሮታል፡፡ 

ሰሜናዊ አፍሪካ እና አንዳንድ የመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት በአረብ አብዮት  ቁም ስቅላቸውን በሚያዩበት ወቅት  ነበር ኢትዮጵያ በታላቁ የአባይ ወንዝ ላይ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ያለችውን የሃል ማመንጫ መርሃ ግብር ይፋ ያደረገችው፡፡ የፖለቲካ ተንታኞችም በኢትዮጵያ ታላቁ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ የተለያዩ አመለካከቶችን አንጸባረቁ ገሚሶቹ የኢትዮጵያ መንግስት ግብጽን ያጥለቀለቀው ህዝባዊ አመጽ ወላፈኑ እንዳይደርስበት ማስቀየሻ ሲሉት ሌሎች ደግሞ የኢትዮጵያ መንግስት የግብጽን መዳከም አይቶ የጀመረው የተቀደሰ ሀሳብ አድርገው ተመለከቱት ፡፡ የወቅቱ ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ ግን የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ቢገባቸው እንደራሳቸው ሁሉ ሊደግፉት ይገባ ነበር ነው ያሉት።

የሙስሊም ወንድማማቾች ጽንሰ ሃሳብ አራማጆች በግብጽ ከፍተኛ ስልጣን መያዝ ቱርክን እና መሪዋን ኤርዶሃንን የመሰሉ መሪዎችንም ሆነ አንዳንድ ሀገሮችን ሲያስፈነድቅ ሳዑዲንም ሆነ አጋሮቿን ደግሞ ሃሳብ ላይ ጣላቸው ፡፡ የአሜሪካም ድጋፍ ተጨምሮበት የፕሬዘዳንት ሙርሲ መንግስት በግብጽ እድሜው ባጭር ተቀጨ፡፡ መራሔ መንግስትነቱን የተረከቡት ፕሬዘዳንት ኤል ሲሲ መንገዳቸውን ከሳዑዲም ሆነ ከአሜሪካ አንጻር ቃኝተው መጓዝ ጀመሩ፡፡ ሀገር የመገንባት እና የማረጋጋት ተግባራቸውን ባንድ በኩል የኢትዮጵያን ታላቁን የህዳሴ ግድብ ግንባታ ሂደት የመቆጣጠር ተግባራቸውን በሌላ በኩል አጧጧፉት፡፡

ምስል Ashraf Shazly/AFP/Getty Images

ኤል ሲሲ የህዳሴውን ግድብ ቢቻል ለማስቆም ባይቻል የሀገራቸው ስጋት በማይሆን መልኩ እንዲከናወን ለማድረግ ግብጽ እና መሪዎቿ ያልፈነቀሉት ድንጋይ የለም፡፡ ይሁንና ኢትዮጵያም በአቋሟ እንደጸናች የግድቡ ግንባታም ከ60 በመቶ በላይ ደረሰ ፡፡ ኢትዮጵያ በዚህ ሁሉ ዓመታት ያላት የኤሌክትሪክ ሃይል ከ4000 ሜጋ ዋት አይበልጥም ነገር ግን ግብጽ ከተለያዩ የሃይል ምንጮች ከ24 ሺህ ሜጋዋት በላይ የኤሌክትሪክ ሃይል ታመነጫለች፡፡ 99 ከመቶ ህዝቧም የኤሌክትሪክ አገልግሎት አግኝቷል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ነው የመካከለኛው ምስራቅ እና የአፍሪካ ቀንድ ፖለቲካ የባሰ ምስቅልቅሉ መውጣት የጀመረው ፡፡ ከሳዑዲ መራሹ የሱኒ ዓረብ ጎራ የተገፋሁ ስሜት ያዘለችው ቱጃሯ ግን ትንሷ ሀገር ቃጣር ግብጽን ለማስቆጣት በሚመስል የኢትዮጵያን ህዳሴ ግድብ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ስትደግፍ ቱርክ እና ሱዳንም በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ለግብጽ ፍላጎት በተቃራኒ ቆመዋል ፡፡

ኢትዮጵያና 100 ሚሊዮን ህዝቦቿ ባይተዋር በሆኑበት የቀይ ባህር መስመር ባሉ ግዛቶች ወታደራዊ የጦር ሰፈር ለማቋቋምም ሆነ የጦር ጀት ተሸካሚ መርከቦቻቸውን ወደ ቀጠናው ለማስገባት የብዙ ሀገራት መንግስታት ረጅም መንገድ ተጉዘዋል፡፡ አቶ ኤሊያስ ባህራን እንደሚሉት ቀይ ባህር ላይ ከሰሜን ስዊዝ ካናል እስከ ደቡብ ባብ ኤል መንደብ ያለው ክፍል ዋነኛ ከሚባሉ የአለም የባህር ላይ መተላለፊያዎች አንዱ ነው፡፡

ለረጅም ዘመን የግብጽ አጋር ሆና የኖረችው ሱዳን ደግሞ ከግብጽም ሆነ ከአረቡ አለም የሙሉ ጊዘ አገልጋይነት የተላቀቀች ይመስላል ፡፡ ሱዳን በኢትዮጵያው ታላቁ የህዳሴ ግድብ ዙሪያ ከግብጻዊው አስተሳሰብ አፈንግጣ ወደ ኢትዮጵያ ጎራ ከመቀላቀሏም በላይ ከግብጽ ጋር ያላትን የድንበር ይገባኛል ጥያቄ አብይ ጉዳይ እያደረገችው ትገኛለች ፡፡  በኤል ሲሲ መራሹ የግብጽ መንግስት  ደስተኛ ያልሆኑትንም የቱርኩን ፕሬዘዳንት ጠይብ ኤርዶጋን በጥንታዊው የኦቶማን ቱርክ ዘመን በቀይ ባህር ላይ የኦቶማን ቱርክ ርዕሰ መዲና የነበረችውን የሱኪ ደሴት እንዲያለሙ አስረክባቸዋለች ፡፡ ሱኪ ከሳዑዲ ዓረቢያዋ የመካ ከተማ በ 60 ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ የምትገን እንደመሆኗ ለሳዑዲም ሆነ ለሳዑዲ መራሹ የአረብ ሱኒ ጎራ ስጋት የሚፈጥር ነው ፡፡የሱዳን ያአቋም ለውጥ ያሳሰባት ግብጽ  በኤርትራ ግዛት የጦር ኃይል ማስፈሯን መገናኛ ብዙሃን እየዘገቡ ናቸው ፡፡ የኤርትራው የማስታወቂያ ሚንስትር የማነ ገብረመስቀል ቢያስተባብሉትም አልጀዚራ ግብጽ በኤርትራ የምታደርገውን ወታደራዊእንቅስቃሴ ይፋ አድርጎታል፡፡ ይህንን ተከትሎም የሱዳን መንግስት በኤርትራ አዋሳኝ ድንበሮቿን መዝጋቷም ሆነ የጦር ሰራዊቷን ተጠንቀቅ ማለቷ እየተዘገበ ይገኛል፡፡ ሱዳን በግብጽ የሚገኙትን አምባሳደሯን በመጥራት ውይይት ማድረጓም ተዘግቧል፡፡ የግብጽ መንግስት ደጋፊ የሆኑ ካይሮ የሚገኙ መገናኛ ብዙሃንም ሱዳንን የግብጽ ባላንጣ ከሆኑት ቱርክና ቃጣር ጋር በማበር በግብጽ ላይ የተነሳች በማለት እየወነጀሏት ናቸው፡፡

ምስል picture alliance/abaca/K. Ozer

ይህ በእንዲህ እንዳለም የታላቁ ህዳሴ ግድብ የፍጻሜ ጉዞም ሆነ የሱዳን መንግስት እንቅስቃሴ ያሳሰበው ወይንም ያላማረው የግብጽ መንግስት የጦር ኃይሉን የኢትዮጵያም ሆነ የሱዳን አጎራባች ወደ ሆነችው ኤርትራ እንዳስገባ መገናኛ ብዙሃን መዘገብ ጀመሩ ፡፡ አቶ ቢንያም እንደሚሉት የቀድሞው ጀነራል ኤል ሲሲ መንግስት ምናልባት በአንድ ድንጋይ ሶስት ወፍ የመግደል ሃሳብ ይኖራቸው ይሆናል፡፡ የምስራቅ አፍሪካ የፖለቲካ ተንታኝ የሆኑት ማርቲን ፕላውት እንደሚሉት በኢትዮጵያ እና በግብጽ መካከል አንድ ችግር ሲኖር ነጸብራቁ ኤርትራ ውስጥ መታየቱ ጥንትም የነበረ ነው ይላሉ ፡፡

አቶ ኤሊያስ ባህራን በበኩላቸው የታላቁ የህዳሴ ግድብም ሆነ የውኃው ፖለቲካ በምንም ዓይነት ወደ ቀጥተኛ ወታደራዊ ግብ ግብ አይገባም ባይ ናቸው፡፡ የቀጠናው ሀገሮች የውጭ ጉዳይ እና የመከላከያ ሚንስትሮች ተከታታይ ጉብኝቶችን ከየትኛውም ጊዜ በላይ ማድረጋቸው፣ ለታሪክ ባለሙያው አቶ አለማየሁ ሸዋ የሁለተኛውን የዓለም ጦርነት ዋዜማ የሚያስታውስ ነው፡፡

አቶ ኤሊያስ እንደሚያስታውሱት የዛሬ ሁለት ዓመት በግብጾ የሻርም አል ሼክ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ ሲናገሩ እኔ እና ኤል ሲሲ በበአባይ ወንዝ በጋራ እንዋኛለን እንጂ አንሰምጥም ብለው ነበር፡፡ «ኢትዮጵያና ግብጽ በዓባይ ወንዝ በጋራ ይዋኙ ይሆን ወይንስ ተያይዘው ይሰምጣሉ?» የሚለውን ለጊዜ እንተወው።

ስለሺ ሽብሩ

አርያም ተክሌ


 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW