1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሠራተኞች የደሞዝ ጭማሪ፤የአ.አ.የአሽከርካሪና ተሽከርካሪ ፈቃድ የአገልግሎት ክፍያዎች ጭማሪ

ዓርብ፣ መስከረም 24 2017

«በጣም የሚያሳዝነው ይህ የህዝብ ሰቆቃ በባለስልጣናቱ አዕምሮ ውስጥ ፈፅሞ አለመመዝገቡ ነው ስለችግሮች የሚያነሳባቸውን ሰው ይጠየፋሉ።እትዮጲያ እንዴት እየበለፀገች እንደሆነ ሲያወሩ በየትኛው ደሴት ላይ እንደሚኖሩ ግር ይላል።ጦርነቶች ቆመው ኢኮኖሚው እንዲያገግም ካልተድረገ የህዝቡ ኑሮ መሽቆቆልም ሆነ የሀገረመንግስቱ መዳከም እየተባባሰ ይቀጥላል።»

Äthiopien | Geldscheine Währung
ምስል MICHELE SPATARI/AFP

የሠራተኞች የደሞዝ ጭማሪ፤የአ.አ.የአሽከርካሪና ተሽከርካሪ ፈቃድ የአገልግሎት ክፍያዎች ጭማሪ

This browser does not support the audio element.

የአዲስ አበባ የአሽከርካሪና ተሽከርካሪ ፈቃድ የአገልግሎት ክፍያዎች ጭማሪ

የኢትዮጵያ መንግስት የኤኮኖሚ ማሻሻያ ያለውን ተግባራዊ ማድረግ ከጀመረ በኋላ ለመንግሥት ሠራተኞች የደሞዝ ጭማሪ ሊያደርግ መሆኑን አስታውቋል። በዚህ ጭማሪም ከ2.4 ሚሊዮን በላይ የመንግስት ሰራተኞች ተጠቃሚ ይሆናሉ ተብሏል።የመጨረሻ ውሳኔ ያላገኘው የደሞዝ ጭማሪ በዝቅተኛ የደሞዝ እርከን ላይ ያሉ ሠራተኞች ከሶስት መቶ ሰላሳ በመቶ በላይ ጭማሪ እንደሚያስገኝ ተነግሯል። እስከ ከፍተኛው የደሞዝ እርከን ያሉ ሠራተኞችም እንደደረጃቸው የደሞዝ ጭማሪ እንደሚደረግላቸው ይጠበቃል። ይሁንና የዋጋ ግሽበት እጅግ እየናረ በቀጠለበት በአሁኑ ወቅት መንግሥት ለሠራተኞች አደርጋለሁ የሚለው የደሞዝ ጭማሪ የሠራተኛውን ኑሮ ሊደጉም መቻሉ ማጠያየቁ አልቀረም።


ዶቼቬለ በዚህ ጉዳይ ላይ ያካሄደውን ውይይት መነሻ በማድረግ በፌስቡክ ከተሰጡ አስተያየቶች መካከል ጌች ድሪባ ለታ በሚል የፌስቡክ ስም የቀረበው ይገኝበታል።ጌች «ጭማሪው ቀርቶ በወሬ ገበያውን በያባብሱ ጥሩ ነው።» ሲሉ ጭማሪው ሠራተኛው እጅ ሳይገባ ወሬው በመቅደሙ ያስከተለውን ችግር በአጭሩ ጠቁመዋል።«እኛም በጣም ገርሞናል ምንም ጨምሪ ሳይደርግ ታውጆ በኑሮ ውድነት መከራችንን አየን።» የሚለው የጃኪ ማንም አስተያየት ነው።ኃይለ ማርያም አንዳርጌ «ቀቢጸ ተስፋ የሆነ ደሞዝ»ሲሉት መስፍን አየነው «የ800 ብር ጭማሪ ምን ያረጋል ቢቀር ይሻላል!!!»ሲሉ አጣጥለውታል። «የነባሩ ደመወዝ የመግዛት አቅም በጣም ቀንሷል፥ የሸቀጦች ዋጋ በጣም ጨምሯል፤ ተመጣጣኝ ና ምክንያታዊ ደመወዝ አልተጨመረም» በማለት ሀሳባቸውን የጀመሩት ተሰማ ሌንዴቦ«መፍትሔው አሁንም በመንግሥት እጅ ያለ ይመስላል።»ካሉ በኋላ « ከሁሉም በላይ ግን ፈጣሪ ያኖራል ተስፋ መቁረጥ አያስፈልግም።»ሲሉ መጽናኛውንም አካፍለዋል። 
«ነጋዴ ከሚጨምረው በላይ፣ የመንግሥት ተቋሟት ጭማሪ ሰዉን እያማረረው ነው፤ አየርመንገድ መብራት ኢሚግሬሽን ይኸው ትናንትናም መንጃ ፈቃድ ምትክ ለማግኘት ከ600 ብር ወደ 5000 ብር ከፍ አድርጎታል ግለሰብ 10 ብር ጨመረ ተብሎ ሲታሸግ በሺዎች የሚጨምረውን መንግሥትን ምን እናድርገው? »የሚለው ደግሞ የነብዩ ሙሴ አስተያየት ነው።
«ሰላም ለሁሉም» በሚል የፌስቡክ ስም የሰፈረ አስተያየት «አሁን እኛ ሀገራችንን ከውስጥም ከውጭም የሚፈታተናት ኃይል በመብዛቱ ለሀገር ህልውና በማሰብ እንጅ መንግሰት አንድ ሺህ ብር ለመጨመር ያን ሁሉ የሚዲያ ፕሮፖጋንዳ በመስራቱ ሰበብ ስግብግቡ ነጋዴ ያቺውም ብር ሳትጨመር መንግሰት ሠራተኛውን አበሳጭቶ ለባሰ ችግር እንዲዳረግ ትልቁን ሚና ተጫውቷል።ስለዚህም የተጨመረው ለዝቅተኛ ተካፋዮች ነው ለሌላ አልተጨመረም ብሎ መግለጫ ይስጥ።» በማለት መፍትሄውን ጠቁሟል።የቀጠለው የደሞዝ ጥያቄ በዎላይታ ዞን

አብዱርመናን ከድር « በጣም የሚያሳዝነው፣ ይህ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየከፋ የመጣው የህዝብ ሰቆቃ በባለስልጣናቱ አዕምሮ ውስጥ ፈፅሞ አለመመዝገቡ ነው። ሁሉም ነገር አልጋባልጋ እንደሆነ እራሳቸውን ስላሳመኑ፣ ስለችግሮች የሚያነሳባቸውን ሰው ይጠየፋሉ። እትዮጲያ እንዴት እየበለፀገች እንደሆነ ሌላውን ሰው ለማሳመን ሲያወሩ በየትኛው ደሴት ላይ እንደሚኖሩ ግር ይላል። መሪዎች ቀልብ ገዝተው ሀገሪቷን እያመሱ ያሉ ጦርነቶች ቆመው ኢኮኖሚውእንዲያገግም ካልተድረገ፣ የህዝቡ ኑሮ መሽቆቆልም ሆነ የሀገረመንግስቱ መዳከም እየተባባሰ ይቀጥላል።» ሲሉ አሳስበዋል።

የትራፊክ መጨናነቅ በባህርዳር ከተማ ምስል Matyas/Pond5 Images/IMAGO

 

የአዲስ አበባ መስተዳድር የአሽከርካሪና ተሽከርካሪ ፈቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን የአገልግሎት ክፍያዎች ጭማሪ 

 

የአዲስ አበባ መስተዳደር የአሽከርካሪና ተሽከርካሪ ፈቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን በሚሰጣቸው የአገልግሎት ክፍያዎች ላይ ጭማሪ ማድረጉ በዶቼቬለ ፌስቡክ ገጽ ላይ ብዙዎችን ያነጋገረ ጉዳይ ነበር።  በቴክኖሎጂ የታገዘ ቀልጣፋ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን የገለጸው ባለሥልጣኑ የዋጋ ጭማሪ ካደረገባቸው አገልግሎቶች ውስጥ የተሽከርካሪ ዋጋ ግምት ማሳወቅ  ከዚህ ቀደም 500 ብር የነበረው አሁን 1,000 ብር ፣የተሽከርካሪ የዋጋ ግምት ለሽያጭ አገልግሎት 2,310 ብር የነበረው ወደ 4,000 ብር፤ የተሽከርካሪ የባለቤትነት ስም ዝውውር አገልግሎት 3,000 ብር የነበረው ወደ 5,000 ብር ፤ለጠፋ የአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ ምትክ ለመስጠት 620 ብር የነበረው ወደ 5,000 ብር ከፍ ማለታቸው ይገኙበታል። በዚህ የአገልግሎት ጭማሪ ላይ ዶቼቬለ ያወያያቸው የፌስቡክ ተጠቃሚዎች የተለያዩ አስተያየቶችን ሰጥተዋል። 


«የወቅቱን የኑሮ ሁኔታን ታሳቢ ያላደረገ ጭማርም ይመስለኛል!» ያሉት በቀለ ከለዳ «ሌላው በአስገዳጅ ሁኔታ ለሚጠፋብህ ሰነድ ምትክ ማረጋገጫ ለመስጠት ከሚወጣው ወጪ ጋራ የማይመዛዘን የተጋነነ ዋጋ መጫን ፈጽሞ ልክ አይደለም!»ብለዋል።ተስፋለም ሌጎ በምሬት ይጠይቃሉ« ለማን ቅሬታ እናቅርብ ሕግ አውጪም አስፈፃምም እናንተው ናችሁ» ሲሉ ሞላ ወዳጁ ደግሞ እንደዜጋ እንሀገር እሚያዋጣ ሳይሆን ተስፋ እንድቆርጥ ያረጉሀል አይደለም በሹፍርና ለመስራት በሀገር ደረጃ ለመኖር ተስፋ የለህም ። አንድ መንጃ ፈቃድ በአመት ስንት ጊዜ ይጠፋል? ! ትራፊክ ፖሊስ ስንት ጊዜ ይይዘዋል ? እንዴት አስበው ሕግ እንደሚወጡ ለመናገር ከበደኝ ብቻ ተስፋ ያስቆርጣል።!!!!» ሲሉ በአራት ቃለ አጋኖ ምልክት ቅሬታቸውን ደምድመዋል። ጌታሁን ግዛቴ «ለጉልበተኛው ጉልበተኛ ይዘዝበት ሌላ ምን ይባላል፣ ሲሉ እርግማን ብጤ ሰንዝረዋል።የኢትዮጵያ በጀትና የቤተ-መንግስት ግንባታ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መንግስት ለህዝብ አገልግሎቶች እያደረገ ያለው ጭማሪ እጅግ የተጋነነ ፍፁም የህዝቡን የመክፈል አቅም ያላገናዘበ ነው!! ምን ያመጣሉ? የሚል የትዕቢት ውሣኔ ይመስላል፣መመርያውን አውጪዎቹም ህዝቡ መሃል እየኖሩ ያሉ አይመስሉኝም!የሚለው ደግሞ የመኮንን አያኒ አስተያየት ነው።«ለማን አቤት ይባላል» ሲሉ አስተያየታቸውን የጀመሩት መላኩ ዋጋዌ ሀይላ «ስንቱ ደሀ ሕዳሴ ግድብ ሲያልቅ አይደል የመብራት ታሪፉ ሊጨመረበት፣እይዞህ በርትተሃል በላብህ በወዝህ የገነባኸው ግድብ ትሩፋቱን ቅመስ ድጎማ ይገባሀል መባሉ ቀርቶ............ አቦ ተዉና ክፉ አታናግሩን ሲሉ ሀሳባቸውን ደምድመዋል።

ሰናይት ጌድዮን አምላካቸውን አንድ ነገር ብቻ ጠይቀዋል።«አምላኬ መንጃ ፈቃዴን ከሌባ ጠብቅልኝ» ሲሊ።አንዱዓለም በዛብህ «ትንሽ አላነሰም ?»በማለት ተሳልቀዋል ።ገብርኤል ጂብሪል ደግሞ« እኔ በበኩሌ የታየኝ መንግስት ምንም ገንዘብ እንደሌለው ነው። »ሲሉ ደስታ በሪሶ በሪሶ በበኩላቸው «ከመጣብን መአት እ/ር ይታደገን» ሲሉ ተማጽነዋል። «ልኑር አትኖርም! ከሀገር ልውጣ አትወጣም የሆነ ላይፍ(ሕይወት) ሲሉ የተማረሩት ደግሞ ዳውድ ሞሐመድ አሊ ናቸው።

እስራኤል በሊባኖስ ባካሄደችው የሚሳይል ድብደባ የተነሳው እሳት ምስል Hussein Malla/AP/dpa/picture alliance

የደሞዝ ጭማሪው «ሳይመጣ የሄደ ተስፋ» ወይስ ደጓሚ ?

የእስራኤልና ሂዝቦላ እንዲሁም ኢራን ጦርነት 

ስለሰሞኑ የእስራኤልና የሂዝቦላ እና የኢራን ጦርነት ወደ ተሰጡ አስተያየቶችን ስናልፍ አብዛኛዎቹን ስንጽፍ የያዙ ፣የሚፈርጁ እና አንዱን አጥላልተው ዘልፈው ሌላው ከፍ ለማድረግ የሚሞክሩትንና የመሳሰሉትን ወደ ጎን ትተን ጥቂቱን ስንመለከት «አለም ለጉልበተኞች ናት ኮሳሳ ሁነህ ከተገኘህ ሁሉም እየተነሳ ይደቁስሀል ጠንከር ማለት ነዉ ወዳጄ የሚለውን የአቡ ሀበሻን አስተያየት እናገኛለን።ዜድ ኮራ « በአሸባሪዎች ምክንያት ንፁሀን ሲሞቱ ያሳዝናል ጌታ በነገር ሁሉ ማስተዋልን ይስጣቸው ብለዋል።ኬቢ ቴ በሚል የፌስቡክ ስም የሰፈረ አስተያየት ኢትዮጵያውያን ስለጦርነቱ አስተያየት ሲሰጡ እንዲያስተውሉ ይመክራል። የእሥራኤልና ሔዝቦላ ጦርነት የፈጠረው ስጋት
« እኛ ግን በማያገባን ለምን እንገባለን የእነሱ ጠብ የመሬት የታሪክ ነው። ሙስሊም ስለሆንክ አረብ አይወድህም ክርስቲያን ስለሆንን እሥራኤል አትወደንም ስለዚህ እኛ እርስ በራሳችን ልንዋደድ ይገባል ዓለም ሀይማኖትን ለፖለቲካ መሣሪያነት ነዉ የሚጠቀምበት እናስተውል ሲሉ የበኩላቸውን ምክር አካፍለዋል። ሰሞኑን በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች አነጋጋሪ በነበሩ ሦስት ጉዳዮች ላይ የተሰጡ አስተያየቶችን ከሞላ ጎደል የቃኘንበት የዛሬው የማኅበራዊ መገናና ዘዴዎች ቅኝት በዚሁ ያበቃል ።
ኂሩት መለሰ
አዜብ ታደሰ 
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW