1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የምርቶች ዋጋ ጭማሪ በአዲስ አበባ

ዓርብ፣ ሐምሌ 26 2016

ሰሞነኛውን የኢኮኖሚ ማሻሻያ ተከትሎ መዲናዋ አዲስ አበባ ውስጥ የዕለት ፍጆታ ምርቶች ላይ የጎላ የዋጋ ጭማሪ እየተደረገ ነው በማለት ነዋሪዎች አማረሩ። ነጋዴዎች በፊናቸው በቀጣይ ብር የበለጠ የሚዳከም ከሆነ የምርቶች ዋጋ ይጨምራል በሚል ምርቶችን የመያዝ አዝማሚያ እያሳዩ ነው ተብሏል።

ፎቶ ከማኅደር፤ አዲስ አበባ የገበያ አዳራሽ
ሮይተርስ እንደዘገበው የዋጋ ጭማሪ ከታየባቸው ሸቀጦች ዘይት እና ሩዝ ቀዳሚዎቹ ናቸው። ፎቶ ከማኅደር፤ አዲስ አበባ የምግብ ሸቀጣሸቀጥ የገበያ አዳራሽምስል Seyoum Getu/DW

የምርቶች ዋጋ ጭማሪ በአዲስ አበባ

This browser does not support the audio element.

 

«በአዲስ አበባ ውስጥ ባለሱቆችና አከፋፋዮች ከአንድ ሁለት ዓመት በፊት ገዝተው በመጋዘናቸው ያከማቹትን ሁላ ነው አሁን ትናንት ስለዶላር ተነሳ ብለው ዕቃ እያስወደዱብን ያሉት» አስተያየታቸውን ለዶቼ ቬለ የሰጡ አንድ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ የተናገሩት።

በዋጋ ጭማሪው የነዋሪዎች ስጋት

ከሰሞኑየኢትዮጵያ መንግሥት በወሰደው የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲ ውስጥየዓለም አቀፍ መገበያያ ገንዘቦች ከብር አንጻር ያላቸው የምንዛሪ ዋጋ በነጻ ገበያ እንዲመራ መወሰኑን ተከትሎ የብር የመግዛት አቅም ከ30 በመቶ በላይ ተዳክሟል። ይህን ውሳኔ ተከትሎም በከፍተኛ ሕዝብ ቁጥር በምትጨናነቀው መዲናዋ አዲስ አበባ ውስጥ በርካታ የምግብ ፍጆታ ዕቃዎች ላይ የዋጋ ጭማሪ ታይቷል። በዚህ የተደናገጡ የመዲናዋ ነዋሪዎችም ከወዲሁ እያስተዋሉ ባሉት የዋጋ ጭማሪዎች ግሽበቱ ከዚህ ከነበረበት ደረጃ እንዳይከፋም ሰግተዋል። «በማንኛውም ሸቀጣ ሸቀጥ ላይ ጨመር አድርገዋል ነጋዴዎቹ። አሁን ስኳር ዱቄት እንደዚህ ያሉ መሠረታዊ ነገሮች ጨምረዋል። ይህ ደግሞ የየዕለት ፍጆታችን ነውና ሕዝቡ እንዴት እንደሚኖር ያስቸግራል» ነው ያሉት።

የብር መዳከም ነጋደዎች ላይ ያሳደረው ጫና

ስማቸውንና የተሰማሩበትን የሥራ ዘርፍ ሳይገልጹ አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡ በአዲስ አበባ ውስጥ በንግድ ላይ ተሰማርተው የሚገኙ ነጋዴ ደግሞ አሁን የበርካታ ነጋዴዎች እርምጃ ዋጋ ጨምሮ ከመሸጥም በላይ ምርት ይዞ የመቆየት ተግባር ይስተዋላል ነው የሚሉት። ይህም ምናልባትም በቀጣይ የበለጠ ብር እየተዳከመ የሚሄድ ከሆነ የዋጋ ጭማሪው ከፍ ሊል ይችላልበሚል ግምት እንደሆነም ተናግረዋል። «የሚሸጠው ሰው አሁን ዶላር ስለጨመረ ብሩ ልወርድብኝ ይችላል በሚል ያለውን ይዞ የመቆም ሁኔታ ነው ያለው። ምርቶችን ለማቅረብ ተስማሙም ውሉን የማፍረስ ነው እንጂ መሸጡ ላይ ብዙም እንቅስቃሴ የለም አሁን። የዶላሩ ነገር ነገ ምን እንደሚሆን ስለማይታወቅ መቆም ነገር አለ። ከፍ ይላል የሚል ፍራቻ ስላለ ሁለት ሳምንት ወይም አንድ ወር ገደማ እንየው የሚል አዝማሚያ አለ» ነው ያሉት።

ሸማቹ ማኅበረሰብ ምናልባትም ወደፊት የዋጋው ጭማሪ እየከፋ ልሄድ ስለሚችል የመግዛት ፍላጎቱ ጎልቶ አቅርቦት ላይ ደግሞ ነጋዴዎች ምርት የሚይዙ ከሆነ የገበያው ስርዓቱ የበለጠ እንዳይበላሽም ስጋት አለ።

ከሰሞኑ የኢትዮጵያ መንግሥት በወሰደው የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲ ውስጥ የዓለም አቀፍ መገበያያ ገንዘቦች ከብር አንጻር ያላቸው የምንዛሪ ዋጋ በነጻ ገበያ እንዲመራ መወሰኑን ተከትሎ የብር የመግዛት አቅም ከ30 በመቶ በላይ ተዳክሟል።ፎቶ ከማኅደር፤ የገበያ ስፍራ አዲስ አበባ ምስል Seyoum Getu/DW

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መንግስት እርምጃ

መንግሥት የሰሞነኛውን የኢኮኖሚ ማሻሻያ ተከትሎ እየተስተዋለ ያለውን የገበያ አለመረጋጋት ለማስተካከል እርምጃዎች ይወሰዳሉ ይላል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድም ትናንት ከፋይናንስ ተቋማት ተወካዮችና ባለድርሻ አካላት ጋር ስወያዩ «ስግብግብ» ያሏቸው ነጋዴዎች ላይ በቀጣይ ከወትሮ የተለየ ጥብቅ ቁጥጥር ይደረጋል ብለዋል።

ዛሬ አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡ የአዲስ አበባ ከተማ ንግድ ቢሮ ኃላፊ አቶ ቢንያም ምክሩ የነጋዴዎች የምርት ዋጋ ጭማሪው በጉልህ መታየቱን አረጋግጠው፤ ድርጊቱ ተቀባይነት የሌለው ነው በማለት የዋጋ ጭማሪው ምክንያታዊ አለመሆኑን አስረድተዋል። ኃላፊው ይህንኑን ለመቆጣጠር እስከ ትናት ከ150 በላይ የችርቻሮና ጅምላ ንግድ መደብሮች መታሸጋቸውን አስረድተዋል። «ሰሞነኛውን የኢኮኖሚ ማሻሻያ ይፋ መሆኑን ተከትሎ በከተማው የተስተዋለው የዋጋ ጭማሪ በምንም አግባብነት የለውም» ያሉት ኃላፊው የዋጋ ጭማሪ ካስፈለገም ቀጣይ የኢኮኖሚው ሁኔታ ታይቶ እንጂ ከዚህ በፊት የገቡ ምርቶች ላይ መሰል ጭማሪ ማድረግ አግባብነት እንደሌለው አንስተዋል። በዚህም ተሳተፉ ያሏቸው 158 የችርቻሮና ጅምላ መደብሮችን ሲያሽግ ከ130 በላይ ለሚሆኑ የንግድ ድርጅቶች ደግሞ ምርቶች በመጋዘን እንዳይያዙ ማስጠንቀቂያ መስጠቱን አመልክተዋል።  

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በትናንት ማብራሪያቸው ከማዳበሪያ እና ነዳጅ ውጪ በርካታ የአገሪቱ ምርት ከዚህም በፊት ሲመሩ የነበረው በትይዩ ምንዛሪ (ጥቁር ገበያ) እንደነበር፤ የፋይናንስ ተቋማት ኃላፊዎችም በዚህ ውስጥ ተሳትፎ እንደነበራቸው ገልጸው፤ አሁን ምርቶች ላይ ዋጋ የሚያስጨምር አዲስ ነገር የለም ማለታቸው ይታወሳል። 

 ሥዩም ጌቱ

ሸዋዬ ለገሠ

አዜብ ታደሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW