1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የምስጋና ዝግጅት ለትዝታው ንጉስ፣ ለአርቲስት ማህሙድ አህመድ

አበበ ፈለቀ
ሐሙስ፣ ኅዳር 26 2017

ከስድሳ ዓመታት በላይ በሙዚቃው ዓለም የቆየው የትዝታው ንጉስ፣ አርቲስት ማህሙድ አህመድ ለእድሜ ዘመን አገልግሎቱ፣ በሙዚቃ ለሙዚቃ ለመኖሩ፣ ለሃገራችን ኪነ-ጥበብ ለበረከተው አስተዋጸኦ፣ በህይወታችን ውስጥ ላኖረው አሻራ፣ ተከበረ፣ ተመሰገነ። በዝግጅቱ ላይ አድናቂወቹ ታድመው፣ ከሙዚቃው ዓለም በአክብሮት ተሰናብተውታል።

 አርቲስት ማህሙድ አህመድ፤ የትዝታው ንጉስ
አርቲስት ማህሙድ አህመድ፤ የትዝታው ንጉስምስል Abebe Feleke/DW

የምስጋና ዝግጅት ለትዝታው ንጉስ፣ ለአርቲስት ማህሙድ አህመድ በአሜሪካዋ የቨርጂኒያ ግዛት

This browser does not support the audio element.

የምስጋና ዝግጅት ለትዝታው ንጉስ፣ ለአርቲስት ማህሙድ አህመድ

ከስድሳ ዓመታት በላይ በሙዚቃው ዓለም የቆየው የትዝታው ንጉስ፣ አርቲስት ማህሙድ አህመድ ለእድሜ ዘመን አገልግሎቱ፣ በሙዚቃ ለሙዚቃ ለመኖሩ፣ ለሃገራችን ኪነ-ጥበብ ለበረከተው አስተዋጸኦ፣ በህይወታችን ውስጥ ላኖረው አሻራ፣  ባሳለፍነው ሳምንት በአሜሪካዋ የቨርጂኒያ ግዛት ተከበረ፣ ተመሰገነ። ዘመን ጊዜ ሁነት የማይሽረውን ታላቅ ስበዕና በማክበሩ ዝግጅት ላይም፣  አድናቂወቹ ታድመው፣ ከሙዚቃው ዓለም በአክብሮት ተሰናብተውታል። የሞያ ልጆቹና አጋሮቹም  የተለያዩ የኪነጥበብ ዝግጅቶችን በማቅረብ ያአክብሮቷን ምሽት አድምቀዋታል። ሰላም ጤና ይስጥልኝ፣ የዛሪው የባህል መድረክ ትኩረት፣ ጋሽ ማህሙድን አክብሮ የመከበሩ ዝግጅት ነው።


ላለፉት ስልሳ ሶስት አመታት በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በዓለም ሙዚቃ ላይ ታላቅ አሻራን አኑሯል፣ በሁላችንም ህይወትና  ትዝታ ውስጥ ጉልህ ስፍራ ይዟል።  ድሮናል፣ አፋቅሮናል፣ የኡወት ተሞክሮዋችን፣ የደስታ የሃዘናችን፣ የፈተና የድላችን አካል ሆኖ ዘልቋል። ሚሊዮኖችን በዜማወቹ አሸንፏል።  ሙዚቃን ህይወቱ አድርጎ ዘመንን፣ ትውልድንና ሁነትን  ተሻግሯል። ዘመን አይሽሬ ስራወችን አበርክቶልናል። ይሄን ታላቅ የሙዚቃ ሰው አርቲስት ማህሙድ አህመድን  የማክበር፣ የማመስገንና ፍቅርን የመስጠት ምሽት ነበር ባሳለፍነው አርብ ምሽት እዚህ ቨርጂኒያ፣ ስፕሪንግፊልድ ውስጥ በታላቅ ድምቀት የተከናወነው።  
በዚህ ዝግጅት ላይ ለመታደም ከዲስና አካባቢዋ ውጪ፣ ከተለያዩ የአሜሪካ ግዛቶች፣ ከካናዳና ከኢትዮፕጵያ ጭምር የመጡም ነበሩ። ጋሽ ማህሙድ ለተደረገለት የክብር ምሽት በራሱ ብቻ ሳይሆን ዛሬ ካጠገቡ በሌሉት፣ የሱን እድል ባላገኙት ጓደኞቹ ስም ጭምር ነው የተቀበለው።

የምስጋና ዝግጅት ለትዝታው ንጉስ፣ ለአርቲስት ማህሙድ አህመድ በአሜሪካዋ የቨርጂኒያ ግዛት ምስል Abebe Feleke/DW


በ1933 ዓ/ም አዲስ አበባ፣ አባኮራን ሰፈር የተወለደው ማህሙድ አህመድ፣ ገና በለጋ እድሜው አሪዞና ክለብ ተብሎ በሚጠራው ክለብ ውስጥ ባገኘው አጋጣሚ ነው ወደ ሙዚቃው ዓለም የገባው። ፍቅርሽም ይቅርብኝ በሰኘው ዜማ፣ ለሙዚቃ ጥሪ መልስ የሰጠው Mአህሙድ አህመድ፣ ለላፉት ስድሳ ሶስት አመታት በሙዚቃ፣ ለሙዚቃ ኖሯል። ከክቡር ዘበኛ፣ ከአይቤክስ፣ ቬነስ፣ ሮሃ፣ ዳህላክ፣ ዋልያስ እና ከራሱ የ3ኤም ባንዶች ጋ በርካታ መድረኮች ላይ ሰርቷል። ጋሽ ማህሙድ ዘመን፣ ትውልድና ሁነት ከማይሽረው የሙዚቃ ብቃቱ በተጨማሪ፣ ግሩም የሆነ ስበዕናው፣ ደግነቱ፣ መልካምነቱና፣ የዋህነቱ፡ በሁሉም ሰው ልብ ውስጥ እንዳስገባው በምሽቱ የነበረው ድባብ ምስክር ነው። ከዳላስ ቴክሳስ፣ ማህሙድ አህመድን ለማክበር የመጣችው አክባሪውና ወዳጁ ማህደር ገ/ስላሴ በዚህ የጋሽ ማህሙድ የስበዕና ብቃት ጽማማለች።

የምስጋና ዝግጅት ለትዝታው ንጉስ፣ ለአርቲስት ማህሙድ አህመድ በአሜሪካዋ የቨርጂኒያ ግዛት ምስል Abebe Feleke/DW


የጋሽ ማህሙድ ዜማወች ከህይወቴ ጋር ተጋምደዋል ይላል ማህሙድ ዝግጅት ላይ ለመታደም ከዴልዌር የመጣው አይታገድ ሲሳይ። የአርቲስት ማህሙድ ሙዚቃወች የፍቅር ህይወቱ ግባዓቶሽ፣ የደስታ ማብሰሪያው ርችቶች ፣ የሃዘን ማስረሻ እንባ አባሾሽ፣ የስራ፣ የትምህርት ዘመኑ ጉዞ ረዳቶች፣ የዝምታ ፅሞናው አጃቢወች መሆናቸውን የገለጸው አይታገድ እዚህ ዝግጅት ላይ አለመገኘት የማይታሰብ ነገር ነበር ብሏል።
ከሜሪላንድ ሲልቨርስፕሪንግ የመጣችው ውቢት መለሰ በበኩሏ ምሽቱ ጋሽ ማህሙድ ያለውን የሰው ፍቅር ያየበት፣ ሁሉም ይሄን እድል ቢያገኝ ብለን የተመኘንበት ነው ብላለች። ማህሙድ መላውን ዓለም በሙዚቃ ስራወቹ ያዳረሰ፣ ከሁሉም በላይ ትዝታው የራሱ አድርጎ፣ የነገሰ የገዘፈበት አንጋፋ ድምጻዊ ነው። በምሽቱ የመህሙድን ዜማ በርካታ አርቲስቶች ያቀረቡ ሲሆን፣ በተለይ የትዝታውን ሙዚቅ የተለያዩ ስንኞችን እየተቀባብሉ በማዜም ለንጉስ ያላቸውን አክብሮት አሳይተዋል።

የምስጋና ዝግጅት ለትዝታው ንጉስ፣ ለአርቲስት ማህሙድ አህመድ በአሜሪካዋ የቨርጂኒያ ግዛት ምስል Abebe Feleke/DW


በምሽቱ የማህሙድን ሙዚቃወች ከ16 አመታት በላይ ሲጫወቱ የቆዩት የአሜሪካው አፍሮ ዜን ኦል ስታር ባንድ አባላት ሙዚቃውን ተጫውተዋል፣ ለመጀመርያ ጊዜም አበአካል አግኝተውታል። ዘጠኛ አባላት ያሉት ይሄው ባንድ በማህሙድ ዜማወች መነሻነት በተለይ በ1960ወቹና 70ወቹ አመታት የወጡ የኢዮጵያ ሙዚቃወችን መጫወት ዋና መለያቸው እንዲሆን ማድረጉን የገለጸው የባንዱ መሪ ጆርጅ ሎው የማህሙድ አህመድ ዜማወች ሙዚቃ ቋንቋውን መናገር ለማይችሉ ተመልካቾች ልዩ ስሜትን የሚያጭሩ፣ ዓለም አቀፍ ብቃት ያላቸው እንደሆኑ ገልጿል። በምሽቱ ለመጀመርያ ጊዜ ያገኘውን ማህሙድንም አመስግኗል።
አርቲስት ማህሙድ አህመድ የበርካታ ዓለም አቀፍ ሽልማቶችም ባለቤት ነው። በ2016 ከፈረንሳይ መንግስት በሃገሪቷ ታላቅ የሚባለውን Officer of the Order of Arts and Letters ክብር ተጎናጽፏል። በአሜሪካዋ፣ የጎርጅያ ግዛት፟ አትላንታ ከተማ ውስጥ  ኦገስት 18 ቀን የማህሙድ ቀን ተብሎ ተሰይሟል። በ2007 የቢቢሲ አለማቀፍ ሙዚቃ ተሸላሚ ሆኗል። በሴኤንኤን አንቶኒ ቦርዴ ፕሮግራም ላይ ልዩ ሽፋን አግኝቷል። ከጎንደር ዩኒቨርሲትይ የክብር ዶክትሬት ተሰጥቶታል።

የምስጋና ዝግጅት ለትዝታው ንጉስ፣ ለአርቲስት ማህሙድ አህመድ በአሜሪካዋ የቨርጂኒያ ግዛት ምስል Abebe Feleke/DW


በዚሁ የማክበር ምሽትም  አርቲስት ማህሙድ ከዋሽንግተን ዲሲ ከተማና፣ ከሜሪላንዷ ሞንትጎመሪ ክ/ከተማ መንግስታት እንዲሁም  ከሌሎች የኢትዮጵያ ማህበራዊ ተቋማት የአክብሮትና የእውቅና ሽልማቶች ተበርክተውለታል። ይሄን ዝግጅት ከጅምሩ የተነሰሱት፣ ደፋ ቀና ሲሉም የከረሙት፣ እናም ለስኬት ያበቁት አስተባባሪወች የጋሽ ማህሙድ ወዳጆች አቶ ፍሰሃ ወልዱ፣ ዶ/ር ተድላ ገ/ጊኦርጊስ፣ ንጉስ ጥላሁን እና ሸዊት ወ/ሚካኤል ናቸው። የአንጋፋውን ድምጻዊ ማህሙድ አህመድን ህይወት እና ውለታ አክብሮ፤ መከበር መታደል እንደሆነ የገለጹት ከአስተባባሪወቹ አንዱ ሸዊት ወልደሚካእኤል ዝግጅቱ ሁሉም በጋራ የተሳተፈበት እንደሆነ ገልጸዋል። ከዚህ ቀደም ለአርቲስቶች የሚዘጋጁ መርሃ ግብሮች በሬስቶራንቶች የሚዘጋጁ እንደሆነ የገለጹት አቶ ሽዊት፣ የአርቲስት ማህሙድ አህመድ የምስጋና ምሽት ግን ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ ትልቁ እንደሆነ ገልጸዋል። በዚህ ዝግጅት ላይ ለመታደም የሚያስችሉ የመግቢያ ቲኬቶች ውስን በመሆናቸው በርካታ ሰውች መግባት እንዳልቻሉ፣ በእለቱም የጥበቃ አገልግሎት የሚሰጡ ሰወች በሰአቱ ባለመምጣታቸው በርካታ ሰወች ያለአግባብ ግባታቸውና፣ ከፍለው የገቡት ቦታ ያላገኙበት ሁኔታና መፈጠሩን ገልጸዋል። ከዚህ ባለፈ ግን ምሽቱ ሁሉም ተደስቶ ያመሸበት እንደሆነ አስታውሰዋል። በዚህ ዝግጅት የተገኘው ሙሉ ገቢውም ለአርቲስቱ የሚውል መሆኑን አስተባባሪወቹ ገልጸዋል።

የምስጋና ዝግጅት ለትዝታው ንጉስ፣ ለአርቲስት ማህሙድ አህመድ በአሜሪካዋ የቨርጂኒያ ግዛት ምስል Abebe Feleke/DW

 

በባህላዊ የሙዚቃ ቡድን የተሰናዱ ዝግጅቶች ለእይታ የበቁ ሲሆን አሜሪካ ተወልደው ያደጉ ልጆች በጋሽ ማህሙድ ዜማ ታጅበው ውዝዋዜ አሳይተዋል። በአርቲስት ታማኝ በየነ የተዘጋጀው የጋሽ ማህሙድን የህይወት ጉዞ የዳሰሰ ዘጋቢ ፊልም ቀርቦ፣ ማህሙድንም፣ ታዳሚውንም በትዝታ ወደኋላ ይዞ ነጉዷል። በሃሳብ በትካዜ አስቆዝሟል፣ አስቋል አስለቅሷል። የማህሙድን ህይወት ሰብሰብ አርጎ አስቃኝቷል። የሃገራችንን ኪንጥበብ ተሸክመው ወድፊት ካራመዱና፣ አለም አቀፍ ደለጃ ላይ ካደረሱ፣ ካሳደጉና ካጎልበቱ ጥቂት ሁነኛ የኪነጥበብ ፈርጦቻችን ውስጥ አንዱ የሆነው አርቲስት ማህሙድ አህመድ እንደ ሁለተኛ ቤቱ በሆነችው አሜሪካ እንኳን ተመላልሶ ሙዚቃን ማቅረብ ከጀመረ 40 አመታትን አስቆጥሯል። 

አበበ ፈለቀ

አዜብ ታደሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW