1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የሩሲያ የዩክሬን ጦርነት ዳፋ በጠፈር ምርምሩ ዘርፍ

ረቡዕ፣ መጋቢት 14 2014

ሳምንታትን ያስቆጠረው የሩሲያና የዩክሬን ጦርነት በሀገራት ኢኮኖሚ እና ማህበራዊ ኑሮ ካሳደረው ተፅዕኖ ባሻገር፤ ቀውሱ ለዓለም አቀፉ የጠፈር ምርምር ጣቢያም ተርፏል።ችግሩ በጊዜ ካልተፈታ የጠፈር ምርምርን ወደ ቀዝቃዛው ጦርነት ዘመን ሊመልሰው ይችላል የሚል ስጋት አሳድሯል።

A view of the Earth and a spaceship. ISS is orbiting the Earth
ምስል፦ Stanislav Rishnyak/Zoonar/picture alliance

ከሩሲያ ጋር በትብብር የሚሰሩ የጠፈር ምርምሮች እየተቋረጡ ነው

This browser does not support the audio element.

በሩሲያና በዩክሬን መካከል እየተካሄደ ያለው ጦርነት ልክ እንደ ሌሎቹ ዘርፎች በዓለም አቀፉ የህዋ ሳይንስ ምርምር እና ትብብር ላይም ሳንካ እየፈጠረ ነው።ሩሲያ በዩክሬን የፈፀመችውን ወረራ ተከትሎ በሩሲያ ላይ የሚጣለው ማዕቀብ የኤሮስፔስ ኢንደስትሪዋን የሚያጠቃልል መሆኑን አሜሪካ ገልፃለች።የአውሮፓ የህዋ ሳይንስ ድርጅት ከሩሲያ ጋር በትብብር የሚሰሩትን «ኤክሶ ማርስ 2022» የተባለውን ተልዕኮ መሰረዙን አስታወቋል።ሩሲያ በበኩሏ የጠፈር ምርምሩን በተናጠል እንደምትቀጥል በመግለፅ ላይ ነች። 

ሳምንታትን ያስቆጠረው የሩሲያና የዩክሬን ጦርነት በሀገራት ኢኮኖሚ፣ ማህበራዊ ኑሮ እና ደህንነት ስጋት ላይ ካሳደረው ተፅዕኖ ባሻገር፤ ቀውሱ ለዓለም አቀፉ የጠፈር ምርምር  ጣቢያም ተርፏል።የሩሲያ የዩክሬን ወረራን ተከትሎ የአሜሪካ እና የአውሮፓ የህዋ ሳይንስ ድርጅቶች ከሩሲያ ጋር በትብብር የሚያደርጉትን የጠፈር ምርምር በማቋረጥ ላይ ናቸው። 
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ሩሲያ ዩክሬንን በወረረች በጥቂት ቀናት ውስጥ በሰጡት መግለጫ በሩሲያ ላይ የሚጣሉ ማዕቀቦች የጠፈር ምርምር መርሀ ግብርን  እንደሚያጠቃልል ተናግረዋል። 
 «ከሩሲያ ከፍተኛ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆኑትን እንቀንሳለን ብለን እንገምታለን። ጦርነቱን ለመግታት ዘመናዊ የጦር ሰራዊት የመገንባቱ  ስራ መቀጠል  የለበትም።የኤሮስፔስ ኢንደስትሪውም የጠፈር መርሀ ግብርን ጨምሮ መቀነስ አለበት። »
ይህንን ተከትሎ ሞስኮ በዓለም አቀፉ የጠፈር ጣቢያ ከጀርመንና ከብሪታኒያ ጋር ካዛኪስታን በሚገኘው የጠፈር ጣቢያ የምታካሂደውን የምርምር መርሀ-ግብር ማቋረጥን ጨምሮ  ተከታታይ የአፀፋ ርምጃዎችን ወስዳለች።
የሩሲያ የጠፈር ኤጀንሲ ሮስኮስሞስ፤ዋና ዳይሬክተር ዲሚትሪ ሮጎዚን በበኩላቸው  በከዋሽንግተን የሚጣለው ማዕቀብ የጋራ ትብብርን ምናልባትም የዓለም አቀፉን የጠፈር ጣቢያ ምርምር ሊያስቆመው ይችላል ብለዋል።
የህዋ ሳይንስ ተመራማሪዎች ግን ትብብሩ መቀጠል አለበት ይላሉ።ካቲ ሎይደርስ የተባሉ የአሜሪካው የጠፈር ምርምር /ናሳ/ ባልደረባም የትብብሩ መቋረጥ አስቸጋሪ መሆኑን ይገልፃሉ። 
«በራሳችን ማሻሻያ ማድረግ ለእኛ በጣም አስቸጋሪ ይሆንብናል የሚል ግምገማ አለን።ይህ ዓለም አቀፍ አጋርነት ነው። በጋራ ጥገኝነት ላይ የተፈጠረ  ዓለም አቀፍ ሽርክናም  ነው። መርሀ-ግብሩን በጣም አስደናቂ ያደረገውም ይህ ነው።» 
የዓለም አቀፉ የህዋ ሳይንስ ድርጅት ምክትል ፕሬዚዳንት እና የህዋ ሳይንስ ተመራማሪው ዶክተር ሶሎሞን በላይም የናሳዋን ባልደረባ ሀሳብ ይጋሩታል።እሳቸው እንደሚሉት የህዋ ሳይንስ ዘርፍ በባህሪው የጋራ ትብብርን የሚጠይቅ ነው።
በጎርጎሪያኑ 1998 ዓ/ም የተጀመረው ዓለም አቀፉ የጠፈር ጣቢያ የቀዝቃዛውን ጦርነት የጠፈር ውድድርን ተከትሎ በአሜሪካ እና በሩሲያ መካከል የነበረውን የሻከረ ግንኙነት ለማሻሻል ታስቦ የተጀመረ የጋራ የምርምር መድረክ ነው።ይህ የምርምር መድረክ ከአሜሪካ፣ ከሩሲያ፣ከጃፓን እና ከ11 የአውሮፓ ሀገራት የተውጣጡ የበረራ አባላትን ያካተተ ቡድን ያለው ነው።ይሁን እንጂ የዩክሬኑን ጦርነት ተከትሎ አሜሪካ በሩሲያ ላይ የጣለችው ማዕቀብ ይህን የትብብር መንፈስ  ወደ ቀዝቃዛው ጦርነት ዘመን ሊመልሰው ይችላል የሚል ስጋት አሳድሯል። ተመራማሪው ዶክተር ሶሎሞንም ችግሩ በጊዜ ካልተፈታ  ህዋን ለሰላም ከመጠቀም ይልቅ ወደ ግጭት ሊያመራ ይችላል በሚል ስጋቱን ይጋሩታል።  
በሌላ በኩል የአውሮፓ የህዋ ሳይንስ ድርጅት በዚህ ሳምንት መጀመሪያ እንዳስታወቀው «ExoMars 2022»የተባለው የጠፈር ምርምር ተልዕኮ በዚህ አመት ሳንካ ገጠሞታል። ይህ የጠፈር ምርምር የአውሮፓ ህብረት እና ሩሲያ ማርስ ላይ በጋራ ያከናውኑት የነበረ  ተልዕኮ ሲሆን፤ ሩሲያ በዩክሬን ላይ የሰነዘረችውን ጥቃት ተከትሎ  ሁለቱ አካላት የሚያደርጉት የጋራ ጥረት በአሁኑ ጊዜ እውን ማድረግ እንደማይችል ድርጅቱ  አስታውቋል። 
ይህ ዜና የተሰማው የአውሮፓ የጠፈር  ድርጅት«ኤክሶማርስ 2022» ተልዕኮን በተመለከተ «ሮስስኮስሞስ» እየተባለ ከሚጠራው የሩሲያ የህዋ ሳይንስ ድርጅት ጋር ያለውን ትብብር ካቆመ በኋላ ነው። ያ በመሆኑ በጎርጎሪያኑ በመጭው መስከረም 2022 ዓ/ም በማርስ ሊደረግ የታቀደው ምርምር  መሰረዙን የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ጆሴፍ አሽባኽር ገልፀዋል።የህዋ ሳይንስ ተመራማሪው ዶክተር  ሰለሞን እንደሚሉት የትብብሩ መቋረጥ በህዋ ሳይንስ ዕድገት ላይ ተፅዕኖ ያሳድራል በተለይ በታዳጊ ሀገራት።
በሩሲያው ክሮስኮስሞስ እና በአውሮፓ የጠፈር ድርጅት  ትብብር የሚሰራው ይህ ተልዕኮ፤ዓላማው  ማርስ ላይ  ህይወት ያላቸው ነገሮች ይገኙ እንደሁ ማጥናት  ነው። «ExoMars» ሁለት ክፍሎች ያሉት ተልዕኮ ሲሆን፤ የመጀመሪያው ክፍል  በጎርጎሪያኑ 2016 ዓ/ም ነበር የተጀመረው።የመስከረም 2022ቱ ሁለተኛው ክፍል ሲሆን ፤ይህ  የተልዕኮ ክፍል በመጀመሪያ የታቀደው በሀምሌ  2020 ዓ/ም ሲሆን፤  ነገር ግን በቴክኒክ  ጉዳዮች እስከ መጭው  መስከረም ወር 2022 ዓ/ም  እንዲራዘም ተደረገ።ያም ሆኖ ይህ ተልዕኮ ተሰርዟል።
ሩሲያ በበኩሏ የማርስን ጎዞ ብቻዋን ለማከናወን እንደምትችል በመግለፅ ፤ ለድርጅቱ  የተሰርዟል ውሳኔ  ምላሽ ሰጥታለች።የሩሲያው የጠፈር ሳይንስ ድርጅት ኃላፊ ዲሚትሪ ሮጎዚን ውሳኔውን ተከትሎ በሰጡት መግለጫ «ሮስኮስሞስ የማርስ ጉዞውን በራሱ ማከናወን ይችላል» ሲሉ ተደምጠዋል።ሀላፊው አያይዘውም ሀገራቸው የራሷን  መርሀ-ግብር በመንደፍ የጠፈር ጉዞውን ከአዲሱ የማስወንጨፊያ  ቦታ ከቮስቴክ ኮስሞድሮም  በተናጥል እንደምታከናውን ገልፀዋል። ዶክተር ሶሎሞን ግን ከሰው ሀይል እና ከሀብት አጠቃም እንዲሁም ከውጤታማነት አንፃር በተናጠል መስራቱ ቀላል አይደለም ባይ ናቸው።
የአውሮፓ የህዋሳይንስ ድርጅት በሩሲያ ምትክ  ከአሜሪካው የጠፈር ጣቢያ ከናሳ ጋር በተልዕኮው ላይ ተባብሮ ለመስራት ጠንካራ ፍላጎት መኖሩን ገልጿል።በ«ኤክሶማርስ» ተልዕኮ  የአውሮፓ የህዋ ሳይንስ ድርጅት  እና ናሳ  ከዚህ ቀደምም በትብብር  ይሰሩ የነበረ ሲሆን ፣ነገር ግን ናሳ በጎርጎሪያኑ 2012 በበጀት አወጣጥ ችግሮች ሳቢያ ስራውን በማቋረጡ በ2013 ዓ/ም ሩሲያ የናሳን ቦታ በመተካት ነበር ትብብሩን የጀመሩት። 
የአውሮፓ የህዋ ሳይንስ ድርጅት የሮቦት ምርምር  ዳይሬክተር ዴቪድ ፓርከር አሁንም ቢሆን ከሩሲያ ጋር የሚደረገው የወደፊት ትብብር ዝግ እንዳልሆነ ጠቁመዋል።ፓርከር እንደገለፁት ከሩሲያ ጋር ያለው ትብብር ከቀጠለ የተቋረጠው ተልዕኮ በ2024  ሊጀመር ይችላል ። ያ ካልሆነ እና አውሮፓ ያለ ሩሲያ ከቀጠለች ግን  ተልዕኮውን  መሰረታዊ በሆነ መልኩ እንደገና መዋቀርን የሚጠይቅ በመሆኑ የማርስ የምርምር ጉዞ በጎርጎሪያኑ 2026 ወይም 2028 ዓ/ም ሊሆን እንደሚችል ሀላፊው አመልክተዋል።የህዋ ሳይንስ ተመራማሪው ዶክተር ሶሎሞን በላይ ግን ከሩሲያ ጋር በዘርፉ ያለው የትብብር መንፈስ እና  መተማመን እንዳይጠፋ ለሳይንሱ እድገት ሲባል በሰከነ መንፈስ  ችግሩን በጊዜ መፍታት ወሳኝ መሆኑን አመልክተዋል።

ምስል፦ Maksim Blinov/TASS/picture alliance
ምስል፦ ESA/Weber
ምስል፦ dpa
ምስል፦ Sergey Mamontov/Sputnik/dpa/picture alliance

ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።

ፀሀይ ጫኔ
አዜብ ታደሰ

 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW