የምግብ ዋጋ ንረት ስጋት
ሐሙስ፣ ነሐሴ 10 2004አሜሪካና ህንድ በተከሰተው ድርቅ ምክንያት ብዙ ሰብል ሳይዝ በመቅረቱ አዲስ የምግብ ቀውስ ሊከተል ይችላል የሚል ስጋት አለ ። ድርቁን ተከትሎ የምግብ ዋጋ የመጨመሩ ስጋት አመዝኗል ። የምግብ ዋጋ አሁን ካለውም በላይ እንዳይንር አንዳንድ የጀርመን ባንኮች ከዚህ ቀደሙ ያደርጉት እንደነበረው የምግብ ዋጋ ግምት መስጠት አቁመዋል ። የጀርመኑ ኮሜርዝ ባንክ ለመሠረታዊ የምግብ ሸቀጦች እስካሁን ሲያቀርብ የነበረውን የዋጋ ግምት ለማቆም ወስኗል ። ባንኩ እዚህ ውሳኔ ላይ በመድረሱ ብዙ አድናቆት ተቸሮታል ። ፉድ ዋች የተባለው መንግሥታዊ ያልሆነው የምግብ ጉዳዮች ተከታታይ ድርጅት የኮሜርዝ ባንክን ውሳኔ ለሌሎች መስሪያ ቤቶችም አርአያ የሚሆን እርምጃ ሲል አወድሶታል ። በአለማችን የምግብ ቀውስ እ.ጎ.አ ከ 2008 ከተከሰተ ወዲህ ባንኮች የሚያቀርቡት የዋጋ ግምት ጠንካራ ትችት እየቀረበበበት ነው ። ባንኮችና የመሳሰሉት ተቋማት የሚሰጧቸው ግምቶች ዋጋ እያናሩ በአለም አቀፍ ደረጃም ረሃብን በማባባስ አሰተዋጽኦ በማድረግ እየተተቹ ነው ። በዚህ የተነሳም እንደ ተችቶቹ
ድሃው ምግብ የመግዛት አቅም አጥቷል ። የምግብ እህል ዋጋ ግምትን ለማቆም የወሰነው ኮሜርዝ ባንክ የዋጋ ግምት የሚያስከትላቸውን ችግሮች አስመልክቶ በባንኮች ላይ የሚሰነዘረው ወቀሳ ብዙም አላስደሰተውም ። ስለዚሁ ጉዳይ ማብራሪያ እንዲሰጥ ዶቼቬለ ቢጠይቅም ፈቃደኛ አልሆነም ። ፉድ ዋች የተባለው ድርጅት ባልደረባ ማርቲን ሩከር ባንኩ ዝምታ የመረጠበትን ምክንያት ያስረዳሉ ።« ኮሜርትስ ባንክ ስለ ችግሩ ነፃ ሆኖ የማይናገረው ወረታቸውን ማፍሰስ የሚፈልጉ ደንበኞቹ ደንግጠው ውሳኔያቸውን እንዳይቀይሩ ነው ። ስለዚህ ባንኩ የዋጋ ግምት መስጠት ያቆመበትን ምክንያት መናገር አይፈልግም ። ፍላጎታችን ችግሩ ሊባባስ ይችላል ብለው በመስጋት የዋጋ ግምት መስጠት ያቆሙ ባንኮችን በአርአያነት ማሳወቅ ነው ። »ከኮሜርዝ ባንክ በተጨማሪ የሽፓርካሰው ዴካ ባንክና የ ባድን ቩርተምበርግ ባንክ ለምግብ ዋጋ ግምት የሚውል ገንዘብ መመደብ አቁመዋል ። አስቀድሞ የሚሰጠው ግምት ለብዙዎች ባለወረቶች ጥሩ የንግድ መስክ ነበር ። የምግብ ዋጋ ለመጨመሩ አንደ አንድ ምክንያት የህዝቡ ቁጥር መጨመር ነው ። ከዚህ ሌላ የተለያዩ ሰብሎች ለነዳጅ ዘይት ምርት ጥቅም ላይ መዋላቸው ለችግሩ አስተዋጽኦ በማድረግ ይጠቀሳል ።
አሁን አሜሪካን የተከሰተው አይነት ድርቅ የእህል ዋጋ ወደ ላይ እንዲተኮስ ሊያደርግ ይችላል ። ከሰኔ ወዲህ የአኩሪ አተር ዋጋ በ30 በመቶ የበቆሎ ደግሞ በ 50 በመቶ ጨምሯል ። አሜሪካን ፣አኩሪ አተርና በቆሎን በብዛት ለውጭ ገበያ የምታቀርብ ሃገር ናት ። በህንድም በዝናብ እጥረት ምክንያት ብዙ ሰብል ጠፍቷል ። ምርት ባነሰ ቁጥር ዋጋ ይጨምራል ።መንግስታዊ ያልሆነው የፉድ ዋች ባልደረባ ማርቲን ሩከር እንደሚሉት አሁንም ከሁሉም በላይ የችግሩ ሰለባ የሚሆነው ድሃው ነው ።
«እጅግ በደኽዩት አገሮች ያሉ ሰዎች ከገቢያቸው 80 በመቶ ወይም ከዚያ በላይ የሚሆን ገንዘብ የሚያወጡት ለምግብ ነው ። እናም በትንሹም ቢሆን ዋጋ ከጨመረ ምግብ መግዛት አይችሉም ። »
የተባበሩት መንግሥታት የምግብና የእርሻ ድርጅት መዘርዝር እንደሚያስረዳው ያለፈው ወር የምግብ ዋጋ የምግብ ቀውስ ካጋጠመበት እጎአ ከ 2008 አመተ ምህረቱ ከፍ ያለ ነው ። በወቅቱ ችግሩን በ 30 ያህል ሃገራት ማረጋጋት ተችሎ ነበር ። ከዚያን ወዲህ ግን ባንኮችና ሌሎች የፋይናንስ ተቋማት በሚያቀርቧቸው የምግብ ዋጋ ግምቶች ምክንያት ዋጋን በማናር ይወቀሳሉ ።
« አስቀድሞ የሚተነበየው የምግብ ዋጋ ለምግብ ዋጋ ንረት 15 በመቶ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ አስልተናል ።»
Welthungerhilfe የተባለው የጀርመን የረሃብ መከላከያ ድርጅት የልማት ጉዳዮች አጥኚ የራፋኤል ሽናይደር አስተያየት ነው ። ይሁንና ተመራማሪዎች አስቀድሞ የሚቀርብ የዋጋ ግምት በምግብ ዋጋ ላይ ተፅእኖ ያሳድራል በመባሉ አይስማሙም ። በዚህ የተነሳም እንደ ዶቼ ባንክ የመሳሰሉ ባንኮች የዋጋ ግምት መስጠታቸውን አላቆሙም ።
ሂሩት መለሰ
ሸዋዮ ለገሠ