1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የምክክር ኮሚሽንኑ የሰሜን አሜሪካ ውይይትና የሕግ ባለሙያ አስተያየት

ታሪኩ ኃይሉ
ዓርብ፣ መስከረም 2 2018

የኢትዮጵያ ሃገራዊ ምክክር ኮሚሽን፣በሰሜን አሜሪካና አካባቢው ከሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ የኢትዮጵያውያን ለሃገራዊ ምክክር ጉባኤ ውይይት የሚደረግባቸው አጀንዳዎች መሰብሰቡን አስታወቀ። ኮሚሽንኑ ባዘጋጀው አጀንዳ የማሰባሰብ መድረክ የተሳተፉ፣ኢትዮያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን አጀንዳዎቻቸውን አቅርበዋል ተብሏል።

የኢትዮጵያ ሃገራዊ ምክክር  ኮሚሽን፣በሰሜን አሜሪካና አካባቢው
የኢትዮጵያ ሃገራዊ ምክክር  ኮሚሽን፣በሰሜን አሜሪካና አካባቢውምስል፦ Solomon Muchie/DW

የምክክር ኮሚሽንኑ የሰሜን አሜሪካ ውይይት እና የሕግ ባለሙያ አስተያየት

This browser does not support the audio element.

የምክክር ኮሚሽንኑ የሰሜን አሜሪካ ውይይት እና የሕግ ባለሙያ አስተያየት 

የኢትዮጵያ ሃገራዊ ምክክር  ኮሚሽን፣በሰሜን አሜሪካና አካባቢው  ከሚገኙ  ኢትዮጵያውያንና ትውልደ የኢትዮጵያውያን  ለሃገራዊ ምክክር ጉባኤ ውይይት የሚደረግባቸው አጀንዳዎች መሰብሰቡን አስታወቀ። የኮሚሽኑ ኮሚሽነር አምባሳደር መሐሙድ ድሪር ከዶቼ ቬለ ጋር ባደረጉት  ቆይታ እንዳሉት፣ ኮሚሽንኑ ባዘጋጀው አጀንዳ የማሰባሰብ መድረክ የተሳተፉ፣ኢትዮያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን አጀንዳዎቻቸውን አቅርበዋል። የሕግ ባለሙያው አቶ ተክለሚካኤል አበበ በበኩላቸው  ፣የኮሚሽኑ የውይይት ሂደት ገለልተኛነት እንደማይታይበት አመልክተዋል። 

ሃገራዊ ኮሚሽኑ በሰሜን አሜሪካንና አካባቢው ለሚገኙ ኢትዮጵያውንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ባዘጋጀው አጀንዳ የማሰባሰብያ ውይይት መድረክ፣ባለፈው ቅዳሜ እንደ ጎርጎሪዮሳዊው ጊዜ አቆጣጠር መስከርም ስድስት ቀን 2025 በካናዳ ቶሮንቶ የውይይት መድረክ አካሄዷል። በአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ለአገራዊ ምክክር ጉባኤ የተሰበሰቡ አጀንዳዎች

የቀረቡ አጀንዳዎች 

በውይይቱ የተነሱት ዋና ዋና ዐሳቦች ምንድናቸው ስንል የጠየቅናቸው ኮሚሽነር መሐሙድ፣ እንደሚከተለው መልሰዋል። ''የቀረቡት አጀንዳዎች ሃገራዊ አጀንዳዎች ናቸው። አገራችንን የሚመለከቱ፣እንግዲህ እነዚህ አጀንዳዎች ተሰባስበው በሙሉ ተጠናቅረው፣ የቅድሚያ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ቅድሚያ ተሰጥቷቸው በሃገራዊ ምክክሩ ጉባኤ ላይ ውይይት ወይም ምክክር ይደረግባቸዋል፤ስለዚህ ወኪሎቻቸውንም መርጠዋል። '' 

የቶሮንቶው ተቃውሞ 

ኮሚሽኑ በካናዳ ባዘጋጀው በዚህ መድረክ ላይ ተገኝተው የተሳተፉ የሚኖራቸውን  ያህል፣ ተቃውሞም የተስተናገደበት ነበር።  የኢትዮ ካናዳውያን ኔትዎርክ ለማኀበራዊ ድጋፍ/ኤክናስ/ እና በካናዳ የኢትዮጵያ ማኀበረሰብ ማኀበር፣ኮሚሽኑ በቶሮንቶ ከተማ በጠራው ስብሰባ ላይ እንዲሳተፉ የተደረገላቸውን ጥሪ ውድቅ ማድረጋቸውን ለዶቼ ቬለ ገልጸዋል። ኤክናስ፤የዋና ዋና ባለድርሻ አካላት መገለል፣የምክክር ኮሚሽኑ ገለልተኝነት እና ተአማኒነት ማጣት፣እየተፈጸሙ ያሉ ያላቸው፣ግፍ ፣መከራና በደል መፍትሄ ለመስጠት አለመቻልን በስጋትነት በመግለጽ በውይይት መድረኩ ላይ አለመሳተፍን መርጧል።  የምክክር ኮሚሽኑ በዋሽግተን ዲሲ ያካሄደው መድረክ

የሕግ ባለሙያው አስተያየት 

በካናዳ ነዋሪ የሆኑት የህግ ባለሙያው አቶ ተክለሚካኤል አበበም፣ኮሚሽኑ ገለልተኛና አካታች  መሆኑን የሚያመለክት ት ነገር እንደማይታይበት ይናገራሉ። ''የምክክር ኮሚሽኑ፣ገለልተኛ እንደሆነ፣አካታች እንደሆነ ይናገራል የፀደቀው ህግ ላይ፤ግን ያን የሚያሳይ ነገር ብዙም አልተመለከትንም። ከዚህ በፊት በነበሩ ዝግጅቶች ላይ የበለጠ የመንግስት ቅርንጫፍ የመምሰል ዐይነት አዝማሚያ ነው ያለው። '' 

የኮሚሽነሩ ምላሽ 

ኮሚሽነር መሐሙድ  ግን ይህንን ትችት አይቀበሉትም። ''ማንኛውም ሃገር፣በሁሉም ሀገሮች አገራዊ ምክክር በተካሄደባቸው ሀገሮች፣ የተመሰረቱ የሀገራዊ ምክክር ተቋማት በሙሉ በመንግስታቱ ነው የተመሰረቱት።  ስለዚህ ይሄ የኢትዮጵያን ሁኔታ የተለየ አያደርገውም። እኛ ደግሞ እንደ ኮሚሽነሮች  ዘመቻ ውስጥ ገብተን ኑ ምረጡን እጩ ነን ብለን፣የተንቀሳቀስን ወይም ቅስቀሳ ያደረግን ሰዎች  አይደለንም። በህዝብ ከተለያዩ ክፍሎች ጥቆማዎች ተሰብስበው በነእዛ ጥቆማዎች መሰረት የመጣን ነን። ''  አቶ ተክለሚካኤል እንደሚሉት፣ ኮሚሽኑ ተስፋ የሚጣልበት አይደለም፤ በመሆኑም እሳቸው የካናዳ ነዋሪ ቢሆኑም በቶሮንቶው የምክክር መድረክ ላይ አልተገኙም። 

የኢትዮጵያ ሃገራዊ ምክክር ኮሚሽን ምስል፦ Solomon Muchie/DW

''እኔ አልነበርኩም፤ከራሴ ጋር ብዙ ተሟገትኹና ልሂድ አልሂድ ሳስበው ፣እንደውም ውይይቱ ምን ላይ ነው?አወያዮች ራሳቸው፣ ልቅም ነው እንዲሁ የተዘራ ነገር ነው። እንጂ በጣም ትኩረት የተደረገበት ውይይት አልነበረም፣ከእዛ አንፃር አንጻር እኔ አልሄድኹም፤ብክነት ነው። ህጋዊ ማድረግ ነው ምክክር ኮሚሽኑን ብዬ አልሄድኩም። '' ኮሚሽኑ የተሻለ ውይይት ማድረግ እንዲችል ምን መደረግ አለበት ለሚለው ጥያቄ፣አቶ ተክሌ አስተያየት አላቸው። ''በእኔ አስተያየት፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ችግሩ ቁርሾው ያለው በኅብረተሰቡ መካከል አይደለም። ለምሳሌ ዐማራና ኦሮሞን፣እንደ ህዝብ ብንጠይቃቸው፣ትግሬና ዐማራውን፣ ዐማራውና ዓፋሩን  ብንጠይቃቸው አብረው ሲነግዱ፣የቆላው ከደጋው፣ የደቡብቡ ከሰሜኑ ሲነገድ፣ስለዚህ ልሂቃኑን በተለያየ መልኩ፣ በፖለቲካ ፓርቲም በመገናኛ ብዙሀን፣በትምህርት የተከማቹበት ቦታ ይታወቃል። ስለዚህ እነሱ ላይ ያተኮረ ውይይት ማድረግ ነው። '' የኮሚሽኑ ኮሚሽነር  አምባሳደር መሐሙድ፣ በሰሜን አሜሪካ የነበረው ተልዕኮ የተሳካ፣ ኢትዮጵያም ለምክክር የተዘጋጀች ናት ባይ ናቸው። ''በሂደቱ የተሳተፉት በሙሉ አጀንዳቸውን አቅርበዋል ፤ስለዚህ ኢትዮጵያ ለውይይት ተዘጋጅታለች ብዬ አምናለሁ። ያገኘነውም ተሞክሮ ይህንኑ ይመስላል። ''

ታሪኩ ኃይሉ

አዜብ ታደሰ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW