1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሠራተኞች እሥር እና እንግልት በሃድያ

ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 24 2015

በደቡብ ክልል ሃድያ ዞን የምሥራቅ ባድዋቾ ወረዳና ሾኔ ከተማ አስተዳደር የሚገኙ መንግሥት ሠራተኞች ለሦስት ወራት ያልተከፈለን ደሞዝ እንዲከፈልን በመጠየቃችን ለእሥርና ለእንግልት እየተዳረገን ነው አሉ ። የደሞዝ ይከፈለን ጥያቄውን ለማቅረብ ሠራተኞቹን አስተባብረዋል የተባሉትን ጨምሮ እስከአሁን አንድ መቶ የሚደርሱ ሠራተኞች መታሰራቸው ተገልጧል ።

Äthiopien Shone city
ምስል Shone city communication office

ሠራተኞች ደሞዝ ይከፈለን ባልን ተንገላታን እያሉ ነው

This browser does not support the audio element.

በደቡብ ክልል ሃድያ ዞን የምሥራቅ ባድዋቾ ወረዳ እና ሾኔ ከተማ አስተዳደር የሚገኙ መንግሥት ሠራተኞች ለሦስት ወራት ያልተከፈለን ደሞዝ እንዲከፈልን በመጠየቃችን ለእሥርና ለእንግልት እየተዳረገን ነው አሉ ። የደሞዝ ይከፈለን ጥያቄውን ለማቅረብ ሠራተኞቹን አስተባብረዋል የተባሉትን ጨምሮ እስከአሁን አንድ መቶ የሚደርሱ ሠራተኞች በፀጥታ አባላት መታሰራቸውን ሠራተኞቹ ለዶቼ ቬለ (DW) ተናግረዋል ። የወረዳው የፀጥታ ኃላፊዎች በበኩላቸው ሠራተኞቹ የታሠሩት የደሞዝ ጥያቄ በማቅረባቸው ሳይሆን መንገድ በመዝጋታቸውና የወረዳውን የካቢኔ አባላት በዱላ በማባረራቸው ነው ብለዋል ። የወረዳው አስተዳደር የሠራተኞችን የደሞዝ በጀት በዋስትና በማስያዝ የወሰደውን የአፈር ማዳበሪያ ዕዳ ባለመክፈሉ ከሁለት ሺህ በላይ የሚሆኑት የወረዳው የመንግሥት ሠራተኞች እስከአሁን የሦስት ወራት ደሞዛቸው እንዳልተከፈላቸው ይናገራሉ ። 

በደቡብ ክልል ሃድያ ዞን የምሥራቅ ባድዋቾ ወረዳ እና ሾኔ ከተማ አስተዳደር የሚገኙ መንግሥት ሠራተኞች ለሦስት ወራት ያልተከፈለን ደሞዝ እንዲከፈለን በመጠየቃችን ለእሥርና ለእንግልት እየተዳረግን ነው አሉ ፡፡ የደሞዝ ይከፈለን ጥያቄውን ለማቅረብ ሠራተኞቹን አስተባብረዋል የሏቸውን ጨምሮ እስከአሁን አንድ መቶ የሚደርሱ ሠራተኞች በፀጥታ አባላት መታሰራቸውን ተናግረዋል።

የወረዳው አስተዳደር የሠራተኞችን የደሞዝ በጀት በዋስትና በማስያዝ የወሰደውን የአፈር ማዳበሪያ ዕዳ ባለመክፈሉ የወረዳው የመንግሥት ሠራተኞች እስከአሁን የሦስት ወራት ደሞዛቸው እንዳልተከፈላቸው ሠራተኞቹ ገልጸዋል ፡፡ በወረዳውና በከተማ አስተዳደሩ በማገልገል ላይ የሚገኙ ከሁለት ሺህ በላይ የመንግሥት ሠራተኞች ላለፉት ሦስት ወራት ያልተከፈለ የደሞዝ ከፍያ እንዲከፈላቸው በተደጋጋሚ ሲጠይቁ መቆየታቸውንም ተናግረዋል ፡፡

ከወረዳ እስከ ዞን ፣ ክልልና የፌዴራል መንግሥት ድረስ አቤቱታቸውን ቢያቀርቡም ሰሚ አለማግኘታቸውን የጠቀሱት ሠራተኞቹ በዚህም የተነሳ ባለፈው ሳምንት ጥያቄያቸውን በሠልፍ ማቅረባቸውን ገልጸዋል፡፡ ይሁንእንጂ የወረዳው ባለሥልጣናት ለጥያቄያቸው ምላሽ ከመስጠት ይልቅ አቤቱታውን በማመልከቻ እና በሠልፍ ለማሰማት የተደረገውን እንቅስቃሴ አስተባብረዋል ባሏቸው ሠራተኞች ላይ እሥር እና ወከባ እያደረሱ ይገኛሉ ሲሉ ነው ከሠራተኞቹ ሦስቱ ለዶቼ ቬለ ገልጸዋል ። 

ዶቼ ቬለ DW በሠራተኞቹ አቤቱታ ዙሪያ ያነጋገራቸው በሃድያ ዞን የምስራቅ ባድዋቾ ወረዳ ፖሊስ አዛዥ ኮማንደር በቀለ በርገና ሠራተኞቹ የታሠሩት የደሞዝ ጥያቄ በማቅረባቸው ሳይሆን መንገድ በመዝጋታቸውና የወረዳውን የካቢኔ አባላት በዱላ በማባረራቸው ነው ይላሉ ፡፡ ሠራተኞቹ ጥያቄያቸውን በሰላማዊ መንገድ በማቅረብ ከሚመለከተው አካል ምላሽ መጠበቅ ሲገባቸው መንገዶችን በድንጋይ በመዝጋት የአካባቢውን ሰላማዊ እንቅስቃሴ ማወካቸውን የተናገሩት አዛዡ «የሠራተኞቹ ጥያቄ የደሞዝ ብቻ አይደለም ፡፡ እንዳንዶቹ ደሞዝን ምክንያት በማድረግ የወረዳውን ሥልጣን ለመንጠቅ የሚንቀሳቀሱ አሉበት» ብለዋል ።

ከደሞዝ ጥያቄው ጋር ተያይዞ መንገድ መዘጋቱን ያረጋገጡት ሠራተኞቹ ይህ ትክክል ባይሆንም ተስፋ በመቁረጥና ሰሚ በማጣት የተደረገ ነው ብለዋል ፡፡ የደሞዝ ይከፈልን ጥያቄያችንን ከወረዳ እስከ ዞን ፣ ክልልና የፌዴራል መንግሥት ድረስ አቅርበን ምላሽ የሚሰጥ አካል አለመገኘቱ እንዳንድ ሠራተኞችን አበሳጭቷል ፡፡ በዚህም የተነሳ ስሜት ውስጥ በመግባት ከአዲስ አበባ አርባምንጭ የሚወስደውን መንገድ ለመዝጋት ተንቀሳቅሰዋል ፡፡ ከዚህ ውጭ የወረዳውን ሥልጣን ለመያዝ ነው የተባለው ክስ መሠረተ ቢስ ነው ፡፡ ኮማንደሩ የማይገናኝ ጉዳይ በማገናኘት ጥያቄውን ፖለቲካዊ መልክ ለመስጠት ያደርጉት ነው» ብለዋል ፡፡

የወረዳውን እንቅስቃሴ ለማወክ ሞክረዋል በሚል እስከአሁን ምን ያህል ሠራተኞች እንደታሠሩ የተጠየቁት ኮማንደር በቀለ በህግ ቁጥጥር ሥር የማዋሉ ሂደት እየተከናወነ የሚገኘው በፌዴራል ፖሊስ በኩል መሆኑን በመጥቀስ ለጊዜው አሃዛዊ መረጃ እንደሌላቸው ተናግረዋል ፡፡ ዶቼ ቬለ DW በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የፌዴራልንም ሆነ የደቡብ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ሃላፊዎችን አግኝቶ ለማነጋገር ያደረገው ጥረት ለጊዜው አልተሳካም ፡፡

ሸዋንግዛው ወጋየሁ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW