የምስጋና ዝግጅት ለቀድሞዋ የኢትዮጵያ ርዕሠ ብሔር ሣኅለ ወርቅ ዘውዴ
ዓርብ፣ ኅዳር 6 2017በቅርቡ የሥራ ዘመናቸው ተጠናቆ ኃላፊነታቸውን ያስረከቡት የኢፌዴሪ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ሣኅለ ወርቅ ዘውዴ ሴቶችን በማገዝ ረገድ አበርከቱት ለተባለ አስተዋጽዖ ዛሬ አዲስ አበባ ውስጥ የምሥጋና ሥነ ሥርዓት ተደረገላቸው። የእውቅና ዝግጅቱን ያሠናዱት በበጎ ፈቃድ የተሰባሰቡ ሴቶች እና የሴት መር ድርጅቶች ናቸው።
ከስድስት ዓመታት በፊት ርእሠ ብሔር ሆነው ሲሾሙ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የ 18 ደቂቃ ንግግር አድርገው እንደነበር ያስታወሱት ሣኅለ ወርቅ ዘውዴ በንግግራቸው ሰላም እና ሴት የሚሉ ቃላትን ደጋግመው መናገራቸውንም እና በዚያ አቅጣጫ መሥራታቸውን ገልፀዋል።በሥነ ሥርዓቱ ላይ ሁለት የቀድሞ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዐፈ ጉባኤዎች ተገኝተዋል።
ስለ ተሰናባቿ እና አዲሱ የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንቶች የሕዝብ አሰተያየት
የኢፌዴሪ ቀድሞዋ ርእሠ ብሔር ሣኅለ ወርቅ ዘውዴ "የሴቶችን አመራር ከፍ ለማድረግ፣ የጾታ እኩልነት እንዲኖር" አበረከቱት ለተባለ አስተዋጽዖ ዛሬ አርብ በሸራተን አዲስ ሆቴል የዕውቅናና የምስጋና ሥነ ሥርዓት ተደርጎላቸዋል። ለስድስት ዓመታት እንዲያገለግሉ ፕሬዝዳንት ሆነው ቃለ መሀላ በፈፀሙበት ወቅት የሰላም እና የሴት ጉዳዮች ላይ አተኩረው እንደነበር አስታውሰዋል።
የኢትዮጵያ አራተኛ ርእሠ ብሔር የመጀመሪያዋ ሴት ፕሬዝዳንት ይህ የታሪክ ክስተት "የማይቻለው ይቻላል የሚል" በጎ ምልከታ መፈንጠቅ ችሎ እንደነበር ገልፀዋል። "በበኩሌ ፕሬዚዳንት እሆናለሁ ብየ ተመኝቼውም፣ አስቤውም ማግባባትም ሰርቼበትም አላውቅም" ሰአዳ ጀማል የፕሬዝዳንት ጽ/ቤት ዘርግቶት የነበረ እና በአምስት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ ላለፉት ሦስት ዓመታት ለሴት ተማሪዎች ይሰጥ የነበረን የሥልጠና ዕድል ስታስተባብር ነበር።
በኢትዮጵያ “ልዩነቶችን በጠብመንጃ እና በኃይል የመፍታት አማራጭ ማክተም አለበት” ርዕሰ-ብሔር ሣህለ ወርቅ ዘውዴ
"ዋና ዓላማው የነገ ሴት መሪዎችን ማፍራት ነው"
ስሒን ተፈራ የሴታዊት የፆታ ፍትሕ ማሕበር መሥራችና አስተባባሪ ሲሆኑ ርእሠ ብሔር ሣኅለ ወርቅ ዘውዴ ባለሥልጣናት በጦርነት ወቅት ዝም ሲሉ ያንን ለማስቆም ጥረት ሲያደርጉ የነበሩ መሆኑን መስክረዋል። "ጦርነትን ለማስቆም ሊሆን ይችላል ኢትዮጵያ ብዙ ዓይነት ችግሮች ሲገጥማት በዲፕሎማሲ ለመፍታት፣ ግጭት ከዚህ በላይ እንዳይባባስ፣ ሰላም እንዲመጣ ከፍተኛ አበርክቶት አድርገዋል"
ኢትዮጵያ ውስጥ የተከሰቱ ግጭትና ጦርነቶችን መነሻ በማድረግ "ቀይ መስመር ተጥሷል" በሚል ንግግራቸው ይታወቁ የነበሩት የቀድሞ ርእሠ ብሔር ሣኅለ ወርቅ ዘውዴ ከኃላፊነት ከመነሳታቸው ጥቂት ቀናት አስቀድመው "ዝምታ ነው መልሴ" የሚል መነጋገሪያ የሆነ ጽሑፍም አጋርተው ነበር። በርታ ብለው ይናገሩ የነበረበትን ምክንያትና ተገቢነትንም ገልፀዉታል።በኢትዮጵያ «ዘላቂ ሀገራዊ መግባባት» ለመፍጠር ቅድሚያ እንዲሰጥ ፕሬዝደንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ አሳሰቡ
በዚህ የምስጋና ሥነ ሥርዓት ላይ ሁለት የቀድሞ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዋና ዐፈ ጉባኤዎች፣ የሥራ ባልደረቦቻቸው፣ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች እና ሴቶች ተገኝተዋል። ከመንግሥት ተወክሎ ንግግር ያደረገም ሆነ የታደመ ስለመኖሩ አልተገለፀም። የመራኂተ ብሔርነቱ ሹመት በተሰጠበት ወቅት ለሀገሪቱ ሴቶች በታላቅ ተምሳሌትነት ይጠቀስ ነበር። በዚህ ሥነ ሥርዓት ላይ ግን በተለይ ከሴት ከሚኒስትሮች የታደመ አልነበረም።በሥነ ሥርዓቱ ላይ አንጋፋው ሰዓሊ ዘሪሁን የትም ጌታ ከሠሯቸው ሥራዎች ሁሉ ወደር የሌለው ያሉትን ስዕል በስጦታ አበርክተውላቸዋል።
ሰሎሞን ሙጬ
ኂሩት መለሰ
እሸቴ በቀለ