የምግብ ሸቀጦች ዋጋ ማሻቀብበአማራ ክልል
ቅዳሜ፣ ሰኔ 7 2017
በአማራ ክልል የአንዳንድ የምግብ ሸቀጦች ዋጋ በእጅጉ ማሻቀቡን ነዋሪዎች እየተናገሩ ነው፣ አንድ የገበያ ጥናት ባለሙያ “የተወሰኑ የምግብ ሸቀጦች የዋጋ ጭማሪ አሳይተዋል” ብለዋል፣ የአማራ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ በበኩሉ ተገቢ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ በሚያሳዩ አካላት ላይ እርምጃ እንደሚወስድ አስጠንቅቋል፡፡
የአንዳንድ የምግብ ሽቀጦች ዋጋ ማሻቀብ
በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በአንዳንድ የምግብ ሸቀጦች ላይ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ በመታየቱ ለብዙዎቹ ፈተና እንደሆነባቸው አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬሌ የተናገሩ ነዋሪዎች አመልክተዋል፡፡ወ/ሮ ሙሉ ሞገስ በዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር የሳህላ ሰየምት ወረዳ ነዋሪ ናቸው፣ የአንዳንድ ሸቀጦች ዋጋ በጣም ማሻቀቡን በስልክ ነግረውናል፡፡“1ኛ ደረጃ በርበሬ ተብሎ አንድ ኪሎግራም የሚሸጠው በ650 ብር ነው፣ “አንደኛ ደረጃ” የሚል ስያሜ ይሰጠው እንጂ ደረጃውም ቢሆን ያን ያክል አይደልም” ነው ያሉት፡፡ አንድ ሊትር ዘይት 300 ብር እየተሸጠ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡
በምዕራብ ጎጃም ዞን የፈረስ ቤት ከተማ ነዋሪ በርበሬ በአካባቢው በኪሎ የመሸጥ ልምድ ባይኖርም በባሀላዊ መገበያያ (መስፈሪያ) ቀድሞ ከነበረው ዋጋው በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን ይናገራሉ፣ የቡና ዋጋም ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ዋጋው ማደጉን አስረድተዋል፡፡
የ አንድ ኪሎግራም ቡና ዋጋ ከ900 ብር በላይ ሆኗል
ቡና ሁለተኛ ደረጃ የሚባለው በኪሎ እስከ 900 ብር እንደሚሸጥ ጠቁመው፣ የተሻለ ደረጃ የሜምጣ ከሆነ ዋጋው እዚህም ሊያድግ እንደሚችል አመልክተዋል፡፡
የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪ የሆኑት ወ/ሮ ሰገነት መኮንን እንዲሁ የኑሮው መወደድ ከቤት ኪራይና ሌሎች ወጪዎች ጋር ተዳምሮ ኑሮን አስቸጋሪ እንዳደረገባቸው ገልጠዋል፡፡በአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ አንድ የገበያ ጠናት ባለሙያ በአንዳንድ የመገብ ሸቀጦች ላይ የዋጋ ጭማሪ መኖሩን አረጋግጠዋል፡፡
80ሺህ የሚሆኑ የንግድ ተቋማት ጉድለት ታይቶባቸዋል
ለአማራ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ለሚመለከታቸው አካላት ተቸማሪ መረጃ እንዲሰጡን ስልክ ብንደውልም ስልካቸውን ሊያነሱልን አልቻሉም የሁን እንጂ የቢሮ ኃላፊው ዶ/ር ኢብራሒም መሐምድ በቅርቡ ለመገናኛ ብዙሐን በሰጡት መግለጫ፣ በህገወጥ መንገድ ገበያውን በሚረብሹ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ ተወስዷል፣ ይህ ወደፊትም ተጥናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡
“.. ህጋዊ ንግድን ለማስፋት የበር ለበር ቁጥጥር ይደረጋል፣ በዚህም እየተገባደደ ባለው በጀት ዓምት በ300 ሺህ የንግድ ተቋማት ላይ በተደረገ ፍተሻ፣ 80ሺህ በሚሆኑት የንግድ ተቋማት ላይ ጉድለት ተገኝቶባቸዋል፡፡” ብለዋል፡፡
ጉድልት ካሳዩ የንግድ ተቋማት መካከል የጅምላ ነጋዴዎች ቅድሚያውን እንደሚወስዱ ጠቁመው፣ እንደየጥፋታቸው መጠን እርምጃ መወሰዱንም ኃላፊው ገልጠዋል፣ ወደፊትም ገበያውን ለመረበሽ በሚሞክሩ አካላት ላይ እርማጃው እንደሚቀጥልና ወደ ህጋዊ አሰራር እንዲመለሱም ሥራዎች እንደሚሰሩ ነው ያብራሩት፡፡
ዓለምነው መኮንን
ሂሩት መለሰ
ፀሀይ ጫኔ