የምዕራብ ጀርመኑ የጎርፍ አደጋ
ማክሰኞ፣ ሐምሌ 13 2013ጀርመንን ጨምሮ ሌሎች የሰሜን ምዕራብ አውሮጳ ሃገራትን ባለፈው ሳምንት ያጥለቀለቀው ጎርፍ ከገደላቸው ሰዎችና ካወደማቸው ቤቶች ሌላ መሠረተ ልማቶችንም እንዳልነበሩ አድርጓል። የአየር ንብረት ቅድመ ትንቢያ የሚመለከታቸው መስሪያ ቤቶች አስቀድመው ስለ አደጋው ባለማስጠንቀቃቸው ጥያቄ ቀርቦባቸዋል። ፖለቲከኞችም ለአደጋው ሰለባዎች ተገቢውን ድጋፍ ባለመስጠት እየተወቀሱ ነው።ካለፉት ጥቂት ሳምንታት ወዲህ፣ በኮሮና ተኅዋሲ ምክንያት በጀርመን የተጣሉ ልዩ ልዩ ገደቦች ላልተው፣ህዝቡ ቀስ በቀስ ወደ ቀደመው የሕይወት ዘይቤው በመመለስ ላይ ነበር። በዚህ መሀል ድንገት ሳይታሰብ ባለፈው ሳምንት ምዕራብ ጀርመንን ያጥለቀለቀው ጎርፍ ዱብ እዳ ሆኖ ደስታውን ወደ ሃዘን ቀይሯል።በአደጋው ከ165 ሰዎች መሞታቸው ተረጋግጧል። የደረሱበት ያልታወቀም ጥቂት አይደሉም። በአደጋው ክፉኛ በተጎዳው በራይንላንድ ፋልስ ፌደራዊ ክፍለ ሃገር 117 ሰዎች ፣በጎረቤት ኖርድ ራይን ቬስት ፋለን ግዛት ደግሞ የ47 ሰዎች ሕይወት መጥፋቱ ትናንት ተረጋግጧል።በባይርን ፌደራዊ ክፍለ ሃገርም አንድ ሰው ሞቷል። በሕይወት ከተረፉትም ቤት ንብረታቸው እንዳልነበረ የሆነባቸው ብዙዎች ናቸው። ሬደ በኖርድራይን ቬስት ፋለን ክፍለ ሃገር ውስጥ የምትገኝ ትንሽ መንደር ናት። በዚያ ከሚገኙ ቤቶች ግማሹን የጎርፉ ማዕበል እንዳልነበሩ አድርጓቸዋል። ነዋሬዎቿም ዘመድ ወዳጅ ጋ አለያም ሆቴል እንደተጠለሉ ነው።ይህ ብቻ አይደለም ከረቡዕ አንስቶ እስከ ዛሬ እኩለ ቀን ድረስ በመንደርዋ መብራት ኢንተርኔት እና የመደበኛ ስልክ አገልግሎት እንደተቋረጠ ነው።ከጥቂት ቀናት ወዲህ ተንቀሳቃሽ ስልክ መስራት ጀምሯል።ከዚያ በፊት ከመንደሯ ውጭ ካሉ ሰዎች ጋር መገናኘት አይችሉም ነበር። ዛሬ ጠዋት በሞባይል ስልክ ያነጋገርኳቸው ዶክተር ሄርማን ዲስሙንድ ሬደ ሲኖሩ 60 ዓመት ሆኗቸዋል።ረቡዕ ለሊት በድንገት ጎርፍ ቤታቸውን ሰብሮ ከገባባቸው ነዋሪዎች አንዱ ናቸው። ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ የኖሩበትን ቤትና ልዩ ልዩ ንብረቶቻቸውን እንዳልነበረ አደርጎባቸዋል።አሁን ከቤታቸው ራቅ ያለ ስፍራ የሚኖሩ ጓደኛቸው ጋ ተጠግተዋል።የቤታቸውን ሁኔታ ለመከታተል በየቀኑ በቢስክሌት እየተመላለሱ ይመጣሉ።እንደዚህ ዓይነት የጎርፍ አደጋ በቴሌቪዥን እንጂ በዓይኔ አይቼ አላውቅም ይላሉ።
«ከዚህ ቀደም ህንድና ባንግላዴሽ ተከስቶ በቴሌቪዥን የምናየው ዓይነት ጎርፍ ነበር የገጠመን ቤቶች ተፈንቅለው የሚወሰዱበት መኪኖች ተጠራርገው ተወስደው አንዱ በአንዱ ላይ የተደራረበበት። እዚህ በአቅራቢያ ያለ አንድ ድልድይ ፈርሷል። በዚህ የተነሳ ከኛ መንደር ወደ ሌላኛው መሄድ አይቻልም።»
ከላፈው ረቡዕ በፊት በነበሩት ሁለት ቀናት ከባድ ዝናብ ጥሎ እንደነበር ዲስሙንድ ያስታውሳሉ።ረቡዕ ለሊት ግን ከተለያየ አቅጣጫ የመጣ ጎርፍ ቤታቸውን አጥለቀለቀው።
«ጨለምለም ሲል ዝናቡም መጣ ከዛ ከሙንስትር አይፍል በኩል ጎርፉ በአንዴ መጣ።የቤት እንሰሳት በረቱን በር በርግዶ ሁሉንም ጠራርጎ ወሰደው።ከዛ በቤቴ ቀኝና በስተግራ በኩል ሌላ ጎርፍ መጣ። የቤቴን በር ይዞት ሄደ ።ያኔ እድለኛ የሆነ ሰው የመጀመሪያው ፎቅ ላይ ብቻ በመውጣት ነበር ራሱን ማዳን የሚችለው።የእሳት አደጋም ማለፊያ ቦታ ስላጣ ወዴትም መሄድ አልቻለም።»
ከሬደ ነዋሪዎች ግማሹ የጎርፉ ሰለባ ሆነዋል እንደ ዶክተር ዲስሙንድ ።400 ከሚሆኑት የመንደርዋ ነዋሪዎች ቢያንስ 200ው በአደጋው ተጎድተዋል። በዚህች ትንሽ መንደር በጎርፍ እንዳልነበሩ የሆኑት ቤቶች ቁጥር ከአንድ መቶ ይበልጣል ።ዶክተር ዲስሙንድ ፣በአደጋው ምድር ቤት ያሉት ክፍሎች በሙሉ በጎርፉ ወድመውባቸዋል። የኤሌክትሮኒክስ የቤት እቃዎቻቸውን ጨምሮ ሌሎችም ንብረቶቻቸው በሙሉ ከአገልግሎት ውጭ ሆነዋል።ከዚህ ሌላ በመንደሪቷ መብራትና ስልክ አለመኖሩ በሌሎች አገልግሎቶችም ላይ ችግር አስከትሏል።
«በመንደሪቷ መብራትና የመደበኛ ስልክ አገልግሎት እንዲሁም ኢንተርኔት ባለመኖሩ ከባንክም ገንዘብ ማውጣት አይቻልም ።በአብዛኞቹ ሱቆች ግብይት የሚካሄደው በጥሪ ገንዘብ ነው። አሁን የሞባይል ስልክ በከፊል መስራት ጀምሯል።ኤሌክትሪክ ስለሌለ የቤት ስልክና የኢንተርኔት አገልግሎት እንደተቋረጠ ነው። አይሰራም ።»
ኢቮን ትሪምቦን የዶክተር ዲስሙንድ ጎረቤት ናቸው። እርሳቸውም ረቡዕ ለሊት የገጠማቸው አይተውም ሰምተውም የማያውቁት ነው።ወሐው ድንገት እስከ አንገታቸው ደርሶ ነበር።
«ጎርፉ ቤቴ ውስጥ ገባ።እኔ ያኔ ከውሾቼ ጋር ላይ ቤት ነበርኩ።ከዛ እየባሰበት ሲሄድ ከነሱ ጋር ወደ ውጭ ዋኝቼ ወጣሁ ከኛ ቤት ጎን አንድ ትንሽ ፀሎት ቤት ነበረች እዛ ጋ ሄጄ ተቀመጥኩ እና ሰው አልነበረም ኋላ ላይ ግን አንድ ሰው በመኪና መጣና አቁሞ ቤተሰቦቼ ጋ ስልክ እንድደውል ተባበረኝ እና እነርሱም መጥተው ከዛ ወሰዱኝ ይሄ የሆነው ደግሞ እሮብ ለሊት ለሐሙስ አጥቢያ ነው።»
ምድር ቤታቸው በውሐ የተዋጠው ትሪንቦን አሁን አያታቸው ጋር ነው ያሉት።ትሪምቦንም ዶክተር ዲስሙንድም እስካሁን ከመንግሥት ምንም ዓይነት እርዳታ አለማግኘታቸውን ነው የሚናገሩት።በሬደ ለጎርፉ ሰለባዎች የተዘጋጀ ጊዜያዊ መጠለያም የለም።አስቀድሞ አካባቢውን ለቅቀው እንዲወጡ አለመደረጉንና ማስጠንቀቂያም እንዳልደረሳቸው ነው ያስረዱት።የጎርፍ አደጋ በደረሰባቸው አካባቢዎች በሙሉ የማስጠንቀቂያው ስርዓት አስቀድሞ የአየር ትንበያውን አለማሳወቁ ከፍተኛ ትችት ገጥሞታል።የአደጋው መጠን ግልጽ እየሆነ በመጣበት በአሁኑ ጊዜ ነዋሪዎችን አስቀድሞ ለማስጠንቀቂያ በቂ ጥረት ተደርጓል ወይ የሚለው ጥያቄ መነሳቱ ቀጥሏል።ባለሞያዎቹ ራሳቸውን ለመከላከል ልዩ ልዩ ምክንያቶችን እያቀረቡ ቢሆንም የሰማቸው የለም።የጀርመን መንግሥት በጎርፉ ጉዳት የደረሰባቸውን መሰረተ ልማት መልሶ ለመገንባት አቅዷል። ከአውሮጳ ኅብረት ይገኛል ተብሎ የሚጠበቀውን እርዳታ ግምት ውስጥ ባስገባው በዚህ እቅድ ከመንግሥት በኩል 200 ሚሊዮን ዩሮ ወይም 236 ሚሊዮን ዶላር አስቸኳይ እርዳታ ለማቅረብ ታስቧል።አስራ ስድስቱ የጀርመን ፌደራል ክፍለ ግዛቶች 200 ሚሊዮን ዩሮ ከሰጡ ደግሞ በአጠቃላይ 400 ሚሊዮን ዩሮ ወይም 470 ሚሊዮን ዶላር ለአስቸኳይ እርዳታ እንደሚውል ነው የተነገረው። የእቅዱ ረቂቅ ነገ ለመንግሥት ካቢኔ አባላት ይቀርባል ተብሏል።መንግሥት፣ የአውሮጳ ኅብረት በተፈጥሮ አደጋ የተጎዱ የኅብረቱን አባል ሃገራት ለመርዳት የሚውለው ገንዘብ እንዲሰጠው ማመልከቻ ያስገባል።የጀርመን አጠጠቃላይ ምርጫ ሁለት ወራት በቀሩት በአሁኑ ጊዜ የመራኂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል መንግሥት የተጎዱ ቤቶችን ለመጠገን ሰዎችም ወደ ቀድሞ ሕይወታቸው እንዲመለሱ ለማገዝ የታቸለውን ሁሉ ጥረት እያደረገ መሆኑን ለማሳየት የፈለገ ይመስላል ።ዛሬ በአደጋው ከተጎዱ አካባቢዎች በኖርድ ራይን ቬስትፋለን የሚገኘውን ባድ ሙንስተርአይፍልን የጎበኙት ሜርክል ገንዘቡ ለተጎጂዎች እንዲደርስ የተቻለው ሁሉ ጥረት እንደሚደረግ ተናግረዋል።ግን ሁሉም ቀላይ አይሆንም ነው ያሉት።
« ከለበሱት ልብስ በስተቀር በእጃቸው ምንም ነገር የሌላቸውን ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን ለመርዳት ገንዘቡ በፍጥነት እንዲመጣ ከናንተ ጋር የተቻለንን ሁሉ እናደርጋለን።ሆኖም አንዳንዶቹ ጉዳዮች ለወራት ብቻ የምንጠይቃቸው አይሆኑም።ምን ያህል ድልድዮች እንደወደሙ ብታዩ ይህ ከጥቂት ወራት በላይ የሚወስድ ነው።»
የተጨማሪ አስከሬን ፍለጋው እንደቀጠለ ነው።በራይንላንድ ፋልስ የደረሱበት ያልታወቀ 170 ሰዎች ፍለጋ መቀጠሉን የኮብሌንዝ ፖሊስ አስታውቋል። ያለፈው ሳምንቱ ጎርፍ በምዕራብ አውሮጳ የተለያዩ ከተሞች በአጠቃላይ የ196 ሰዎችን ሕይወት ነው ያጠፋው። በጎረቤት ቤልጂግም ቢያንስ 31 ሰዎች ሞተዋል።በኔዘርላንድስም እንዲሁ የሰዎች ሕይወት ጠፍቷል።በቤልጅየም የደረሱበት ያልታወቀው ቁጥር ደግሞ ከ160 ወደ 70 ዝቅ ብሏል።በአደጋው የሞቱት ዛሬ ታስበዋል።
የጎርፉ አደጋ ሰለባዎች ትሪንቦንም ሆኑ ዶክተር ዲስሙንድ እንደሚሉት አንዳንድ ችግሮቻቸው ፋታ የሚሰጡ አይደሉም።በአፋጣኝ መብራት ያስፈልጋቸዋል። ቤታቸው የገባው ወሐ ያስከተለውን እርጥበት የሚያደርቅ መሣሪያ ከምንም በላይ አስፈላጊ ነው።ታዲያ እነዚህ መሠረታዊ ያሏቸው ጉዳዮች እንዳሰቡት ይሟሉላቸው ይሆን?አሁንም በጥያቄ ምልክት ያለ ጉዳይ ነው። ለአሁኑ ግን የአካባቢ ጥበቃ ባለሞያዎች ሰሜን ምዕራብ አውሮጳን ያጥለቀለቀው ጎርፍ የአየር ንብረት ለውጥ ማስጠንቀቂያ መሆኑን ልንረዳ ይገባል እያሉ ነው። በነርሱ አስተያየት የችግሩ መከላከያ ከወዲሁ ሊታሰብበት ይገባል።
ኂሩት መለሰ
ነጋሽ መሐመድ