«ሥራ ላይ ያለው የምርጫ ሕግ የሕዝብን ድምጽ ያፍናል»
ሐሙስ፣ ጥቅምት 27 2018
ቀጣዩ ሀገራዊ ሰባተኛ ምርጫ ከመካሄዱ በፊት የምርጫ ሕጉ መሻሻል እንዳለበት የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክርቤት አሳሰበ። ምክርቤቱ ትናንት ለሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት በጻፈው ደብዳቤ ቀጣዩ ምርጫ ሁሉም ፓርቲዎች በጋራ ምክርቤቱ ውይይቶች የተስማሙበት የተመጣጣኝ ድምፅ ውክልና ሥርአት ተግባራዊ የሚሆንበት መንገድ እንዲፈለግ ጥሪ አቅርቧል።
«የምርጫ ሕጉ ይቀየር»
ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ቀጣዩን ሰባተኛ ሀገራዊምርጫ ለማካሄድ ያስችለኛል ያለውን የምርጫ የጊዜ ሰሌዳ አውጥቶ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር በዝግ መክሯል። ፓርቲዎቹም ከምርጫው በፊት ይቅደም ያሉትን ለቦርዱና ይመለከታቸዋል ላሏቸው አካላት አቅርበዋል። ከምርጫው በፊት መሻሻል አለባቸው ብለው ካነሱአቸው ዋናዋና ጉዳዮች በሀገሪቱ ያለው የሰላምና ጸጥታ ጉዳይ እንዲሁም አሁን በሥራ ላይ ያለው የአብላጫ ድምፅ የምርጫ ሥርዓት ዋናዎቹ ናቸው። በተለይ ፓርቲዎች ባገኙት የድምፅ መጠን በምክርቤት እንዲወከሉ የሚያስችላቸው የተመጣጣኝ ውክልና ድምፅ ተግባራዊ እንዲሆን ነው የጋራ ምክርቤቱ የጠየቀው።
ምክርቤቱ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ለኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድና ለጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት በጻፈው ደብዳቤ ሰባተኛው ሀገራዊ ምርጫ ከመካሄዱ በፊት የሕግ ማሻሻያ እንዲደረግ ጠይቋል። «አሁን በሥራ ላይ ያለው የአብላጫ ድምጽ የምርጫ ስርዓት ካሉት ውሱንነቶች መካከል የመራጮች ድምፅ መባከንና ተፎካካሪ ፓርቲዎች በምርጫ የማሸነፍ ዕድል እንዳይኖራቸው ያደርጋል» ያለው ደብዳቤው ከምርጫው በፊት የሕገመንግሥት ማሻሻያ ተደርጎ በተመጣጣኝ ውክልና የምርጫ ሥርአት እንዲተካ ጠይቋል።
የጋራ ምክርቤቱ አክሎም የዕጬዎች የድጋፍ ፊርማ አሰባሰብ፣ ከመንግሥት ስለሚሰጥ የገንዘብ ድጋፍ፣ እንዲሁም የምርጫ የጊዜ ሰሌዳን በተመለከተም መሻሻል አለባቸው ያላቸውን ጉዳዮች አካቷል።
የጋራ ምክርቤቱ አባል የሆነው የገዳ ሥርዓት ለኦሮሞ ነጻነት ፓርቲ የምርጫ ሕጉ ካልተሻሻለ በሚቀጥለው ምርጫ እንደማይሳተፍ ባወጣው መግለጫ ይፋ አድርጓል። የድርጅቱ ፕሬዝደንት አባቦኩ ሮብሌ ታደሰ በሰጡን ተጨማሪ አስተያየት የአብላጫ ድምፅ የምርጫ ሥርዓት እንዲቀየር የፈለግነው «አፋኝ ስለሆነ ነው» ብለዋል።
« በሀገራችን ያለው የአብላጫ ድምጽ የምርቻ ሥርአት የሕዝብን ድምጽ ሲያፍን የነበረ ነው።»
አቶ ሮበሌ ታደሰ አክለውም የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክርቤት አባል የሆንነው ፓርቲዎች የምርጫ ሥርዓቱ እንዲቀየር ተስማምተንና ተፈራርመን ለሚመለከተው አካል አቅርበናል ይላሉ።
የባለሙያ አስተያየት
የሕገመንግሥና የሰብአዊ መብት ተመራማሪና ባለሙያ አቶ በላቸው ግርማ አብላጫ ድምጽ የሚባለው የምርጫ ስርአት አብዛኛው የሚሠራው ሁለት ተቀናቃኝ ፓርቲዎች ብቻ ባሉበት ሀገር እንደሆነ ያብራራሉ።
« አብላጫ ድምጽ የሚባል በደንብ የሚሰራው ሁለት ተፎካካሪ ፓርቲዎች ባሉበት ሀገር ነው።»
በኢትዮጵያ ካሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ብዛት አንጻር ተመጣጣኝ ውክልና የሚያስገኝ የምርጫ ሥርዓት መከተል ፓርቲዎች በአንድ ፓርቲ ሳይደፈጠጡ ባገኙት ድምፅ የሚወከሉበት እንደሆነ አቶ በላቸው ገልጸዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ምላሽ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አሕመድ ባለፈው ጥቅምት 18 ቀን 2018 ዓ.ም. የመንግሥት የዓመቱ የትኩረት አቅጣጫ ላይ ለምክርቤት አባላት ማብራሪያ በሰጡበት ወቅትም ጉዳዩ ተነስቶ እንደነበር ይታወሳል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከምክርቤቱ አባላት ምርጫውን አስመልክተው ለቀረቡ ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ « ሀገራዊ ምክክር፤ ያለውን ሥርዓት የሚያጠናክር እንጂ የሚያፈርስ አደለም፤ ይሁንና ምርጫን፣ በጀትን፣ የወታደር እንቅስቃሴን የሚያስቆም ሀገራዊ ምክክር አንፈልግም» በማለት አብራርተዋል።
አያይዘውም ሀገራዊ ምክክሩ የምርጫ ስርዓቱ ላይ የሚያመጣው ለውጥ ካለና ከምርጫው በፊት ከታየ ደግሞ ያኔ በሚወሰደው መንገድ የሚታይ መሆኑን በመግለጽ ምርጫው እንደሚካሄድ ገልጸዋል።
በዚህ ጉዳይ ላይ ተጨማሪ ማብራሪያ እንዲሰጡን ለፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክርቤትና የምርጫ ቦርድ የሥራ ሀላፊዎች ያደረግነው ተደጋጋሚ ሙከራ ለጊዜው አልተሳካልንም።
ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር
ሸዋዬ ለገሠ