የረሃብ ስጋት በኢትዮጵያ
ዓርብ፣ ሰኔ 17 2014ኢትዮጵያ ዉስጥ በተከሰተ ድርቅ እና በተለያዩ አካባቢዎች በሚደረጉ ግጭቶች ከ 20 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ለረሃብ ተጋልጦአል ሲል የተባበሩት መንግስታት የዓለም የምግብ ድርጅት (WFP) ገለፀ። የዓለም የምግብ ድርጅት ከሚቀጥለዉ ወር ጀምሮ የሚሰጠዉ የምግብ ድጋፍም ሊቀንስ ይችላል ሲል አስጠንቅቋል። የኢትዮጵያ መንግስት ግን ከ19 ሚሊዮን ለሚበልጥ ሕዝብ ርዳታ እንደሚሰጥ ገልፆ በሃገሪቱ ረሃብ ስጋት እንደሌለ አስታዉቋል።
የተባበሩት መንግስታት የዓለም የምግብ ድርጅት (WFP) ትናንት ይፋ ባደረገዉ መግለጫ በድርቅ የተጎዱት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በኦሮሚያ፣ ሶማሌ እና ደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ዉስጥ ይገኛሉ። የድርጅቱ የምስራቅ አፍሪቃ ዳይሬክተር ሚሻኤል ዳንፎርድ እንደተናገሩት በኢትዮጵያ የሚታየዉ የምግብ እጥረት በዓለም ሃገራት ከሚታየዉ የምግብ እጥረት ሁሉ የከፋዉ ነዉ።
« በኢትዮጵያ የሚታየዉ እውነታ ዛሬ ከማንኛቸውም የዓለም ሀገራት ሁሉ የከፋ ነው። ይህ ደግሞ የምስራቅ አፍሪቃን በተለይም ደግሞ የአፍሪቃ ቀንድን ሁኔታ የሚያሳይ ነው። ባለፈው ዓመት በዚህ ሰዓት 50 ሚሊዮን ሰዎች በምግብ ዋስትና ከፍተኛ መጠን የተቸገሩ፣ በጣም የተራቡ ነበሩ። ይህ ቁጥር ዛሬ 89 ሚሊዮን ደርሶአል። የረሃብተኛዉ ቁጥር ወደ 90% መጨመሩን አይተናል። ይህ በሃገሪቱ በሚታየዉ ግጭት ፣ አየር ንብረት እንዲሁም የኮቪድ ወረርሽኝ ጥምር ተፅእኖ ነው። አሁን ደግሞ በሃገሪቱ ከፍተና የኑሮ ዉድነት እና የዋጋ ግሽበት እያየን ነዉ። ይህ ደግሞ በአብዛናዉ በዩክሬኑ ጦርነት ምክንያት የተከሰተ ነዉ።»
በሶማሌ ክልል ከሚገኙት 11 ዞኖች መካከል በተለይ ሸበሌ ሲቲ እና ዳዋ ዞኖች የረሃብ አደጋዉ አሳሳቢ ሆንዋል ያሉን በሶማሌ ክልል የዳዋ ዞን አደጋ መከላከልና ዝግጁነት ዋና ተጠሪ ዚያድ ኢብራሂም፤ በዞኑ ከብቶች አልቀዉ ግመሎች እየሞቱ ናቸዉ ብለዋል። የዓለም የምግብ ድርጅት በየወሩ ለአንድ ሰዉ ይሰጠዉ የነበረዉን የእህል ርዳታ ከ15 ኪሎ ወደ 10 ኪሎ ቀንሶታል።
«በሶማሌ ክልል የበልግ ዝናብ አልነበረም። ባለፉት ወራቶች በድርቁ ሳብያ ከብቶች አልቀዋል አሁን ደሞ ግመሎች እየሞቱ ነዉ። በክልሉ የአስቸኳይ የምግብ እርዳታ የሚፈልገዉ ሰዉ ቁጥር አምስት ሚሊዮን ደርሶአል። ባለፈዉ አመት ሁለት ሚሊዮን አካባቢ ነበር። በሶማሌ ክልል ከሚገኙ አስራ አንድ ዞኖች መካከል፤ ሦስt ዞኖች ማለት ሲቲ ዳዋ እና ሸበሌ ዞኖች በድርቁ ክፉኛ የተጠቁ ናቸዉ። የተባበሩት መንግስታት የዓለም የምግብ ድርጅት (WFP)ቀደም ሲል ለአንድ ሰዉ 15 ኪሎ በየወሩ ሲሰጥ የነበረዉን እህል በጀት የለም በማለት አሁን የሚሰጠዉ አስር ኪሎ ብቻ ነዉ።»
እንደ መንግሥታቱ ድርጅት ዘገባ ከሆነ ወደ 300,000 የሚጠጉ ሰዎች ለመጠጥ ውኃ እና ግጦሽ ሳር ፍለጋ ተፈናቅለዋል። በምግብ እጥረት ምክንያት በኢትዮጵያ ግማሽ ሚሊዮን ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው ለመቅረት መገደዳቸዉንም አትቶአል። ከሦስት ሳምንታት በፊት በአፋር ክልል በተደጋጋሚ በተስተዋለው ጦርነትና ድርቅ ሳቢያ በምግብ እጥረት ወደ ሆስፒታል ከገቡ ህጻናት መካከል ከ30 በላይ የሚሆኑት ህይወታቸው ማለፉን ሆስፒታሉ ማስታወቁ የሚታወስ ነዉ፡፡ በኢትዮጵያ ረሃብ የለም ያሉት የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ አቶ ደበበ ዘዉዴ ትግራይን ሳይጨምር ከ 19 ሚሊዮን በላይ ተረጂዎች በሃገሪቱ ዉስጥ እንዳሉ አልሸሸጉም።
« በኢትዮጵያ በድርቅም በግጭትም የተጎዱ ወገኖች አሉ። ረሃብ የሚባለዉ ግን አይደለም። አቅርቦት ሲታጣ ነዉ ረሃብ የሚባለዉ። አሁን ለምሳሌ እና በአፋር አማራ ኦሮምያ፤ ሶማሌ እና ደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልል፤ ከግጭት ጋር በተያያዘ ለእለት ደራሽ ተረጅዎች፤ ምግብና ምግብ ነክ እርዳታ ይሰጣል። በእነዚህ አምስት ክልሎች 19።15 ሚሊዮን ህዝብ ድጋፍ ይቀርብለታል።»
የተባበሩት መንግሥታት የምግብ ድርጅት በሰሜን ኢትዮጵያ ለ19 ወራት በዘለቀው ጦርነት በተለይም በአፋር፣ በአማራ እንዲሁም በትግራይ ክልሎች ከ 13 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ለሰብአዊ እርዳታ መዳረጋቸዉን ገልፆአል። በትግራይ ከ 20 በመቶ በላይ ህፃናት ደግሞ በተመጣጠነ ምግብ እጦት እየተሰቃዩ መሆኑን አስታዉቋል። የዩክሬኑ ጦርነት ከፍተኛ ተፅኖ ማሳደሩን የገለፀዉ የዓለሙ የምግብ ድርጅት ኢትዮጵያ የእርሻ ማዳበርያን ጨምሮ የስንዴ ምርትን ከዩክሬን እና ከሩስያ ትገዛ እንደነበር እና በጦርነቱ ምክንያት በኢትዮጵያ የሚታየዉ የምግብ እጥረት በሚቀጥለዉ ዓመት አስከፊ ሊሆን ይችላል ሲል ስጋቱን ገልፆአል።
አዜብ ታደሰ
ነጋሽ መሐመድ