1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የምዕራብ ጀርመኑ የኖርድራይንቬስትፋለን ፌደራዊ ክፍለ ግዛት የአካባቢ ምርጫ ውጤት

ኂሩት መለሰ
ማክሰኞ፣ መስከረም 6 2018

ባለፈው እሁድ በምዕራብ ጀርመኑ የኖርድራንቬስትፋለን ፌደራዊ ክፍለ ግዛት የተካሄደው ምርጫ በፌደራል መንግሥቱ ላይ የሚያስከትላቸው ምንም ዓይነት መዘዞች አይኖሩም ፤ ግን አዲሱ የጀርመን ጥምር መንግሥት በጎርጎሮሳዊው ግንቦት 6 ቀን 2025 ዓ.ም. ከተመሰረተ ወዲህ የሜርስና የመንግሥታቸው የመጀመሪያው አስፈላጊ የህዝብ አስተያየት መፈተሻ ሆኗል ።

የኖርድራይን ፌደራዊ ክፍለ ግዛት ጠቅላይ ሚኒስትር ሄንድሪክ ቩስት ፓርቲያቸው የአካባቢውን ምርጫ በማሸነፉ እጃቸውን ከፍ አድርገው ደስታቸውን ሲገልጹ
የኖርድራይን ፌደራዊ ክፍለ ግዛት ጠቅላይ ሚኒስትር ሄንድሪክ ቩስት ፓርቲያቸው የአካባቢውን ምርጫ በማሸነፉ እጃቸውን ከፍ አድርገው ደስታቸውን ሲገልጹምስል፦ Revierfoto/IMAGO

የምዕራብ ጀርመኑ የኖርድራይንቬስትፋለን ፌደራዊ ክፍለ ግዛት የአካባቢ ምርጫ ውጤትና አንድምታው

This browser does not support the audio element.

ባለፈው እሁድ  በምዕራብ ጀርመኑ በኖርድራይን ቬስትፋለን ፌደራዊ ክፍለ ግዛት በተካሄደው የምክር ቤትና የከንቲባዎች አካባቢያዊ ምርጫ ቁጥሩ ወደ 13.7 ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝብ ድምጽ ሰጥቷል። በዚህ ክፍለ ግዛት ቁጥሩ 18 ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝብ ይኖራል። በምርጫም ወግ አጥባቂው የክርስቲያን ዴሞክራት ኅብረት ፓርቲ አብላጫ ድምጽ በማግኘት አሸንፏል። ውጤቱ ለፓርቲው በተለይም ከጥቂት ወራት በፊት የሀገሪቱ መራኄ መንግስት ሆነው ለተመረጡት የፓርቲው ሊቀ መንበር ፍሪድሪሽ ሜርስ ፈተናውን ያለፉበት ትልቅ ድል ተደርጎ ተወስዷል።

ሆኖም የጥምሩ መንግስት አካል የሆነው የመሀል ግራው የሶሻል ዴሞክራቶቹ ፓርቲ በጀርመንኛው ምህጻር SPD በዚህ ምርጫ ያገኘው ውጤት አነስተኛ መሆን እንደቀድሞው ማነጋገሩ አልቀረም። የአካባቢ ጥበቃ ተሟጋቹ የአረንጓዴዎቹ ፓርቲ ደግሞ ከSPD የባሰ አይሸነፉ ሽንፈት ሽንፈት ገጥሞታል። 

ምንም እንኳን በዚህ ወሳኝ በተባለ ምርጫ ወግ አጥባቂው CDU ቢያሸንፍም «ቅድሚያ ለጀርመን» የሚለው መጤ ጠል ተብሎ የሚጠራው «አማራጭ ለጀርመን» በጀርመንኛ AfD የተሰኘው ፓርቲ ግን ብዙ አትርፏል። የዚህ ፓርቲ ደጋፊዎች ቁጥር እየጨመረ ቢሄድም ፓርቲውን የሚቃወሙትም ቁጥርም ቀላል አይደለም። ከመካከላቸው አንዱ እኚህ አስተያየት ሰጭ ናቸው።ለምን ሊመርጡ እንደመጡ ሲጠየቁ AfD እድሉን eንዳያገኝ ብለው መሆኑን ተናግረዋል።

« ትልቁ የምጠብቀው ነገር ሰማያዊ መለያ ቀለም ያለው AfD እዚህ ምንም እድል የለውም። ይህ ነው እኛ ትኩረት ሰጥተን የምንጠብቀው።  ለዚህም ነው በጠዋት ተንስተን በጥሩ መንፈስ ልንመርጥ የመጣነው። ይህ ትልቁ ስጋታችን ነው። ችግሮች ቢኖሩም እንኳን ችግሩ ምን ላይ እንደሆነ ከመፈለግ ይልቅ ህዝብን በህብ ላይ የሚያነሳሱ ናቸው። እንደዚህ ያለ ፓርቲ አንፈልግም።ለዚህም ነው ለምርጫ የወጣነው።» 

ሌላዋ አስተያየት ሰጭ ደግሞ በአካባቢያቸው ለአዛውንቶች ትኩረት እንዲሰጥ እንደሚፈልጉ ከነምክንያታቸው ተናግረዋል።
«ድዩስቡርግ አካባቢ በሚገኘው በኖይንካምፕ ለአዛውንቶች አንድ ነገር መደረግ አለበት መንገዶቹ ለአዛውንቶች አይመቹም ፤ ያደናቅፋሉ። እንደሚመስለኝ አዛውንቶች ተረስተዋል። በድዩስቡርግ ብዙ ተሰርቷል። የምጠብቀው ትናንሽ ነገሮችን ነው። እንደሚመስለኝ አዛውንቶች ተረስተዋል። በዲዩስቡርግ ብዙ ይሰራል። ይህ በጣም ትልቅ ነገር ነው። ሆኖም ለአዛውንቶች ይሄ ተደረገ ተብሎ የተጻፈ ግን አላነበብኩም። በእድሜ የገፉ በጥቂቱም ቢሆን መዝናናት ምቹ የሆኑ ነገሮችን የማግኘት መብት አላቸው ።ያንን እንጠብቃለን።»

መራኄ መንግሥት ፍሪድሪሽ ሜርስና የኖርድራይን ቬስትፋለን ጠቅላይ ሚኒስትር ሄንድሪክ ቩስትምስል፦ Bonn.digital/IMAGO

የምዕራብ ጀርመን ግዛቶች ምርጫ የሀገሪቱን አቅጣጫ የሚወስን ህዝበ ውሳኔ 

ከመራጮች አስተያየትወደ ምርጫው ውጤትና አንድምታው ስንመለስ በምርጫው ውጤት መሠረት ወግ አጥባቂው የክርስቲያን ዴሞክራት ኅብረት ፓርቲ33.3 በመቶ ድምጽ በማሸነፍ ቀዳሚውን ቦታ ሲይዝ የሶሻል ዴሞክራቶቹ ፓርቲ ደግሞ በ22.1 በመቶ ድምጽ ሁለተኛ ሆኗል። አማራጭ ለጀርመን AfD 14.5 በመቶ ፣የአረንጓዴዎቹ ፓርቲ ደግሞ 13.5 በመቶ ድምጽ አግኝተዋል። AfD የአረንጓዴዎቹን ፓርቲ ሲበልጥ የአሁኑ የመጀመሪያው አይደለም። ባለፈው የካቲት በተካሄደው የጀርመን አጠቃላይ ምርጫም ፓርቲው የአረንጓዴዎቹን ፓርቲ በልጦ ነበር ።

እናም በእሁዱ ምርጫ ቀላል የማይባል ድምጽ የተነፈጉት አረንጓዴዎቹ በግልጽ ተሸናፊ ሲሆኑ፣ AFD ግን በዚሁ ግዛት ከአምስት ዓመት በፊት ማለትም በጎርጎሮሳዊው 2020 ካገኘው ካለፈው ወደ ሦስት እጥፍ የሚበልጥ ተጨማሪ ድምጽ አሸንፏል። ይህም በምርጫው ከተወዳደሩት ከሌሎቹ ፓርቲዎች ጋር ሲነጻጸር አሁን በመረጠው ህዝብ ቁጥር ማደግ አሸናፊ ተብሏል።

በኖርድራይን ቬስትፋለን የAfD መሪ ማርቲን ቨንሴንትስ ምርጫውን ሀገሪቱ በምትከተለው አቅጣጫ ላይ የተካሄደ ህዝበ ውሳኔ ብለውታል። የተሸነፉትን ፓርቲዎችም «ለመራጮች ፍላጎት ጆሮ ያልሰጠ በመራጮች ይቀጣል ።» ሲሉ ወርፈዋቸዋል።  በኖርድራይን ቬስትፋለን ምክር ቤት የጌልዝንኪርሸን የህዝብ ተወካይ የAfD ፓርቲ አባል ኤንዚ ሴሊ ዛካርያስ ፓርቲያቸውን በግዛቱ መራጮቹን ያጠናከረ ሲሉ አወድሰዋል።

« ለAfD በጣም ግልጽ የሆነው መራጮቻችንን አጠናክረናል። ያገኘነው የተበሳጩ ሰዎችን ድምጽ አይደለም፤ ወይም ስልታዊ አቀራረብ አይደለም። ይልቁንም መራጮቻችንን አጠናክረናል።  አካባቢያዊ ምርጫም የሚያሳየው ይህኑኑ ነው።»

«ቅድምያ ለሀገራችን» የሚለው አማራጭ ለጀርመን በምህፃሩ AFD በምርጫ ዘመቻ ላይምስል፦ Oliver Mueller/Funke Foto Services/imago images

ከጎርጎሮሳዊው 2020 ወዲህ በጀርመን ምን ተለውጧል?

የዶቼቬለው የየንስ ቱራው  የእሁዱን ምርጫ ውጤት ለመገምገም ከዛሬ አምስት ዓመቱ ምርጫ ውጤት ጋር ማነጻጸር አያስፈልግም ይላል ። በ2020 ጀርመን በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ውስጥ  ነበረች።ያኔ AfD እንደ አሁኑ በሀገሪቱ ያን ያህል ታዋቂ አልነበረም። ከዚያ በቀጠሉት ዓመታት የኖርድ ራይን ቬስትፋለን ግዛት ህዝብ መጀመሪያ ፣የሶሻል ዴሞክራቶች የአረንጓዴዎቹ እና የነጻ ዴሞክራቶቹ ፓርቲ የተጣመሩበት የፌደራል መንግስት ሦስቱንም ወገኖች ከፍተኛ ድጋፍ ካሳጣ መራር ውዝግብ በኋላ ሲወድቅ አይቷል ።

በወቅቱ የመኖሪያ ቤት እጥረት፣ የሀገር ውስጥ ፀጥታ እና የተገን አሰጣጥ ፖሊሲ አስፈላጊ የነበሩ ቢሆንም እንደአሁኑ ግን አልገዘፉም። በ2020 የዩክሬኑ ጦርነት አልተጀመረም የመካከለኛው ምሥራቅ ግጭትም አልተባባሰም። በሌላ አነጋገር፣ ዛሬ በጀርመን ዜጎች ላይ ስጋት ያስከተሉት አብዛኛዎቹ ጉዳዮች በ2020 አልነበሩም። 

የተወሰነው ክፍሉ በኖርድራይን ቬስት ፋለን በሚገኘው አህር በተባለ ሸለቆ በጎርጎሮሳዊው ሐምሌ 2021 ዓ.ም. የደረሰውና የ135 ሰዎችን ሕይወት ያጠፋው የጎርፍ አደጋ በርካታ ንብረቶችን አውድሟል። ያኔ አደገኛው ጎርፍ ያስከተለው ጥፋት መዘዞች እስካሁን ድረስ ሙሉ በሙሉ አልተወገዱም። ይህንንም AfD ዐብይ መቀስቀሻ በማድረግ ሊጠቀምበት ችሏል። የእሁዱ ምርጫ ውጤት ለአሸናፊው ለክርስቲያን ዴሞክራት ኅብረት ፓርቲ CDU አስደሳች ቢሆን  ማሳሰቡ ግን አልቀረም።

የኖርድራይን ቬስትላፈን  ጠቅላይ ሚኒስትር ሄንድሪክ ቩስት ይህንኑ ስጋታቸውን ባለፈው እሁድ ሲገልጹ «ፓርቲያቸው አሸናፊ ቢሆንም ጉዳዩ እንዲሁ ሊተው የሚጋባ እንዳይደለ ተናግረዋል።  ያገኙትን ውጤት ግን ህዝቡ በድጋሚ ያበረከተልን ስጦታ ሲሉ ማወደሳቸው አልቀረም።

"ይህ ድንቅ የምርጫ ውጤት ለተግባራዊ መፍትሄ-ተኮር የመሀል ፖለቲካ የተሰጠ ግልጽ የሆነ ድምጽ ነው። ሁላችንም በናርድራይን-ቬስትፋሊያ፣ በናርድራይን-ቬስትፋሊያ በማንኛውም ደረጃ የሚገኝ CDU ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ ታላቅ ስራ ሰርተናል። እና ዛሬ መራጮች ይህንን በድጋሚ ሸልመውናል." ድኅነትንና ፍልሰትን በሚመለከት ትክክለኛው መልስ ምንድነው ማኅበራዊ ስርዓታችንስ እውነት ፍትሀዊ ነውን ሲሉም ቩስት ጥያቄ አንስተዋል። በዋነኝነት AfD ተጠናክሮ መውጣቱ ከምንም በላይ የሚያሳየው የተቃውሞ ድምጽ ነው ብለው እንደሚያምኑም ተናግረዋል። 

በኖርድራይንቬስትፋለኑ የአካባቢ ምርጫ የተወዳደሩ ፓርቲዎች የምርጫ መወደደሪያ ማስታወቂያዎች ምስል፦ Christoph Hardt/Panama Pictures/picture alliance

CDU እና እህት ፓርቲው የክርስቲያን ሶሻል ኅብረት ፓርቲ CSU ከሶሻል ዴሞክራቶቹ ፓርቲ ጋር ተጣምረው የመሰረቱት አዲሱ የፌደራል ጀርመን መንግስት የዶቼቬለው የንስ ቱራው እንደዘገበው ፍሪድሪሽ ሜርስ ባለፈው ግንቦት መራኄ-መንግስት ሆነው ከተመረጡ በኋላ በህዝብ ዘንድ ያለው ተቀባይነት ቀንሷል።  እናም ኔዘርናላንድስ እና ቤልጅየምን በሚያዋስነው የኖርድራይን ቬስትፋለን ግዛት የተካሄደው የአሁኑ የአካባቢ ምርጫ ውጤት በተለይ ከዚሁ ግዛት ለተገኙት ለመራኄ መንግሥት ሜርስ ጠቃሚ ሆኖ ተገኝቷል።

በህዝብ ብዛት ከጀርመን ፌደራዊ ክፍለ ግዛቶች 4ተኛ ደረጃ በያዘው በምዕራብ ጀርመን የሚገኘው የኖርድራይን ቬስትፋለን ፌደራዊ ክፍለግዛት ባለፈው እሁድ የተካሄደው ምርጫ የሜርስ አገዛዝ መፈተኛ ነበር። ሜርስ ቀኝ ጽንፈኛው AfD የተሻለ ውጤት እንደሚያስመዘግብ ጠብቀው ነበር። ባለፈው ሳምንት ከምርጫው በፊት እንደተናገሩት  የተሻለ የምርጫ ዘመቻ ለማካሄድ  እና ትኩረት ሊሰጧቸው የሚገቡ ጉዳዮችንም ለመለየት እሁድና ሰኞ የምርጫውን ውጤት በጥሞና መርምረው እንደሚወስኑ ተናግረዋል።

ኂሩት መለሰ 

ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር 
 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW