የሥልጣን ሽግግር ሂደቱን የጀመረው የቱለማ ገዳ
ዓርብ፣ ሰኔ 13 2017
ስርዓቱ የቀጣይ ስምንት ዓመታት ሕግን የማርቀቅ፣ የማሻሻልና የማሸጋገር ሥራ ላይ ነው ተብሏል። የቱለማ ኦሮሞን በአባገዳነት ያስተዳደሩት አባገዳ ጎበና ሆላም በቀጣይነት ሥልጣናቸውን ለአዲስ አባገዳ ያስረክባሉ።
በቱለማ የኦሮሞ ጎሳ በየስምንት ዓመት ሥልጣን እያሸጋገሩ አገር የማስተዳደር ሚናቸውን የሚወጡ አምስት የገዳ ስርዓት ፓርቲዎች አሉ። ሚችሌ፣ ዱሎ፣ ሮባሌ፣ ብርመጂ እና ሆረታ ይሰኛሉ። ያለፉትን ስምንት ዓመታት የሥልጣን ዘመናቸውን እያጠናቀቁ ያሉት የቱለማ አባገዳ ጎበና ሆላ ከፓርቲያቸው ሆረታ ጋር የሥልጣን ጊዜያቸው በመጠናቀቅ ዋዜማ ላይ ናቸውና አሁን ለሚችሌ የገዳ ስርዓት (ፓርቲ) እና በሂደቱ ለሚመረጡት አባገዳ ስፍራውን ሊለቁ በዱከም አካባቢ በሚገኘው ኦዳ ነቤና አቃቂ አካባቢ ባለው ጨፌ ቱማ ወይም ሕግ በሚረቅበት ስፍራ ስርዓቱ እየተከናወነ ነው።
ሥልጣን ልረከብ መዳረሻ ላይ ያለው የሚችሌ ገዳ (ፓርቲ) አባል የሆኑትና በስርዓቱ እየተሳተፉ የሚገኙት የስርዓቱ አዋቂ ኪያ ከበደ ለዶይቼ ቬለ እንደነገሩት፤ አሁን በቱለማ ኦሮሞ ገዳ ስርዓት የተጀመረው የኦዳ ነቤ እና ጨፌ ቱማ መሰባሰብ የሚጠቃለለው በሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር ነው። «ዋናው ነገር የሥልጣን (ባሊ) ማሸጋገር ነው» በማለትም በየስምንት ዓመት የሚከናወነው ስርዓቱ አሁን ላይ ሆረታ የሚባለው ስርዓት ለምችሌ (ሙደና) ሥልጣኑን ለመስጠት ዝግጅት ላይ እንደሚገኝ አመልክተዋል። ከሰሞኑ በተለይም ከቅዳሜ ሰኔ 7 ቀን 2017 ዓ.ም. ጀምሮ ወደ ኦዳ ነቤ ያቀኑት የስርዓቱ ታዳሚዎችም ወደ ጨፌ ዶንጎራ እና አቃቂ ወደሚገኘው የጨፌ ቱማ (ሕግ በሚረቅበት ስፍራ) የሕግ ማርቀቅ ሥራውን እያከናወኑ መሆኑን አስረድተዋል።
የኦዳ ነቤው መሰባሰቡ ዋና ዓለማ የተጣሉትን ማስታረቅ እና ችግሮችን በንግግር መፍታት ነው የሚሉት ኪያ፤ በቱለማ ልጆች መካከል ሥልጣኑን ለማስተላለፍ አሁን እየተከናወነ ያለው ሕግን የማርቀቅና የማሻሻል ሥራው ግን ረዘም ያለ ጊዜ ሊወስድ እንደሚችልም ጠቁመዋል። «አሁን ሥልጣኑን እያሳለፉ ያሉት ያው ከሦስቱ የቱለማ ልጆች (ጂሌ፣ ዳጪ እና በቾ) ሆነው አዲሱ ወደ ሥልጣን የሚመጣው ምችሌ ከሆረታ ፓርቲ የሆነውን ጎበና ሲያስተዳድርበት የነበረውን ስርዓት ይቀይራል» በማለት በየስምንት ዓመቱ ሕጎች ሊቀየሩና ሊስተካከሉ (ሊሻሻሉ) እንደሚችሉም ገልጸዋል። ሆኖም የማይሻሻሉ ሕጎች አሉ የሚሉት የአዲሱ የቱላማ ሥልጣን ተረካቢ እጩ ፓርቲ አባሉ ሕጎች እንደማይጻፉና የገዳ ስርዓቱን ለመምራት ኃላፊነት የሚረከበው አባገዳ ሁሉንም የስርዓቱን 390 አንቀጾች በቃል ለመያዝ ሃላፊነት እንደሚጣልበትና አሁን እየተከናወነ ያለው ስርዓት ይህንን እንደሚካተትም አስረድተዋል።
አቶ ኪያ በስርዓቱ የስምንት ዓመት የሥልጣን ዕድሜ ትልቁ የሥልጣን ዘመን ገደብ መሆኑን በመጠቆም፤ ከዚያም በፊት በአራት ዓመት ሥልጣን እንዲከትም የማድረግ እድል መኖሩን ጠቁመዋል።«ማስተዳደር ካልቻለ ሥልጣኑ በአራት ዓመት ሊያበቃ ይችላልም» በማሌ ትልቁ የሥልጣን ገደብ ግን ስምንት ዓመት መሆኑንና ከዚያ በፍጹም እንደማይሻገርም አስረድተወዋል።
አሁን እየተካሄደ ያው የስርዓቱን ሕግ የማስተላለፍ ሥራው መች እንደሚጠናቀቅ አይታወቅም ያሉት ኪያ ምችሌ ቀጣይ ስምንት ዓመታትን የሚያስተዳድርበት ሕግ የማውጣት ሥራ ስርዓቱ በሚፈቅድላቸው አካላት ተሳትፎ እየተከናወነ መሆኑን አስረድተዋው። ለቀጣይ አንድ ዓመት በሚወጣው ሕግ ላይ የህዝብ ውይይት ተደርጎ የሥልጣን ሽግግሩ ተፈጻሚ እንደሚሆንም አመልክተዋል፡፡
«ይህን ሕግ አውጥቻለሁ ይሆናል አይሆንም የትኛው ጥሩ የትኛው መጥፎ ነው በሚል ለአንድ ዓመት ሕዝብ ካወያየ በኋላ ሕዝብ የጠላውን ሕግ በመተው ሕዝብ የወደደውን ለማጽደቅ በቀጣይ ዓመት ተመሳሳይ ጊዜ ለስምንት ዓመታት ገቢራዊ የሚሆነውም ሕግ ካጸደቀ በኋላ አዲስ አባገዳንም መርጦ ስርዓቱን እንደሚሩ ያደርጋልም» በማለት የዛሬ ዓመት ስምንተኛ የሥልጣን ዓመታቸውን የሚጠናቅቁት የቱለማ አባገዳ ጎበና ሆላ የግድ በሌላ አባገዳ ይተካሉም ብለዋል።
ሥዩም ጌቱ
ሸዋዬ ለገሠ
ታምራት ዲንሳ