1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የምስራቅ አፍሪቃ ምስቅልቅል፣ የሱዳን አብነት

ሰኞ፣ ኅዳር 6 2014

የ1960ዎቹ ማብቂያና የሰባዎቹ መጀመሪያ አብዮቶች፣የ1980ዎቹ ማብቂያና የዘጠናዎቹ መጀመሪያ መፈንቅለ መንግስቶችም ሆኑ፣ ኢትዮጵያ ኤርትራን፣ ሶማሊያ ሰሜን፣ ሱዳን ደቡብ ግዛቶቻቸዉን ማስገንጠላቸዉ የሶስቱን ሐገራት ሕዝብ በየግጭት ጦርነቱ ከመማገድ ባለፍ ለሕዝቡ ልማት፣ዕድገት፣ሰላም ዲሞክራሲ የተከረዉ አለመኖሩ ነዉ ሰቀቀኑ።

Sudan Khartum | Proteste gegen Militärregierung
ምስል AFP/Getty Images

ምሥራቅ አፍሪቃ ሰላም ያጣ ግን የሠላም ተስፋ የሚጨናጎልበት ምድር

This browser does not support the audio element.

ሶማሊያ ዛሬም ለንቋንሷ ሰላሟ የሚጠበቀዉ በምዕራባዉያን ገንዘብ-ዲፕሎማሲ በአፍሪቃ ሕብረት ጦር ነዉ።የግዛት እንድነቷን፣ሉዓላዊነቷን፣ የሕዝቧን ደሕንነት የሚያስጠብቅ ጠንካራ መንግሥት የላትም።ኤርትራ ዓለምን ረስታ፣ በዓለም ተረስታ፣ በድሮ ወዳጆችዋ ተጠልታ ግን በአዲስ አበቦች ድጋፍ ቁልቁል እየዳከረች ነዉ።በፖለቲካ ዉዝግብ፣ በጎሳ ጥላቻ፣ ግጭት፣ እስካምና ያዘገመችዉ ኢትዮጵያ ዘንድሮም እንደ አምና ሐቻምናዉ የሟች ቁስለኛ፣ የተደፈሩ፣ የተፈናቀሉ ዜጎችዋን ብዛት እያሰላች፣ ቀሪ ዜጋዋን ለዉጊያ ጦርነት ታስፎክራለች።ታሰልፋለችም።በመፈንቅለ መንግሥት ኖራ፣መፈንቅለ መንግሥት የሚወገዝ፣የሚደገፍባት ሱዳንም ከ1960ዎቹ (ዘመኑ በሙሉ እንደጎሪጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) መጀመሪያ ጀምሮ እንደኖርችበት በአደባባይ ሰልፍ፣በግጭት ዉግዘት ትርገበገባለች።ምሥራቅ አፍሪቃ! ሰላም እየናፈቀዉ የሰላም ተስፋ የሚጨናጎልበት  ምድር።የምሥራቅ አፍሪቃ ምስቅልቅል መነሻ፣ የሱዳኖች ማጣቃሻ እንድምታዉ መድረሻችን ነዉ ላፍታ አብራችሁን ቆዩ።

 አንዳዴ ለአመፅ፣ግጭት፣መጠፋፋት አንድ ይመስላሉ።ሱዳኖች ደቡብና ሰሜን ብለዉ ሲጠፋፉ አስታራቂዉ የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገስት ነበሩ።የኤርትራ ነፃነት ተዋጊዎች ደጋፊ፣የአፄ ኃይለ ስላሴ  ተቃዋሚዎች፣ የአዉሮፕላን ጠላፊዎች ጭምር ከለላ ሰጪም ግን ሱዳን ነበረች።ሶማሊያ አባሪ-ተባባሪ።በደርግ ዘመን የካርቱም-አዲስ አበባ-ሞቃዲሾ ገዢዎች አልፎ-አልፎ ሲወዳጁ ወይም የተወዳጁ ሲመስሉ ብዙ ጊዜ ሁለት ለአንድ እየተቧደኑ አንዳቸዉ ሌላቸዉን ለመጣል ሲጠላለፉ 1989 ደረሱ።

ምስል /AP/dpa/picture alliance

ግንቦት 1989።ካርቱምም፣ አዲስ አበባም ላይ መፈንቅለ መንግስት ተደረገ።የካርቱሙ፣ ኮሎኔል ዑመር ሐሰን አልበሽርን ቤተ-መንግሥት ዶሎ ተሳካ። የአዲስ አበባዉ ከ30 የሚበልጡ የኢትዮጵያ ምርጥ የጦር መኮንኖችን ሕይወት ገብሮም ከሸፈ።ባመት ከመንፈቁ ጥር 1991፣ የሶማሊያዉ የረጅም ጊዜ ገዢ ማርሻል መሐመድ ዚያድ ባሬ ከስልጣን ተወገዱ።ሶማሊያም እስከዛሬ ከምትዳክርበት የጥፋት፣ዉዝግብ፣የዘረፋ-ቁርቁስ ማጥ ተቀረቀረች።ባምስተኛ ወሩ ግንቦት 1991 አስመራና አዲስ አበባ ላይ የሆነዉ ሆነዉ።

የፖለቲካ ተንታኝና ደራሲ ዩሱፍ ያሲን ካንዱ ወደሌላዉ የሚዛመት «በሽታ» አንበለዉ እያሉ ግን ይሉታል።

ሱዳኖች የሚኮሩ፣ደጋግመዉ የሚያወሱ፣ የሕዝብ ትብብር፣ ኃይልና አቅም የተመሰከረበትን አብዮት ያደረጉት ጥቅምት 1964 ነበር።ካርቱም ላይ የጄኔራል ኢብራሒም አቡድ መንግሥት በተወገደ በአምስተኛ ዓመቱ ጥቅምት 1969 ዚያድ ባሬ «አብዮት» ባሉት መፈንቅለ መንግሥት ቪላ ሞግዲሾን ተቆጣጠሩ።

ምስል Privat

በአምስኛ ዓመቱ የካቲት ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያም ከጥንታዊቱ፣ ሰፊይቱ ኢትዮጵያ አናት ላይ ያስቀመጠዉ በዚያንጊዜ አገላለፅ «ግብታዊዉ አብዮት ፈነዳ።»

የ1960ዎቹ ማብቂያና የሰባዎቹ መጀመሪያ አብዮቶች፣የ1980ዎቹ ማብቂያና የዘጠናዎቹ መጀመሪያ መፈንቅለ መንግስቶችም ሆኑ፣ ኢትዮጵያ ኤርትራን፣ ሶማሊያ ሰሜን፣ ሱዳን ደቡብ ግዛቶቻቸዉን ማስገንጠላቸዉ የሶስቱን ሐገራት ሕዝብ በየግጭት ጦርነቱ ከመማገድ ባለፍ ለሕዝቡ ልማት፣ዕድገት፣ሰላም ዲሞክራሲ የተከረዉ አለመኖሩ ነዉ ሰቀቀኑ።

ሶማሊያ በ2017 የካቲት፣ ኢትዮጵያ በ2018 መጋቢት፣ ሱዳን በ2019 ሚያዚያ ያደረጉት ፖለቲካዊ ወይም የመሪዎች ለዉጥ ደግሞ እስከዚያ ዘመን ድረስ የነበረዉን የሕዝብ ስቃይ ሰቀቀን ለማስወገድ ትልቅ ተስፋ ተጥሎበት ነበር።

በተለይ አዲስ አበባና ካርቱም ላይ የተደረገዉ ለዉጥ የሕዝብ ግፊት፣የወጣቶች ሰልፍ፣ የሕይወት መስዋዕትነት ዉጤት ስለነበር የእስከዚያ ዘመኑን ሸፍጥ መካካድ ያስወገደ፣ ድፍን ዓለም ያደነቀዉ፣ የአፍሪቃ አብነት ተደርጎ ነበር።ግን ባጭር ተቀጨ።

ኢትዮጵያ ዛሬ በጦርነት፣መገዳደል ትርምስ ዜና ከአፍቃኒስታን ቀጥላ አንዳዴም ቀድማ የዓለም መገናኛ ዘዴዎች ቀዳሚ ርዕስ ናት።ሱዳን ከ1960ዎቹ ጀምሮ እንደኖረችበት በአደባባይ ተቃዉሞ ሰልፍ፣ በሰልፈኛ ፀጥታ አስከባሪ ግጭት ግድያ ከሁሉም በላይ በመፈንቅለ መንግሥት ዜና ብዙ ጊዜ ኢትዮጵያን ስትከተል አልፎ አልፎ ትቀድማለች።ምስራቅ አፍሪቃ! እስከመቼ? አቶ የሱፍ የሩቅ ተስፋ ይጠቁማሉ።ተስፋዉ እዉን የሚሆነዉ ደግሞ እንደ አቶ ዩሱፍ ኢትዮጵያ የሕዝቧን እልቂት ፍጅት ማስወገድ ስትችል ነዉ።ሌሎቹ ይከተሉ ይሆናል።ተከተሉም አልተከተሉ ግን የቅርብ ዘመኑን ምስቅልቅል ለማስወገድ አንድ ቦታ አንድ ነገር መደረግ አለበት እንደ አቶ ዩሱፍ።

ምስል Eduardo Soteras/AFP/Getty Images

ኢትዮጵያን ሕዝብ፣ የሚያጠፋ፣ ሐብት ንብረቱን የሚያወድመዉን ጦርነት ለማስወገድ ተኩስ አቁም፣ድርድር፣ ዉይይት እንዲደረግ ጉዳዩ የሚመለከታቸዉ የዉጪም፣የዉስጥም ወገኖች የሚያሰነዝሩት ሐሳብ እስካሁን ተቀባይነት አላገኘም።ጦርነት፣ ፉከራ፣ቀረርቶ፣ ዘመቻዉ ግን ቀጥሏል።

ሱዳንም ጄኔራል አብዱል ፈታሕ አል ቡርሐን ከስልጣን ያስወገዱት የጠቅላይ ሚንስትር አብደላ ሐምዶክ የሲቢል መስተዳድር ወደ ስልጣን እንዲመለስ የሚደረገዉ ጥሪ፣ ያደባባይ ሰልፍና ጩኸት አላባራም።ሰልፎቹን ከሚያደራጁት አንዱ መሐመድ አልሳዲቂ ፍላጎት፣ ሥጋት፣ጭንቀታቸዉን ይገልፃሉ።

                              

«አብደላ ሐምዶክ በጣም አስፈላጊ ሚና ሊኖራቸዉ ይገባል ብለን እናምናለን።የሲቢላዊዉ መስተዳድር ምሳሌ ናቸዉ።በጣም አሳሳቢ ወቅት ላይ ነን።ቀዉሱን ለማስወገድ፣ ሱዳንን ከከፋ ጥፋት ለማዳን  ብሔራዊ መግባባት ያስፈልገናል።»

የሱዳን ሕዝብ የአደባባይ ሰልፍ፣የምዕራቦች ግፊት፣የአረቦች የይስሙላ ሽምግልናም ሆነ የተባበሩት መንግሥታት ማስጠንቀቂያ ለጄኔራል አብደልፈታሕ አልቡርሐን እስካሁን ከቁብ የሚቆጠር አልሆነም።የጦር መኮንኖች የበዙበት አዲስ መንግስት መስርተዋል።ምርጫ እስኪደረግ የርዕሠ-ብሔርነቱን ሥልጣን እንደያዙ ለመቀጠል ወስነዋልም።

ምስል Loredana Sangiuliano/SOPA Images/ZUMAPRESS.com/picture alliance

ጠቅላይ ሚንስትር ሐምዶክ ወደ ስልጣን ይመለሳሉ የሚለዉ ተስፋ ለካርቱም አደባባይ ሰልፈኞች እንጂ ለጄኔራሉ «ያበቃለት» ይመስላል።ይሁንና ምርጫ ከተደረገ በኋላ ጄኔራሉ ራሳቸዉ ከሱዳን ፖለቲካ እንደሚገለሉ ቃል ገብተዋል።ዩሱፍ ያሲን  ይጠይቃሉ።

                                           

እኚያ ዝምተኛ፣ቀዝቀዝ፣ ለዘብ፣ ወደ እስልምናዉ ዘንበል ያሉት ጄኔራል የ2019ኙ የአደባባይ ሰልፍ እስኪጠናከር ድረስ በሱዳን ፖለቲካ ዉስጥ ብዙም አይታወቁም ነበር።እንደ ወታደር ግን ደቡብ ሱዳንና የዳርፉር ላይ በተደረጉ ዉጊያዎች ተካፍለዋል።በ2015 የመንን ለወረረዉ ለሳዑዲ አረቢያ መራሹ የአረብ ሐገራት ጦር የሱዳንን ወታደር አዝማች ነበሩ።ከሁሉም በላይ የአልበሽር ታማኝ ናቸዉ።

በ2011 የያኔዉን የግብፅ ፕሬዝደንት ሁስኒ ሙባረክን በመቃወም በተለይ ተሕሪር አደባባይ ይደግ የነበረዉን ሰልፍ ይከታተሉ ነበር።ካይሮን ያዉቋታል።የጦር አዛዦችዋ ደግሞ ሸምገል ያሉት አስተማሪዎቻቸዉ፣ አብነቶቻቸዉም፣ ሌሎቹ የኮርስ ተጋሪዎቻቸዉ ናቸዉ።

የያኔዉ የግብፅ መከላከያ ሚንስትር ፊልድ ማርሻል መሐመድ ሁሴይን ተንታዊ በ2011 ተሕሪር አደባባይ የተሰለፈዉን ሕዝብ እንደጎበኙ ሁሉ፣ አል ቡርሐንም በ2019 አል በሽርን በመቃወም ካርቱም አደባባይ ተሰልፎ የነበረዉን ሕዝብ ጎበኙ።

ምስል STRINGER/AFP/Getty Images

«ሶስት ሆነን ቀጠሮ ያዝንና አልበሽር ጋ ገባን» አሉ ጄኔራል  አል ቡርሐን በቅርቡ «ከዚያ ሁሉም ነገር ያበቃለት መሆኑን ነገርኳቸዉ።» ቀጠሉ።የሽግግር ሉዓላዊ ምክር ቤት የሊቀመንበርነት ስልጣንን እንደያዙ መጀመሪያ የጎበኙት ካይሮን፣ ያነጋገሩት በመፈንቅለ መንግስት ሥልጣን የያዙትን  ሞክሼያቸዉን ጄኔራል አብዱልፈታሕ አል ሲሲን ነበር።ሁለቱም የካይሮ ጦር አካዳሚ ምሩቆች ናቸዉ።አብሮ የኖረ ይወራረሳል እንዲሉ አረቦች።ማን ተጃለሰ ተዋረሰ።

ነጋሽ መሐመድ

ኂሩት መለሰ                     

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW