1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኤኮዋስ በኒጀር ሀይል ሊያሰማራ ነው

ቅዳሜ፣ ነሐሴ 6 2015

በምዕራብ አፍሪቃዊቷ ሀገር ኒጀር የተካሄደው መፈንቅለ መንግስት ተከትሎ የምዕራም አፍሪቃ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ የፖለቲካ ቀውሱን ለመፍታት ወታደራዊ ሀይል ለማሰማራት አቅዷል።ሩሲያ በበኩሏ ርምጃው ሀገሪቱን ወደማያባራ ግጭት ይወስዳል ስትል አስጠንቅቃለች።

Nigeria Abuja | ECOWAS-Treffen zur Lage in Niger
የምዕራብ አፍሪቃ የኤኮኖሚ ማኅበረሰብ ጉባኤ በናይጄሪያ አቡጃምስል KOLA SULAIMON/AFP

ኤኮዋስ በኒጄር ወታደራዊ ሀይል ሊያሰማራ ነው

This browser does not support the audio element.


በምዕራብ አፍሪቃዊቷ ሀገር ኒጀር ያለፈው ሀምሌ 26 ቀን 2023 ዓ/ም የተካሄደው መፈንቅለ መንግስት ሀገሪቱን ብቻ ሳይሆን ሌሎች ሀገራትን እንዲሁም  ዓለም አቀፍ እና አህጉራዊ  ድርጅቶችንም እያወዛገበ ነው።
የኒጀር ወታደራዊ ሁንታ፤ ፕሬዚዳንት መሀመድ ባዙምን በመፈንቅለ መንግስት ከስልጣን ማስወገዱን ተከትሎ የተባበሩት መንግስታት እና ፈረንሳይ፣ ጀርመን እና ሜሪካን የመሳሰሉ የምዕራባውያን ሀገራት  እንዲሁም  የአፍሪቃ ህብረትየኒጀር ወታደራዊ ኹንታ ከስልጣን ያወረዳቸውን ፕሬዝዳንት መልሶ ስልጣን ላይ እንዲያስቀምጥ ወትውተዋል።ያ ካልሆነ ግን በሀገሪቱ አለመረጋጋት እና ሽብርተኝነት ይነግሳል ሲሉ ስጋታቸውን ገልፀዋል።  ከሁሉም በላይ ግን መፈንቅለ መንግስቱን ተከትሎ የሀገሪቱ ዜጎች ሁኔታውን ያማርራሉ። 
«ከመፈንቅለ መንግስቱ ወዲህ በእውነቱ ሀገራችን በጣም በመጥፎ ሁኔታ ላይ ነው ያለችው።»ብለዋል አንድ የኒያሚ ነዋሪ።
በሌላ በኩል ተመራጩ የኒጀር መሪ መሀመድ ባዙም ከባለቤታቸው እና ከልጃቸው ጋር  ኒያሚ በሚገኘው ፕሬዚዳንታዊ ቤተ መንግስት ያለፈው ሃምሌ 26 ቀን በጠባቂዎቻቸው ተይዘው ከታሰሩ ወዲህ በችግር ላይ እንደሚገኙ እየተገለፀ ነው።
አንድ አማካሪያቸው እንዳሉት ባዙም እና ቤተሰባቸው መብራት፣ ምግብ፣ ውሃ እና መድሃኒት በሌለበት ታስረዋል።  
ይህንን ተከትሎ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ስለ ባዙም እና በቤተሰቦቻቸው ሁኔታ በጣም ስጋት እንደገባቸው ገልጸዋል።
የመንግስታቱ ድርጅት ቃል አቀባይ ያለፈው ረቡዕ  ባወጣው መግለጫም፤ ባዙም ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በአስቸኳይ እንዲፈቱ እና ወደነበሩበት እንዲመለሱ በድጋሚ ጥሪ አቅርቧል።
የምዕራብ አፍሪቃ ሀገሮች የኢኮኖሚ ማህበረሰብ በእንግሊዝኛው ምህፃሩ /ECOWAS/ ቀውሱን ለማርገብ ፤ስልጣኑን በሀይል የተቆጣጠረው ወታደራዊ ሀይል በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ስልጣኑን ለፕሬዚዳንቱ እንዲመልስ ቀነ ገደብ አስቀምጦ ነበር። ይም ሆኖ የኒጀር ወታደራዊ ሀይል  የቀረበውን ሃሳብ ወደ ጎን በመተው በቀድሞው ፕሬዝዳንት ማማዱ ታንጃ መንግስት የኒጀር የኢኮኖሚ እና ፋይናንስ ሚኒስትር የነበሩትን እና በአሁኑ ጊዜ በቻድ ውስጥ በአፍሪካ ልማት ባንክ የምጣኔ ሀብት ባለሙያ ሆነው የሚሰሩትን ላሚን ዘይኔ አሊ መሃማን አዲስ ጠቅላይ ሚንስትር አድርጎ መሾሙን ያለፈው ሳምንት ይፋ አድርጓል።ነገሩ ያሳሰበው የምዕራብ አፍሪካ ኢኮኖሚ ማህበረሰብ (ECOWAS) ያለፈው ሀሙስ በናይጄሪያ ዋና ከተማ አቡጃ የአባል ሀገራቱን መሪዎች በመያዝ አስቸኳይ ጉባኤ አድርጓል። የኒጀር ወታደራዊ ኹንታ ከስልጣን ያወረዳቸውን ፕሬዝዳንት መልሶ ስልጣን ላይ እንዲያስቀምጥ የሰጡት የጊዜ ገደብ ማብቃቱን ተከትሎ ባካሄዱት በዚህ  ጉባኤ፤ የኒጀሩን ቀውስ ለመፍታት ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት ይልቅ በዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች እንደሚገፉ ተናግረዋል። የወቅቱ የኤኮዋስ ሊቀመንበር የናይጀሪያው ፕሬዝዳንት ቦላ አህመድ ቲኑቡ ለዲፕሎማሲያዊ ድርድሮች እና ለውይይት ቅድሚያ  መስጠት ወሳኝ ነው ሲሉ ጉባኤው ከመጀመሩ በፊት ተናግረዋል ። 
«የመፈንቅለ-መንግሥቱን መሪዎች ጨምሮ ሁሉም ወገኖች ፣ሥልጣን እንዲለቁና ፕሬዝዳንት ባዙምን ወደ ስልጣን እንዲመልሱ ለማሳመን በምር ውይይት ማሳተፍ አለብን። በኒዠር ሕገ መንግሥታዊ አስተዳደር   በአስቸኳይ እንዲሰፍን ለማረጋገጥ ሁሉንም መንገዶች አሟጦ መጠቀም አለብን።»
ከአንድ ወር በፊት በትረ ስልጣኑን የተቆጣጠሩት የኒጀር መፈንቅለ መንግስት መሪዎች ግን የኤኮዋስ ጉባኤ በተጀመረበት ያለፈው ሀሙስ 21 ሚኒስትሮችን ሰይመው አዲስ መንግስት መመስረታቸውን ይፋ አድርገዋል።ድርጅቱ የኒጀርን ፖለቲካዊ ቀውስ በ ዲፕሎማሲ ለመፍታት እንደሚፈልግ ሲገልፅ  የቆየው  ቢሆንም ፣ በአቡጃ በተደረገው አስቸኳይ ጉባኤ  ማጠናቀቂያ ላይ ባወጣው መግለጫ  ግን «በኒጀር ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱን ወደ ነበረበት ለመመለስ» “የተጠባባቂ ሃይሉ” በተጠንቀቅ እንዲጠብቅ ትዕዛዝ  ማስተላለፉን የምዕራብ አፍሪቃ ሀገራት የኢኮኖሚ ማህበረሰብ  ኮሚሽን ፕሬዝዳንት፤ ኦማር ቱሬ ተናግረዋል። 
«የመከላከያ ጉዳዮች ዋና መመሪያ ሰጭ ኮሚቴ፤ በአስቸኳይ የምዕራብ አፍሪቃ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ /ECOWAS/ ተጠባባቂ ሃይል እንዲሰማራ አዟል።ይህም የኒጀር ሪፐብሊክ ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱን ወደ ነበረበት ለመመለስ ነው ።»ኒዠር፦ የኢኮዋስ ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት ይሳካ ይሆን?
ይሁን እንጅ  እንደ ቀጠናዊ የሰላም አስከባሪ እና የሽብርተኝነት ስጋትን እንዲሁም በምዕራብ አፍሪካ ያለውን ኢ-ህገመንግስታዊ የመንግስት ለውጥ ለመቀልበስ  የተቋቋመው የECOWAS ኃይል ፤መቼ ፣እንዴት እና ምን ያህል ሀይል በሀገሪቱ እንደሚያሰማራ ድርጅቱ በውል አልገለፀም።
ኢኮዋስ ከዚህ ቀደምም  በኒጀር  ማዕቀብ የጣለ ሲሆን፤ የድርጅቱን የወቅቱን  የመሪነት ቦታ የያዘችው ናይጄሪያም ለኒጄር የምትሰጠውን የኤሌክትሪክ አቅርቦት አቋርጣለች።
 ከጋና አክራ ፤ የሰላም እና ጸጥታ ተንታኝ ኢማኑኤል ቤንሳህ ለDW እንደተናገሩት የአሁኑ የኢኮዋስ መሪ የናይጄሪያው ፕሬዝዳንት ቦላ ቲኑቡ  አንዳንድ ውሳኔዎችን ለማድረግ ቸኩለዋል ባይ ናቸው።
«እንደማስበው አንዳንዶቻችን የሚሰማን የመፈንቅለ መንግሥቱን ግርግር  እንዲያበቃ በማድረግ ተፈላጊ እና አግባብነት ያለው ሰው ለመሆን ወደሚፈልገው  ቦታ በችኮላ ለመግባት እየሞከረ  መሆኑን ነው። ነገር ግን ይህንን ብቻውን ማድረግ አይችሉም።»
ተንታኙ አያይዘውም በሀገሪቱ  ወታደራዊ ሀይል ከማሰማራት ይልቅ አሁንም ቢሆን ዲፕሎማሲያዊ ጥረት እንዲደረግ ይመክራሉ።ለኒጀር ምን መፍትሄ ይገኝ ይሆን ?
«ኢኮዋስ በአሁኑ ጊዜ በጥሩ ሁኔታ ላይ አይደለም።ምንም እንኳ ድርጅቱ አሁንም  ጥሩ  ከበሬታ  አላቸው ከሚባሉት ውስጥ አንዱ ቢሆንም፣ ነገሮችን በእርጋታ እናድርጋቸው  ዲፕሎማሲም እንከተል።»
ሩሲያ በበኩሏ መፈንቅለ መንግስቱን ተከትሎ ወደ ኒጄር ወታደራዊ ሀይል ማሰማራት ሀገሪቱን ለማያባራ ግጭት መዳረግ ነው በማለት  አስጠንቅቃለች።
በመፈንቅለ መንግስት ስልጣን በያዙ ወታደራዊ መንግስታት የሚገዙት የኒጀር ጎረቤት ሀገራት  ማሊ እና ቡርኪናፋሶም በኒጀር ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት ማድረግ በአገሮቻቸው ላይ ጦርነት  እንደ ማወጅ  ይቆጠራል ብለዋል። 
የኒጀር መፈንቅለ መንግስት መሪዎችም ያለፈው ማክሰኞ  የኤኮዋስ፣ የተባበሩት መንግስታት እና የአፍሪካ ህብረት ተወካዮችን ያካተተ ጥምር ቡድን ወደ አገሪቱ ለመላክ የቀረበውን ጥያቄ ውድቅ አድርገዋል።
አንድ የኒያሚ ነዋሪም ዲፕሎማሲያዊ ጥረት እንዲቀጥል  መፈለጋቸውን ይናገራሉ።
«እንደማስበው ፖለቲከኞች ወታደራዊ ጣልቃገብነት ሳይሆን የፖለቲካ መፍትሄ ቢያደርጉ የተሻለ ነው።» 
በጎርጎሪያኑ ግንቦት  28 ቀን 1975 ዓ/ም የተመሰረተው ኢኮዋስ 15 አባል ሀገራት ያሉት ሲሆን ከነዚህም ውስጥ ስምንቱ ፈረንሳይኛ ፣ አምስቱ እንግሊዘኛ ሁለቱ ደግሞ የፖርቹጋል ቋንቋ  ተናጋሪዎች ናቸው።
ወደ 400 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች  መኖሪያ በሆነው በዚህ ክልል፤ህብረቱ የሰዎች እና የሸቀጦችን ነፃ እንቅስቃሴ በማመቻቸት አባላቱ በኢኮኖሚ ራሳቸውን እንዲችሉ  ለማድረግ ይሰራል። ከዚህ በተጨማሪም የፖለቲካ አለመረጋጋት ሲያጋጥም የአባል ሀገራቱን የጋራ ወታደራዊ ሃይሎችን በመላክ  እና ጣልቃ በመግባት በአካባቢው የሰላም አስከባሪ ኃይል ሆኖ ያገለግላል።
ከዚህ አኳያ ድርጅቱ በጎርጎሪያኑ በ1990 ዓ/ም በላይቤሪያ የነበረውን አስከፊ የእርስ በርስ ጦርነት ለማስቆም የሰላም አስከባሪ ሃይልን አሰማርቷል።
በግንቦት 2012 በጊኒ ቢሳው ፣በጥር 2017 በጋምቢያ ሀይል አስገብቷል።ባለፈው አመትም ፕሬዝደንት ኡማሮ ሲሶኮ ኢምባሎን ከስልጣን ለማውረድ በተደረገ ሙከራ ጊኒ ቢሳውን ለማረጋጋት ከናይጄሪያ፣ሴኔጋል፣አይቮሪ ኮስት እና ጋና   የተውጣጡ 600 ወታደሮችን አሰማርቷል ።
ነገር ግን ታዛቢዎች እንደሚሉት ECOWAS ትልቁ የማስገደጃ መሳሪያው አባል ሀገራትን ማገድ ሲሆን፤እስካሁን  ማሊ፣ ጊኒ፣ ቡርኪናፋሶ እና በአሁኑ ወቅት ደግሞ ኒጀር በየሀገራቱ የተካሄዱ መፈንቅለ መንግስቶችን ተከትሎ ከአባልነት አግዷል።

የምዕራብ አፍሪቃ የኤኮኖሚ ማኅበረሰብ ጉባኤ በናይጄሪያ ኣ,ቡጃ ምስል Gbemiga Olamikan/AP/picture alliance
የኤኮዋስ ፕሬዚዳንት ኦማር ቱሬ እና የኤኮዋስ ጉባኤ ተሳታፊዎች /ከግራ ወደ ቀኝ/ምስል KOLA SULAIMON/AFP
የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት ቦላ ቲንቡምስል Gbemiga Olamikan/AP/dpa/picture alliance
አሊ ላሚኒ ዛይን የቀድሞ የኒጄር የኤኮኖሚ እና የገንዘብ ሚንስቴርምስል Karen Bleier/AFP/Getty Images
የኒጄር ፕሬዚዳንት ሙሀመድ ባዙምምስል Boureima Hama/AFP/AP/dpa/picture allaince

 

ፀሀይ ጫኔ

እሸቴ በቀለ

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW