1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የረጋ ዘይት እና ጤናማ አመጋገብ

ማክሰኞ፣ ነሐሴ 28 2016

አመጋገብ ለተለያየ የጤና እክል ሊያጋልጥ እንደሚችል የህክምና ባለሙያዎች ሆኑ የስነምግብ ባለሙያዎች መናገር ከጀመሩ ውሎ አደረ። አንዳንዶች እንኳን ለህመም የሚያበቃ ሆድ የሚሞላ ምግብ ማግኘት እንደሚቸግራቸው በሚነገርበት በዚህ ወቅት አመጋገባችሁ ላይ ጥንቃቄ አድርጉ ማለቱ የቅንጦት ሳይሆን ጤናማ ሕይወት ለመምራት መሠረታዊ ጉዳይ ነው።

አዲስ አበባ ገበያ ቦታ
አዲስ አበባ የገበያ ስፍራ ፎቶ ከማኅደርምስል Seyoum Getu/DW

ጤና እና አካባቢ

This browser does not support the audio element.

 

«ለጤናና አካባቢ ፕሮግራም  አዘጋጆችና  አቅራቢዎች  በሙሉ  የከበረ  ሠላምታ  እያቀረብኩ በመቀጠል  በኛ  ሐገር  ማኅበረሰቡ  በሰፊው እየተጠቀመ ስላለው የረጋ የምግብ ዘይት እያስከተለ ስላለው የጤና ጠንቅ ለመጠየቅ ስለፈለኩ ነው፤ ይህን ፈሳሽ ያልሆነ ሙቀት ያልነካው፤ ወደፈሳሽነት የማይቀየር ዘይት ሁሉም ሰው ይጠቀመዋል።

አቅሙ ያለው በቤቱ ፈሳሹን ብቻ የሚጠቀም ቢሆንም በሆነ አጋጣሚ በግብዣ ቦታም ሆነ በየሆቴል በሚሠሩ ምግቦች ሳይጠቀመው አይወጣም።

የእኔ ጥያቄ ምንድነው እጅግ በጣም ብዙ ሰው እግሬን ቆረጠመኝ፣ ወረረኝ፤ አሳሰረኝ ነው የሚለው ወደ ጤና ተቋማት ሲኬድ የረጋ ዘይት አታዘውትሩ ከማለት ውጪ በግልፅ ስለጉዳቱ በድፍረ,ት እየተነገረ አይደለም፤ የዚህ ዓይነቱን የጤና ችግርም እኔ ከአራት ዓመት ወዲህ ተጠቂ ሆኛለሁ፤ ሀኪም ቤት ስሄድም ከሀኪሞች የሚሰጠኝ የጥንቃቄ ምክር ይህንኑ የረጋ ዘይት አታዘውትሩ ነው፤ ሕመሙ ሪህ እንደሚባል ጭምር ነው የጤና ባለሙያዎች የሚያስረዱት፤ እናም ይህ የረጋ ዘይት ከተመረተበት ሀገር ወደ እኛ ሲገባ የጥራት ቁጥጥር ስለማይደረግ ነው ወይስ ከኅብረተሰቡ አጠቃቀም ችግር የሚመጣ ነው? በዚህ ላይ ባለሙያ ጠይቃችሁ ምላሽ ብትሰጡኝ እያልኩ የዛሬ መልእክቴን ላብቃ፤ የእናንተው ጥቁር አሚን ከደሴ።»

የምግብ ሸቀጥ መሸጪያ የገበያ አዳራሽ ፎቶ ከማኅደርምስል Seyoum Getu/DW

የዶቼ ቬለ የዘወትር አድማጭና ተሳታፊ የደሴው ጥቁር አሚን፤ በቅድሚያ ስለተሳትፎዎ ከልብ እናመሰግናለን። እርስዎ ያነሱት የረጋ ዘይት ጉዳይ ኢትዮጵያ ውስጥ መነጋገሪያ ከሆነ ከርሟል። ለምግብ ማብሰል ዘይትን በብዛት ከመጠቀም ካለው የኅብረተሰቡ ልማድ አኳያ በመነሳትም እንዲህ ያለው ዘይት በብዛት ወደገበያው ከገባ ወዲህ ተላላፊ ባልሆኑ ህመሞች የሚያዘው ሰው ቁጥር ስለመጨመሩም ይነገራል። እርግጥ ነው ይህ እራሱን የቻለ ጥናት በጤና ጥበቃ በኩልም ሆነ በሀገሪቱ የመድኃኒትና ምግብ ጥራት ቁጥጥር ባለሥልጣን መሥሪያ ቤት አማካኝነት ሊደረግበት እንደሚገባ ይታመናል።

ዘይት ምግብ በማብሰሉ ሂደት ከግብዓቶች አንዱ እንደመሆኑ በቅድሚያ ጥያቄዎችን ያቀረብነው ለስነምግብ ባለሙያው ለአቶ አብነት ተክሌ ነው። አቶ አብነት ላለፉት ስምንት ዓመታት ባቋቋሙት ስለአመጋገብ የምክር አገልግሎት የሚሰጥ ተቋም በርካቶችን ያማክራሉ።

እሳቸው እንደሚሉት ዘይትን ኢትዮጵያውያን ምግባችንን ለማጣፈጥ የምንጠቀምበት እንደመሆኑ ከሽንኩርትም ሆነ ከበርበሬ አለያም ከተለያዩ አትክልቶች ጋር በሙቀት የምንፈልገውን ጣዕም እንዲያመጣ መጥበሳችን የተለመደ ነው። በእንዲህ ያለ ሂደት የተዘጋጀውን ምግብ ስንመገብም ለሰውነት የሚስማማበት ጊዜ የመኖሩን ያህል ላይስማማም ይችላል። ብዙዎች ዘይትን ለምግብ ማጣፈጫነት እንጠቀመው እንጂ ስለምንነቱም ሆነ በሙቀት ሲግል ስለሚኖረው ባህሪ እጅግም መረጃው ያለን አይመስልም።

በትራንስ ፋት ከሚጠቀሱ ምግቦች አንዱፎቶ ከማኅደር ምስል picture-alliance/dpa/A. Burgi

 

በአመጋገብ ጤና ረገድ የተሻለ የሚባል የዘይት ዓይነት እንዴት ያለው ነው የሚለው የብዙዎች ጥያቄ እንደሚሆን እንገምታለንና የጤናማ አመጋገብ አማካሪውን አቶ አብነት ተክሌን ጠይቀናቸዋል። የስነምግብ ባለሙያው ከረጋው ዘይት ይልቅ ፈሳሹን ያልረጋውን ዘይት መጠቀምን ይመክራሉ።

ለመሆኑ የምትገዙት የታሸገ ዘይት በውስጡ ምን እንዳካተተ መረጃ እንዳለው ልብ ብላችሁት ይሆን?

ዘይትም ሆነ የገበታ ቅቤ በውስጡ የሚኖረው በዘርፉ ሙያዊ አቀገላለጽ ትራንስ ፋት ወይም ጤናማ ያልሆነ ስብ፤ መጠን ዝቅተኛ እንዲሆን ይመከራል። ትራንስ ፋት ፈሳሽ የሆነን የምግብ ዘይት ወይም ቅቤ በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ እንዲረጋ ሲደረግ የሚፈጠር የስብ ዓይነት እንደሆነ ነው መረጃዎች የሚያመለክቱት። እንዲህ ያለው ስብ በጀርመንም ሆነ በአውሮጳ ኅብረት አባል ሃገራት ደረጃ በምግቦች፤ በዘይትም ሆነ በገበታ ቅቤ ውስጥ መጠኑ ከ2 በመቶ እንዳይበልጥ ተደንግጓል።  

ጠያቂያችን እሳቸውን ጨምሮ አብዛኞች ሪህ በመባል ለሚታወቀው ህመም መዳረጋቸውንም አንስተዋል። ዝርዝር ማብራሪያውን ለማድመጥ ሙሉ ዝግጅቱን ያድምጡ።

ሸዋዬ ለገሠ

እሸቴ በቀለ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW