የሩሲያን ኤኮኖሚ ከዓለም አቀፉ ገበያ ሚገፉት ማዕቀቦች
ረቡዕ፣ የካቲት 23 2014
ሩሲያ በዩክሬን ጦርነት ምክንያት ምዕራባውያን የጣሉባት ማዕቀብ የሚያሳድረው ጫና ያሰጋቸው የአገሪቱ ዜጎች ከባንካቸው ጥሬ ገንዘብ በእጃቸው ለማስገባት ይጣደፋሉ። ጥድፊያ ብቻውን ግን አይበቃም። የኤቲኤም ማሽኖች ባሉበት ረዥም ሰልፍ ይጠብቃቸዋል። በሴንት ፒተርስበርግ ከተማው ነዋሪው ፓይቶር "ካለፈው ሐሙስ ጀምሮ ሁሉም ሰው ጥሬ ገንዘብ ለማውጣት ከአንዱ የኤቲኤም ማሽን ወደ ሌላው እየተጣደፈ ነው። አንዳንዱ እድለኛ ይሆናል፤ ሌላው አይሳካለትም።" ሲል ሁኔታውን ይናገራል።
በዋና ከተማዋ ሞስኮ ተመሳሳይ ሰልፍ የገጠመው ሰርጌይ "የስዊፍት አገልግሎት ሲቋረጥ የዕለት ፍጆታዎች እንዴት እንደምንገዛ አናውቅም። ከውጪ አገራት ለምንገዛቸው ሸቀጦች በሙሉ ክፍያ የሚፈጸመው በካርድ ነው። እንዴት እንሸምታለን? እኔ የምሰራበት መደብር እንዴት ከጣልያን አልባሳት መግዛት ይችላል? በሌላው ረገድ እንዴት ተጽዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል አላውቅም። በሩሲያ ሁሉም ነገር እየሰራ ነው። ይሁንና እጥረት ሊከሰት ይችላል" በማለት አስረድቷል።
ለሩሲያው ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቱን ሥራዎች ከፍ ያለ ክብር እንዳላቸው የሚናገሩት ታቲያና "ያን ያክል ሐብታም ስላልሆንኩ እኔን አይጎዳኝም። እኔ አማካኝ ገቢ ነው ያለኝ። ነገር ግን አገራችንን ይጎዳታል" የሚል አቋም አላቸው። ይሁንና "በተለያዩ ዘመናት በርካታ ውጣ ውረዶችን ያለፍን ሕዝቦች ነን። ይኸንንም እንወጣዋለን ምክንያቱም ለታላቅ ጥሩ ነገር የሆነ ነው" ባይ ናቸው። ሩሲያ ጎረቤቷን ዩክሬንን በመውረሯ የተጣሉባት ማዕቀቦች እንደ ፓይቶር፣ ሰርጌይ እና ታቲያና ያሉ የአገሬው ሰዎችን ጥሬ ገንዘብ በእጃቸው እንዲያስገቡ ከማጣደፍ ባሻገር በአገሪቱ የፋይናንስ ገበያ ላይ ብርቱ ጫና አሳድሯል።
አሜሪካ፣ የአውሮፓ ኅብረት እና ካናዳ ቁልፍ ያሏቸውን የሩሲያ ባንኮች ስዊፍት ከተባለው አገልግሎት ለማገድ የተስማሙት ባለፈው ቅዳሜ ነበር። በእንግሊዘኛ ምህጻሩ ስዊፍት ተብሎ የሚጠራው የዓለም አቀፍ ባንኮች የግንኙነት ሥርዓት ደህንነቱ የተጠበቀ የመልዕክት መለዋወጫ መንገድ ሲሆን ድንበር ተሻጋሪ ክፍያዎች በፍጥነት የሚፈጸሙበት፣ ዓለም አቀፍ ንግድን የሚያመቻች ነው።
የአውሮፓ ኮሚሽን ፕሬዝደንት ኡርሱላ ፎን ደር ላየን ውሳኔው "እነዚህ ባንኮች ከዓለም አቀፉ የፋይናንስ ሥርዓት ውጪ የሚያደርጋቸው ሲሆን በዓለም ሥራቸውን የማከናወን አቅማቸውን ይጎዳል። ስዊፍት ትልቁ የባንኮች የርስ በርስ የክፍያ ሥርዓት ነው። ባንኮችን ከአገልግሎቱ ውጪ ማድረግ በመላው ዓለም የሚያደርጉትን የገንዘብ ዝውውር የሚያቆም ሲሆን ሩሲያ ወደ ውጪ የምልትልካቸውን እና ከዓለም ገበያ የምትሸምታቸውን ሸቀጦች ወዲያው ያቆማል" ሲሉ ዳፋው በባንኮች እንደማይወሰን አስረድተዋል።
ከ200 በላይ በሚሆኑ አገሮች ከ11,000 በላይ የፋይናንስ ተቋማትን የሚያገናኘው ስዊፍት ትላንት ማክሰኞ ባወጣው መግለጫ እስካሁን ማዕቀቡ የትኞቹን የሩሲያ ባንኮች እንደሚመለከት ዝርዝር እንዳልደረሰው አስታውቋል። ከ50 ገደማ አመታት በፊት ሥራ ላይ የዋለው እና መቀመጫውን በቤልጅየም ያደረገው ስዊፍት "ተግባራዊ የሚሆኑ የማዕቀብ ሕጎችን" እንደሚያከብር ገልጿል። በዚህም "ሕጋዊ መመሪያ" ሲደርሰው የተመረጡትን የሩሲያ ባንኮች ከዓለም አቀፉ ግልጋሎት ውጪ እንደሚያደርግ አረጋግጧል። የምዕራባውያኑ እርምጃ ግን በዚህ ብቻ የተገታ አይደለም።
ኡርሱላ ፎን ደር ላየን "የሩሲያን ማዕከላዊ ባንክ ጥሪት እናሽመደምዳለን። ይኸ የገንዘብ ዝውውሩን ያቆመዋል፤ ማዕከላዊ ባንኩ ጥሪቱን እንዳይሸጥ ያደርገዋል። በስተ-መጨረሻ የሩሲያ ልሒቃኖች ገንዘባቸውን በገበያዎቻችን እንዳይጠቀሙ እናግዳለን። እነዚህ እርምጃዎች ፑቲን ጦርነታቸውን በገንዘብ ለመደጎም እንዳይችሉ ያደርጋቸዋል" ብለው ነበር።
የአውሮፓ ኅብረት የፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን የቅርብ ሰዎችን ጨምሮ ማዕቀብ የጣለባቸውን 26 የሩሲያ መንግሥት ልሒቃን ከትላንት በስቲያ ሰኞ ይፋ አድርጓል። ማዕቀብ ከተጣለባቸው መካከል የፕሬዝዳንቱ ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ እና የሩሲያ መንግሥት ንብረት የሆነው ሮዝኔፍት የተባለ የነዳጅ ኩባንያ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢጎር ሲቺን የመሳሰሉ ባለሥልጣናት፤ አሊሸር ኡስማኖቭ እና ሚካሒል ፍሪድማንን የመሳሰሉ ባለጠጎች ይገኙበታል።
በማዕቀቦቹ ቀድሞ መንገራገጭ የጀመረው የሩሲያ የመገበያያ ገንዘብ ሩብል ነው። ባለፈው ሰኞ አንድ ሩብል በ0.9 የአሜሪካን ሳንቲም መመንዘሩን አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል። የአውሮፓ ኅብረት፣ አሜሪካ፣ ብሪታኒያ እና ካናዳ የሩሲያ ማዕከላዊ ባንክ ጥሪቱን እንዳያንቀሳቅስ ማገዳቸውን ይፋ ያደረጉት ባለፈው ቅዳሜ ነበር። የአሜሪካ ግምዣ ቤት ኃላፊ ጃኔት የለን እንዳሉት እርምጃው "ሩሲያ አፍራሽ እንቅስቃሴዋን በጥሪቷ እንዳትደግፍ ያደርጋታል።" ይኸ ውሳኔ ባንኩ በውጭ ምንዛሪ ያከማቸውን 630 ቢሊዮን ዶላር የሚደርስ ገንዘብ ጥቅም ላይ ማዋል እንዳይችል ያደርጋል።
የአውሮፓ ኅብረት የዉጪ ግንኙነት ኃላፊ ጆሴፕ ቦሬልን "ከሩሲያ ማዕከላዊ ባንክ የገንዘብ ክምችት ግማሹ በቡድን ሰባት አባል አገራት ባንኮች የተቀመጠ ነው። ይኸ ይታገዳል። እኛ እርምጃ ልንወስድበት በምንችልበት ቦታ የሚገኘው የሩሲያ ማዕከላዊ ባንክ የገንዘብ ክምችት ከ50 በመቶው ትንሽ አነስ ያለ ነው። በሞስኮ ወይም በቻይና የሚገኘውን የሩሲያ ባንክ ክምችት ማገድ አንችልም" ብለዋል። "የሩሲያ ባለሥልጣናት ባለፉት አመታት የገንዘብ ክምችታቸውን እኛ ልናግዳቸው በማንችላቸው ቦታዎች ሲያስቀመጡ ቆይተዋል" ያሉት ጆሴፕ ቦሬል በገንዘብ ረገድ ሩሲያ ለእንዲህ አይነት ሁኔታ ዝግጅት ስታደርግ ነበር" ሲሉ ተናግረዋል።
ምዕራባውያኑ በሩሲያ ማዕከላዊ ባንክ ላይ የጣሉት ገደብ የፑቲን መንግሥት የውጭ ምንዛሪ ክምችቱን በመሸጥ የምንዛሪ ተመኑ የተዳከመውን ሩብል ለመታደግ የሚያደርገውን ጥረት ከንቱ ያደርገዋል። ባንኩ ከተደራራቢዎቹ እርምጃዎች በኋላ የፖሊሲ ወለድ መጠኑን ከ9.5 በመቶ ወደ 20 በመቶ ከፍ አድርጓል። በውጭ ንግድ የተሰማሩ ኩባንያዎችም በእጃቸው የሚገኘውን የውጭ ምንዛሪ እንዲሸጡ ትዕዛዝ ተሰጥቷቸዋል።
የሩሲያ ማዕከላዊ ባንክ ገዢ ኤልቪራ ናቡዩሊና ባለፈው ሰኞ ተናግረዋል። "የሩሲያ ኤኮኖሚ ሁኔታዎች በፍጥነት ተለውጠዋል። የተጣሉ ማዕቀቦች በሩብል የምንዛሪ ተመን ላይ ከፍተኛ ለውጥ አስከትለዋል። ወርቅ እና የውጭ ምንዛሪ ክምችት የመጠቀም ዕድል የጠበበ ነው" ሲሉ ተናግረዋል። "ስዊፍትን የሚተካ የአገር ውስጥ የክፍያ ሥርዓት አለን" ያሉት የባንኩ ገዢ "የውጭ አገር ተሳታፊዎች መቀላቀል ይችላሉ" የሚል ግብዣ አቅርበው ነበር።
የሩሲያው ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሰርጌይ ላቭሮቭ፣ የአገሪቱ የመከላከያ ሚኒስትር ሰርጌይ ሾይጉ እንዲሁም የጦሩ ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄኔራል ቫለሪ ጌራሲሞቭ ማዕቀብ ከተጣለባቸው መካከል ናቸው። በመሪ ደረጃ እንዲህ እንደ ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን አይነት ብርቱ እርምጃ የገጠማቸው የሰሜን ኮሪያው ኪም ጆንግ ኡን፣ የቤላሩሱ አሌክሳንደር ሉካሼንኮ እና የሶርያው በሽር አል-አሳድ ናቸው። ልዩነቱ ቭላድሚር ፑቲን ምዕራባውያኑን የሚገዳደር፤ ዓለምንም የሚያሰጋ የኑክሌር ጦር መሳሪያ የታጠቀችው ሩሲያ መሪ መሆናቸው ነው።
ፕሬዝደንቱ ባለፈው እሁድ የአገራቸው የኑክሌር ኃይሎች "በተጠንቀቅ" እንዲጠባበቁ ትዕዛዝ መስጠታቸውን ይፋ ሲያደርጉ ምዕራባውያን ሩሲያ ላይ የጣሏቸውን ማዕቀቦች "ኢ-ፍትሐዊ" ብለዋቸው ነበር። ማዕቀቦቹ የሩሲያን ኤኮኖሚ ከዓለም አቀፉ ሥርዓት ውጪ ሊያደርገው እንደሚችል ተንታኞች እምነታቸው ነው።
እሸቴ በቀለ