1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የምጣኔ ሀብት ምሁር ተመራማሪና ካህን ዶክተር ያብባል ሙሉዓለም ዋለ

ረቡዕ፣ ጥቅምት 12 2018

ዶክተር ያብባል የምጣኔ ሀብት ተመራማሪ ብቻ አይደሉም፤ካህንም ጭምር እንጂ። በአማራ ክልል ደቡብ ጎንደር ደብረ ታቦር ከተማ ተወልደው ያደጉትና የ1ኛና የ2ተኛ ደረጃ ትምሕርታቸውን የተከታተሉት ያብባል 2ተኛ ደረጃን እስኪጨርሱ ድረስ ትኩረታቸው በቀለም ትምሕርት ላይ ብቻ ነበር። ዩኒቨርስቲ ከገቡ በኋላ ግን የቤተ ክህነት ትምሕርትም ቀልባቸውን ሳበ።

ዶክተር ያብባል በጉባኤ ላይ ገለጻ ሲያደርጉ
ዶክተር ያብባል በጉባኤ ላይ ገለጻ ሲያደርጉምስል፦ Privat

የምጣኔ ሀብት ምሁር ተመራማሪና ካህን ዶክተር ያብባል ሙሉዓለም ዋለ

This browser does not support the audio element.


የ43 ዓመት ጎልማሳ ናቸው ከእድሜያቸው አብዛኛውን በትምሕርትና በምርምር ሥራ ነው ያሳለፉት። በአሁኑ ጊዜ ቦን ከተማ በሚገኝ በአንድ የጀርመን የልማትና የዘላቂነት ጥናትና ምርምር ተቋም ውስጥ ይሠራሉ። በልጅነታቸው ብዙም ትኩረት ባልሰጡት፣ ሆኖም ዩኒቨርስቲ ከገቡ በኋላ ይበልጥ ፍላጎቱ ባደረባቸው በአብነት ወይም በቆሎ ትምሕርትም ገፍተው ለዲቁናና ለክህነት ማዕረግ በቅተው ከሀገር ቤት አንስቶ በሚኖሩባት በጀርመን ሀገርም እያገለገሉ ነው፤ ጀርመን የዶክትሬትና የድኅረ ዶክትሬት ትምህርታቸውንና ምርምራቸውን የሰሩት ኢትዮጵያዊው የምጣኔ ሀብት ምሁር እና ካህን ዶክተር ያብባል ሙሉዓለም ዋለ። አባታቸው ወጣቱ ያብባል ሕክምና እንዲማሩ ነበር የሚመክሯcቸው ። እርሳቸው ግን ስሙ ሲጠራ ደስ የሚያሰኘኝ ያሉትን ኤኮኖሚክስን መረጡ።

ዶክተር ያብባል አሁን በሚሠሩበት በGerman Institute of Development & Sustainability በእንግሊዘኛው ምህጻር IDOS የጥናትና ምርምር ተቋምውስጥ ከሚያከናውኗቸው የምርምር ተግባራት በተጨማሪ በፖሊሲ አማካሪነትም ይሠራሉ። ይበልጥ የሚያተኩሩት ደግሞ በልማት ፋይናንስ ላይ ነው። ለመጀመሪያ ጊዜ ጀርመን የመጡት የዛሬ 18 ዓመት ነው። ያኔ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የድህረ ምረቃ ተማሪ ነበሩ። ሰሜን ጀርመን በሚገኘው የኪል ዩኒቨርስቲ የአጭር ጊዜ ምርምርና ጥናት አድርገው ተመለሱ። የድኅረ ምረቃ ትምህርታቸውን አጠናቀው በ2000 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በመምህርነት መሥራት በጀመሩ በሁለት ዓመት የነጻ ትምሕርት እድል አግኝተው ለዶክትሬት ዲግሪ ትምሕርት ተመልሰው ወደ ኪል ዩኒቨርስቲ መጡ። 

የምጣኔ ሀብት ምሁር እና ካኅን ዶክተር ያብባል ሙሉዓለም ዋለምስል፦ Privat

የዶክትሬት ዲግሪ ትምሕርታቸውን ከጨረሱ በኋላ እዚሁ ጀርመን በጎቲንገን ዩኒቨርስቲ የድኅረ ዶክትሬት ዲግሪ ምርምር ቀጥለው በዩኒቨርስቲው በምርምርና የማስተርስ እና የመጀመሪያ ዲግሪ ተማሪዎችን በማስተማርም ለ8 ዓመታት ቆይተዋል። በምርምር ፣ በፖሊሲ አማካሪነትና በስልጠና ተግባራት ላይ በተሰማራው በቦኑ በIDOS አይዶስ ወይም በጀርመን የልማትና ዘላቂነት ተቋም ውስጥ በተመራማሪነት መሥራት ከጀመሩ ደግሞ አራት ዓመት አልፏቸዋል። ዶክተር ያብባል በጀርመን በትምሕርቱም ሆነ በሥራ ቆይታቸው በርካታ ምርምሮችን አካሂደዋል። አብዛኛዎቹም በልማት ፋይናንስ ላይ ያተኮሩ ናቸው።

ዶክተር ያብባል የምጣኔ ሀብት ተመራማሪ ብቻ አይደሉም፤ ካህንም ጭምር እንጂ ። በአማራ ክልል ደቡብ ጎንደር በደብረ ታቦር ከተማ ተወልደው ያደጉትና የአንደኛ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምሕርታቸውን  የተከታተሉት ዶክተር ያብባል ሁለተኛ ደረጃን እስኪጨርሱ ድረስ ትኩረታቸው በቀለም ትምሕርት ላይ ብቻ ነበር። አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ከገቡ በኋላ ግን የቤተ ክህነት ትምሕርትም ትኩረታቸውን ሳበ። ይህን ፍላጎታቸውንም ዩኒቨርስቲ በትምሕርት ላይ ሳሉ በተፈጠረ አጋጣሚ ማሳካት ቻሉ። 

ዶክተር ያብባል መደበኛ ሥራቸውንና የክህነት አገልግሎታቸውን ከሥራና ከክህነት አገልግሎት ጋር አቅማቸው በፈቀደ መጠን ጎን ለጎን ለማስኬድ ለቤተሰባቸውም በቂ ጌዚ ለመስጠት እንደሚሞክሩ ተናግረዋል ። በአሁኑ ጊዜ በብሬመን የቅዱስ እስጢፋኖስ ቤተ ክርስቲያን ደብር አስተዳዳሪ ዶክተር ያብባል በተለያዩ የጀርመን ከተሞች በሚገኙ ዐብያተ ክርስቲያንም አገልግሎት ይሰጣሉ። 

ሙሉውን ዝግጅት 

ኂሩት መለሰ 

ሸዋዬ ለገሠ 


 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW