1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሞት ፍርድ የሚያሰጋቸው ጀማል እና ሀሰን

ዓርብ፣ ግንቦት 5 2014

ኢትዮጵያውያኑ ጀማል እና ሀሰን ሳውዲ አረቢያ እስር ቤት ከገቡ 13 ዓመት አለፋቸው። ወጣቶቹ በነፍስ ማጥፋት ወንጀል ተከሰው የሞት ፍርድ ተበይኖባቸዋል። የወጣቶቹ ቤተሰቦች እንደሚሉት ከሆነ ወጣቶቹ ወንጀሉን አልፈጸሙም። ይግባኝ ካልተባለም ፍርዱ ተግባራዊ ሊሆን የቀረው የአንድ ወር ያህል ጊዜ ነው በማለት አፋጣኝ ትብብር ይሻሉ።

Deutschland Berlin | Gegen die Todesstrafe | Aktion gegen Folter
ምስል Wolfram Steinberg/dpa/picture alliance

የሞት ቅጣት የሚያሰጋቸው ጀማል እና ሀሰን

This browser does not support the audio element.

ምንም እንኳን 108 ሀገራት የሞት ፍርድን ሙሉ በሙሉ ቢያስቆሙም፤ አሁንም ድረስ ቅጣቱ ተግባራዊ በሚሆንባቸው ሀገራት ብዙ ሰዎች በሞት ይቀጣሉ። እንደ ሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ድርጅት አምነስቲ ኢንተርናሽናል ዘገባ ከሁለት ዓመት በፊት በዓለም ላይ  ቢያንስ 28,567 ሰዎች የሞት ፍርድ ተበይኖባቸው ፍርዱ የሚፈጸምበትን ቀን ይጠባበቃሉ።
የዛሬው የወጣቶች ዓለም ዝግጅት ሳውዲ አረቢያ ውስጥ የሞት ፍርድ ስለተበየነባቸው ሁለት ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ጉዳይ ይሆናል። እነሱም ጀማል እና ሀሰን ይባላሉ። የሀሰን እህት ዓለም ወርቅ እንደሚሉት ሀሰን ለእስር የተዳረገው  ከ13 ዓመት በፊት ፖሊስ በደረሰው ጥቆማ ጀማል እና ሀሰን አብረው ይኖሩ የነበረበት ቤት ሲገባ ነው። «ሪያድ ከተማ የቀን ስራ ሰርቶ የተኛበት ቤት ነበር።» ከእሱ ጓደኛ ጋር የተጣላ አንድ ሀበሻ ነበር እሱም ለፖሊስ ጥቆማ ልኮ ይሰክራሉ፤ ይደበድባሉ ብሎ አስያዚያቸው የሚሉት ዓለምወርቅ « ፖሊሶችም ያልሞተ ሰው አስተኝተው መምቻ ሰጥተው የምትመቱት አስመስሉ ብለው ዱላ ሰጥተው በቪዲዮ ቀርፀው እስር ቤት አስገቧቸው ይላሉ። ጀማል እና ሀሰን ለረዥም ጊዜ ጭለማ ቦታ ታስረው ከቆዩ በኋላም ፍርድ ቤት ቀርበው እንደነበር እና የማያውቁት ወረቀት ላይ የጣት አሻራቸውን እንዲያኖሩ ተገደው እንደነበር  የሀሰን ታላቅ እህት ዓለም ወርቅ ይናገራሉ።  « ጀማል እና ሀሰን ለመጀመሪያ ጊዜ ፍርድ ቤት የቀረቡት ከአምስት ዓመት በኋላ ነው። ከ 8 ዓመት በኋላ ደግሞ የሞት ፍርድ ተበየነባቸው» ይላሉ የሀሰን እህት።
እንዲህ እያለ እስካሁን 13 ዓመታት የተቆጠሩ ሲሆን አሁን ግን ይግባኝ ለማስገባት የ30 ቀናት ጊዜ እንደተሰጣቸው  ይህ ካልሆነ ግን ወጣቶቹን የሞት ፍርድ እንደሚያሰጋቸው የተከሳሽ ቤተሰቦች ይናገራሉ። የጀማል እህት የሆኑት ፋንታነሽ በበኩላቸው ለዶይቸ ቬለ እንደተናገሩት፤ ወጣቶቹ ለረዥም ዓመታት የታሰሩበትን ምክንያት ዐያውቁም ነበር። « ያው እንደሚያዘው ሰው የተያዙ ነበር የመሰላቸው። ኃላ ነው ሰው ገድላችኋል እየተባሉ ሲደበደቡ ከተኛንበት ነው የተያዝነው አሉ» የሚሉት የጀማል እህት የተቀረጸው ቪዲዮ ትወና ነው ይላሉ።
ወጣቶቹ ሰው ሲደበድቡ እንደሆነ የሚያሳይ ቪዲዮ እየተቀረፁ እንደሆነ ዕያወቁ ለምን ለመቀረፅ ፈቀዱ? ለምንስ የማያውቁት ወረቀት ላይ ፈረሙ?  የሀሰን እህት ዓለም ወርቅ ምክንያት ነው የሚሉት« ብትር በዝቶባቸዋል፣ ቋንቋ አይችሉም እንጂ ሰው ገድለው ቢሆን ኖሮ እስካሁን አይታሰሩም ነበር።»
 ጀማል ከመታሰሩ አንድ አመት በፊት ወደ ሳውዲ አረቢያ መሄዱን የሚናገሩት እህቱ  እሱም እንደ አብዛኛው ኢትዮጵያውያን ሕይወቱን ለመቀየር ብሎ ከኢትዮጵያ እንደተሰደደ ይናገራሉ። « እናቴን አሳልፍላታለሁ ብሎ ነበር።»  የጀማል እና የ ሀሰን ትውውቅ የ6 ቀናት ብቻ ነበር የሚሉት የሀሰን እህትም ስለወንድማቸው ሲናገሩ እያለቀሱ ነው።  ሀሰን ወደ ሳውዲ የተሰደደው እንጨት ሸጠው የሚያሳድጉ እናቱን ለመርዳት ብሎ ነበር። « ወንድ ልጅ ስትወልድ ይሞቱባት ስለነበር። እንዲያድግልኝ ብላ በሴቶች አስመስላ ለማሳደግ አንቺ ብላ ነበር ያሳደገችው፤ 20 ዓመት ሲሞላህ አንተ እልሀለሁ ትለው ነበር።» ሀሰን ግን 20 ዓመት ሳይሞላው ወደ ሳውዲ ተሰደደ።  ሀሰን ወደ ሳውዲ የተሰደደውም አርሶ እንዲበላበት እህቱ የገዙለትን በሬ ሸጦ እንደሆነ በመናገር አስቸኳይ ትብብር ይጠይቃሉ። የጀማል እህትም የኢትዮጵያ ኤምባሲን እና ማኅበረሰብን ይማፀናሉ። 
የጀማል እና የሀሰንን ጉዳይ በሚመለከት ሳውዲ አረቢያ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ያውቅ እንደው ለመጠየቅ በሳዑዲ አረቢያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሌንጮ ባቲ ጋር ደውለን ነበር። አምባሳደሩ ጉዳዩ በቆንስላ በኩል እንደተያዘ እና ለቆንስላው ሠራተኛ አቶ አብዱል ጀባር  እንድንደውል ነግረውን ነበር። ሆኖም አቶ አብዱል ጀባር  ለሚዲያ ለመናገር  የአምባሳደሩን ፍቃድ እንደሚሹ በመግለፅ በጉዳዩ ላይ አስተያየት ከመስጠት  ተቆጥበዋል። ከዚያም በኋላም ምንም እንኳን በተደጋጋሚ አምባሳደር ሌንጮ ጋር ብንደውልም ልናገኛቸው አልቻልንም። 
ሳውዲ አረቢያ ውስጥ የሚፈጸመው የሞት ፍርድ ከፍተኛ መሆኑንን የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች በመግለፅ በተደጋጋሚ ቅሬታ  ሲያሰሙ ቆይተዋል። የሀገሪቱ የመገናኛ ብዙኃን ከሁለት ወር ገደማ በፊት እንደዘገቡት ሳውዲ አረቢያ ውስጥ በተለያዩ ወንጀሎች የተከሰሱ 81 ሰዎች በአንድ ቀን ተገድለዋል። የወጣቶቹ ቤተሰቦች እንደገለጡልን ከሚመለከተው አካል በአፋጣኝ ርዳታ ካላገኙ የወጣቶቹ ሕይወት አደጋ ላይ ወድቋል። 


ልደት አበበ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW