1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የምግብ ዋስትና ቀውስ ድሐ ሃገራትን ወደ ቻይና?

ሐሙስ፣ ሰኔ 23 2014

ዩክሬን ውስጥ በተቀሰቀሰው ጦርነት ምክንያት የተከሰተው የምግብ ዋጋ ንረት በርካታ ሰዎችን ወደ ጠኔ አፋፍ ገፍቷቸዋል። የG7 የበለጸጉት ሃገራት ቃል የገቡትን ርዳታ የማያቀርቡ ከኾነ ድሃ ሃገራት ዐይኖቻቸውን ወደ ሌላ አቅጣጫ ሊያማታትሩ ይችላሉ።

G7 und Partnerländer auf Schloss Elmau
ምስል Andrew Parsons/Avalon/picture alliance

180 ሚሊዮን ሰዎች ለምግብ ቀውስ ሊጋለጡ ይችላሉ

This browser does not support the audio element.

ዘንድሮ የቡድን 7 የበለጸጉ ሃገራት ጉባኤን ያስተናገደችው ጀርመን ውስጥ የተሰባሰቡ ሃገራት በዓለም ዙሪያ ያንዣበበው ረሐብ እጅግ እንዳሳሰባቸው ገልጠዋል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዓለም «ብርቱ የረሐብ ቀውስ» እንዳንዣበበባት በመግለጥ ሲያስጠነቅቅ ሰነባብቷል። በዓለማችን 180 ሚሊዮን ሰዎች በቀጣይ ስድስት ወራት ውስጥ ለምግብ ቀውስ ሊጋለጡ እንደሚችሉም ይኸው ዓለም አቀፍ ድርጅት ይፋ አድርጓል።

ከእነዚህ ውስጥ ኢትዮጵያ፤ የመን፤ ደቡብ ሱዳን፤ ሶማሊያ እና አፍጋኒስታን የሚኖሩ 750,000 ያህል ሰዎች ለጠኔ እና ሞት አደጋ መጋለጣቸውም ተዘግቧል። በዓለም ዙሪያ ድህነትን ለማዋጋት የተቋቋመው እና ዋን ካምፔይን የተባለው መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ኃላፊ ኤድዊን ኢኮሪያ፦ በርካታ የአፍሪቃ እና ሌሎች በዓለም ዙሪያ ያሉ ድሃ ሃገራት ውስጥ አደጋው ሌላም ጣጣ ሊያስከት እንደሚችል ጠቁመዋል።

«በእርግጥ ችግሩ በዓለም ዙሪያ ነው የተከሰተው። ግን እዚህ የዓመታዊ ገቢው ከፍተኛ ስለሆነ ሰዉ ከነገሮች ጋር ሁኔታዎችን ሊያመቻች ይችላል።  አንጡራቸውን በሙሉ ማለት በሚቻል መንገድ ለምግብ በሚያውሉ ድሐ ሃገራት ውስጥ ግን ከፍተኛ አደጋ ጋርጧል። አደጋውም የምር የማኅበራዊ ቀውስ እና አለመረጋጋትን ሊፈጥር ይችላል።»

ምስል Susan Walsh/AP/picture alliance

የረሐብ አደጋው በዓለም ዙሪያ ባሉ በተለይ በደሐ ሃገራት ላይ ሊከሰት እንደሚችል ከታወቀ ሰነባብቷል። ምክንያቱም የዝናም ወቅቱ በተደጋጋሚ ጊዜያት በተከታታይ ጭርሱኑ ስቷል። ዝናሙ አልፎ አልፎ ጠብ ቢል እንኳን እጅግ ከተጠበቀው በታች ነበር።  የኹኔታውን አስጊነት በመገንዘብ አቅም ያላቸው ሃገራት እና ተቋማት ረሐቡን ለመቀልበስ የርዳታ እጃቸውን ለመዘርጋት ቃል ከገቡ ሰነባብተዋል። የቡድን 7 የበለጸጉ ሃገራት በስብሰባቸው ወቅትም ኾነ ከዚያ በፊት ቃል መግባታቸው ብቻ በቂ አይደለም ይላሉ ኤድዊን ኢኮሪያ።

«ጉዳዩ ቃል ስለመግባት ብቻ አይደለም። ቃል የተገባውን በሚገባው ልክ ለመተግበር ዕቅድ ስለማውጣት እና ኹነኛ ንድፍ ስለማስቀመጥም ነው። ያንንም የምር መውሰድ አለባቸው።»

የበለጸጉት ሃገራት በዓለም ዙሪያ ስለሚያፈሱት መዋእለ ንዋይ አዲስ እቅዳቸውን በጉባኤያቸው ወቅት ይፋ አድርገዋል። ተጠቃሚ ሃገራት ግን አሁንም ድረስ ተጨባጭ ውጤቶችን ለማየት እየጠበቁ ነው ይላሉ ኤድዊን ኢኮሪያ። በተለይ አፍሪቃ አብዛኛው መሬቷ ማምረት እየቻለ በምግብ ራሷን አለመቻሏን ያጠይቃሉ።

«አፍሪቃ 60 ከመቶው የሚታረስ መሬት እያላት ዋነኛ ምግብ አስመጪ አኅጉር ናት። እውነታ ነው። ስርዓቱ እጅግ አስቀያሚ ነው። ሰዉ ከእነ ቤተሰቡ የሚያርሰው ከአንድ ኼክታር ባነሰች የበሬ ግንባር መሬት ነው። እና ታዲያ እንዴት ብለን ነው ራሳችንን መግበን ለሌላው ለመሸጥ የሚሆነውን ያህል ማምረት የምንችለው። ተግዳሮት ነው።»

ምስል Laily Rachev/Presidential Secretariat Press Bureau

የቡድን 7 የበለጸጉ ሃገራትን ጨምሮ ምዕራባውያን ሩስያ ዩክሬንን በመውረሯ ችግሮች መወሳሰባቸውን በማስረገጥ ሌሎች ሃገራትም በተቀናጀ መልኩ ተቃውሟቸውን እንዲያሰሙ ይሻሉ።  የዋን ካምፔይን ኃላፊው ኤድዊን ኢኮሪያ ግን በተለይ አፍሪቃውያን መቃወም ቢፈልጉ እንኳን አይችሉም ይህን ዕውነታ ምዕራባውያኑ በቅጡ አልተገነዘቡትም ባይ ናቸው።

«እውነቱን እንነጋገርና፤ አፍሪቃ ሩስያን ተቃውሟ መዝለቅ የምትችል ይመስላችኋል? ቻይናንስ ተቃውሟ ትችለዋለች ትላላችሁ? ምክንያቱም ያን ብታደርግ አፍሪቃውያንን ወዴት እንደሚወስዳቸው ታውቃላችሁ

ኢኮሪያ በጥያቄያቸው ብቻ አልተወሰኑም። አፍሪቃ በምታገኘው ርዳታ ብቻ ምንጊዜም ምዕራባውያንን ልትደግፍ ትችላለች የሚል የረዥም ጊዜ የተሳሳተ ግንዛቤ አለ ሲሉ ተችተዋል። ቻይና አፍሪቃ ውስጥ በምታፈሰው መጠነ ሰፊ መዋእለ ንዋይ እና ሩስያ ዩክሬንን በመውረሯ ያ ምልከታን ሳይቀይረው እንዳልቀረ አስምረውበታል። በዚህም አለ በዚያ የG7 የበለጸጉት ሃገራት ቃል የገቡትን ርዳታ በጊዜ የማያቀርቡ ከኾነ ድሃ ሃገራት ዐይኖቻቸውን ወደ ሌላ አቅጣጫ ማማተራቸው እንደማይቀር ተገልጧል።

ክሪስቲ ፕላድሰን /ማንተጋፍቶት ስለሺ

አዜብ ታደሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW