1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሞጣ ቃጠሎን ባወገዘው የጅግጅጋ ሰልፍ የሰው ሕይወት አለፈ

ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 14 2012

በጅግጅጋ ከተማ የተካሔደ ሰልፍ ሲጠናቀቅ በተቀሰቀሰ ኹከት ሰዎች መሞታቸውን እና መጎዳታቸውን የዐይን እማኞች እና አንድ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣን አስታወቁ። በአማራ ክልል ሞጣ ከተማ የተፈጸመውን የሐይማኖት ተቋማት የማቃጠል ድርጊት ያወገዘው ሰልፍ ሲጠናቀቅ በጸጥታ አስከባሪዎች እና በወጣቶች መካከል ግጭት መፈጠሩን እማኞች አስረድተዋል

Äthiopien Protest von Muslimen
ምስል Mohammed Olad/Somali Regional government

በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ በዛሬው ዕለት በሞጣ የእምነት ተቋማት መቃጠላቸውን ለማውገዝ በተካሔደ ሰልፍ መገባደጃ ብጥብጥ እና ኹከት ተቀስቅሶ የሰው ሕይወት ማለፉን የዐይን እማኞች እና የክልሉ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣን አስታወቁ። በጅግጅጋ በሚገኘው ስታዲየም የተካሔደው ሰልፍ ሲገባደድ በተነሳው ብጥብጥ እና ኹከት ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ሰዎች መቁሰላቸውን በቦታው የነበሩ የዐይን እማኞች ገልጸዋል።

ሰልፉ ባለፈው አርብ በአማራ ክልል ምሥራቅ ጎጃም ዞን ሞጣ ከተማ የመስጊዶችን መቃጠል ሲያወግዝ መቆየቱን የገለጹ አንድ የዐይን እማኝ «ወደ ቤት ሲገቡ ረብሻ ተጀመረ» ሲሉ ተናግረዋል። ከጸጥታ አስከባሪዎች የተጋጩ ወጣቶች «ድንጋይ ወረወሩና በጥይት ተመቱ። አንድ ሰው ቆስሎ ወደ ሆስፒታል ተወሰደ። አንዲት ወጣት ሴት እና አንድ ልጅ ሞተዋል» ሲሉ ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉት የዐይን እማኝ ለዶይቼ ቬለ አስረድተዋል።

የሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት የኮምዩንኬሽን ጉዳዮች አማካሪ አቶ መሐመድ ኦላድ ወጣቶች በብዛት የታዩበት ሰልፍ ሲገባደድ በተቀሰቀሰ ብጥብጥ እና ኹከት የአንድ ሰው ሕይወት ማለፉን ለዶይቼ ቬለ አረጋግጠዋል።

«ሞጣ ከተማ የነበረውን የመስጊድ እና የቤተ እምነት ቃጠሎ ለማውገዝ ጅጅጋ ከተማ እና እዚሁ አካባቢ የሚኖር ሕዝብ ሰልፍ ወጥቷል» ያሉት አቶ መሐመድ በስም ባልጠቀሷቸው ኃይሎች «ወደ ብጥብጥ እና ወደ ኹከት» ለመቀየር ሙከራ መደረጉን ገልጸዋል።  

አቶ መሐመድ «በጣም ጥሩ ነበረ። ግን ወደ መጨረሻ አካባቢ ሰልፉ ሊያልቅ ሲል የተወሰኑ ኃይሎች ለማደናቀፍ፤ ወደ ብጥብጥ እና ወደ ኹከት እንዲቀየር ሙከራ አድርገው ነበር። ከዚያ በኋላ የክልሉ የጸጥታ ኃይሎች ወዲያው ሁኔታውን በቁጥጥር ሥር አድርገዋል። የተወሰነ ጉዳት ደርሷል። የአካል ቁስለት ደርሷል። አንድ ግለሰብ ወደ መጨረሻ በተፈጠረ ኹከት እና ብጥብጥብ ሕይወታቸው እንዳለፈ ማረጋገጥ እንችላለን» ሲሉ አስረድተዋል።

ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ በከተማዋ ጎዳናዎች የሞጣውን የሐይማኖት ተቋማት ቃጠሎ የሚያወግዙ መፈክሮች ይዞ መታየቱን የጅግጅጋ ነዋሪዎች ለዶይቼ ቬለ አረጋግጠዋል።

ዶይቼ ቬለ ያነጋገራቸው ሁለት የዐይን እማኞች እንዳሉት በጅግጅጋ ስታዲየም የተካሔደው ሰላማዊ ሰልፍ ሲጀመር ብጥብጥም ሆነ እረብሻ አልነበረም።

በጅግጅጋ የሚኖሩ ሁለተኛ የዐይን እማኝ «መጀመሪያ ሰላማዊ ሰልፉ ሰላማዊ ነበረ። አንዳንድ ጣልቃ ገቦች ናቸው የቀየሩት፤ በሰላማዊ ሰልፍ መካከል አንዳንድ አካላቶች ወደ ረብሻ ለመቀየር ሞክረው ነበር። ነገር ግን በአካባቢው በነበሩ የጸጥታ ኃይሎች ነገሩ ሊከሽፍ ችሏል» ብለዋል።

ባለፈው አርብ በሞጣ ከተማ የእምነት ተቋማት ከተቃጠሉ በኋላ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ድርጊቱን የሚቃወሙ ሰላማዊ ሰልፎች እየተካሔዱ ነው። ባለፉት ቀናት በሻሸመኔ፤ ሐረር፣ አወዳይ እና ከሚሴ በተካሔዱ ሰላማዊ ሰልፎች አደባባይ የወጡ ዜጎች መንግሥት የጥቃቱን አቀነባባሪዎች ለሕግ እንዲያቀርብ በተደጋጋሚ ጠይቀዋል። የአማራ ክልል ፖሊስ ሶስት መስጊዶች፤ አንድ ቤተ-ክርስቲያን፤ 18 ሱቆች መቃጠላቸውን እና አንድ መቶ አስራ አንድ ሱቆች መዘረፋቸውን አስታውቋል። አገሪቱን እንደ አዲስ ለውጥረት በዳረጋት የሐይማኖት ተቋማት ቃጠሎ የተጠረጠሩ ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ፖሊስ አስታውቋል።

መሳይ ተክሉ

እሸቴ በቀለ

ሸዋዬ ለገሠ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW