1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የምግብ ዝግጅት ባለሙያው በሀምቡርግ (ጀርመን)

ዓርብ፣ ሰኔ 14 2016

ስደት ላይ የአደገኛ ዕጽ ተጠቃሚነት እንደስልጣኔ በማየት ከሕይወት ጎደና የሚወጡ፤ በየቁማር ቤቱ ሲቋመሩ የሚውሉ ለቁጥር የሚታክቱ ናቸው። ሼፍ ሙለር ግን የመጣህበትን ዓላማ አለመርሳትና ተስፋ አለመቁረጥን ይመክራል።

ሼፍ ሙለር ፒዛ በማዘጋጀት ላይ እያለ
ሼፍ ሙለር ፒዛ በማዘጋጀት ላይ እያለምስል privat

ሼፍ ሙለር

This browser does not support the audio element.

አስመራ ውልደትና እድገቱን አድርጎ፣ ዓዲግራት፣ መቐለ፣ አዲስ አበባ፣ሱዳን፣ሊብያና ጣልያን አጫጭር ቆይታ በማድረግ አሁን መገኛው ጀርመን ሐምቡርግ ከተማ አድርጓል። ወጣት ሙሉጌታ ጳውሎስ ወይም በማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በሚታወቅበት ስም ሼፍ ሙለር።
ሙሉጌታ ገና የኑሮ ቀንበር መሸከም በማይችልበት ለጋ እድሜው ከእሱ በታች ያሉት ወንድምና እህቶቹን የማሳደግ ግዴታ በሱ ላይ አረፈ። ይህ በለጋ ዕድሜው የተጫነበት የኑሮ ቀንበር በሐገር ውስጥ ሰርቶ ለማሳካት የማይችልበት ሁኔታ መኖሩን ከተገነዘበ በኋላ ስደትን እንደአማራጭ መውሰዱን አጫውቶናል።
ጊዜ አላባከነም። በሥራ ዕጥነትና በኑሮ ውድነት ተመሳሳይ ችግርና  ተመሳሳይ የመሰደድ ፍላጎት ካላቸው ወጣቶች ጋር   ጉዞ ወደአውሮጳ ታቀደ ፤ በሱዳን በኩል ሊብያ ከዚያም ጣልያን። 

ሙሉጌታ ለአገሩ እንግዳ ለሰው ባዳ በሆነበት ጣልያን ብዙ ግዜ አላባከነም። ስደት ሲያልም አገርቤት ትቶአቸው የመጡ ረጂ የሌላቸው ቤተሰቦቹን የንሮ ሁኔታ ማሻሻል ዓላማ ስለነበረው አገርቤት እንደሚታየው ሥራ የማማረጥ ችግር እንዳልነበረበት አጫውቶናል። በመሆኑም በሕይወቱ እሰራዋለሁ ብሎ አልሞት አስቦት የማያውቅ ሥራ መስራት ጀመረ። ወደ ባሕር ጠልቆ በመግባት በዋጋ ውድ የሆኑ የዓሳ ዝርያዎችን አውጥቶ መሸጥ። ቀጥሎም መርከብ በሚያመርት ድርጅት በብየዳ ሙያ እያገለገለ እራሱንና ቤተሰቡን ማስተዳደር ቀጠለ።

ሼፍ ሙለር የኢትዮጵያን ምግቦች ለታዳሚዎች ሲያቀርብምስል privat


ወጣቱ ሙሉጌታ አሁን በጀርመን ሐገር ሐምቡርግ ከተማ ውስጥ በአንድ ታዋቂ ሆቴል የምግብ ዝግጅት ባለሙያ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል። ሼፍ ሙለር። 
"ጣልያን እያለሁ ቀለል ያሉ በፍጥነት የሚዘጋጁ ምግቦችን እሰራ ነበር። ይህ ለግል ንሮዬ እንጂ በማንኛውም ምግቤት ተቀጥሬ ሰርቼ አላውቅም። ይሁንና ምግብ የማዘጋጀት ሙያን በተመለከተ ፍቅሩ በውስጤ ስለነበረ ከዩቱብ እየተማርኩ ሙያውን ለማዳበር ችያለሁ። በአሁኑ ሰአት ሐምቡርግ ጀርመን ውስጥ በሚገኝ አንድ ትልቅ ሆቴል በምግብ ዝግጅት ባለሙያነት አገለግላለሁ።"
ሼፍ ሙለር የአፍሪቃ ፌስቲቫሎች በሚዘጋጁበት ጊዜ የኢትዮጵያን ምግቦችን በማቅረብ የሐገሩን ምግብ እያስተዋወቀ የገቢ ምንጩንም የሚያሰፋበት እንቅስቃሴዎችም እንደሚያደርግ አጫውቶናል። በፌስቲቫሎቹ የሐበሻ ምግብን የሚበሉ ጀርመናውያን በርበሬው እያቃጠላቸው፤ ምላሳቸውን በትንፋሻቸው እያቀዘቀዙ በፍቅር በልተው በአድናቆት ይለዩታል። ይህ የጀርመኖቹ መጋቤ ምላሽ ለስራው ብርታት እንደሚሰጠውም አጫውቶናል።

በሐምቡርግ ከተማ በተዘጋጀው የአፍሪቃ ፌስቲቫል ሼፍ ሙለር የኢትዮጵያ ባሕላዊ ምግቦችንና ቡና ለታዳሚዎች ሲያቀርብምስል privat


የጀርመኖች ቋንቋ ለሌሎች ዜጎች ከባድ እንደሆነ ይነገርለታል። ቁጥብና ዝምተኛ ጸባያቸውም ቶሎ ተግባብቶ ለመቀላቀል ከባድ ያደርገዋል የሚለው ሼፍ ሙለር ዓለማ ካለህ ግን ይህ ከባድ አደለም ይላል። 
"በባቡር ስትሄድ ጀርመኖች ዝም ነው የሚሉት፤ ቋንቋውም ከባድ ነው። ግን ፍላጎት ካለ ሁሉንም ነገር ይለመዳል። ጀርመኖች ጥሩዎች ናቸው። ሥራም አለ፤ በተለይም እዚህ እኔ የምኖርበት ሐምቡርግ ከተማ ሥራ ሞልቷል። እና በሂደት እየተላመድክ የመጣህበትን አላማ ታሳካለህ"
ስደት የሚመከር ባይሆንም ከሐገር ከተወጣ ግን የመጣህበትን ዓላማ መዘንጋት አይገባም ይላል ሼፍ ሙለር። ብዙ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን የመኖሪያና የሥራ ፍቃድ ቢኖራቸውም ከማሕበረሰቡ ጋር ተዋህደው ሕጋዊ ስራ ከመስራት ይልቅ ከመንግስት የሚቆረጥላቸውን የማሕበራዊ ዋስትና ብር እየተቀበሉ በድብቅና በሕገወጥ መንገድ ለአጫጭር ሰዓታት በመስራት ንሮአቸውን ሳይቀይሩ፤ የተሰደዱበት ዓላማ ሳያሳኩ የቀሩ እንዳሉ ይታወቃል።
እንዲያም ሲል በዚህ ኖሮ ላይ የአደገኛ ዕጽ ተጠቃሚነት እንደስልጣኔ በማየት ከሕይወት ጎደና የሚወጡ፤ በየቁማር ቤቱ ሲቋመሩ የሚውሉ ለቁጥር የሚታክቱ ናቸው። ሼፍ ሙለር የመጣህበትን ዓላማ አለመርሳትና ተስፋ አለመቁረጥን ይመክራል።

ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር

አዜብ ታደሰ
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW