1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የምሥራቅ ኮንጎ ሠላምና የአካባቢዉ ሕዝብ

ሐሙስ፣ ኅዳር 5 2006

ኮብለር የሌሎች አማፂ ቡድናት አባላትም ትጥቃቸዉን እንዲፈቱ ጠይቀዋል።ትጥቅ ካልፈቱ ግን ዓለም አቀፉ ጦር በሐይል እንደሚያስፈታቸዉ ዝተዋል።ይሁንና የኪንሻሳና የካምፓላ ባለሥልጣናት አዲስ እሰጥ አገባ መግጠማቸዉ ምሥራቃዊ ኮንጎ «ዘላቂ ሠላም» ለማስፈን የተለፋዉን ሁሉ መና እንዳያስቀረዉ እያሰጋ ነዉ።

Auf dem ild: Links: Edward Mwangachuchu, Abgeordneter, Vorsitzender der CNDP (Congres National pour la Défense du Peuple) Mitte: Mashako Mamba, Abgeordneter Rechts: Francois Ruchogota, Generalsekretär, Führer der M23-Delegation Kampala, Uganda 4.2.2013 Foto: John Kanyunyu / DW
ያልተሳካዉ ድርድርምስል DW/J.Kanyunyu

የኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ መንግሥት በቅርቡ የተሸነፈዉን የM 23 አማፂ ቡድን አባላት ትጥቅ የሚፈቱ፥ የሚበተኑበት እና ከመንግሥት ጦር ጋር የሚቀየጡበትን ግልፅ ሥልት እንዲከተል የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠየቀ።የኮንጎ መንግሥት ለዚሑ ዓለማ ከM23 ጋር ሊያደርገዉ የነበረዉን ሥምምነት እንደማይፈርም አስታዉቆ ዩጋንዳ ዉስጥ የሚደረገዉን ድርድር አቋርጧል። የምሥራቃዊ ኮንጎ ሕዝብ የኪንሻ መንግሥት አቋምን በመደገፍ ደስታዉን እየገለጠ ነዉ።የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ልዩ መልዕክተኛ አብደላሕ ዋፊይ እንደሚሉት ግን የአማፂዉ ቡድን አባላት ትጥቅ ፈተዉ ከሕብረተሰቡ ወይም ከጦሩ ጋር ካልተቀየጡ ዘላቂ ሠላም ማስፈን አይቻልም።


የኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊ መንግሥት ጦር ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጦር ጋር ግንባር ፈጥሮ M23ን ዳግም በማያንሠራራበት ደረጃ ድባቅ መቶታል።ከጦር ሐይሉ ድል በኋላ የአማፂዉ ቡድን አባላት የወደፊት እጣ ፈንታ ይወስናል የተባለዉን ሥምምነት የድል ብሥራት ፌስታ-ፈንጠዚያዉ ያልበረደለት የኪንሻ መንግሥት ዉድቅ አድርጎታል።እንዲያዉም የኪንሻ ባለሥልጣናት በያዝነዉ ሳምንት ይፈረማል ተብሎ ይጠበቅ የነበረዉን ዉል ዉድቅ ያደረጉት «የዩጋንዳ አደራዳሪዎች ተፅዕኖ ሥላበዙብን» በማለት የካምፓላ አቻዎቻቸዉን ወቅሰዋል።

አከርካሬዉ ተሰብሮ የተበታተነዉ አማፂ ቡድን M23 በጣሙን በሩዋንዳ፥ በመጠኑም ቢሆን በዩጋንዳ እንደሚረዳ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በተለያየ ጊዜ አስታዉቆ ነበር።በዚሕም ሰበብ የኪንሻ መንግሥት የካምፓላዉን ድርድር አቋርጦ ለመዉጣቱ ዩጋንዳዎችን መዉቀሱን ብዙዎች ከምር ተቀብለዉታል።

M23 የተመሠረተ፥ የመሸገ፥ የተንቀሳቀሰበት እና አሁን በቅርቡ የተደመሠሠበት የምሥራቃዊ ኮንጎ ነዋሪ ሕዝብ ደግሞ የመንግሥቱን ወቀሳ-ዉንጀላን ከመቀበልም አልፎ ስምምነቱ ባለመፈረሙ፥ የዶቸ ቬለዉ ዘጋቢ ጋየ ኮቬነ እንደታዘበዉ፥ እንደ ዳግማዊ ድል ነዉ የተደሰተዉ።

«የመንግሥት መልዕክተኞች የካምዓላዉን ሥምምነት አንፈርምም በማለታቸዉ የምሥራቅ ኮንጎ ሕዝብ ደስ ብሎታል።እዚሕ ጎማ ዉስጥ-በተለይ፥ የመንግሥት ወታደሮች ሚንስቶች የባለቤቶቻቸዉ ጀግንነት ለማድነቅና ድሉን ለመደገፍ ሠልፍ ወጥተዉም ነበር።ሠልፈኞቹም ሆኑ ሌሎቹ ነዋሪዎች መንግሥት ትክክለኛዉን ይዘት በቅጡ ሳይመረምር ዉል እንደይፈራረም ጠይቀዋል።»

የኮንጎን ጦር ለድል ያበቀዉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባለሥልጣናት ግን የጦር ሜዳዉ ድል በሠላም ዉል ካልፀነ ባካባቢዉ ዘላቂ ሠላም ማስፈን አይቻልም ባይ ናቸዉ።በኮንጎ የዋና ፀሐፊ ፓን ጊ ሙን ልዩ መልዕክተኛ አብደላሕ ዋፊይ እንደሚሉት የኪንሻ መንግሥት የአማፂዉ ቡድን አባላት ትጥቅ ፈተዉ ሲሆን ከጦሩ፥ ይሕ ካልሆነም ከሠላማዊዉ ሕዝብ የሚቀየጡበትን ሥልት መቀየስ አለበት።

የአማፂዉ ቡድን አባላት ትጥቃቸዉን ፈተዉ ከማዕከላዊዉ መንግሥት ጦር ወይም ከሕብረተሰቡ ካልተቀየጡ ዋፊይ እንደሚሉት በኪቩ (ምሥራቃዊ ኮንጎ) ሠላም ማስፈን አይቻልም።ከዚሕ ያደርሳል የተባለዉን የካምፓላዉን ሥምምነትን የኪንሻ መንግሥት ዉድቅ ማድረጉ ከተሰማ በሕዋላ ምሥራቃዊ ኮንጎ ግጭት ተከስቷል የሚል ዘገባ ተሰራጭቶ ነበር።ኮንጎ የሠፈረዉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጦር (MONUSCO) የበላይ ማርቲን ኮብለር ወሬዉን ሐሰት ብለዉታል።

«ሥለዚሕ ነገር ምንም አይነት መረጃ የለኝም።ዛሬ ራሱ ጦር ግንባር ነበርኩ።ከጦሩ አዛዥ ጋር ተነጋግሬያለሁ።ሥለ ሁኔታዉ ምንም የሚታወቅ ነገር የለም።የሲቢል ማሕበረሰቡም ያወጣዉ መግለጫ፥ የለም።ሞኑስኮም ምንም አይነት መረጃ የለዉም።»

ኮብለር የሌሎች አማፂ ቡድናት አባላትም ትጥቃቸዉን እንዲፈቱ ጠይቀዋል።ትጥቅ ካልፈቱ ግን ዓለም አቀፉ ጦር በሐይል እንደሚያስፈታቸዉ ዝተዋል።ይሁንና ከM 23 ጋር ይፈረማል ተብሎ የነበረዉ ሥምምነት ባለመፈረሙ የኪንሻሳና የካምፓላ ባለሥልጣናት አዲስ እሰጥ አገባ መግጠማቸዉ ምሥራቃዊ ኮንጎ «ዘላቂ ሠላም» ለማስፈን የተለፋዉን ሁሉ መና እንዳያስቀረዉ እያሰጋ ነዉ።

ምስል Phil Moore/AFP/GettyImages
የቀድሞዉ አማፂምስል picture-alliance/dpa
ኮብለርምስል Junior D.KannahAFP/Getty Images)

ነጋሽ መሐመድ

አርያም ተክሌ




ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW