1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሦስት የሳህል አገራት አዲስ ኅብረት እጣ ፈንታ

ቅዳሜ፣ ኅዳር 29 2016

«የሦስቱ ሀገራት ፀረ-ፈረንሳይ ስሜት ጠንካራ መሆን ብቻውን ሰርጎ ገቦችን ለመዋጋት በቂ ያደርጋቸዋል ማለት አይደለም። ተልዕኮአቸውን ለማሳካት የሚያስችል አቅምና መሠረተ ልማት የላቸውም። ምንም ዓይነት ኮንፈደሬሽን ቢቋቋም አሁን በአካባቢው የሚካሄደውን የአሸባሪዎች እንቅስቃሴ አያስቆምም »

በመፈንቅለ መንግሥት ሥልጣን የያዙት የማሊው መሪ አሲሚ ጎይታ፣የኒዠሩአብዱራህማኑ ቲያኒ እና የቡርኪናፋሶው ኢብራሂም ትራኦሬ
በመፈንቅለ መንግሥት ሥልጣን የያዙት የማሊ፣የኒዠር እና የቡርኪናፋሶ መሪዎች ምስል Francis Kokoroko/REUTERS; ORTN - Télé Sahel/AFP/Getty; Mikhail Metzel/TASS/picture alliance

ከሳህል ቡድን አምስት ኃይል የወጡት አዲሱ የማሊ የቡርኪናፋሶና የኒዠር ኅብረት ፋይዳ

This browser does not support the audio element.

ሦስት የምዕራብ አፍሪቃ ሀገራት በሳህል አካባቢ የሚንቀሳቀሱ አክራሪ ሙስሊሞችን ለመዋጋት ከተቋቋመው ቡድን አምስት ከተባለው የጋራ ኃይል ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ በይፋ ተሰናብተዋል። ከጋራ ኃይሉ የወጡት በመፈንቅለ መንግሥት ስልጣን የያዙ መሪዎች የሚያስተዳድሯቸው ማሊ፣ ቡርኪናፋሶ እና ኒዠር ናቸው። የሦስቱ ሀገራት ከቡድኑ መውጣት ቻድና ሞሪታንያን ብቻ በቡድኑ አባልነት አስቀርቷል። የሳህል አካባቢ ከጎርጎሮሳዊው 2014 ዓ.ም. አንስቶ ጽንፈኞች የሚንቀሳቀሱበት አካባቢ ነው። በዚያ የተነሱ ግጭቶችም ሰብአዊውን ቀውስ አባብሰው ከ24 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን እርዳታ ጠባቂ ሆነዋል።  ቡድኑን የዛሬ 9 ዓመት ንዋክሾት ሞሪታንያ ውስጥ የመሰረቱት ቡርኪናፋሶ ፣ቻድ፣ማሊ ሞሪታንያና ኒጀር ናቸው።ቻድና ሞሪቴንያ አሁንም የቡድኑ አባል ቢሆኑም ሦስቱ ሀገራት ቡድኑን ለቀው መውጣታቸው ኅብረቱን አዳክሟል ይላል የዶቼቬለው አይሳክ ካሌድዚ ዘገባ። 


ቡድኑን ለቆ በመውጣት ከማሊ ጋር ያበሩት ቡርኪናፋሶና ኒጀር አምስት አባላት ያሉትን በቡድን የተቋቋመበትን ዓላማዎች ከግብ ማድረስ ተስኖታል ሲሉ ተችተዋል። ሦስቱ ሀገራት በጋራ ባወጡት የጋራ መግለጫ የሳህል አካባቢን የፀጥታና የልማት ዞን ለማድረግ የተጀመረው ጥረት ባለፉት አሰራሮች ምክንያት መጓተቱን ጠቅሰው የነጻነታችንና የክብራችን ሂደት ከአሁኑ የቡድኑ ቅርጽ ጋር አይጣጣምም ብለዋል።

በጂቦ ቡርኪናፋሶ ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድንለ ተፈናቃዮች የምግብ እርዳታ ሲያከፋፍል ምስል MSF/Nisma Leboul

የማሊ የቡርኪናፋሶና የኒጀር ጥምረት መጨረሻ

የሦስቱ ሀገራት መግለጫ ይህን ቢልም የፀጥታ ጉዳዮች አዋቂው አዲብ ሳኒ ለዶቼቬለ በሰጡት አስተያየት ሦስቱ ሀገራት አዲሱ የሦስቱ ሀገራት የፀጥታ ስምምነት ስኬታማ የመሆን እድል የለውም ብለዋል። «ሦስቱ ሀገራት በአሸባሪ ቡድኖች ጫና ስር መሆናቸው ይታወቃል። አዲሱ ኮንፌደሬሽን ምንም ዓይነት ውጤት ላይ መድረሱ በጣም አስቸጋሪ ነው የሚሆንበት።» 
እርሳቸው እንዳሉት ሦስቱ ሀገራት የሳህል አገራት ኅብረት በእንግሊዘኛው ምህጻር (AES) ሲሉ የሰየሙትን ኅብረት የመሰረቱት ባለፈው መስከረም ነው። ሆኖም አዲሱ ኅብረት ብዙ አስተዋጽኦ ሊያደርግ የሚችልበት አቅም እንዳለው የሚያሳይ ምንም ነገር የለምም ። 


«የማሊ መንግሥት በሦስት ግንባሮች እየተዋጋ ነው። ኒዠር ውስጥ ደግሞ የፈረንሳይ ጦር ከሀገሪቱ ከወጣ በኋላ ከቁጥጥር ውጭ የሆኑ ጥቃቶች ቁጥር ጨምሯል። በዓለማችን የሚደርሱ የሽብር ጥቃቶችን ደረጃ የሚያወጣው ቴሮሪዝም ግሎባል ኢንዴክስ የተባለው ተቋም ባለፈው ዓመት እንዳስታወቀው ቡርኪናፋሶ ሽብር ተጽእኖ ከሚያደርግባቸው ሀገራት ሁለተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች። ከዚህ ሌላ በንጽጽር ሲታይ የቀራትን አነስተኛ መሬት ጠብቆ ለማቆየትም ውጊያ እያካሄደች ነው።ምክንያቱም አሁን መንግሥትን የሚወጉት ሚሊሽያዎች ከሀገሪቱ ከግማሽ በላይ የሚሆነውን አካባቢ ተቆጣጥረዋል።»  እናም  ሳኒ በራሳቸው የውስጥ ጉዳዮች የተጠመዱት ሦስቱ ሀገራት ኅብረት ቢፈጥሩም ምንም ትርጉም ያለው ውጤት ላይ አይደርሱም ይላሉ።

የፈረንሳይ ወታደሮች በቡርኪናፋሶ ከዛሬ አራት ዓመት በፊት ምስል Philippe De Poulpiquet/MAXPPP/dpa/picture alliance


ፀረ -ምዕራባውያን ስሜት 


ሦስቱ ሀገራት ከቀድሞ ቅኝ ገዥያቸው ከፈረንሳይ ጋር ግንኙነታቸውን አቋርጠዋል። ፈረንሳይ ደግሞ በሳህል ቡድን አምስት 
ውስጥ ከፍተኛ ሚና ያላት ሀገር ናት። ከቡድኑ አፈንግጠው የወጡት ሦስቱ ሀገራት ባወጡት መግለጫ በተዘዋዋሪ  ፈረንሳይን በተመለከተ በቀጥታም ባይሆን በጥቅሉ «የሳህል ቡድን አምስት» በአጋርነት ስም ትዕዛዝ የሚሰጡ ኃይሎች ህዝባችንን እንደ ህጻን በመቁጠር ሉዓላዊነቱን ባለመቀበል ህዝባችንን በመጉዳት  የውጭ ሀገራትን ጥቅም ማስጠበቅ አይችልም።» ሲሉ ከቡድኑ የወጡበትን ምክንያት ገልጸዋል።
ሙታሩ ሙሙኒ ሙክታር የምዕራብ አፍሪቃ ጽንፈኝነትን መከላከያ ማዕከል ዋና ሃላፊ ናቸው። የሦስቱ ሀገራት ኅብረት ቅርጽና አቋም አዲስ አልሆነብኝም ይላሉ። 
«ለመንግስታቶቻቸው ጥበቃና ፣ ራሳቸውን ለመከላከል አዲስ ኅብረት መፍጠሩ ትርጉም አለው። ሆኖም ኅብረቱ  ጽንፈኛ ጥቃቶችን በመከላከል ረገድ ምን ያህል ውጤታማ ይሆናል የሚለው ወደፊት የሚታይ ነው የሚሆነው። ምክንያቱም ሁሉም ሀገራት አቅምን በተመለከተ በዘላቂ የገንዘብ እርዳታ ችግር ፣ችግሩን ለመከላከል በሀገር ውስጥ መልካም ፈቃድ በመታጣቱ   በጣም ተፈትነዋል። »
ሦስቱ ሀገራት ባጸደቁት መተዳደሪያ ደንብ አሸባሪነትንና የተደራጀ ወንጀልን ለመዋጋት ቃል ገብተዋል። ሙክታር እንዳሉት የሦስቱ ሀገራት ፀረ-ፈረንሳይ ስሜት ጠንካራ መሆን ብቻውን ሰርጎ ገቦችን ለመዋጋት በቂ ያደርጋቸዋል ማለት አይደለም። ሦስቱ ሀገራት ተልዕኮአቸውን ለማሳካት የሚያስችል  አቅምና መሠረተ ልማት የላቸውም። ሦስቱ ሀገራት ከምዕራብ አፍሪቃ የልማት ማኅበረሰብ በምህፃሩ ኤኮዋስ እንደታገዱ ነው። ከድርጅቱ ጋር ያላቸው ግንኙነትም ላሽቋል። የሳህል የፀጥታ ችግር ከተባባሰ መጥፎ ዜና ነው ሲሉ የገለጹት ሳኒ ምንም ዓይነት ኮንፈደሬሽን ቢቋቋም አሁን በአካባቢው የሚካሄደውን የአሸባሪዎች እንቅስቃሴ አያስቆምም ብለዋል።ስለዚህ በርሳቸው እምነት እነዚህ ሦስት አገራት የፀጥታውን ችግር ለመቀነስ የሚያስፈልገውን ዓለም አቀፍ እገዛ ለማግኘት ከኤኮዋስ ጋር የነበራቸውን ግንኙነት ወደ ቀድሞ ደረጃ መመለስ ቅድሚያ ትኩረት ሊሰጡት የሚገባ ጉዳይ መሆን አለበት። የአካባቢው የጸጥታ ችግር 4.9 ሚሊዮን ሰዎችን አፈናቅሏል። 

አይሳክ ካሌድዚ
ኂሩት መለሰ
አዜብ ታደሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW